Wednesday, January 23, 2013

አቤት! አቤት! አቤት!. . . በደል አዳምጡ፤ መፍትሄ ስጡ


በአንድ ወቅት ዜና ላይ “ኢትዮጵያዊነት መብትና ክብር ነው” ማለትን ሰምቼ ነበር በእኔ ትርጉም የዚህ ዓረፍተ ነገር ትክክለኛ ተጠቃሚዎች ያላቸው ሀብታሞች፣ የፖለቲካ ባለወንበሮች፣ ሕገወጥ ደላሎችና ከራይ ሰብሳቢ ተብለው የተፈረጁ ግለሰቦች ናቸው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፣ ከደረሰብኝና እየደረሰብኝ ካለው ተከራይቶ የመኖር መብት ጥሰትና በደል አኳያ” አለን ትዕግስቱ ብለን የሰየምነው የመረጃ ምንጫችን።
እንደ ትዕግስቱ የበደሉ መነሻ ደግሞ ገዥ ፖለቲከኞቻችን ራስን ብቻ ማዳመጥ እንጂ ሌላውን አለማዳመጥ፣ ሕገ ወጥ ድርጊትን ከጅምሩ ባለመቅጨት ሥር እስኪሰድ በቸልተኝነት ወይም የግለሰብ ጉዳይ ነው ብለው ዝም ብለው መመልከት ያዳበረው ችግር ነው። የግለሰብ ችግር ወደማህበራዊ ችግር ይህም ወደፖለቲካዊ ችግር እንደሚሸጋገር ግንዛቤ አላገኘም። አንዳንዴ ደግሞ አንዳንድ ባለሥልጣኖቻቸው ከደላሎች ሕገ ወጥ ድርጊት ተጠቃሚዎች ናቸው ወይስ እነሱና በቤት ኪራይ ሰብሳቢነት ታሳታፊዎች ናቸው የሚል ጥርጣሬም እንዳለው ነግሮናል። 

በዚህም የተነሳ አለ ትዕግስት “ለእኔ ኢትዮጵያዊነት በተለይም ደሀው እያለቀሰ ከእናቱ ማህፀን የወጣበት፣ እያቀሰ የሚያድግበት፣ እያለቀሰ የሚኖርበት በመጨረሻም እያለቀሰ የሚሞትበት አገር እየሆነችብኝ ነው” “ወንድሞቼ መጠለያ ማጣት ቀላል ነገር አይደለም ያለአንገት ማስገቢያ ጎጆ በልቶ መኖር፣ ለብሶ ማጌጥ፣ ጠጥቶ መርካት ወልዶ ማሳደግና መዳር ይከብዳል። ሕገወጥ ደላሎች ከቤት አከራዮች ጋር በመመሳጠር ተከራዩን ለኑሮ ዝቅጠት፣ ለማህበራዊ ግንኙነት ቀውስ ፣ ለአእምሮ ጭንቀት፣ ለሞራል ውድቀት ወዘተ እየዳረጉት ይዝናናሉ። የጭካኔ ድርጊታቸው “ሕግ የለም ወይ” የሚያሰኝ ነው። ከዚህ በላይ ምንም አልላችሁም ብሎን በብስጭት ገፅታ ተለየን።
በአከራይ ፣ ተከራይና ደላላ ጉዳይ ብዙ ተብሏል፣ ተፅፏል፣ ተተችቷል። ግን እንደምናየውና እንደምንሰማው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና ተከራይቶ የመኖር መብትን በመጋፋት የቁም ስቃይን እያበረከተ እንጂ ምንም የቀለለ መፍትሄ በማሳየት ላይ ካለመሆኑም በላይ ደላሎች በስልክ ግንኙነት በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ክልል ከተሞች የቤት ኪራይ ዋጋ እንዲንር በማድረግ ላይ በመሆናቸው እኔና ጓደኞቼ ይህን ችግር እንደገና ብናነሳው ተባብለን ማስረጃ በማሰባሰብ ይህን ጽሁፍ ለማቅረብ ተነሳሳን።
በእርግጥ ማዳመጥ መቻል ታላቅ የአመራር ብቃት፣ የብልህነት መሰረትና መለኪያም ነው። ከማህበረሰብ ለሚነሳ ጉዳይ ሁሉ መልሱ መስጠት አለበት የሚል ግምትና እምነት የለንም። ለሁሉም የማህበረሰብ መጠይቅ መልስ የሚሰጥ አገርም ሆነ መንግስት የለም። ምክንያቱም ስሜታዊነትን አስከትሎ እቅፉን አሽመድምዶ መደፍጠጥን የሚያስከትል በመሆኑ ለመልስ አሰጣጥ መንግስታዊ ዘዴና ብልሃት አለው። ትልቁ የመሪና ተመሪ ልዩነትም በቅሬታ አያያዝና አፈታት ላይ ነው። ግን መሪ ራሱን ብቻ በማዳመጥ ማመዛዘን፣ ማሰላሰልና መገንዘብ ተስኖት የእናንተን ወዲያ ተውት “ተቀባይነት የለውም” ወይም ጥያቄን ማስተናገድ ሙሉ ለሙሉ የመሪነት ሚናን መነጠቅ ነው በሚል ስጋትና ፍርሃት ከማህበረሰብ ለሚነሳ የፈጠጠና ያገጠጠ ቅሬታ በአግባቡ በልኩና በመጠኑ ስፋት ልክ መልስ ላለመስጠት ምን ሲደረግ “እምቢ!” “እምቢ!” የሚባል ከሆነ ግትርነት ፀንሶ በመውለድ ጉዳት የሚያስከትል ቀና አስተሳሰብ መላበስ የመልካም አስተዳደር አንድ ገፅታ ነው ባዮች ነን።
መደመጥና ማዳመጥን በተመለከተ ጊዜው ቢዘገይም ትዝታው ሕያው ነውና ከአርባ ዓመታት በፊት ያጋጠመኝና የተገነዘብኩትን ለፅሁፋችን አብይ ርዕስ ያደረግኩትን አቤት! አቤት! አቤት! ጉዳይ ልግለጽላችሁ። በወቅቱ የጠቅላይ ግዛት ገዥ ወይም እንደራሴ ከቤታቸው ወደቢሮ ሲሄዱና በሚያልፉበት መንገድ በሰፈር ዳኛ፣ በጭቃ ሹም ወይም በባላባት በደል የደረሰባቸው ዜጎች ሸክሜን አቅሉልኝ፣ በደሌን አዳምጡልኝ ለማለት አቤት! አቤት! አቤት! በማለት ቃላቸውን ያሰማሉ።
በአንድ ወቅት ከትምህርት ቤት ቀርቼ በአጋጣሚው የሰማሁት አቤቱታና ያየሁት ፈንጠዚያ ከህሊናዬ አይጠፋም። ታሪኩ እንደዚህ ነው። እንደራሴው ከመኖሪያ ቤታቸው አጥር ግቢ ወጥተው ወደቢሮ ሲያመሩ ሽኝት የተለመደ ባህል ነበርና ለማጀብ ከተሰበሰበው ህዝብ መካከል አንዱ “አቤት! አቤት! አቤት!” ማለት ጀመረ። እንደራሴውም ቆም ብለው በእልፍኝ አስከልካያቸው (የፕሮቶኮል ሹም እንደማለት ነው) እንዲቀርብ አደረጉና ጠጋ ብለው ለጥቂት ደቂቃዎች ያህል አነጋገሩት። ምን እንዳሉት ግን አልሰማሁም። አቤት! ባዩ ግን በድንገት ወደላይ እንጣጥ ብሎ በመዝለል እልልታውን አቀለጠው። አዘላለሉ በአሁኑ ውቅት ቢሆን ኖሮ የደህንነት ሰራተኛው አደጋ ሊጥል ነው በማለት በካራቴ ከመቅስፈት ይዘርረው ነበር። ሰውየው በዚህም አላቆመም ወደፊት እየሮጠ በቅርብ ርቀት በሚገኘው ሰንደቅ ዓላማ ስር ወድቆ በመንከባለል ደስታውን እንደገለጠ በአጃቢዎች እየተሸኙ አጠገቡ የደረሱት እንደራሴ በፈገግታና በደስታ አስጠግተውት ወደቢሮ ይዘውት ገቡ። ከዚያወዲህ የተፈፀመውን አላውቅም።
ግን አሁን ላይ ሆኜ ያንንን ምስኪን አቤት ባይ ሳስታውሰው እንደዚያ ያስዘለለውና ያስፈነጠዘው ጉዳይ አቤቱታቸውን አዳማጭ አግኝቶ መደመጥ በመቻሉ ያገኘው ርካታ ነበር። ደስታው፣ እንደሰው መቆጠሩ ነበረ ቡርቃው እርግጥ ወቅቱ የራሱ የሆነ ድከመትና የአስተዳደር በደል ይኖረዋል። ግን ማንም መንግስትና አመራር የእኔ የአገዛዝ ዘመን መጥፎ ነው ብሎ በራሱ ላይ አይመሰክርም። የእኛ ደግሞ የባሰ ነው እያንዳንዱ መንግስት ራሱን መካብና መቆለል ይወዳል። የራሱን ጉድፍና ጉድለት ጉያው ሸጉጦ ያለፈውን ማብጠልጠልና ማንኳሰስ ያበዛል። ከእኔ በላይ የአመራር ብቃት ላሳር ነው ይላል። ይህ ለምን ይደረጋል ማለት አዳጋች ነው። በሁሉም አገሪቱ በትረ ሥልጣን የያዙ መንግስታት ልማድና ተግባር በመሆኑ ቁለላውን በማዳመጥ መታዘቡ ይቀላል፤ ግን ማዳመጥ መቻል ቀላል ችሎታ አይደለም።
በእኛ እምነት የአገራችን ትልቅ ችግርና መላ ያጣው አንዱና ዋነኛ ጉዳይ ሕግን አክብሮ አለማስከበርና ሌላው ደግሞ ራስን ብቻ አጥብቆ መውደድ ነው። ከአፋዊ ክብር ያለፈ ለህግ መከበር በተግባር የተደገፈ ግምት ባለመስጠቱ አጭበርባሪው፣ አምታቹ፣ አስመሳዩና ጥቅም አሳዳጁ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሌላውን ለመበደል መሯሯጡ የተለመደ ሆኗል። ለዚህም እንደ አብነት አድርገን የምንጠቅሰው በአዲስ አበባ ከተማ እንደ አሸን ሳይሆን ከዚያም በላይ የተፈለፈሉትና ሕገ ወጥ ደላሎች ለኪራይ ቤት መወደድና ለተከራዮች መጠነ ሰፊ በደል የተነሳሱት በሕግ አምላክ የሚላቸው ኃይል በመጥፋቱ ነው።
ሕገ ወጥ ደላሎች ለሥራቸው ማከናወኛ ምንም ገንዘብ ወይም ካፒታል የላቸውም። ያላቸው መሳሪያ ተንቀሳቃሽ ስልክና አግባቢ አፍ ብቻ ነው። የዕለት ጉርሳቸውን የቀን ልብሳቸውን የለሊት ማደሪያናቸውን ገንዘብ የሚያገኙት በአከራይና ተከራይ መካከል ጣልቃ ገብተው ከሁለት ወገን በውድም ሆነ በግድ የሚያገኙት ገቢ በመሆኑ ይሉኝታንና ህጋዊነትን ከመጤፍ አይቆጥሩትም። ህገ ወጥ ስራቸውን የተፈቀደ አሰራር አድርገው የሚገምቱት በመሆኑ ቀብራሮች ናቸው።
እኔና ጓደኞቼ የአዲስ አበባን ሁሉንም ክፍለ ከተሞች ማለት ይቻላል ተዘዋውረን በአከራይ፣ ተከራይና ደላላ ጉዳይ ሰዎችን አነጋግረናል። በህገ ወጥ ደላሎችም ምክንያት ያልሰማነው የበደል ዓይነት የለም። በኮንዶሚኒየም አካባቢም በየካ፣ በጀሞ፣ በጎፋ፣ በቦሌ፣ በላፍቶ፣ በቂርቆስና በሌሎም ጎራ ብለን ለቡድን ሥራችን ጠቃሚና ወካይነት ያላቸውን መረጃዎች አሰባስበናል።
እናም ከጆሞ በመካኒሳ በኩል ወደላፍቶ ቁጥር አንድ ኮንዶሚኒየም ብቅ አልን። ወደግቢውም ስንዘልቅ አንድ የጥበቃ አባል ለብቻው ቆሞ አግኝተን የኪራይ ቤት የምንፈልግ መሆኑን ነገርነው ። ጥበቃውን ያነጋገርነው ከጆሞ ኮንደምኒያም ባገኘነው ልምድ በደላላ ሥራ ከተሰማሩት መካከል የጥበቃ አባላትም እንደሚገኙበት በመረዳታችን ነው። እናም የጥበቃ አባሉ በጥያቄያችን ተደስቶ ተፍነከነከ። የቤት ኪራይ ችግር እንደሌለና በቅርቡም ሰዎች እንደሚለቁ ገልጦልን ውጤቱን ሊነግረን እንዲችል የስልክ ቁጥራችንን እንድንሰጠው ጠየቀን። ምን ያህል ክፍል ቤት እንደምፈልግ ሳይጠይቀን ማለት ነው። ዘግይቶ ግን ባለስንት መኝታ ቤት እንደምንፈልግ ጠይቀን። ሁሉንም ዓይነት ማለት ስቱዲዮ፣ ባለአንድና ባለሁለት መኝታዎች እንደምንፈልግ ነገርነው። ምንም ችግር የለም ብሎ የስልኩን ቁጥሩን ሰጥቶን ከመለያየታችን በፊት ግን የኪራይ ቤቶች እንደየደረጃቸው ከብር 2000 እስከ ብር 4500 እንደሚከራዩ አበሰረን። በጣም ውድ ናቸው ማለት ነው እንደተረዳነው።
ወደፊት ስንሔድ አሁንም ስሙን ለደህንነቱ በማሰብ ዓለሙ ብለን የሰየምነውን ተግባቢና ተደማጭ ሰው አጋጠመን። የሚከራይ ቤት የምንፈልግ መሆኑን ነገርነው። በአንክሮ ተመለከተን እና እዚህ ግቢ ምን እግር ጣላችሁ? ማንስ ነው የጠቆማችሁ?፤ በኪራይ ስም ለደላላ ብዝበዛና ስቃይ ትጋለጣላችሁ ይቅርባችሁ አለን”። እንዴት? አለው አንዱ ጓደኛችን። “እዚህ ግቢ ተከራይቶ መኖር የሚቻለው ግፋ ቢል አራት ወራት ጠንካራ ከተሆነም ዓመት ነው። ዙሩ ፈጣን ነው። ከዚያ በኋላ ደላላው ተከራይን ለማፈናቀል እዚያ ከምታዩት ሊስትሮዎች ይጀምራል። ጫኝና አውራጅ ቆራሌው፣ ጥበቃ ሠራተኛው፣ የቤት እመቤቱ፣ ባለሸቀጥና ግሮሰሪ ነጋዴው፣ ኮንዶሚኒየም አስተዳደር ኮሚቴ ምን አለፋችሁ በዚህ ግቢ ሳር ቅጠሉ በድለላ ሥራ የተሰማራ ነው ብሎ ሳይጨርስ እይዋት ያችን “መቶ” አለን። “ስሟ ነው መቶ” አልኩት አይደለም ቅጽል ስሟ ነው። የድብቅ! እንደዚህ የተድበለበለችው ተከራዩን በማፈናቀልና አዲስ በምታስገባው ተተኪ ተፈናቃይ በምታገኘው ያልተቋረጠ ገቢ ነው። ህገወጥ ደላሎች ከአከራይና ተከራይ አጠቃላይ የኪራይ ክፍያ ከሁለቱም ወገን ከአስር እስከ አስራ አምስት በመቶ የኮሚሽን ክፍያ ይጠይቃሉ። በዚህም ቢያንስ ከብዙ ተፈናቃዮችና ገቢዎች በወር ከአስር ሺህ እስከ ሀያ አምስት ሺህ ብር ገቢ ያገኛሉ። ለዚህ ገቢያቸው ምንም የገቢ ግብር አይከፍሉም። ገቢያቸው እንዳይቋረጥ ደግሞ ከወዲያ ወዲህ በመሯሯጥ ተከራዮችን ማፈናቀል አለባቸው ማለት ነው። በግብር በኩል አከራዮች ለመንግስት የሚከፍሉት ገቢ ኢምንት ነው ወይም ምንም አይከፍሉም፤ ተቆጣጣሪ የላቸውምና።
“እኔ አለ ዓለሙ ከባለቤቴና ከአንድ ልጄ ጋር በዚህ ግቢ ሶስት ቤቶች ተከራይቻለሁ የገባሁት በስድስት መቶ ኪራይ ነበር አሁን ኪራይ አምስት እጥፍ በማሻቀቡ ወደስቱዲዮ በመግባት ተከራይቼ ተቀምጫለሁ። ከበድ ያሉ የቤት ዕቃዎቼን ሸጨ ጨርሼ ጓዘ ቀላል ሆኛለሁ። በቤት ኪራይ ጉዳይ የባለቤቱን የአንገት የጆሮና የጣት ወርቅ ሸጠናል። እኔም የጣት ወርቄን ሸጨ የአንገት ሀብል ብቻ ቀርቶኛል። አሁን ከእስቱዲዮ ወደ ቆርቆሮ በቆርቆሮ በሆነ የግል ቤት እየፈላለግንነው። የቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት ትንሽ ቀለል ያለ ኪራይ አለው። ቢያንስ ዙሪያውና ጣሪያው ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሆነ ቤት በዚህ አካባቢ ከብር 1000-1700 ይገኛል። እናም እዚህ ግቢ ተከራይታችሁ ግቡ ብዬ አልመክራችሁም” በማለት ከልቡ አጫወተን።
በየካ ቁጥር 2 ኮንዶሚኒየም ደግሞ አንድ ተከራይ እንዲህ አለን። “በአካባቢዬ አሁን የለቀቁበት ቤት የማውቃቸው ደላሎች መጥተው ቤቱን ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ለሌላ ሰው በተሻለ ዋጋ ያከራየነው ስለሆነ እንድትለቅ ነው የመጣነው” አሉኝ። እንዴት ነው ነገሩ ቤቱን እናንተ አላከራያችሁኝም፤ ምን አገባችሁ እናንተ ብላቸው “ያልንህን አድርግ ከፈለግክ አከራይህን ጠይቀው” ብለውኝ ሄዱ። እነሱ እንዳሉትም ለአከራዬ ስደወል “ወንድሜ ጊዜው የጥቅም ነው እኔም ጥቅሜን እፈልጋለሁ። አንተ ከምትከራይበት የተሻለ ዋጋ ያገኘሁ ስለሆነ ቤቱን ልቀቅልኝ፤ እነሱ በነገሩህ የጊዜ ገደብ” አለኝ። “የኮንዶሚኒየም ቤት አከራዮች እኛ ተከራዮችን የባንክ ብድር እዳቸው ሂሳብ ማወራረጃ አድርገውናል። በጣም ነው የሚያሰቃዩን። ሁሉም ባይሆኑ አብዛኛው የኮንዶምኒየም አከራዮች ይሉኝታ ብሎ ነገር አይታይባቸውም። ከደላሎች በኩል ደግሞ ኪራይ የመኖር ህልውናቸው በመሆኑ አፈናቅሎ መጠቀም ዋና ስራቸው ነው” አለን።
“ደላሎች ከቤት ማፈናቀል ብቻ ሳይሆን በአከራይ ተከራይ መካከል ገብተው ተከራይ እስከ አንድ ዓመት ቅድሚያ ክፍያ እንዲከፍል የሚያደርጉ በመሆኑ በደላቸው ድርብ ብቻ ሳይሆን ድርብርብ ነው። ተከራይ በቅድሚያ ክፍያ በመጨነቅ ለብድር ወይም ጌጣ ጌጥም ለመሸጥ ይገደዳል። በኪራይ ቤቱ የሚኖር ሰው በአንድ ጊዜ የብዙ ወርቅ ቅድመ ክፍያ እንዲከፍል መገደድ ይከብዳል። ደላሎች ይህን የሚያደርጉት ገቢያቸውን ለማሳደግ በመሆኑ ለተከራይ ስቃይ ደንታ የላቸውም። ድርጊታቸው ሰውን ለእብደትና ለድህነት የሚዳርግ ነው” አለን።
የድለላ ሙያ በህግ ገደብ የሚሰራ ተግባር ነው። በአገራችን ግን በልቅነት የተተወ ሥራ በመሆኑ አብዛኛው ደላላ ሕገ ወጥ ነው። ይህ ሲባል ጥቂት ሕግና ሥርዓት አክባሪ፣ አገልጋይ ደላሎች የሉም ማለቴ አይደለም። ብዙዎቹ ግን ሥራው ከበድ ያለ ጥቅም ያለው በመሆኑም “የእከሌ ድለላ ሥራ” በማለት ማስታወቂያ ለጥፎ ተከራይን በቁም እንዲገፍ የተፈቀደ ሥራ ሆኗል የደላሎች እኩይ ሥራ ለሙስናም ምንዳ ሆኗል። ምክንያቱም ከአቅም በላይ ኪራይ እንዲከፍል የሚገደድ ተከራይ በመጨነቅና በመጠበብ የእምነት ማጉደል ተግባር ሊያከናውን ይችላል። ለሥርቆትም ይዳረጋል ማለቴ ነው።
የቀበሌ አመራሮች የሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ሥራ ማስታወቂያ ሲለጠፍ ከመቅስፈት ተከታትለው ቤቱን ያሽጋሉ፣ ግን የድለላ ሥራ ማስታወቂያ በየመኖሪያ ቤቱ፣ በአማካይ ስፍራዎችና በየመንገድ ዳር ሲለጠፍ ዘወር ብለውም አይመለከቱትም። በዚህም የተነሳ ህገ ወጥ ድለላው እየተባባሰ ነው። ደላላነት የንግድ ዘርፍ ነው። ንግድ ደግሞ ህጋዊ ግብርና ህጋዊ አሰራር ይፈልጋል። ሕገ ወጥ ድለላ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አንዱ መገለጫ ነው። ምርጫ በመጣ ቁጥር መልካም አስተዳደር ማዕከል አድርጎ በስብሰባ መጠመድ ሳይሆን ህገወጥ አሰራርን ከጅምሩ ለመቋጨት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው።
