Monday, December 31, 2012

የብሔራዊ ደኅንነት ዋስትና ያስፈልጋል !



በእረፍት ጊዜያችን ወይም በሥራ አጋጣሚ በእግር ወይም በተሽከርካሪ ስንንቀሳቀስ በከተማችን ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ኤምባሲዎችን እናስተውላለን፡፡ በተለይ ደግሞ የኃያላኑ አገሮች ኤምባሲዎች ጥበቃና ፀጥታ የሚነግረን አለው፡፡ ወደ ሽሮሜዳ ስትሄዱ እጅግ በሚገርም ሁኔታ የተገነባው የአሜሪካ ኤምባሲ በሩቅ ርቀት የተሠሩለት የኮንክሪት መከላከያዎች ድንገተኛ ጥቃቶችን ታሳቢ ያደረጉ ይመስላሉ፡፡ በሾላ መስመር የአንግሊዝ ኤምባሲም እንዲሁ የኮንክሪት መከላከያዎች የተበጁለት ነው፡፡ በሌሎች ሥፍራዎችም ስትሄዱ የዓለም አቀፍ ተቋማት ጥበቃ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው ትረዳላችሁ፡፡ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ፖለቲካ ምክንያት ሁሌም ቅድሚያ የሚሰጠው የፀጥታና የደኅንነት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የተጠናከረ ጥበቃ የሚያስገነዝበን በተለይ ኃያላን አገሮች ለብሔራዊ ደኅንነታቸው ምን ያህል ጥንቁቅ መሆናቸውን ነው፡፡


ከኤምባሲና ከተቋማት ጥበቃ በላይ ከፍ አድርገን ስናስብ ደግሞ የአገር ደኅንነት ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የብሔራዊ ፀጥታና ደኅንነት ጉዳይ የእያንዳንዱ አገር ተቀዳሚ ጉዳይ ሲሆን፣ ከዚህ በስተጀርባ ያለውና ከለላ የሚያስፈልገው ሉዓላዊነት ነው፡፡ በዓለም ላይ ለብሔራዊ ደኅንነት ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ አንድ አገርና ሕዝብ ሉዓላዊነታቸው የሚከበረው ብሔራዊ ደኅንነታቸው አስተማማኝ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ይህ ብሔራዊ ደኅንነት አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲ፣ ፖለቲካና የማይበገር የመከላከያ ኃይል ሲኖር ነው፡፡

በብሔራዊ ደኅንነት ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የአንዲት አገር ህልውና በአስተማማኝ ሁኔታ ሊከበር የሚችለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለዜጎች የሥራ ዕድል፣ የኑሮ ዋስትናና የተደላደለ ሕይወት መፍጠር ሲችል ነው፡፡ በፖለቲካው መስክም ዜጎች እኩል ሆነው ነፃነታቸውና መብታቸው ሲከበርና በሕግ የበላይነት ሥር መተዳደር ሲችሉ ነው፡፡ የአገሪቱ ዲፕሎማሲ ለአገሪቱ ተፈላጊነትና ተደማጭነት ሲያመጣላት፣ በአኅጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ መፍጠር ስትችልም ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ የአገሪቱን ዳር ድንበር በብቃት ማስከበር የሚችል የጦር ኃይል፣ ዘመናዊና የተራቀቁ የጦር መሣርያዎች፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የደኅንነት ተቋም ሲኖሩ ደግሞ የበለጠ ይሆናል፡፡

የብሔራዊ ደኅንነት ጽንሰ ሐሳብ በአብዛኛው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአሜሪካ አማካይነት የተዋወቀ ሲሆን፣ በመጀመርያ ዋነኛ ትኩረቱ የጦር ኃይል የበላይነት ላይ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀስ በቀስ ይህ ጽንሰ ሐሳብ ከወታደራዊ የበላይነት በተጨማሪ ኢኮኖሚን፣ ፖለቲካን፣ የሕዝብን ማኅበራዊ እሴቶችና የመሳሰሉትን ማካተት ጀመረ፡፡ በጊዜ ሒደትም ብሔራዊ ደኅንነት እየሰፋ የኢኮኖሚ፣ የኢነርጂና የአካባቢ ጥበቃ ደኅንነትን እያካለለ ነው፡፡ የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት የተለመዱት የውጭ ጠላቶች ብቻ ላይ የሚያተኩር አይደለም፡፡ በተጨማሪም በአገር ውስጥ እንደ ዕፅ አዘዋዋሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደ ሥጋት ሲጠቀሱ በአንዳንድ አገሮች የተፈጥሮ አደጋዎችም ይካተታሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደ ብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት የሚቆጠሩት አላስፈላጊ ተፅዕኖ ለመፍጠር በአንድ አገር ሉዓላዊነት ላይ ሲያሴሩ እንደሆነ በባለሙያዎች ይነገራል፡፡

ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመለስ የአገራችን ብሔራዊ ደኅንነት የሚያሳስበን ለምንድን ነው? እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ካለችበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ከታሪኳ የምንረዳው በርካታ ወረራዎች ተካሂደውባታል፡፡ ከእነዚህ ወረራዎች መካከል ታላቁ የአድዋ ጦርነትና የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ በእጅጉ ይታወሳሉ፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የስድስት አገሮች ተጎራባች የሆነችው ኢትዮጵያ ከአካባቢው አገሮች አንፃር የተረጋጋችና ትልቅ አገር ብትሆንም፣ በጎረቤቶቿ ሰላም ማጣት ምክንያት ሁሌም እንቅልፏን አጥታ ነው የምታድረው እንዲሁም በአገር ውስጥ ባለው የፖለቲካ ሽኩቻ እና መንግስት አምባገነንነት የሰፈነባትከመሆኑ አንፃር ሲታይ ሰላም የደበዘዘ ይመስላል ፡፡ ከሃያ ዓመታት በላይ መንግሥት አልባ ሆና የቆየችው ሶማሊያ አሁን መጠነኛ የሆነ ጅምር ሰላም ቢታይባትም ገና አለየላትም፡፡ ለዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት አድርገው ከተፋጁ በኋላ የተለያዩት ሁለቱ ሱዳኖች ጉዳይ ገና ውሉ አልተቋጠረም፡፡ ከዓለም ተገልላ ምን እየሠራች እንደሆነ በማትታውቀው ኤርትራ ውስጥ ያለው አመራር እስከ መቼ በአንባገነን እንደሚቀጥል አይታወቅም፡፡ የኢትዮጵያ መልካም ጎረቤት የምትባለው ጂቡቲ በወደቧ ተመክታ አንድ ቀን እጃችንን ከመጠምዘዝ ላለመታቀቧ ማረጋገጫ የለንም፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር ሰላሟ የሚታወከው ኬንያ በተነፃፃሪ ሁኔታ ሰላማዊ ብትመስልም በሙስና የሚታማው መንግሥቷ አካሄድ ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያሉት ጎረቤቶቻችን የተረጋጉና በኢኮኖሚ ትስስር አብረውን የሚሠሩ አጋሮቻችን ካልሆኑ የጠላት መሣርያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሁሌም ማሰብ ይገባናል፡፡ በብሔራዊ ደኅንነታችን ላይ ስንነጋገር በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ሊነሳ የሚችለውን ሥጋት ሁሌም አጀንዳችን ካላደረግን ትልቅ ችግር ሊገጥመን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመረችው ታላቁ የህዳሴ ግድብና ወደፊት የሚገነቡት የተለያዩ ግድቦች ለሕዝቡ ብልፅግና ሊያመጡ የሚችሉት ደኅንነታቸው አስተማማኝ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አገሮች አማካይነት የተጀመረው ‹‹የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ›› ፕሮጀክት የወለደው በቅርቡ ከግብፅና ከሱዳን በስተቀር የተፈረመው የትብብር ማዕቀፍ ዋነኛ ዓላማው ውኃውን በፍትሐዊነት መጠቀም ቢሆንም፣ ሁለቱ የግርጌ አገሮች የተዋጣላቸው አይመስሉም፡፡ ግብፅ የህዳሴ ግድቡ በዓመት የምታገኘውን የውኃ ድርሻ እንደሚቀንስባት ስታጉረመረም፣ ሱዳን ደግሞ ግድቡ የሚይዘው ውኃ የተለቀቀ እንደሆነ ጠራርጎ ያጠፋኛል ትላለች፡፡ ይህ ፍራቻ የወለደው አባዜ ሁለቱን ለአላስፈላጊ ሴራ ሊያነሳሳቸው እንደሚችል እየሰማን ነው፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት በዊኪሊክስ አማካይነት አፈትልኮ የወጣው መረጃ የእነሱን ፍርኃትና የፈሪ በትር ሴራ በሚገባ ያጋለጠ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ግብፅ በዘመነ ሙባረክ በዓባይ ላይ የሚደረግን ማንኛውንም እንቅስቃሴ በኃይል ለማስቆም ወይም ለማውደም ፍላጎት እንደነበራት ቢነገርም፣ ይኼ ፍላጎት ዛሬም እንደሚኖር አለመጠርጠር የዋህነት ነው፡፡ በአንድ ወቅት ