Monday, November 11, 2013

ጅል መንግስት የጅል ህዝብ ውጤት ነው ! (አሌክስ አብረሃም)

ሰሞኑን በሳውዲ ህዝብና መንግስት እየተፈፀመ ያለውን ያልሰለጠነ እና ኋላ ቀር ድርጊት በርካቶች እያወገዙት ቢሆንም አንዳንዶች ግን እርምጃው ልክ ነው የሚል አስተያየት ሲሰጡ እየሰማን ነው …. የሚገርመው ደግሞ እነዚህ አስተያየት ሰጭወች ኢትዮጲያዊያን መሆናቸው ነው !
የአስተያየት ሰጭወቹ መከራከሪያ ቃል በቃል ኢትዮጲያዊያን (አበሾች) ሳውዲን አቆሽሸዋታል ሌብነት ሽርሙጥና መጠጥ መቸርቸር በአበሾች ተስፋፍቷል ይባስ ብሎም አበሻ የቤት ሰራተኞች አሰሪወቻቸውን በግፍ እየገደሉ ነው የሚል ‹‹በደፈናው›› ሃሳብ ያቀርባሉ ! ቀጥለውም የሳውዲ መንግስት ሰባት ወር ታግሶ ህጋዊ እንዲሆኑ ለምኗል አስታሟል (እንደውም ትእግስቱ በዝቷል) አይነት ሃሳብ ይመርቁበታል ፡፡

