Wednesday, January 9, 2013

‘‘የሕሊና ሰላም አለኝ’’ አንዱአለም አራጌ


በሽብርተኝነት የወንጀል ክስ ቀርቦበት በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ተብሎ የዕድሜ ልክ የተፈረደበት የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አመራር የነበረው አንዱአለም አራጌ ‘‘የሕሊና ሰላም አለኝ’’ ሲል ለፓርቲው አመራሮች ተናገረ። 
አንዱአለም ይሄንን ቃል የተናገረው ባለፈው እሁድ ታህሳስ 28 ቀን 2005 በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተገኝተው ለጠየቁት የፓርቲው አመራር አካላት ነው። የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳን ጨምሮ ሌሎች 15 የሚሆኑ የፓርቲው አመራሮች፣ የጽ/ቤት ሰራተኞችና የፓርቲው አባላት የገናን በአል ምክንያት በማድረግ በማረሚያ ቤቱ በመገኘት ጠይቀውታል። 

የፓርቲው አመራሮች አንዱአለምን የጎበኙት ከታሰሩ ከበርካታ ወራት በኋላ በቡድን በመሆን ሲጠይቁት የመጀመሪያ ሲሆን ማረሚያ ቤቱም በሕገ-መንግስቱ መሠረት አመራሮቹ እንዲጠይቁት ልዩ ትብብር ማድረጉ ተገልጿል። የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አቶ አንዱአለምን የጎበኙት የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ በአካል በተገኙበት ለ30 ደቂቃ ያህል እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል። 
አንዱአለምን ለመጠየቅ እድሉን ካገኙት መካከል የፓርቲው የስራ አስፈፃሚ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ ጉብኝቱን አስመልክተው በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ አቶ አንዱአለም በጥሩ ሞራል ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል። 
በጉብኝቱ ወቅት አንዱአለም ‘‘ለእኔ አታስቡ፣ ማንም ላይ ጥፋትና ክፋት ለመስራት ተነሳስቼ አይደለም የታሰርኩት። የህሊና ሰላም አለኝ፤ በማንም ላይ ጥፋት ለመስራት ተነሳስቼ ብታሰር ኖሮ የህሊና እዳውን አልችለውም ነበር። እኔ የሚያሳስበኝ በሀገራችን የፍቅርና የመተሳሰብን ዋጋ አለማወቃችን ነው’’ ማለቱን አቶ ዳንኤል ተናግረዋል። 
አንዱአለም ለፓርቲው አመራሮች ሰላማዊ ትግሉ በብዙ መልኩ ፈተና ውስጥ መግባቱን በመግለፅ የፓርቲው አመራሮች ጠንክረው እንዲታገሉ ማሳሰቡን የገለፁት አቶ ዳንኤል፣ በሌላ በኩል አቶ አንዱአለም ካሉት እስረኞች በተለየ በጥቂት ጎብኚዎች ብቻ እንዲጠየቅ መደረጉ፣ በህገ-መንግስቱ መሠረት በሃይማኖት አባቶች፣ በወዳጅ ዘመድና በህግ አማካሪ እንደማይጠየቅ እንዲሁም አምስት ታራሚዎች በሚታሰሩበት ክፍል ውስጥ አንዱአለም በታሰረበት ክፍል ውስጥ ግን ተጨማሪ አንድ ሰው እንዲታሰር በመደረጉ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ በተገኙበት ቅሬታውን መግለፁን አቶ ዳንኤል አያይዘው ገልፀዋል። 
ክፍሏ ጠባብ በመሆኗ የትንፋሽና የልብ ችግር እንዳለበት አንዱአለም ገልጿል ያሉት አቶ ዳንኤል ከውጭ ምግብ እንደልብ እንደማይገባለት ገልጾልናል ብለዋል። ቅሬታውን ሲያቀርብ በወቅቱ የነበሩት የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ በሰጡት ምላሽ ማረሚያ ቤቱ ከሌላው እስረኛ በተለየ የአንዱአለምን ሰብአዊ መብት እንደማይነካ እና ስድስት ሆኖ እንዲታሰር የተደረገውም ለደህንነቱ መሆኑን ተናግረዋል፤ ሲሉ አቶ ዳንኤል ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል። 
በተመሳሳይ የፓርቲው አመራሮች ቂልንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኘውን ሌላኛውን የፓርቲውን የብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ናትናኤል አያሌውን መጎብኘታቸውም ታውቋል።
                                                                ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment