Tuesday, December 11, 2012

አበሻ እንኳን አሜሪካ ማርስ ላይ ቢወጣም መከፋፈሉ አይቀርም!



የዛሬውን ፖለቲካዊ ወግ በጥያቄ እንድጀምር ፍቀዱልኝ፡፡ ጥያቄው ደግሞ ለናንተ ነው፡፡
“በዘንድሮ የከፍተኛ ተቋማት ተመራቂዎች ላይ ምን ለየት ያለ ነገር አስተዋላችሁ?” በተለይ በኢቴቪ መስኮት ከምረቃ በኋላ ምን እንደሚሰሩ ሲነግሩን የሰነበቱትን ተመራቂዎች ማለቴ ነው፡፡ ተመራቂዎቹ ለኢቴቪ ጋዜጠኞች የሰጡትን ምላሽ የታዘቡ አንዳንድ ተመልካቾች፤ ሁሉም አንድ ዓይነት ጥያቄ ከነመልሱ የተሰጣቸው ይመስላሉ የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ ነገርዬውን ስታዩት ግን እውነት ይመስላል (መረጃ ማቅረብ ባይቻልም!)
“ከመንግስት ሥራ ጠባቂ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ መሆን ነው የምፈልገው” ከሁሉም “የኢቴቪ ተመራቂ” አንደበት የሚሰማ ምላሽ ነበር፡፡
ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ ባለድግሪ ኮብልስቶን ጠራቢዎችን አስመልክቶ ሁለት የአገሪቱ አንጋፋ ምሁራን በሰጡት አስተያየት፤ ማንም የፈለገውን ተምሮ የፈለገው ሥራ ላይ የመሰማራት መብት እንዳለው ገልፀዋል (በደንብ እስማማለሁ!)
ተመራቂዎቹም እየነገሩን ያሉት የልባቸውን ከሆነ “እሰየው” ብለናቸዋል (ንግግራቸው የተጠና ተውኔት ቢመስልም) አንድ ግልፅ ያልሆነልኝ ነገር ግን አለ - ተመራቂዎቹ “ሥራ ፈጠራ” የሚሉት ያንኑ ኮብልስቶን ይሆን እንዴ?

በነገራችሁ ላይ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁይነዲን ሳዶ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምረቃ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ፣ ሳይቸግራቸው ስለፈረደበት ኮብልስቶን አንስተው ተቃውሞ ገጥሟቸዋል አሉ - “ኮብልስቶን! ኮብልስቶን!” በሚል ጩኸት የታጀበ፡፡ ለነገሩ ተመራቂዎቹ ቢቃወሙም አይፈረድባቸውም፡፡ አያችሁ… ኮብልስቶን የመጣችው የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ እንደሆነ ተመራቂዎቹ ባይጠፋቸውም ባልተማሩት የሥራ ዘርፍ እንደተሰማሩ ሲቀሰቀሱ ግን ምን ያድርጉ… (ቢጨንቃቸው እኮ ነው!) ወይ ደግሞ ቀድሞውኑ በኮብልስቶን ሙያ ማስመረቅ የአባት ነው፡፡
እኔ የምለው … ለኢህአዴግ ድምፅ እየሰጠን 21 ዓመት ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ለዋልንለት ውለታ ምላሹ ኮብልስቶን ሆነ ማለት ነው? (በቀጣዩ ምርጫ ያገናኘን!) እንደው ለመሆኑ ግን… ኢህአዴግ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የሚያሰልፈን ለባለድግሪዎት የኮብልስቶን ሥራ እየሰጠ ነው  እንዴ? (እኔ አላማረኝም ያለው አቀንቃኝ ማን ነበር?)
ሰሞኑን ስለ ኮብልስቶን የተለቀቀውን “ሲንግል” ግን ሰምታችኋል? ኦሪጅናሉ ወይም መጀመሪያ ላይ የወጣው “የተማረ ይቅበረኝ አለች ኮብልስቶን” የሚል ሲሆን  ትንሽ ቆይቶ ተሻሽሎ የወጣው ደግሞ “የተማረ ይጥረበኝ አለች ኮብልስቶን” የሚል ነው፡፡ ይሄን ነጠላ ዜማ እንደሰማሁኝ እንደሌሎች ጓደኞቼ ሁሉ ፈገግ ማለቴን አልክዳችሁም፡፡ ትንሽ ቆይቼ ግን ስጋት ቢጤ አደረብኝ፡፡ ለምን መሰላችሁ? ዛሬ “የተማረ ይቅበረኝ…” ወይም “ይጥረበኝ” አለች ከተባለ፣ ነገ ደግሞ ተነስታ ድግሪ የሌለው አጠገቤ እንዳይደርስ ብትል የማን ያለህ ይባላል (ኮብልስቶንን ማለቴ ነው) እንዴ… ድግሪ አልባ የሆነው የአገሬ ወጣት ሁሉ… ሥራ አጥ (ፈት) መሆኑ አይደለ! እኔ በበኩሌ ለዚህ ችግር ተጠያቂ የማደርገው ሌላ ማንንም ሳይሆን ራሱን ኢህአዴግን ብቻ ነው (ወደደም ጠላም) እሱ አይደለም እንዴ… ለባለድግሪና ማስተርስ ተመራቂዎች ኮብልስቶንን እነሆ ያለው! አሁን ምን እንደ ሰጋሁ ታውቃላችሁ … ነገ ደግሞ አያ በሬ ተነስቶ “ባለድግሪ ብቻ ይረሰኝ” ቢለንስ? እውነቴን እኮ ነው… ገበሬው ና ልረስብህ ብሎ በሬውን በአለንጋ ዦጥ ሲያደርገው “የተማረ ገበሬ ቢሆን እኮ አይገርፈኝም ነበር” እያለ ሊያንጓጥጠው ይችላል፡፡ የኋላ ኋላም በሬዎች የሥራ ማቆም አድማ ሊመቱ ይችላሉ - “ያልተማረ ገበሬ አይነካንም” በሚል፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ ቀለም ያልዘለቀው የአገሬ አርሶ አደር ሁሉ አርሶ ላይበላ ነው ማለት ነው (ጦቢያም ፆሟን አደረች አትሉም!) ያን ጊዜ ታዲያ ኢህአዴግም ጉዱ ይፈላል (እሱስ የእጁን ነው!)
እንግዲህ ከ20 ዓመት በላይ እየተወዛገበም ቢሆን አብሮን የኖረውን የኢህአዴግን ዓመል አሳምረን እናውቅ የለ … አሁን ሽንጡን ገትሮ የሚከራከርለት “የኮብልስቶን ስትራቴጂ” ከጥቂት ጊዜ በኋላ “የታለመለትን ግብ ስቷል” ብሎ መገምገሙ አይቀርም፡፡ (ቢፒአርን ያስታውሷል!) እስከዛው ግን ለኮሌጅና ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች “ኮብልስቶን 101” የሚል ኮርስ ቢዘጋጅላቸው ተማሪዎችን ከምርቃት በኋላ ግራ ከመጋባት ያድናቸዋል የሚል የፈረጠመ እምነት  አለኝ፡፡ እኔ ግን ከሁሉም ያስፈራኛል ምን መሰላችሁ? የአዲሱ ትውልድ ነገር! (የህፃናቱን ማለቴ  ነው) ምን መሰላችሁ? አሁን ለምሳሌ አንዱን የጦቢያ ህፃን “ስታድግ ምንድነው መሆን የምትፈልገው?” ስትሉት “ኮብልስቶን ማንጠፍ ወይም መጥረብ” ቢላችሁስ? (ኢህአዴግ ደስታውን አይችለውም!)  ደግሞም የማይልበት አንዳችም ምድራዊ ምክንያት የለም፡፡ ህፃኑ በኢቴቪ የሚያየው እኮ የዩኒቨርስቲ ምሩቃን ሳይንቲስት ወይም ኢንጂነር አሊያም ሃኪም ይሆናሉ ሲባል አይደለም! ኮብልስቶን ይጠርባሉ ሲባል እንጂ! ህፃኗን ሴት “ስታድጊ ምን መሆን ትፈልጊያለሽ?” ስትሏት ደግሞ “እንደ እከሌ …አረብ አገር መሄድ” እንዳትላችሁ ነው መፍራት! ምን ታድርግ … የአክስት ልጅ፣ የጐረቤት ልጅ፣ ታላቅና ታናሽ እህት ሲሄዱ ነዋ የምታቀው - ሲሰደዱ! (አድነነ ከመዓቱ!)
ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ የተማረው የሰው ሃይል በኮብልስቶን “ሙያ” ላይ መሰማራቱ ለምን አጀንዳ ሆነ ያሉት የከተማና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር፤ ወደ ውጭ እየጐረፈ ያለው ኢትዮጵያዊ ባለድግሪና ባለማስተርስ በዘበኝነት ይሰራ የለም ወይ የሚል መከራከርያ ማቅረባቸውን ሰምቼ ሲገርመኝ ነው የሰነበተው፡፡ (ማን ነበር “እነዚህ ሰዎች ጤና የላቸውም እንዴ?” ያለው!)
እኔ ግን ምን ጠረጠርኩ መሰላችሁ? ኢህአዴግ በዩኒቨርስቲ 30/70 ያለው 30 ለሶሻል ሳይንስ፣ 70 - ለኮብልስቶን ማለቱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እንዴ የድግሪና የማስተርስ ነገር ሲነሳ እኮ ከኮብልስቶን ውጪ ሌላ ነገር ከአፉ አልወጣ ብሏል - አውራው ፓርቲያችን!!
ጦቢያን ከኮብልስቶን አንድዬ ይገላግላት ብለን ወደ ሌላ አጀንዳ እንለፍ፡፡ እኔ የምለው … ሰሞኑን ከወደ አሜሪካ የተናፈሰውን ወሬ ሰምታችኋል? ላለፉት 28 ዓመታት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ የሚያከብሩት የስፖርትና የሙዚቃ በዓል ባሳለፍነው ሳምንት ለሁለት ተከፍሎ መከበር መጀመሩን ማለቴ ነው፡፡ ነባሩ የሰሜን አሜሪካው የስፖርት ፌዴሬሽን የ29ኛ ዓመት ዝግጅቱን ካለፈው አርብ ጀምሮ በዳላስ እያካሄደ ሲሆን ከዋናው የስፖርት ፌዴሬሽን ተገንጥሎ የወጣው ቡድን፤ በሼህ አል አሙዲ ስፖንሰርነት በዋሺንግተን አር ኤፍ ኬ ስታዲየም ፕሮግራሙን ባለፈው አርብ ጀምሯል ተብሏል፡፡ ለሦስት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያውያን በጋራ ሲያካሂዱት የነበረው ዝግጅት ለሁለት የተከፈለበት ሰበብ ደግሞ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በክብር እንግድነት በመጋበዛቸው እንደሆነም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
እኔ በበኩሌ የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌዴሬሽን ለሁለት የተከፈለበት ምክንያት ተደርጐ የቀረበው ሰበብ ብዙም አላሳመነኝም፡፡ ወ/ት ብርቱካን በክብር እንግድነት ስለተጋበዙ አይመስለኝም ፌደሬሽኑ ለሁለት የተከፈለው፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት የተከፈለውን ቡድን አል አሙዲ ስፖንሰር ስላደረጉትም ነው ብዬ አላምንም፡፡ ለመከፈሉና ለመከፋፈሉ ሁነኛው ምክንያት አበሽነታችን ይመስለኛል፡፡ መርሳት የሌለብን ዋናው ቁምነገር ምን መሰላችሁ? አሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራ ወገኖቻችን እኮ ያው የአበሻ ደም ያላቸው ናቸው - ከአገራቸው ለረዥም ጊዜ ርቀው ስለኖሩ አበሽነታቸው ይለቃቸዋል ማለት አይደለም፡፡ የአበሽነት ደም እንዲህ በቀላሉ የሚለቅ እንዳይመስላችሁ (መራር ነዋ!)
እናም ነገርዬውን መመልከት ያለብን “ነብር ዥንጉርጉርነቱን…አበሻ መከፋፈሉን መተው ይቻለዋልን?” ከሚለው አዲስ አባባል አንፃር ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ ይሄኛው የመከፋፈል ዜና ብዙ የተወራለት ከወደ አሜሪካ ስለመጣ ይሆናል እንጂ እዚህ በአበሻ ምድር በጦቢያ ቢሆን እኮ እንደዜናም ላንሰማው እንችል ነበር፡፡ ለምን ብትሉ? መከፋፈል፣ መሰነጣጠቅ፣ መጠላለፍ፣ መወቃቀስ፣ መቦቃቀስ፣ መበታተን፣ መፈራረስ፣ ወዘተ የዕለት ተዕለት ህይወታችን ነዋ! ትዳር ይፈርሳል፤ ቤተሰብ ይበተናል፤ ማህበራት ይሰነጠቃሉ፤ ፖለቲከኞች ይጠላለፋሉ፤ … ፓርቲዎች ይሰነጣጠቃሉ … ወዘተ… በቃ አበሻ ካለ መከፋፈል አለ፡፡ ለ”ወንዱ” የአበሻ ልጅ መከፋፈል ብርቁ አይደለም እኮ (አይደንቀውም!)
ምናልባት በርቀት ለሚታዘበን መከፋፈሉ ያለው በፖለቲካው ጐራ ብቻ ሊመስለው ይችላል (ወይ እኛን አለማወቅ!) ሆኖም የሲቪል ማህበራት፣ አክስዮኖች፣ ዕድሮች፣ ጓደኛሞች ወዘተ ዋና ሥራቸው እኮ መከፋፈልና መሰነጣጠቅ ነው፡፡ እስቲ ስንት የደራስያን ወይም የመምህራን አሊያም የጋዜጠኞች ወይም ደግሞ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ማህበራት እንዳሉ ጠይቁ፡፡  አንዱ ሦስት ወይም አራት ቦታ መከፋፈሉን ትሰማለችሁ፡፡ ለምን?  የሚለውን ጥያቄ አስከትሉ፡፡ ይኼኔ የአበሽነትን ምስጢር በደንብ ትረዱታላችሁ፡፡ በአበሻ አገር በማህበር፣ በድርጅት፣ በአክስዮን፣ በኢንቨስትመንት፣ በፖለቲካ ወዘተ የተቋቋመ ወይም የተመሰረተ ….የፖለቲካ፣ የሙያ፣ የቢዝነስ፣ የጥበብ፣ የኢኮኖሚ፣ የመብትና የትምህርት ወዘተ ማህበርም ሆነ ድርጅት አሊያም ግንባር ለጊዜው አንድ መስሎ ይታይ እንጂ መከፋፈሉ አይቀሬ ነው፡፡ (“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለው ተረት ምንጩ ይጠና!)
እኔ እንደውም አንዳንዴ አውራው ፓርቲ ኢህአዴግ እንደ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዴት ሁለት ሦስት ቦታ አልተከፋፈለም ብዬ ራሴን እጠይቅና … ትዝ ሲለኝ  ኢህአዴግ ፈፅሞ ሊከፋፈል እንደማይችል እገነዘባለሁ፡፡ ግን እኮ ጠንካራ ሆኖ አይደለም! … የስልጣን ባለቤት ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ (ልከፈልስ ቢል ሥልጣን ትቶ ወዴት ይከፈላል?) እናም… ኢህአዴግን ከመከፋፈል የአበሻ አባዜ የገላገለው ሌላ ሳይሆን ሥልጣኑ ነው፡፡ (ማን ነበር “የኢህአዴግ ኦክስጂን ሥልጣን ነው” ያለው?) ከምሬ ነው… ኢህአዴግ የሥልጣን ባለቤት ባይሆንማ ኖሮ ይሄኔ 10 ቦታ ተሰነጣጥቆላችሁ ነበር፡፡ ለምን የተባለ እንደሆነ መልሱ … አበሻ ስለሆነ ነዋ!
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል … አበሻ አገር አብሮ ሰርቶ አብሮ መበልፀግ “ሃራም” ነው (ሃጢያት!) አብሮ መፈራረስና አብሮ መውደቅ ግን እንደ አበሻ የሚችልበት የለም - በደሙ ውስጥ ያለ ነዋ! (በነገራችሁ ላይ ፖለቲካው እንዲህ ውጣ ውረድ የሆነብን እኮ በሌላ አይደለም … በአበሽነታችን የተነሳ ብቻ ነው) እናም የዳያስፖራዎቹ ዓመታዊ የስፖርትና ሙዚቃ ፌስቲቫል ለሁለት ተከፍሎ መከበሩ ሊገርማችሁ ፈፅሞ አይገባም፡፡ ደሞ ነገርዬውን ዝም ብላችሁ አታጋኑት) ለምን መሰላችሁ? እንዲህ ስታጋንኑት … በሚመጣው ዓመት ደግሞ በእጥፍ ተከፋፍለው “ሰርፕራይዝ!” ሊሉን ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም አበሻ አንዴ መከፋፈል ከጀመረ በደንብ ነው ክፍልፍል የሚለው፡፡ አንዴ መሰንጠቅ ከጀመረ በደንብ ነው ስንጥቅጥቅ የሚለው፡፡ አንዴ መነጣጠል ከጀመረ በደንብ ነው ንጥልጥል የሚለው፡፡ አንዴ መገንጠል ከጀመረ በደንብ ነው ግንጥልጥል የሚለው፡፡ አንዴ መፈራረስ ከጀመረ በደንብ ነው ፍርስርስ የሚለው - ቆፍጣናው ሃበሻ!!
አያችሁ… የሰሜን አሜሪካው ዓመታዊ የስፖርት በዓል ለሁለት ተከፍሎ የተከበረው እንደተባለው አል አሙዲ ስፖንሰር በማድረጋቸው ወይም የአንድነት የቀድሞ ሊ/መንበር ወ/ት ብርቱካን የክብር እንግዳ በመሆናቸው አይደለም፡፡ ሁለቱም ሰበብ ናቸው - ተራ ሰበቦች!
የሰሜን አሜሪካው መከፋፈል መንስኤው ሌላ ሳይሆን አበሽነት ነው፡፡
እውነቴን እኮ ነው - የተከፋፈሉት በሌላ ምክንያት አይደለም! የአበሻ ደም ስላላቸው ብቻ ነው - (መራራ ደም!) የተከፋፈሉት እኮ ሃሞተ ኮስታራ ስለሆኑ ነው፡፡ (ይሄ ደግሞ ሊያኮራን እንጂ ሊያሳፍረን አይገባም)
አያችሁ… ማመቻመች፣ ማግባባት (መግባባት)፣ ማስማማት (መስማማት)፣ ማዋሃድ (መዋሃድ)፣ ማቀናጀት (መቀናጀት)፣ ማወያየት (መወያየት)፣ ወዘተ ለአበሻ ደም አይስማሙትም - አለርጂኩ ናቸው፡፡ ከአበሻ ደም ጋር የሚስማማው ወይም የሚዋደደው መከፋፈል፣ መጠላለፍ፣ መሰነጣጠቅ፣ መቃቃር፣ መወቃቀስ፣ መቡዋቀስ፣ መጠላላት፣ መተጋተግ፣ መገነጣጠል፣ መነጣጠል፣ መፈራረስ ወዘተ የሚሉት ናቸው፡፡ (ቀላል ሃብት እንዳይመስላችሁ!)
እዚህ አገር ያሉ አንዳንድ “ጨዋ” አበሾች ዳያስፖራዎቹን ሲወቅሱ ሰምቼ ተገረምኩ፡፡  “አሳፋሪዎች ናቸው! ገመናቸውን ሰው አገር…” እንዴት ነው ነገሩ … አበሻ እንኳንስ ሰው አገር (አሜሪካ) ይቅርና ማርስ ላይ ቢወጣስ ደሙ ይለወጣል እንዴ? አበሽነቱ ይቀየራል? ከመከፋፈል አባዜው ይላቀቃል? Never!!
ለማንኛውም ግን መተባበርና ማበር (እንደድር ቢያብር) እንዲሁም በህብረት ሆኖ በፍቅር መኖር ፈፅሞ ለማይደላው ቆፍጣናው የአገሬ ልጅ (አበሻ) የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህንን ግጥም እነሆ በረከት፡-
ፈራን ፍቅር ፈራን
ልጅነት የለገሰንን
የፍቅር ዓምላክ በጥበቡ
በረቂቅ ያለበሰንን
በመለኮት የቀባንን
ህብረት ፈራን… ፍቅር ፈራን… (መግባባት መደማመጥ ፈራን …)
                                  ኢትዮጵያ በክብር ለዘለለም ትኑር !!!

No comments:

Post a Comment