Monday, December 3, 2012

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጉባዔ ተግባሩና ተግዳሮቱ


1. ህግ የማያከብር መንግስት
የኢህአዴግ መንግስት የፍትህ የዳኝነትና የፖሊስ አካላት እንዲቋቋሙ አድርጓል፡፡ እነዚህ የፍትህ አካላት አንዳንድ የሚወስዱትን ህገ-ወጥ እርምጃ ሳይ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሳይሆን የኢህአዴግን መንግስት ለሚቃወሙ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በአጠቃላይ የተለየ ሐሳብ የሚያራምዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመጫን የተመሰረቱ ይመስሉኛል፡፡ በማንኛውም ወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ ፖሊስ መጀመርያ ግለሰቡን ..ከኢህአዴግ የፖለቲካ ታማኞች.. አንዱ መሆኑን እና አለመሆኑን ከኢህአዴግ ባለስልጣናት ይሁንታ ካላገኘ የማሰር አቅም አይኖረውም፡፡ የፍትህ አካላትም ክስ የሚመሰረቱበትን የግለሰቡን ማንነት አስቀድመው ከኢህአዴግ የፖለቲካ ታማኞች ውጭ መሆኑን ማረጋገጥ የግድ ይላቸዋል፡፡ ዳኞችም እንግዲህ በአንፃሩ ከኢህአዴግ መንግስት በአመለካከት ያልተለዩ ከሆኑ ወንጀል ቢፈፅምም ተጠርጣሪ ጠያቂ አለበት ማለት ይከብዳል፡፡ የፖለቲካ ታማኝነቱ ሳይታወቅ የተከሰሰ ..አባል.. እንኳ በችሎት ላይ እያለም ክሱ እንዲሰረዝለት የሚደረግበት አጋጣሚ አለ፡፡

የኢህአዴግ መንግስት ሁሉም ዜጋ በህግ ፊት እኩል ነው እያለ ሲፅፍና ሲናገር እንሰማለን፡፡ ኢህአዴግ ይህንን ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በአመለካከት ከኔ እስካልተለያየህ ድረስ ማለቱ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በአስተሳሰብ የተለየ እስካልሆንክ ሰው ብትገድል እንኳ በእርቅ ነፃ መውጣት ትችላለህ፡፡ ስልጣንህን ተገን በማድረግ የህዝብ ንብረትና ገንዘብ ብትዘርፍ ዘመነኛ ተብለህ ልትሸለማለህ ትችል እንደሆነ እንጂ ሙሰኛ አያሰኝህም፡፡
2.ፀረ ዴሞክራሲያዊ መንግስት
የህግ የበላይነት ባልተከበረበት ሀገር ስለዴሞክራሲያዊ መብቶች ማንሳት ተገቢ አይደለም፡፡ ሁለቱን ለብቻቸው ነጥሎ ማየት ሁኔታውን ጎልቶ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ዴሞክራሲ እየገነባ እንደሆነ በየቀኑ ከመቶ ጊዜ በላይ ራሱ በሞኖፖል ይዞ በሚቆጣጠራቸው የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እየነገረን ነው፡፡ ..ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ.. ነው በሚለው ብሂል ሄደን እኔ የምኖርበትን ኢትዮጵያ ያለውን ሃቁን ብናይ እንኳን ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ተግባራት በላዩ ላይ ተንሰራፍቶበት ይገኛል፡፡ ተቃዋሚዎች መዘጋጃ ቤት ላይ ስብሰባ ህዝቡን ሲጠሩት አስቀድሞ ፖሊሲ በመላክና በማስፈራራት እንዲበተኑ ያደርጋል፡፡ የመንግስት ሰራተኛ ከሆነ በነጋታው ግምገማ እንቀመጥ ተብሎ በተቃዋሚዎች ስብሰባ የተገኘበትን እንደ ምክንያት በመፈለግ እንዲቀጣ ነጋዴ ከሆነ ደግሞ ግብር እንዲጨመርበት ይደረጋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሃሳብን በነፃ እንዳይገልፅ ታፍኖ እየኖረ ነው፡፡
ሌላው ይቅርና በየቀኑ ለሚገጥመው ችግር እንኳ አቤት ማለት አይችልም፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት ችግሮች አንዱ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ነው፡፡ በወር ሁለት ጊዜ ብቻ ውሃ የሚያገኝ ቀበሌ አለ፡፡ ህዝቡ ለእንደዚህ አይነት ችግሮች ለባለስልጣናት አቤት ማለት ሳይፈታ ሲቀርም በሰላማዊ ሰልፍ ችግሩን ለመግለፅ አይፈቀድለትም፡፡ በኑሮ ውድነት አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እየተሰቃየ ባለበት ወቅት ህወሓት/ኢህአዴግ እኛ ከሌለን ትግራይ/ኢትዮጵያ ተበታተናለች፤ ህዝቡም ይጠፋል የሚል መዝሙር እንዲዘመር ያደርጋል፡፡
የመንግስት ሰራተኛው፤ ባለስልጣናት የሚፈፅሙትን የሙስና ቅሌት እያዩ ለማጋለጥ አይችሉም፡፡ በወገን፣ በአድልዎ፣ በዘመድ አዝማድ የማይገባቸውን ጥቅም ሊያገኙ እያዩ እንዳላዩ፣ እየሰሙ እንዳልሰሙ ሆነው ቀኑን እየቆጠሩ ይገኛሉ፡፡
የመንግስት ሰራተኛ የህወሓት/ኢህአዴግ አባል ካልሆነ የተለየ አመለካከት አለው በሚልና ይህ አመለካከት ደግሞ ኢትዮጵያን የሚበታትን፣ የትግራይ /ኢትዮጵያ ህዝብ እንዳይኖር ስለሚያደርግ ግለሂስ አድርግ እየተባለ እየተገደደ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲ ተግባር አይደለም ትላላችሁ?
በተባበሩት መንግሥታት የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ሥርዓት ሦስት ዓይነት አደረጃጀት አለው፡፡ እነዚህም በዓለም አቀፍ ስምምነቶቹ የተመሠረቱት የተለያዩ አካላት (Treaty Bodies) የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር (OHCHR) እና የሰብዓዊ መብት ጉባዔ (Human Rights Council) ናቸው፡፡ 

ጉባዔው የቀድሞውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተክቶ በመሥራት ላይ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ለ60 ዓመታት የሰብዓዊ መብት የማስጠበቅ ተግባር ነበረው፡፡ የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን እ.ኤ.አ በኤፕሪል 2005 የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ያለበትን ሁኔታ ሲገልጹ፣ ‹‹…We have reached a point at which the commission’s declining credibility has cast a shadow on the reputation of the United Nation system as a whole, and where piecemeal reforms with not be enough.›› ዋና ጸሐፊው ይህንን ንግግር ባሰሙበት ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ኮሚሽኑን በሰብዓዊ መብት ጉባዔ ለመተካት ተስማማ፡፡ እ.ኤ.አ. ማርች 15 ቀን 2006 ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት በውሳኔ ቁጥር 60/251 ጉባዔውን መሠረተና ሥራውን አስጀመረ፡፡ 

ጉባዔው እንደተካው ኮሚሽኑ አዲስ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መስፈርቶችን የማዘጋጀትና በየትኛውም የዓለም ክፍል ለሚታይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መልስ የመስጠት ሰፊ ተግባር ተሰጥቶታል፡፡ ሆኖም በተባበሩት መንግሥታት ካሉት ሌሎች የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ሥርዓቶች በተለየ ጉባዔው የሚመረጠው ከአገሮች ከተመረጡ ተወካዮች ነው፡፡ ባለሙያዎች የማማከር አገልግሎትና በሌሎች ልዩ ሥርዓቶችና ጉዳዮች (Special procedure and thematic areas) ዕርዳታ ከሚያደርጉ በቀር የጉባዔው ዋና ተግባር የሚከወነው በአገሮች ተወካዮች ነው፡፡ ጉባዔው እስካሁን በአጭር ጊዜ ከኮሚሽኑ የተሻሉ ሥራዎችን እንደሠራ የሚነገርለት ቢሆንም፣ የተወሰኑ ተግዳሮቶችና ትችቶች ይቀርቡበታል፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ በአዲስ አባልነት ጉባዔውን ከሚቀላቀሉት አገሮች መካከል አንዷ በመሆን ተመርጣለች፡፡ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 12 ቀን 2012 በተደረገው ምርጫ ኬንያ፣ ኮትዲቮር፣ ጋቦንና ሴራሊዮን ከአፍሪካ ተጨማሪ የክልሉን ውክልና ያገኙ አገሮች ሆነዋል፡፡ በአመራረጡ ሥርዓት ሒደት ኢትዮጵያን ጨምሮ በተወሰኑ አገሮች ላይ የተወሰኑ ተግዳሮቶች በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የቀረበ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት አባል አገሮችን አብላጫ ድምፅ በማግኘት የጉባዔው አባል ሆናለች፡፡ አባልነቱ ለአገሮች የራሱ የሆነ ፋይዳ ያለው ሲሆን፣ ከአባልነቱ ጎን ለጎን ከኢትዮጵያ የሚጠበቁ ዕርምጃዎች መኖራቸው የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ስለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጉባዔ አመሠራረት፣ ተግባርና ተግዳሮት ግንዛቤ የሚፈጥር ትንተና ከማድረግ ጎን ለጎን አገራችን አባል ሆኖ የመመረጧን ፋይዳ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡   

ከኮሚሽን ወደ ጉባዔ
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ1946 ሲሆን 52 አባል አገሮች ነበሩት፡፡ የኮሚሽኑ አባላት የአምስት ክልላዊ ቡድኖችን የሚወክል ሲሆን፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን መስፈርቶች (Standards) እንዲያዘጋጅ ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር፡፡ በዚህም እ.ኤ.አ በ1948 የፀደቀውን የሰብዓዊ መብቶች ሁሉን አቀፍ መግለጫን (Universal Declaration of Human Rights) አዘጋጅቷል፡፡ ኮሚሽኑ በሥራው የአገሮችን ሉዓላዊነት ማክበርን በጥንቃቄ መመልከቱ አጠቃላይ የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎችን መከታተል ላይ ትኩረት ይሰጥ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. 1967 ጀምሮ ግን አገር ተኮርና የተለያዩ ጉዳዮችን የተመለከቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መመልከት ጀመረ፡፡ ሆኖም ይህ ተግባሩ ሥራው ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረውና አገሮች ኮሚሽኑን መደበቂያና ጠላቶቻቸውን ማጥቂያ ሲያደርጉት እንደቆዩ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡  

የሰሜን/ደቡብ የሰብዓዊ መብት ፖለቲካዊ ልዩነትም የኮሚሽኑን መተማመን አሳጥቶታል፡፡ ሰሜኖቹ ኮሚሽኑ በሱዳን የሚፈጽመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን መከታተሉን ሲያደንቁ፣ እስራኤልንና አሜሪካን ያለአግባብ ተጠያቂ ማድረጉን ይቃወማሉ፡፡ ደቡቦቹ ደግሞ ተቃራኒ ሐሳብ በማራመድ የአሜሪካና የእስራኤል ተጠያቂነት በቀላሉ ስለመታየቱ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ልዩነት ጠርዝ የያዘው ሱዳን እ.ኤ.አ በ2001 የኮሚሽኑ አባል ስትሆንና እ.ኤ.አ በ2004 ደግሞ ዳግም ስትመረጥ ሲሆን፣ ሊቢያም እ.ኤ.አ በ2003 ኮሚሽኑን የመሰብሰብ ዕድል ሲያጋጥማት የሰሜኖቹ በኮሚሽኑ ላይ የነበራቸው መተማመን ተሟጧል፡፡ ከዚህም የከፉ ሌሎች ምክንያቶች እንደነበሩ ጽሑፎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታትም በኮሚሽኑ ላይ መተማመኑን ማጣቱን በአደባባይ መግለጽ ጀመረ፡፡ ከላይ በመግቢያው የተመለከትነው የኮፊ አናን ንግግር ለዚህ በቂ አስረጅ ነው፡፡ 

የጉባዔው አመሠራረትና ተግባር
ለጉባዔው መመሥረት ምክንያት የሆነው የቀድሞው ኮሚሽን የነበረበትን ችግር ለመቅረፍና የሰብዓዊ መብት አከባበርን ለማሳደግ ታስቦ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ. ማርች 15 ቀን 2006 የሰብዓዊ መብት ጉባዔ እንዲቋቋም ውሳኔ (Resolution) አስተላለፈ፡፡ ውሳኔው በመግቢያው ጉባዔው ኮሚሽኑን ለመተካት እንደተጠቀመና ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት መከበር እንዲኖር እንደሚሠራ ይገልጻል፡፡ በዚሁ መሠረት ጉባዔው ኮሚሽኑ የሚሠራቸውን ሥራዎች የማያስቀጥል ሲሆን፣ በተጨማሪም ጉባዔው በአባል አገሮች ላይ ሁሉ አቀፍ ወቅታዊ ግምገማ (Universal Periodic Review) የማከናወን አዲስ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ሥርዓት የሁሉም የተባበሩት መንግሥታት አባል አገሮች የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ሁኔታ እንዲገመገም የሚፈቅድ በመሆኑ፣ በኮሚሽኑ የተወሰኑ አገሮች ላይ የማተኮር ችግርን እንደሚቀርፍ ይታመናል፡፡ ይህ ግምገማ በየአራት ዓመቱ በአገሪቱ ላይ የሚደረግ ሲሆን፣ የራሱ ሥርዓትና አካሄድም ተዘጋጅቶለታል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2009 ሪፖርት ያቀረበች ሲሆን፣ በጉባዔው የተሰጡትን አስተያየቶች ለመተግበር ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ማዘጋጀቷ ይታወቃል፡፡ ከግምገማው ባለፈ ጉባዔው ማንኛውም የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የመመርመርና ለጠቅላላ ጉባዔው ሪፖርት የማድረግ ሥልጣን የተሰጠው በመሆኑ ኮሚሽኑ ያከናውናቸው የነበሩ የልዩ ገለልተኛ ሥርዓቶቹና የተወሰኑ ጉዳዮችን የመመልከት ተግባራት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የማሳተፍ፣ የቴክኒክ ድጋፍ፣ የግለሰብ አቤቱታ ሥርዓትን ሁሉ እንዲያካትት ተደርጓል፡፡    

ንጽጽራዊ ምልከታ
የጉባዔውን ተግባርና አመራረጥ ከኮሚሽኑ ጋር በሚደረግ ንጽጽር ማየት የጉባዔውን ድርሻ የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ጉባዔው 47 አባል አገሮች ይኖሩታል፡፡ ኮሚሽኑ በ53 አገሮች ይመራ ነበር፡፡ የጉባዔው ቁጥር እንዲያንስ የሚፈልጉ ምዕራባውያን ጥረታቸው ባለመሳካቱ የጉባዔው አባላት ቁጥር አሁንም ቢሆን መብዛቱን ይገልጻሉ፡፡ ከኮሚሽኑ በተሻለ ጉባዔው ለሰብዓዊ መብት አፈጻጸም የተሻሉ ምቹ ሁኔታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው አደረጃጀቱ ነው፡፡ ኮሚሽኑ የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጉባዔ (ECOSOC) ተቀጽላ አባል የነበረ ሲሆን፣ የሰብዓዊ መብት ጉባዔው ግን የጠቅላላ ጉባዔው (General Assembly) አካል ሆኗል፡፡ ይህ ጉባዔው በተባበሩት መንግሥታት የተሻለ ተሰሚነት ያለው እንዲሆን፣ እንዲታይና የጠቅላላ ጉባዔውን ቀጥተኛ ድጋፍ እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡ ሁለተኛው የሰብዓዊ መብት ጉባዔው ቋሚ አካል ተደርጎ በመቋቋሙ በዓመት ሦስት ጊዜ ለአሥር ሳምንታት አስፈላጊ ሲሆንም ልዩ ስብሰባዎችን ያደርጋል፡፡ ይህ ጉባዔው በዓመት አንድ ጊዜ ለስድስት ሳምንታት ከሚሰበሰበው ኮሚሽን የተሻለ ቋሚ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ሦስተኛውና ዋናው ጉባዔው ከተጨመረለት ተግባር የሚመነጭ ነው፡፡ ጉባዔው የተባበሩት መንግሥታት አባል አገሮችን የአቻ ለአቻ ግምገማ (Universal Periodic Review) በማቋቋሙና በመተግበሩ የአገሮችን ሰብዓዊ መብት የመፈጸምን ቁርጠኝነት ያጠናክራል፡፡

የጉባዔው አመራረጥ
ጉባዔው ከኮሚሽኑ የሚለይበት ሌላው ነጥብ የአባላቱ አመራረጥና እጩዎቹ የሚመረጡበት መስፈርት ነው፡፡ የጉባዔው አባል አገሮች የሚመረጡት በተወሰነው የክልላዊ ስብጥር ሲሆን፣ አገሮች በቀጥታና በነጠላ በሚስጥር በሚሰጥ ድምፅ ይመረጡና የጠቅላላ ጉባዔውን አብላጫ ድምፅ እንዲያገኙ ይጠበቃል፡፡ የኮሚሽኑ አባልነት ምርጫ ይከናወን የነበረው በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉባዔ (ECOSOC) 54 አባላት ሲሆን፣ ያለምርጫ ቀድሞ በተደረገ ክልላዊ ስምምነት ነው፡፡ ይህ የኮሚሽኑ አመራረጥ አጠያያቂ የሰብዓዊ መብት ሪከርድ ያላቸው አገሮች የኮሚሽኑ አባል እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ 

የሰብዓዊ መብት ጉባዔው አባል አገሮች ሲመረጡ አገሮች በቀጥታ የእጩዎቹን አገር የሰብዓዊ መብት ሪከርድና ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅን ለማሻሻል የሚገቡትን ቃል በመመዘን ይወስናል፡፡ እንዲህ ዓይነት የምርጫ መስፈርት በኮሚሽኑ ወቅት አልነበረም፡፡ በጉባዔው እስካሁን የሚመረጡ አገሮች ሰብዓዊ መብትን ለማሻሻል በፈቃደኝነት ቃል ይገባሉ፡፡ የተመረጡ አገሮች ደግሞ ሁሉም በጉባዔ የአባልነት ቆይታቸው የአቻ ለአቻ ግምገማ ያከናውናሉ፡፡ በጉባዔው የተመረጡ አገሮች በሰፊና  ወጥ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ኃላፊ ሆነው ከተገኙ ጠቅላላ ጉባዔው ከአባልነት ሊያነሳቸው ይችላል፡፡ የጉባዔው አባልነት መለዋወጥንም ለማበረታታት አንድ አገር ጉባዔውን ሳይለቅ ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ መመረጥ አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነት የምርጫ ገደብ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት በኮሚሽኑ እንደነበራቸው ዓይነት ቋሚ ቦታ ላያገኙ የሚችሉበትን አጋጣሚ ያስተገብራል፡፡

የጉባዔው ተግዳሮቶች
ጉባዔው ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም የሠራውን መልካም ሥራ ያክል የተወሰኑ ተግዳሮቶች አሉበት፡፡ ጉባዔው የተመሠረተበትን ጊዜ፣ የአጠባበቅ ክፍተት (Protection gap) መፈጠሩንና ሥራውን በተመለከተ የተለያዩ ሐሳቦች ይንፀባረቃሉ፡፡ ከተለያዩ መረጃዎች ለዚህ ጽሑፍ በሚጠቅም መልኩ ተግዳሮቶችን ጠቅለል አድርገን ለማቅረብ እንሞክር፡፡   

የመጀመሪያው ከጉባዔው የመጀመሪያ ምሥረታ ጋር በተያያዘ የታዩ ችግሮች ናቸው፡፡ ጉባዔው እንደተቋቋመ አደረጃጀቱን የማጠናከር ሥራዎች ላይ አተኩሯል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ታዛቢዎች የማደራጀቱ ሥራ ቀድሞ ቢከናወን ኖሮ ጉባዔው እንደተመሠረተ በዓለም ላይ በተፈጠሩት የሰብዓዊ መብት ቀውሶች ውስጥ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ የኮሚሽኑ ሥራ ማቆም አሳማኝ የነበረ በመሆኑ ያለበቂ ዝግጅት ጉባዔው በፍጥነት ተቋቁሟል፡፡ ይህም ጉባዔው ሊሠራቸው የነበሩ ሰብዓዊ መብቶችን የመጠበቅ ክፍተት እንዲኖር አድርጓል፡፡ 

ሁለተኛው ጉባዔው ሥራ ከጀመረ በኋላ ይመለከታቸው የነበሩ አገር ተኮር ጉዳዮች ላይ የሚቀርብ ትችት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሰብዓዊ መብት ቀውሶች የነበሩባቸውን አገሮች (ዳርፉር፣ በርማ፣ ኮሎምፒያ፣ ሶማሊያ ወዘተ.) በተመለከተ ዕርምጃ ለመውሰድ መቸገሩንና ቤላሩስና ኩባን የመሰሉ አገሮች ላይ ጉባዔው የጀመረውን ዕርምጃ ማቋረጡ በአንዳንዶች በማሳያነት ይቀርባል፡፡ ከዚህም ሌላ እንደ ኮሚሽኑ ጉባዔው እስራኤልን የመሳሰሉ አንዳንድ አገሮችን በመለየት ውግዘት ማብዛቱን ይገልጻል፡፡ ጉባዔው አገር ተኮር የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎች ላይ ማተኮሩ ከተሰጡት ሌሎች ተግባራት እንዳያዘናጋው ሥጋት አለ፡፡

ሦስተኛው ተግዳሮት ከጉባዔው አባልነት ጋር በተያያዘ የሚነሳ ነው፡፡ ጉባዔው ለአባልነት በኮታ ከመምረጥና በአብላጫ ድምፅ ከማፀደቅ ሌላ መስፈርት አለማስቀመጡ ያስተቸዋል፡፡ የጉባዔው መመሥረቻ ሰነድ አባሉ ሰብዓዊ መብትን በማስፋፋትና በማስጠበቅ ያደረገውን አስተዋጽኦ ከግምት እንዲገባ ቢደነግግም፣ አፈጻጸሙ ከሐሳቡ የራቀ ይመስላል፡፡ በአንድ ጽሑፍ አሜሪካዊ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሁኔታውን ሲገልጽ፣ ‹‹No state, no matter how poor its human rights record, is barred from membership. Even states under security council sanction for human right abuse, may become member›› ይላል፡፡ ሌሎች ደግሞ የጉባዔው አባልነት ምርጫ የውድድር መንፈሰ የሌለበት መሆኑ የአባላቱ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ እንዳይታይ ያደርገዋል ይላሉ፡፡ ይህን ሐሳብ እንደሚያራምዱት ሰዎች አመለካከት በተለይ ከአፍሪካ፣ ከእስያና ከላቲን አሜሪካ የሚቀርቡ እጩዎች ካለው ክፍት ወንበር ጋር ተመጣጣኝ ስለሚሆን መመረጣቸው አይቀሬ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይህም የኮሚሽኑ ተግባርና አካሄድ እንዳይደገም ማሥጋቱ አልቀረም፡፡ በሌላ በኩል ግን የአባልነት መስፈርት ከዚህ በፊት ከነበረው የኮሚሽኑ መስፈርት የተሻለ በመሆኑ እጩዎች የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎችን ለመሻሻል ቃል እስከገቡ ድረስ ጠቀሜታው ሊዘነጋ አይገባም፡፡

ሌላው ተግዳሮት ከአቻ ለአቻ ግምገማው ጋር በተያያዘ የሚገቡ ሥጋቶች ናቸው፡፡ ይህ የጉባዔው ተግባር አዲስ እንደመሆኑ መጠን በጥንቃቄና በተገቢው ክትትል ካልተሠራ ትርጉም እንዳያጣ ሥጋታቸውን የሚገልጹ ምሁራን አሉ፡፡ በዚህ ረገድ የባለሙያዎች በሒደቱ አለመሳተፋቸውና የመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተሳትፎ ገደብ ተጠቃሽ ነው፡፡ የግምገማው ሒደት በተገምጋሚው አገር መመራቱ፣ የግምገማው ጊዜ ማነሱና በጉባዔው የሚሰጡ አተያየቶች አተገባበር በጊዜ አለመወሰኑ ወዘተ. በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚነሱ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

ጉባዔውና ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት ጉባዔው የምትታወቀው በተገምጋሚነት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ኦገስት 4 ቀን 2009 ኢትዮጵያ ለጉባዔው ከሰብዓዊ መብት አከባበር አንፃር ያላትን የሕግ ማዕቀፍና የሰብዓዊ መብት መሠረተ ልማት ያጋጠማትን ተግዳሮትና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የምትፈልገውን ትብብር በሪፖርት አካትታ አቅርባለች፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥምረትም ተያያዥ ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን፣ ጉባዔው የኢትዮጵያን ሪፖርት ገምግሞ 148 አስተያየቶች ሰጥቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 98ቱን ኢትዮጵያ ተቀብላ ለመተግበርና ለማስተካከል ቃል ገብታለች፡፡ ሌሎቹን የተወሰኑትን ኢትዮጵያ እያሰበችበት መሆኗንና በቅርብ ጊዜ እንደምታሳውቅ የገለጸች ሲሆን፣ የተወሰኑትን ደግሞ አለመቀበሏን የጉባዔው ግምገማ ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያ ካልተቀበለቻቸው ውስጥ የሞት ቅጣትን ማስቀረት፣ የሰብዓዊ መብት ጉባዔ ልዩ ሥርዓቶችን መጋበዝ፣ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅን መከለስ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን መፍቀድ የተወሰኑት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን አስተያየቶች ለመተግበር ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር በመቅረፅ እየንቀሳቀሰች መሆኑም ተገልጿል፡፡ 

ጉባዔውና ኢትዮጵያ ከግምገማ ውጭ የሚያገናኛቸው ነገር ደግሞ በዚህ ሳምንት ተከስቷል፡፡ ይኸውም ኢትዮጵያ የጉባዔው አባል ሆኖ የመመረጧ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 18 ቀን 2012 በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ የጉባዔው አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ በአብላጫ ድምፅ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ አባልነት ቀድሞውንም በአፍሪካ ኅብረት የተደገፈና ክፍት የነበረው የክልሉ መቀመጫ ከእጩዎች ጋር ተመጣጣኘ በመሆኑ መመረጧ አጠራጣሪ አልነበረም፡፡ ሳራ ትሪስተር የተባሉ የፍሪደም ሃውስ የሥራ ኃላፊ፣ ‹‹Assessing the 2012 UN Human Rights Council elections: One third of candidates un qualified membership›› በሚል ጽሑፋቸው ከተመረጡት አገሮች ውስጥ ከምዕራባውያን ውጪ የነበሩት እጩዎች ቀድሞውኑ ቦታውን እንደሚያገኙ የታወቀ ነበር ይላሉ፡፡ ጸሐፊው አገሮች ለጉባዔው በአባልነት ለመመረጥ ቢያንስ 97 ድምፅ ማግኘት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ እስካሁን በነበሩት ምርጫዎች ድምፅ ሳያገኙ የቀሩ እንዳልነበሩ ይገልጻሉ፡፡

እንደ እርሳቸው አገላለጽ፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ጥሩ መዝገብ የሌላቸው ኢትዮጵያ ኩባ፣ ሊቢያና ሳዑዲ ዓረቢያ ሳይቀሩ መመረጣቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ኢትዮጵያን በተመለከተ ቀላል የማይባል ፈተና ተጋርጦ እንደነበር የመንግሥት ባለሥልጣናት በቴሌቪዥን በቀጥታ ስርጭት ቀርበው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ እንደ ፍሪደም ሃውስ ግምገማ ከአፍሪካ የቀረቡት እጩዎች በሰብዓዊ መብት መዝገባቸውና በተባበሩት መንግሥታት ድምፅ አሰጣጥ ታሪካቸው ለመመረጥ የማይመከሩ (Not recommended) እና አጠያያቂ (Questionable) በሚል ተፈርጀዋል፡፡ የሆኖ ሆኖ ሁሉም የአፍሪካ እጩዎች የጉባዔውን አባልነት አግኝተዋል፡፡

ከጉባዔው አባልነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ የሰብዓዊ መብት ሪኮርድ ሥጋቶች ከጉባዔው ዓላማ አንፃር ሲታይ ውኃ የማይቋጥር ሊሆን ይችላል፡፡ ሲጀምር ለጉባዔው ጠቃሚ የሚሆነው የአባሉ ተሳትፎ (Engagement) እንጂ ጥራት (Quality) አይደለም፡፡ የጠቅላላ ጉባዔው ኃላፊነቱን እንደሚወጡ በአብላጫ ድምፅ የተቀበላቸው አባላት ለመሥራታቸው በቂ ዋስትና ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ግን የጉባዔው ዓላማ ጥሩ የሚባል መዝገብ ያላቸውን በአንድ ቅርጫት ማሰባሰብ ሳይሆን አገሮች በጋራ ለሰብዓዊ መብት እንዲሠሩ ማስቻል ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ የምዕራብ አገር አምባሳደር፣ ‹‹The whole idea of the council was not to pick the good guys as its members, because there are none but to bring member states together to negotiate the best outcome for human rights as peers›› ሲሉ የተናገሩት ይህን በአግባቡ ይገልጸዋል፡፡ 

ሌላው ግን መታየት ያለበት አገሮች የጉባዔው አባል ለመሆን የሚገቡት ቃልና ተስፋ ነው፡፡ አገሮቹ የጉባዔው አባል ከሆኑ በኋላ የገቡትን ቃል ለመፈጸም የተሻለ የሞራል ግዴታ ስለሚሰማቸው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት አያያዛቸውን እንደሚያሻሽሉ ተስፋ ማድረግ ብልህነት ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ለአባልነት ስታመለክት ወደ ሦስት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን ለመፈረም ቃል መግባቷ፣ በሁሉ አቀፍ ወቅታዊ ግምገማ የሚሰጡ አስተያየቶችን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን መግለጽ፣ እንዲሁም  ከጉባዔው ልዩ ሥርዓት (Special Procedure) ጋር በትብብር ለመሥራት ፈቃደኝነቷን መግለጽ በአገሪቱ ለሚወሰዱ የሰብዓዊ መብት ዕርምጃዎች ዋስትናና መሠረት መሆኑ አይቀርም፡፡ግን ይሆናል የሚለው አጠያያቂ ቢሆንም ማለት ነው ?

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጉባዔ አባል ሆና መመረጧ የራሱ ፋይዳ አለው፡፡ ሲጀምር የአባልነት ተሳትፎዋ በሰብዓዊ መብት አያያዝ የተሻሉ ከሆኑ አባል አገሮች ልምድ ለመውሰድ ትችላለች፡፡ በጉባዔው  የሚደረጉ ግምገማዎች፣ ምርመራዎችና ሪፖርቶች ኢትዮጵያ ከሌሎች በጎ ልምድ በመውሰድ የሰብዓዊ መብት ሕግጋትን ለመቅረፅ፣ ተቋማትን ለማደራጀትና ለማጠናከር ያስችላታል፡፡ ሌላው የአገሪቱ መልካም ገጽታም ይገነባል፡፡ ኢትዮጵያ አለኝ የምትለውን የሰብዓዊ መብት መዝገብ በመጠበቅና የጉባዔው አባል ለመሆን የገባቻቸውን ተስፋ በማማላት ገጽታዋን መቀየር ትችላለች፡፡ አገሪቱም በምርጫው ሒደት ተግዳሮት የሆኑባትን ትችቶች ለማስተባበልና የዜጎችን የሰብዓዊ መብት መከበር በልማት ዕቅዶቿ ውስጥ በማካተት ቁርጠኝነቷን ለማሳየት ዐቢይ አውድ ይሆናታል፡፡ኢትዮጵያ በሰብአዊ መብት ረገጣ ግንባር ቀደም አገር መሆኗ አያጠያይቅም! ምርጫውም በምን መስፈርት እንደሆነ አጠያያቂም ነው፡፡ግን የሚበጀውን ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እመኛለው !!
             ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!

No comments:

Post a Comment