Wednesday, November 13, 2013

መንግስት የሌለው ህዝብ አገሩ ‹‹መንግስት›› በውጭ ደግሞ ሌሎች ይገድሉታል፣ ያስሩታል፣ ይደበድቡታል……፡፡

ትልቁ የስልጣን ማማ ላይ ቆሞ አገርና የሚመራ (የሚገዛ አይደለም) የፖለቲካ አካል መንግስት ነው፡፡ ለዜጎቹ ጥቅም፣ ለአገር ደህንነትና ሰላም፣ ብልጽግና ሳይሆን ለስልጣኑና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚባዝን የፖለቲካ ቡድን ግን በምንም መስፈርት መንግስት ብሎ መጥራት አይቻልም፡፡ ለእኔ ኢህአዴግም እነደዚህ ነው፡፡ መንግስት የሚያሰኘውን መስፈርት መካከል አንድም ነገር አሟልቶ አይቼው አያውቅም፡፡

ዱር ለገደል የሚንከራተቱ አማጺያን፣ ማፍያዎች፣ ርህራሄ የላቸውም የሚባሉ አሸባሪዎች ሳይቀሩ የሚወክሉት ህዝብ በሌሎች አደጋ እንዳይደርስበት ይከላከላሉ፡፡ አደጋ ሲደርስበት ይጠይቃሉ፡፡ ፍትህ እንዲያገኝ ያደርጋሉ፡፡ አሸባሪዎችና ማፍያዎች እንኳን በሌሎች አገራት የደረሰን በደል የሌሎቹን በማገት አሊያም በሌላ መንገድ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ይህኛው መንገድ ሰላማዊ ባይሆንም ለህዝባቸው ያላቸውን ክብርና ቆራጥነት የሚያሳይ ነው፡፡ ፍልስጤሞች አንድ ፍልስጤማዊ ችግር ሲደርስበት ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን በማንቀሳቀስ፣ አጸፋ በመስጠትና በሌሎች መንገዶች ይታገላሉ፡፡
ኢህአዴግ ሳውዲዎችን እንዲያግት፣ አንዲገድል ወይንም እንዲያስር አይደለም፡፡ ‹‹መንግስት›› የሚለውን የተከበረ ስም ተሸክሞ ግን ‹‹ህገ ወጥ ስለሆኑ ነው የተባረሩት፣ የታሰሩት፣ የተገደሉት›› ማለቱ ተግባሩን ከማፍያዎቹም የወረደ ያደርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ፣ ቃለ አቀባይ፣ ፓርቲ፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ደህንነት……….ብሎ የሰየመ የፖለቲካ ቡድን ቢያንስ ቢያንስ ሳውዲዎች በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያድርጉትን ጦርነት ማውገዝ ነበረበት፡፡ የሶማሊያ ዜጎች በተለያዩ አገራት ችግር ሲደርስባቸው አሸባሪው አልሻባብ ድምጹን ከፍ አድርጎ ያወገዘበት፣ ያስፈራራበት ጊዜያት በርካቶች ናቸው፡፡
ሁለት ስውዳውያን የአገር ድንበር ጥሰው ስለገቡ በመታሰራቸው አገሪቱ ብቻ ሳትሆን የአውሮፓ ህብረትም ጭምር ጮኸቱን አስምቷል፡፡ ኢህአዴግም አዲስ አበባ ውስጥ ሲጽፉ የታሰሩት ኢትዮጵያውያን ሳይፈቱ የግዱን በሽብርተኞቹ አገር ሶማሊያ በኩል ድንበር ተሸግረው የገቡትን ባለ መንግስት ዜጎች የግዱን ለቋቸዋል፡፡ መንግስት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ደግሞ ፖሊስ እያሳደደ ሲገላቸው ማንም አልቆመላቸውም፡፡ ምንም ጫና ያልተደረገባትና በታሪክ ለኢትዮጵያ ጠላት የሆኑት ሳውዲዎች ደግሞ ጭካኔያቸውን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ትኩስ ስንቅ ያቀበሉት ሳውዲና ሌሎች አረቦች ናቸውና ኢትዮጵያውያን እየቆሰሉ፣ እየሞቱም ቢሆን ሳውዲዎች በሰላም ዳቧቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ያመርታሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይነግዳሉ፡፡ ይኖራሉ፡፡ ይህ ኢህአዴግ ለሳውዲዎች የሚያድገው ውለታው መሆኑ ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ይልቅ ለገዳዮቹ ርህራሄን ያበዛውም ለዚህ ነው፡፡
የአገርን ብሄራዊ ጥቅም፣ ክብርና የዜጎችን መብት እስከነካ ድረስ የአንድም የ70 ሺህ ህዝብም የቀጠፈ አለመግባባት ጦርነት ነው፡፡ ኢህአዴግ ከሻዕቢያ ጋር በተጣላበት ወቅት የአስመራው ማፍያ ዜጎቻችን ሲያባርር ኢህአዴግም በአጸፋው ‹‹ኢትዮጵያዊ ነን!›› ያሉትን ኤርትራዊያን ጭምር በተመሳሳይ መልኩ አባርሯል፡፡ ያኔ ኤርትራዊያን እንዲባረሩ የፈለገ አልነበረም ባይባልም በርካታ ኢትዮጵያውያን ግን ደስተኛ አልነበሩም፡፡ በሳውዲ እየፈጸመች በምትገኘው ተግባር ግን የኢትዮጵያውያን ልብ ደምቷል፡፡ ኢህአዴግ ግን ምንም አላለም፡፡
