Monday, December 10, 2012

አገራችንን የማን እንደሆነች አላወቅናትም !

በመካከላችን አንድነት የሚኖረው መቼ ነው? መተሳሰብ የሚሰፍነው መቼ ነው? ለየራሳችን ፍላጎት መተሳሰቡን (‹‹የመረዳዳት ባህላችንን››) እናቆየውና የራሳችን የሁላችን ስለምንላት ሀገራችን የጋራ አስተሳሰብ አለን? አይመስለኝም፡፡ ብዙዎቻችን ከራሳችን ውጭ ማንም ያለ አይመስለንም፡፡ ሀገሪቱም ከእኛ ውጭ አሳቢ እንደሌላት እንድመድማለን፡፡ አለዚያም ሀገሪቱን ረግጠን እና በሀገሪቱ አላግጠን ለማለፍ መለኮታዊ ቅባት እንደተቸረን ይሰማናል፡፡ ይህማ ባይሆን እኩልነታቸውን አስከብረናል በምንልበት ሀገር ዘለፋን አፈናጥረን በተውን ! 

አቶ መለስ በገነቡት ሥርዓት ውስጥ እንከኖች እንደነበሩ ቢያንስ ከተቃዋሚዎች አንደበት ነጋ ጠባ እንሰማለን፡፡ 
አንዳንዶቹን እኛም እናውቃቸዋለን፡፡ ፓርቲያቸውም አይክደውም፡፡ በየቀበሌውና በየወረዳው እንዲሁም በየክልሉ እንደ “ማፍያ” መደራጀት የቀራቸው “የመንግስት ሌቦች” እና በዝባዦች መኖራቸውን ማንም አይክድም ፡፡ ልማታችንን የጎተቱት እነማን ሆኑና? ዛሬም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ብሔር ተኮር ጥያቄዎች ይነሣሉ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከቀበሌ ጀምሮ ያሉት የስልጣን እርከኖች በአንድ ብሔር አባላት የተያዙ እንደሆኑ ሀሜት ይናፈሳል ብቻ ሳይሆን እውነትም ጭምር ነው፡፡ 
ሐዋሳ ከተማን አስመልክቶ ጥያቄ ተነሥቷል፣ከደቡብ ኢትዮጵያ የተፈናቀሉት አማሮች መጠጊያ ማጣታቸው እስካሁንም እያነጋገረ ይገኛል፣ ኦጋዴን ውስጥ ያልተፈታ ችግር አለ፣ የኑሮ ውድነት ዜጎችን አስጨንቆ ይዟል፣ ከተሞች በምእራባዊያን ባሕል ተወረዋል ፣ የትምህርት ጥራት ችግር አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል፣ ሥራ አጦች በርክተዋል ፣ ካድሬ መሆን የመኖርያ ፈቃድ ከመሰለ ቆይቷል፣ የመኖርያ ቤት እጥረት አሳሳቢ ነው፣ ሃይማኖታዊ አክራሪነት የሁልጊዜ ስጋት ነው፣ የፕሬስ ነጻነት አለ የሚሉ የሉም ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዳለ በተደጋጋሚ ይስተጋባል፣ ቋንቋን፣ መሬትን፣ ባሕልን ወዘተ የተመለከቱ ጥያቄዎች ዘወትር ይነሣሉ፡፡ ለእነዚህ እና መሠል ጉምጉምታዎች ቀጥተኛ እና ቀና የሆኑ መልሶችን መስጠት የሚቻለው አስተዳደር ቢመጣለት ሕዝቡ ደስታውን አይችለውም፡፡ በዚያኛው ትውልድ ውስጥ አቋመ ጠንካራ ነበር የሚባልለት ኢህአፓ፣ ደርግ ከሶማሊያ መንግስት ጋር ያደረገውን ጦርነት ይቃወም ነበር (ለሶማሊያ ይረዳ ነበር?) ኢህአዴግም ከአሁኗ ሶማሊያ ጋር ያደረገው ጦርነት ከአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ውጭ በሌሎች ተቃውሞ የገጠመው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
የዚህ ሁሉ ምንጩ ቢያንስ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሀገሪቱን የጋራ አድርገን አገራዊ መግባባት ላይ መድረስ ስላቃተን ይመስለኛል፡፡ (ቢንላደን ለሁሉም አሜሪካዊያን እንጅ ለቡሽ አሊያም ለኦባማ ብቻ ጠላት እንዳይደለ ልብ ይሏል) 
በርካታ ኀዘንተኞች “የመለስን ራዕይ እናሳካለን፣ የጀመሩትን እናስጨርሳለን” የሚሉ ትላልቅ መፈክሮችን ሲያስተጋቡ መስማት በመንግስትና በካድሬዎች የተለመደ ሆኗል፡፡
 ሕዝብ ሲያጉረመርምባቸው የነበሩ ጉዳዮች በእርጋታ ሊጤኑ እንደሚገባቸው መረዳት መልካም ነው፡፡ በየጊዜው የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች የጩኸት ሰበብ የሆኑ የተለያዩ አዋጆች፣ ደንቦች፣ ክልከላዎች፣ አፈናዎች ወዘተ---በአዲሱ ተተኪ አስተዳዳሪ ምላሽ ሊያገኙ ይገባል ብንል የተሳሳትን አይመስለኝም፡
እውነት እቺ አገር የማን ናት? 
የተቃዋሚዎች ወይስ የኢህአዴግ? የእኛ የዜጎች ሁሉ ወይስ የጥቂት ባለጊዜዎች?በደንብ አስበን በደንብ መክረን በደንብ አገናዝበን ለራሳችን መልስ ልንሰጥበት የሚገባ ሁነኛ ጥያቄ ነው፡፡
ያኔ ብቻ ነው “እቺ አገር የአንድ ፓርቲ እዳ ናት ወይስ የሁላችን እዳ?” ለሚለው ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ መድረስ የምንችለው፡
                                  ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!

No comments:

Post a Comment