Thursday, November 14, 2013

በግብጽ ኢትዮጵያውያን እየተሸጡ ነው!

የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ማህበር በግብጽ ባወጣው መግለጫ በሱዳን እና በግብጽ የድንበር ከተሞች በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ ድርጊት ዘርዝሮ አቅርቧል።
ራሻይዳ ( ቀይ አረቦች) የሚባሉት በሱዳን የሚገኘውን ስደተኞች ካምፕ በድንገት ጥሶ በመግባት በቶር መሳሪያ አስገድደው ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በማፈን ሚሊና በረሀ ውስጥ ከወሰዱዋቸው በሁዋላ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ ኢትዮጵያውያን ጋር በመቀላለቀል፣ ለግብጻውያን ሽፍቶች ይሸጡዋቸዋል።
ግብጻውያን ሽፍቶችም በድብቅ ወደ እስራኤል ድንበር አቅራቢአ በሚገኘው ሲና በረሀ በውሰድ በተለያዩ ዋሻ ያስቀምጧቸዋል።

ሽፍቶች እስከ 33 ሺ የአሜሪካን ዶላር የሚይጠቁ ሲሆን፣ ይህን መክፈል ያልቻሉ ኢትዮጵያውያን እጣ ፋንታቸው ስቃይ ብሎም ሞት ነው።
ድብደባ፣ በኤሌክትሪክ እንዲያዙ በማድረግ ማሰቃየት፣ በቀለጠ ጎማ ጀርባቸው እንዲቃጠል ማድረግ፣ እግራቸው ለርጅም ጊዜ በካቴና እንዲታሰር ማድረግ፣ ውሀ በሚጠማቸው ጊዜ ጋዝ ቀላቅለው መስጠት፣ በቀን ውስጥ በእግራቸው ተቀምጠው እንዲተኙ ማድረግ፣ እንዲሁም ከእስረኞች ፊት ሌሎች ጓደኞቻቸውን በጥይት መግደል ከማሰቃያ መንገዶች መካከል ተጠቅሰዋል።
በስቃይና በመከራ የከረሙት እስረኞች ገንዘብ ካልተላከላቸው ኩላሊታቸው እንዲወጣ ተደርጎ ለግብጽ የህክምና ባለሙያዎች ይሸጣል።
ከዚህ ሁሉ መከራ ፓሊስ የታደጋቸው ደግሞ አደገኛ ወንጀለኞች በሚታሰሩበት አናተር በሚባለው የካይሮ እስር ቤት እንዲገቡ ይደረጋል። በእስር ቤቱ ውስጥ ወንዶች ይደበደባሉ፣ ይደፈራሉ። ሞተው አስከሬናቸው የሚጣልም ብዙ ናቸው።
ላለፉት 5 አመታት በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራዊያን መኖራቸውን የገለጸው ማህበሩ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ግፍ ደግሞ ከወንዶችም የባሰ ነው ብሎአል።
ብዙ ሴቶች በኤች አይቪ ቫይረስ ከመያዛቸውም በላይ፣ በእስር ቤት ውስጥ አርግዘው እንዲወልዱ ተደርጓል። አብዛኞቹ የሚወለዱት ህጻናትም በምግብ እጦት እዛው እስር ቤት ውስጥ ይሞታሉ።
ማህበሩ ከወንበዴዎች እጅ አምልጠው የመጡ 17 ኢትዮጵያውያን ካይሮ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስደተኖች ጽ/ቤት ውስጥ ከላላ አግኝተው እንደሚኖሩ ማህበሩ ገልጿል።
ዲያቆናት ሳይቀሩ ከሸገራ የስደተኖች ካምፕ ተወስደው መሸጣቸውን የገለጸው ማህበሩ፣ ከሞት ተርፈው ካይሮ ከገቡት መካከል ሰውአለ ደነቀው፣ ከጎጃም ፍኖተሰላም፣ በላይ ገብረመስቀል፣ ከርሲ፣ አትክልት ንጉሴ ከትግራይ ኢሮብ፣ ሀፈር ብርሀን ከትግራይ ጉዶም፣ ተስፋይ ንጉሴ፣ ከትግራይ አምባላጌ፣ ሞላ ሰንበታይ፣ ከትግራይ አምባላጌ፣ ናትናኤል ሞላ፣ ከጎንደር አርማጭሆ፣ ኤፍሬም መከተ ከወሎ አማራ ሳይንት ፣ ሻምበል ማህረግ፣ ወሎ ወልዲያ፣ ደመቀ ታሪኩ፣ ጎጃም ማርቆስ፣ ሀምዛ፣ ኦሮሚአ ጅማ፣ ወንዶሰን እንድሪስ ከትግራይ፣ ካሊድ ኦሮሚአ ጅማ፣ ሙላት አግማስ፣ ጎጃም ባህርዳር፣ ጌታሁን ሽፈራው፣ ጎንደር እንፍራንስ፣ ጽጌረዳ ተሾመ፣ ደቡብ አዋሳ፣ ቤዛ ተሾመ፣ ደቡብ አዋሳ፣ ትእግስት ገብሬ፣ ጎንደር እንዲሁም ዋሂድ ካህሳይ ከትግራይ ይገኙበታል።
ማህበሩ ኢትዮጵያውያን የችግሩን አሳሳቢነት ተረድተው አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቋል። 

No comments:

Post a Comment