ኢህአዴግ የኢትዮጵያውያን መንግስ ቢሆን ኖሩ እርምጃ መውሰድ የነበረበት በሳውዲ ላይ ነበር፡፡ኢህአዴግ መንግስት ቢሆን ኖሮ የሚያስከብረው የህዝብን ጥቅም፣ ክብርና መብት ነበር፡፡ የሚፈጽመው ደግሞ ህዝብ ያለውን መሆን ነበረበት፡፡ መንግስት የሌለው ህዝብ አገሩ ቤተ ‹‹መንግስት›› ውስጥ ያሉት በውጭ ደግሞ ሌሎች ይገድሉታል፣ ያስሩታል፣ ይደበድቡታል……፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በደል ይህን ያህል ከብዷል፡፡ መንግስት አልባነት ይህን ያህል ያሰቃያል፡፡
የአንድ የኢህአዴግ ባለስልጣንን ልጅ ቴሌ፣ ደህንነት፣ የአየር መንገድ፣ የገንዘብ ሚንስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር፣ ኤምባሲው….. ብቻ በርካታ ‹‹ተቋማት›› ተንከባክበው ወደ ቻይና ይልኩታል፡፡ ሲመለስ፣ ምግብ፣ ገንዘብ፣ መልጭዕት ሲላክለትም እነዚህ መስሪያ ቤቶች ያሸረግዳሉ፡፡ ባለስልጣኑ፣ ልጁ ዘመዱ፣ ካድሬ፣ የፓርቲ አባል፣ ፓርቲ……ሁሉም ሲሸኙ፣ ሲመለሱ እነዚህ መስሪያ ቤቶች ተመሳሳይ የማሸርገድ ተግባራቸውን ይወጣሉ፡፡
ልክ የአጼው ልጅ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥሩ ስንት ነው ስትባል ‹‹500 ብንሆን ነው፡፡›› እንዳለችው የኢህአዴግና ተቋማቱ ህዝብ የኢህአዴግ ባለስልጣናት፣ ዘመድ አዝማዶች ሆነዋል፡፡ ኢህአዴግ መንግስት የሆነው ለእነዚህ ጥቂቶች ነው፡፡ ሌላውን ህዝብ ማንም አያስታውሰውም፡፡ የሌሎች አገራት መንግስታት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ሌሎች ለቀሪው ህዝብ ቢያዝኑም እንደ መንግስት ሆነው ሊረዱት፣ ሊያድኑት አይችሉም፡፡ ቤተ ‹‹መንግስት›› ውስጥ ያሉትም ቢሆን ይህን አይፈቅዱም፡፡
ኢትዮጵያዊ መንግስት አልባዋ ሶማሊያ ውስጥ ቢታገት፣ ኬንያና ታንዛኒያ ውስጥ ቢታሰር፣ ሳውዲ ውስጥ ቢገደልና ቢሰቃይ፣ ማዕከላዊና ቃሊቱ ውስጥ ቢሰቃይ ፍትህ የሚሰጠው፣ ክብሩን የሚመልስለት ‹‹በህዝብ፣ ለህዝብ፣ የህዝብ›› የሆነ መንግስት የለውም፡፡ አንዱንም አያሟላም፡፡
ሻዕቢያ ዜጎቻችን ከማባረር ጀምሮ ምርኮኞችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል እስከፈለገው ድረስ የፈነጨብን ኢህአዴግ የመንግስትነት ክብር እንደሌለው ጠንቅቆ በማወቁ ነው፡፡ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ በመላው አለም በዜጎቻችን ላይ በደል የሚፈጽሙት ሁሉ ኢህአዴግ ለዜጎቹ ጠላት መሆኑን ስለሚያውቁ፣ መንግስት እንደሌለን ስለገባቸው ነው፡፡ እንዲያውም አብዛኛዎቹ በደሎች የሚፈጠሩት ‹‹መንግስት›› ነኝ የሚለው ኢህአዴግ ‹‹በሏቸው!›› የማለት ያህል መልዕክቶችን ስለሚያስተላልፍ ነው፡፡ እነሱ ደግሞ ባልተወለደ አንጀታቸው ይጨፈጭፏቸዋል፡፡ ያሰቃዩቸዋል፡፡
አገራቸው ውስጥ ሥልጣን ላይ ያለው አካል ያልተከበሩ ዜጎች በውጭ አገር በደል ቢደርስባቸው አይገርምም፡፡ እንዲያውም ኢትዮጵያውያን የአገራቸው ገዥ ከሚያደርስባቸው ይልቅ የሌሎቹን በደል የተሻለ ነው ብለው መጉረፋቸውን ቀጥለዋል፡፡ እንደ ኢህአዴግ ቢሆንማ እንደ ቀድሞዎቹ እስራኤላዊያን ተበትነን አልቀን ነበር፡፡
መንግስት የሌለው ህዝብ ዋናው ተግባር የመንግስት ምስረታ ነው፡፡ እስከዚያ ግን በተደራጀ መልኩ ከውጭም ቢሆን የሚደርስበትን በደል መመከት የግድ ይለዋል፡፡ አይደለም ሰላማዊ ትግል የሚያደርግ ህዝብ ማፍያዎችና አሸባሪዎች እንኳን ለዜጎቻቸው ይጨነቃሉ፡፡ እናም ሳውዲ እየፈጸመችው የምትገኘውን በደል ለኢህአዴግ ከማመልከት ይልቅ ህዝብ የአገርና የዜጎችን መብት የሚያስጠብቅ የራሱን እርምጃም መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ዜጎቻችን በሳውዲ ጎዳናዎች እየተገደሉ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር አገራችን ውስጥ ወደሚገኘው የሳውዲ ኤምባሲ አቅንተን የፈጸሙት ተግባር አስጸያፊና ህገወጥ መሆኑን መንገርኮ አንድ ነገር ነው፡፡
Getachew Shiferaw 

No comments:

Post a Comment