መንግስት ህዝብን ከህገ ወጥ አሰራር የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት። የዓለም ባንክ በዘመናዊ ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ መንግስታት አምስት አብይ ጉዳዮችን የማከናወን ኃላፊነት እንዳለባቸው እ.ኤ.አ በ1997 በወጣው መረጃ አመልክቷል። ይኸውም፣ የህግ ማዕቀፍን የማዘጋጀት፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲን የመንደር፣ የመሰረታዊ አገልግሎትንና መሰረተ ልማትን የመንግስት ተጋላጮችን የመንከባከብና አካባቢን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁሟል።
የባንኩን ጥቆማ የወሰድኩት በመንግስት አመራር የባንኩ ጥቆማ ጣልቃ መግባት አለበት ለማለት ሳይሆን ጠቃሚ ጥቆማ በመሆኑ ነው። እናም ዛሬ ተከራዮች በህገወጥ ደላሎችና በአልጠግብ ባይ አከራዮች መመሳጠር የተነሳ ለተለያየ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነልቦናዊና የሞራል ችግር የተጋለጡ በመሆኑ ይህ ፈሩን የሳተና ከልካይ ያጣው የህገ ወጥ ድለላ ስራ ህጋዊ መስመር እንዲይዝ መንግስት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ለችግር የተጋለጡና በመጋለጥ ላይ ያሉትን ተከራዮች አለሁላችሁ ሊላቸው ይገባል።
መንግስት በትራንስፖርት፣ በሸቀጣሸቀጥና በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ጣልቃ በመግባት ዋጋን ይቆጣጠራል፤ ይመራል። ይህ ደግሞ ኃላፊነቱ ነው። በነፃ ገበያ ስምና ግለሰብ መብት ሰበካ ያለምንም ገደብና ከልካይ ዋጋው ከጊዜ ወደጊዜ በመናር ህዝብን በማሰቃየት ላይ ያለው የቤት ኪራይ ጉዳይ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል። የመንግስት ባለሥልጣናት ይህን አስከፊ አሰራር እንደግለሰብ ግንኙነት ተመልክተው ዝም ማለት የለባቸውምና አቤት! አቤት! አቤት! በደልን አዳምጡ በአግባቡ መልስ ስጡ እንላለን።
                        ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
                                     ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment