Wednesday, November 20, 2013

በዶ/ር መረራ ጉዲና መፅሐፍ ላይ ሊደረግ የነበረው ውይይት ተሰረዘ

በዘሪሁን ሙሉጌታ

በቅርቡ ለሕትመት የበቃው “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞ እና የህይወቴ ትዝታዎች” በሚል ርዕስ ለሕትመት በበቃው መፅሐፍ ባለፈው አርብ ሕዳር 6 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ሊካሄድ የነበረው ውይይት ተሰዘረ።
ውይይቱ ተዘጋጅቶ የነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የጀርመን ተቋም የሆነው የፍሬዲሪክ ኤቨርት ፋውንዴሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ዲፓርትመንት ጋር በመተባበር ነው። ተቋሙ ከዚህ በፊት የንባብ ባህልን በማበረታታት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተለያዩ የሀገሪቱ ምሁራን በታተሙ መፅሐፎች ላይ ሕዝባዊና ምሁራዊ ውይይት ሲያካሂድ ቆይቷል።
በህዳር 6 ቀን 2006 ዓ.ም ፕሮግራምም ላይ የመፅሐፉ ደራሲ ዶ/ር መረራን ጨምሮ ሌሎች ተጋባዥ ምሁራን አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ፕሮግራም ተዘጋጅቶ በጉጉት ሲጠበቅ ነበር። በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢም የፕሮግራሙ ማስታወቂያ ተለጥፎ ሲያበቃ ለጊዜው ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደርጎ የዕለቱ ዝግጅት ተሰርዟል።
የመፅሐፉ ደራሲ ዶ/ር መረራ ጉዳዩን በማስመልከት ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ መፅሐፉ ኢህአዴግን ሳያስጨንቀው የቀረ አይመስለኝም ብለዋል። በተለይ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን እየመራ ያለበት “ቀልድ” ሀገሪቱን የትም አያደርሳትም የሚለው የመፅሐፉ መደምደሚያ በኢህአዴግ ባለስልጣናት ላይ ቅሬታ መፍጠሩን አፍቃሪ መንግስት ከሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ታትመው ከሚወጡ ፅሁፎች እየተረዳሁ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ዲፓርትመንት ኃላፊ ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ ስለጉዳዩ ጥያቄ ቀርቦላቸው የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አዳራሹን እንደሚፈልገው በመግለፁ ዝግጅቱ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መደረጉን ለሰንደቅ ጋዜጣ አረጋግጠዋል። የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ የጀርመን ተቋም የሆነው ፍሬድሪክ ኤቨርት ፋውንዴሽን መሆኑን ጠቅሰዋል። የዚህን ተቋም የፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ያሬድ ፈቃደን አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
“የኢትዮጵያ ፖለቲካና ምስቅልቅል ጉዞ እና የህይወቴ ትዝታዎች” የሚለው የዶ/ር መረራ መፅሐፍ በቅርቡ በሀገሪቱ ከወጡ የፖለቲካ መፅሐፎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment