የጸለምት ወረዳ ባለስልጣናት፣ በዋልድባ ያለዘር ልዩነት ለዘመናት የኖሩ መነኮሳትን ትግሬ ካልሆናችሁ በዚህ ገዳም ውስጥ መኖር አትችሉም በማለት ከፍተኛ ግፍና መከራ እየፈጸሙባቸው መሆኑን ዘጋቢያችን መነኮሳቱ የጻፉትን አቤቱታ ዋቢ በማድረግ በላከልን ዘጋባ ገለጸ።
እንደ ዘጋቢያችን ሪፖርት መነኮሳቱ ለክልሉ የወያኔ ባለስልጣናትና ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጻፉት አቤቱታ እንዳሉት ባለስልጣናቱ ግፍና በደል የሚፈጽሙባቸው በጣት የሚቆጠሩ የነሱን መነኮሳት፣የአካባቢውን ታጣቂዎችና ሚሊሺያዎች በመጠቀም ነው።
በመሆኑም መነኮሳቱ ይህን አቤቱታ ለማቅረብ ወደ ጎንደር ሲጓዙ ቀጥታውን መንገድ በመተው የሁለት ቀን መንገድ ለመጨመርና በረሃ ለበረሃ ለመንከራተት ተገደዋል።ቀጥታውን መንገድ ለመጠቀም የመረጡትም ለእስር ተዳርገዋል።
በአቤቱታው እንደተገለጸው የደረሰባቸውን ግፍና በደል ለማሰማት የተንቀሳቀሱት መነኮሳት ሰላሳ አንድ ሲሆኑ፣ በርካቶች የዘርኝነት ጥቃቱ ሰለባዎች ገዳሙን በመልቀቅ ተሰደዋል። ባለስልጣናቱም መነኮሳቱን በማዋከብ፣በመደብደብና በማሰር ከበታተኑ በኋላ ወደ ገዳሙ በመሄድ በማንአለብኝነት የራሳችን የሚሏቸውን ሰዎች በልዩ ልዩ የሃላፊነት ቦታ በመመደብ የገዳሙን ስርዓት አፋልሰው ሄደዋል ሲሉ አቤቱታ አቅራቢዎቹ አማረዋል።
በመጨረሻም በተደጋጋሚ በደረሰባቸው በደል፣ግፍና የዘረኝነት ጥቃት በገዳማቸው መኖር አለመቻላቸውን፣ የሌላ ሃገር ዜጋ ይመስል በገዛ ሃገራቸው በመንፈሳዊ በዓታቸው እንዳይኖሩ የማያውቁትን ፖለቲካ ተገን ባደረገ ዘረኛ አስተሳሰብ ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁን በመግለጽ ይህ ችግር በእነርሱ ላይ ብቻ የሚቆም ባለመሆኑ ውሎ አድሮ ችግሩ ከመባባሱና ጠባሳ ከመተው በፊት የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈልጉ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
No comments:
Post a Comment