እናም ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ዜጎች ቢጉላሉ ቢታሰሩ ቢንገላቱና ቢገደሉ ጭምር የሳውዲ መንግስት ተጠያቂ አይደልም በማለት ጭፍን ፍርዳቸውን ያሳርጋሉ !
እናተ የባእድ ከበሮ የምትደልቁ ከንቱወች !
ሽርሙጥናን ወደሳውዲ ያስገቡት አበሾች አይደሉም !! ሌብነትን እና መጠጥ ቸርቻሪነትንም ቢሆን አበሾች ወደሳውዲ አላስገቡትም ይሄ ‹‹ዜጎቻችን የተቀደሱ ንፅሃን ናቸው አበሾች ገብተው በከሉን እንጅ ›› ከሚሉት የሳውዲ ተመፃዳቂወች ተረት የተወሰደ ነው ፡፡
ከአራት አመት በፊት ይመስለኛል ስኮትላንድ የምታመርተውን ውስኪ በአለማችን ላይ ከሚረከቡ አገራት (ምርጥ ደንበኞች ) መካከል ሳውዲ በሁለተኛነት ነበር ስሟ ቂብ ብሎ የወጣው ምንም እንኳን ባለስልጣናቱ ኡኡ ቢሉም !!
ይሄን ውድና ብዛት ያለው የአልኮል መጠጥ የሳውዲን የማያፈናፍን የአልኮል መጠጥ ከልካይ ህግ አሳልፈው ያስገቡት አበሾች ናቸው የሚል ሰው ካለ የዋህ መሆን አለበት !! ሳውዲ ውስጥ በድብቅ መጠጥ የሚሸጡ የየትኛውም አገራት ዜጎች መጠጡን የሚረከቡት በሚሊየን ዶላር ኢንቨስት አድርገው ይሄንኑ ንግድ ከተያያዙት ሃብታም እና ባለስልጣናት ጋር ከተወዳጁ የሳውዲ ዜጎች ነው፡፡
ለሽርሙጥናውም ቢሆን የአበሻ ሴቶች አገራቸው ላይ ባይሄዱም በየምክንያቱ ወደኢትዮጲያ ብቅ እያሉ በትልልቅ ሆቴሎች እና በየተከራዩት አፓርታማቸው በሴተኛ አዳሪነት ላይ ከተሰማሩ ሴቶች ጋር ሲያመነዝሩ ቆይተው የሚመለሱት እነዚሁ ከሳውዲ ‹‹ንፁሃን ዜጎች›› የወጡ ናሙወች ናቸው !! ሽርሙጥናን ያስተማሯቸው አበሾች አይደሉም እንደውም እኛ አበሾች እራሳችን ይህን ፀያፍ ድርጊት ከአረቦቹ በኋላ ጣሊያኖች ያመጡብን ቁሸት ነው !!
የሚገርመው ይሄ ተራው ዜጋ ቀርቶ የንጉሳዊያን ቤተሰቦች እና የሳውዲ ታላላቅ ሰወች ሳይቀሩ ታላቁ የእረመዳን ወር ሲገባ ከፆሙ ሽሽት ወደ አውሮፓና አሜሪካ እንደሚፈረጥጡ የሆቴሎቹ መረጃ ያሳያል … በረመዳን ወር ታላላቅ የቅንጦት ክፍሎችና መዝናኛ ስፍራወች በባለሃብት አረቦች (የሚበዙት የሳውዲ ዜጎች ) ይያዛሉ ! ኦሳማ ቢላደን አንዴ ሲናገር የሳውዲ የነገስታት ቤተሰቦችንና ባለሃብቶችን ‹‹ከእምነት የራቁ በምእራባዊያን ብልጭልጭ እንደልጅ የተገዙ የነቀዘ ስነልቦና ያላቸው ›› ብሏቸው ነበር
እና እነዚህ በመጠጥ በዝሙትና በቅንጦት የነቀዙ ዱርየወች ሳውዲ ላይ ከበረዶ የነጣ ጀለቢያቸውን ለብሰው ጥምጣማቸውን አሳምረው በእነሱ ስራ ወገባቸው ጎብጦ አምስት አስር ለደሃ ቤተሰቦቻቸው የሚልኩ እህቶቻችንና ወንድሞቻችንን ‹‹ አበሾች አነቀዙን ›› ሲሉ መስማት ይገርማል ፡፡ ማንኛውም አገር ፍፁም ዜጋ የለውም …. ያጠፋን ሲቀጡ ግን ፊት እያዩና በድህነት ልክ ሳይሆን ፈጣሪን በመፍራትና ሰበአዊነትን በማክበር መሆን አለበት !!
አሜሪካዊያን አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪወች ሳውዲ ውስጥ ተይዘው ያውቃሉ ያውም ሴቶች…. በሴተኛ አዳሪነት ተሰማርተው ተይዘውም ያውቃሉ የሳውዲ መንግስት ግን እንደአምባሳደር በክብር ነበር ወደአገራቸው የሸኛቸው …ሳውዲ ውስጥ ምእራባዊያን እንዳሻቸው ሲዝናኑ ዜጎቻቸው ጋር ሲያመነዝሩ የሳውዲ ፖሊሶች ድመት ናቸው ! ደሃ አገራት ላይ ግን አንበሳ !
ይህ በፈጣሪ ህግ የሚመራ አገር አለኝ ከሚል መንግስት የማይጠበቅ ፀያፍ ድርጊት ነው !! ፈጣሪ የሰው ፊት አያይም ! ፈጣሪ ሃብት እና ምድራዊ ሃይል ተመልክቶ አያደላም …. ፈጣሪ አንዱን ፈርቶ ሌላውን በድህነቱ ምክንያት አይንቅም !
የሳውዲወች የሰሞኑ አጠቃላይ እርምጃ ህዝቡ በጓዳው ሲሰራ የኖረውን በደል በመንግስት ደረጃ እውቅና እንደሰጠው የሚያሳይ የጅል ህዝብና የጅል መንግስት የተቀናጀ ግፍ ነው !! በኢትዮጲያዊያን ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው የደሃ ህዝቦች ላይ የተሰነዘረ የንቄትና የማን አለብኝነት አምባገነናዊ ጥቃት ነው !!
ኢትዮጲያዊያን የሳውዲ መንግስትንና ህዝባቸውን በሚጎዳ ህገወጥ ነገር ውስጥ ቢገኙ እንኳን አሁን በሚሄዱበት መንገድ መሄዳቸው ተቀባይነት የሌለው ብልህነት ያልታከለበት የጅል መንግስትና የጅል ህዝብ ድርጊት ነው ! ጅል መንግስት ደግሞ ከጅል ህዝብ ይወለዳል !
እኛም ኢትዮጲያዊያን ግፍ እየተፈፀመባቸው ባሉ ወገኖቻችን ላይ የባእድ ከበሮ ከመደለቅ ምንም ይሁኑ ምን ወገኖቻችን ናቸውና በዚህ የችግር ወቅት ከጎናቸው ልንቆም ይገባል ፡፡

No comments:

Post a Comment