Saturday, December 22, 2012

ኢትዮጵያ ላይ ላዩን ስትታይ፤ የተረጋጋች ሰላማዊ አገር ትመስላለች።

                                     ክፍል አንድ
ከመስረታዊው ጥያቄ የምንነሳ ከሆነ ግን፤ ለማሰብ የመፈለግና ያለመፈለግ ጉዳይ ካልሆነ በቀር የፓለቲካ ነገር እጅግ በጣም ቀላል ነው። 
“እያንዳንዱ ሰው፣ በራሱ ሃሳብና ውሳኔ፣ በራሱ ፈቃድና ምርጫ፣ የራሱን ሕይወት የመምራት ነፃነት ሊኖረው ይገባል ወይስ አይገባም?” ...ይሄው ነው ዋናው የፖለቲካ ጥያቄ። ለጥያቄው የምንሰጠው ምላሽ ደግሞ፣ ጠቅላላ የፖለቲካ አቋማችንን ይወስናል። ሌሎቹ የፖለቲካ አጀንዳዎች... መርሆችና ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂና ህጎች በመሉ ከዚህ ጥያቄ ዝርዝርና ምንዝር ናቸው። ጥያቄውን ገልብጠን ልናየው እንችላለን። “የሌሎችን ሕይወት እንዳሻው የማዘዝ ስልጣን የያዘ አካል መኖር አለበት ወይስ የለበትም?”... የፖለቲካ መሰረታዊ ጥያቄ የዚህን ያህል ቀላል ነው። ጥያቄው፣ ጥቅም የሌለው ጊዜ ማሳለፊያ ወይም ጊዜ ማጥፊያ እንደሆነ አድርገን የምንቆጥረው ከሆነ፤ ጥርት አድርገን ለማሰብ አለመፈላጋችንን ያመለክታል። ራሳችንን ለመሸወድ ስንፈልግ ነው፤ ጥያቄውን የምናጣጥለው። አመቺ መስሎ ሲታየንማ፤ “መብቴ ነው፤ ንብረቴ ነው፤ ነፃነቴ ነው፤ በራሴ ሃሳብና ምርጫ የራሴን ሕይወት መምራት መብቴ ነው” ብለን እንከራከራለንኮ። ግን ይህንን ሃሳብ ከምር መሰረታዊ የፖለቲካ መርህ አድርገን ልንቀበለው አንፈልግም። ለምን ቢባል፣ ያልተመቸን ጊዜ፣ “ከግለሰብ መብትና ነፃነት በፊት የአገር ልማት፣ የህዝብ ጥቅም፣ የብሄር ብሄረሰብ ተዋፅኦ ይቀድማል” እንላለን። ለአገር ልማት በሚል ሰበብ ቅድሚያ ብድር ለማግኘት፣ ለህዝብ ጥቅም ተብሎ በሌሎች ሰዎች ላይ የዋጋ ተመን እንዲታወጅ፣ የብሄር ብሄረሰብ ተዋፅኦ በሚል ሰበብ ስልጣን ለመሻማት ስንፈልግ፤ የግለሰብ ነፃነትን እናጣጥላለን። አመቺ ሆኖ ሲታየን፤ “የሃሳብና የሃይማኖት ነፃነት፣ የመደራጀትና የመምረጥ መብት ይከበር” እንላለን። የማይመቸን ሃሳብ ለማፈንና በሰዎች ህይወት ላይ ለማዘዝ ስንፈልግ ደግሞ፤ “ከግለሰብ ነፃነት በፊት፣ አገራዊ መግባባትና የሃይማኖት ትዕዛዝ ይቀድማል” እንላለን። የነፃነት ነገር... እንደሁኔታው የምንጥለውና የምናነሳው፤ እንደአስፈላጊነቱ የምንክበውና የምንረግጠው፤ እንደአመቺነቱ የምንጮህለትና የምንጮህበት እንዲሆን እንፈልጋለን። ለዚህ ነው፤ መሰረታዊውን ጥያቄ የምናጣጥለው፤ ብዙም ልናስብበት የማንፈልገው። ነገር ግን፤ ልናስብበት ስላልፈለግን ብቻ መሰረታዊ ጥያቄነቱ አይሰረዝም። ሰው እስካለ ድረስ መሰረታዊው ጥያቄ ሁሌም ይኖራል። የነበረ፣ ያለና የሚኖር ጥያቄ ነው - በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም አገር - ዛሬ በዘመናችንና እዚ በአገራችን ጭምር።

የአገራችንና የዘመናችን ዋና ዋና የፖለቲካ አጀንዳዎች ብዬ የማስባቸው ርዕሰ ጉዳዮችም፣ ከዚሁ መሰረታዊ የግለሰብ ነፃነት ጋር የተያያዙ ናቸው - ከሃሳብ ነፃነት፣ ከመደራጀት ነፃነትና ከመምረጥ ነፃነት ጋር የተያያዙ። በአንድ በኩል ከመንግስት የሚነጩ ሶስት ፈተናዎች አሉ። የሰዎችን ሃሳብ በማፈን የሚካሄድ መንግስት ፕሮፓጋንዳ የግለሰብ የሃሳብ ነፃነትን ይጥሳል። 1ለ5 የተሰኘው አደረጃጀትን ጨምሮ በመንግስት የሚካሄድ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ የግለሰብ የመደራጀት ነፃነትን ይጥሳል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር የሌለበት የአንድ ገዢ ፓርቲ ገናናነት፣ የግለሰብ የመምረጥ ነፃነትን ይጥሳል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከተለያዩ ፓርቲዎች ወይም ቡድኖች የሚመነጩና የግለሰብ ነፃነትን የሚጥሱ ተጨማሪ ሶስት ፈተናዎች አሉ - የሃይማኖት አክራሪነት፣ በብሄር ብሄረሰብ የመቧደን ዘረኝነት፣ ለፖለቲካ ስልጣን ተብሎ የሚካሄድ አሸባሪነት። 
ከላይ የተጠቀሱት ሶስት ሶስት ፈተናዎችን፣ መንታ መንታ አድርገን ልናያቸው እንችላለን። የመንግስት ፕሮፓጋንዳም ሆነ የሃይማኖት አክራሪነት የመጠንና የስልት ልዩነት ቢኖራቸውም፤ “እኛ የነገርንህን ሃሳብ የግድ መከተል አለብህ” በማለት የግለሰብን የሃሳብ ነፃነት ይጥሳሉ። የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካና የዘረኝነት ቅስቀሳም እንዲሁ፤ “የትውልድ ሃረግ እየቆጠርክ ተደራጅ” በሚል የሚያስገድዱ ናቸው። የአንድ ገዢ ፓርቲ ገናናነትና የፖለቲካ አሸባሪነትም እንዲሁ፤ “የመምረጥ መብት የለህም፤ ያዘዝንህን ፈፅም” በሚል የፈላጭ ቆራጭ መንፈሳቸው ይዛመዳሉ። በሌላ አነጋገር፤ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው።ፈተናዎቹ፣ ለኢትዮጵያ የሰላምና የግጭት ጉዳይ መሆናቸውን ለመገንዘብ የሚያስቸግሩ አይመስሉኝም። በዚያው መጠን፣ የግለሰብ ነፃነት መከበርና አለመከበር፣ በሕይወት የመኖርና ያለመኖር፣ የብልፅግናና የድህነት ጥያቄ ነው ማለት ይቻላል - ለአገሪቱ የሰላምና የግጭት ጉዳይ ጋር የተቆራኘ ነውና። ለነገሩ፤ ኢህአዴግ “ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ ነው” እያለ በተደጋጋሚ እንደሚናገርና እንደሚፅፍ ይታወቃል። “የግለሰብ ነፃነት ለኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ ነው” ቢባል ይበልጥ ትክክለኛ ይሆናል። 
ኢትዮጵያ ላይ ላዩን ስትታይ፤ የተረጋጋች ሰላማዊ አገር ትመስላለች። ነገር ግን፤ በቀላሉ ልትቃወስ የምትችል አገር ነች። የአፈና ፕሮፖጋንዳ፣ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካና የአንድ ገናና ፓርቲ ስርዓት አገሪቱን ለሃይማኖት አክራሪነት፣ ለዘረኝነት ቅስቀሳና ለፖለቲካ አሸባሪነት እጅጉን የተጋለጠች እንድትሆን አድርጓታል። 
የፖለቲካ ነገር ጭራና ቀንዱ መግቢያና መውጫው የማይታወቅ፤ በዚህ በኩል ሲይዙት በዚያ የሚያፈተልክ ውስብስብ ጉዳይ የሚመስላቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም - አንዳንዶቹ ውስብስብነቱ ቢማርካቸውም ብዙዎች ይሸሹታል። ግን ከፖለቲካ የሚያመልጥ የለም። በታክስ ጫና ወይም በዋጋ ንረት ኑሯቸው የሚናጋው፤ በ97ቱ አይነት የምርጫ ቀውስ ወይም በሃይማኖትና በብሄረሰብ ግጭት ህይወታቸው አደጋ ላይ የሚወድቀው በፖለቲካ ምክንያት ነው። ሙስናና አድልዎ፣ ፕሮፓጋንዳና አፈና... የፓለቲካ ጉዳይ ናቸው። ከፖለቲካ መሸሽ፣ የትም አያደርስም። ተጋፍጠን ነፃና ዲሞክራሲ አገር መገንባት ብቻ ነው ያለን ዕድል! ዘረኛውን መንግስት ለመጣል ኢትዮጵያዊነት ስሜት ሊኖረን ግድ ይላል ያለበለዚያ አገርን ለበይ ሰቶ ዳር ሆኖ መመልከት ይሆናል !
                                                                        ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!
                                                                                            ከዘካሪያስ 

No comments:

Post a Comment