Saturday, December 8, 2012

“ሹመት፤ ማዕረግ ሳይሆን የአገልግሎት ቃል ኪዳን ነው”

መሥራት ካልቻላችሁ ለምን ሾምኳችሁ ከሚል አለቃ ይሠውረን፡፡ መሥራት ሳይችሉ ሹመትን ለሹመት ብቻ ብለው ከሚቀበሉም ባለሟሎች ያድነን፡፡ የህዝብን ብሶት የሚፈቱ እንጂ ህዝብን እናስወግድ የሚሉ እንዳይገጥሙን እንፀልይ፡፡ ለህዝቡ ነው ለእኔ የቆምከው? የሚል ሹም ላያችን ላይ እንዳይንሰራፋ ነቅተን እንይ፡፡ የሚያስረዳ፣ ዐይን - የሚገልጥና ለመልካም አስተዳደር የቆመ ባለሥልጣን እንጂ እኔ ያዘዝኩህን ብቻ ፈጽሞ የሚል አይዘዝብን! ገደል እንዳንገባ ገደሉን የሚያጥርና ከመውደቅ የሚያድነን እንጂ “ወዶ ገደል ገባ!” ከሚል ኃላፊ ያድነን፡፡ ከሚያየው የማያየው የሚሻልባት አገር ሳትሆን፤ ልቦና የሰጠው ህዝብ የሚኖርባት አገር ትሆን ዘንድ የልባችን ይሙላልን፡፡ 

“ሹመት፤ ማዕረግ ሳይሆን የአገልግሎት ቃል ኪዳን ነው” ይላሉ ፈረንጆች፡፡ ብቃትና ዕውቀት ዋና ነገር ነው፡፡ ተዐብዮ - አልባ መሆን ዋናና ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ አሠሪውም ሆነ ሠራተኛው አወቅሁሽ ናቅሁሽ የማይባባሉበት ሥርዓት እንዲኖር የሁላቸውም ጥራት ወሳኝ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል!
ማናቸውም ሹመት የሌላ ሥልጣን መሳለጫ መንገድ ነው ብሎ ማሰብ አገርንም ህዝብንም ይጐዳል - የግል ዕድገትን እንጂ የአገር እድገትን እንዳናስብ ጫና የሚፈጥር እሳቤ በመሆኑ! ባለሙያነት፣ ተዓማኒነት፣ ኃላፊነትን የመሸከም ብቃት ያለው ሹም ኢወገናዊ መሆንን እንደ ታላቅ መልህቅ ሊያስር ይገባል፡፡ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል”ን ተረት ካላደረግነው፤ ድህነት ተረት አይሆንም! ከትላንትና እንማር! አገርን ያጠፋ ህዝብን የጐዳ አያሌ ነገር አይተናል፡፡ ያንን ከወዲሁ ካላሰብንና አርቀን ካላስተዋልን፤ 
“የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም!”
“የጃፓንን ጠባሳ ያየ በውሃ አይጫወትም!”
“የአሜሪካንን ጠባሳ ያየ በንፋስ አይጫወትም!” የሚለው አባባል ገና አልገባንም ማለት ነው!
አንድ የአፈ-ታሪክ ንጉሥ ህዝብ እያጉረመረመና እያደመ ሲያስቸግራቸው እንዲህ ያደርጉ ነበር አሉ፡፡
“እገደል አፋፍ ላይ ትልቅ ድንኳን ጣሉ” ይሉና ያዛሉ፡፡
“ከየት እስከ የት?” ይላቸዋል ባለሟሉ፡፡
“ህዝባችንን የሚይዘውን ያህል አስፍታችሁ ትከሉት”
“የዚያን የሚያህል ድንኳን ከየት እናገኛለን ንጉሥ ሆይ?”
“ቀጣጥላችሁም ቢሆን በሰፊው ስሩልኝ ብያለሁ፤ ብያለሁ፡፡ ይሄን ይሄንን መሥራት ካልቻላችሁ ለምን ሾምኳችሁ?!” ብለው ቱግ ብለው ይቆጣሉ፡:
                ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር !! 
                                ከዘካሪያስ

No comments:

Post a Comment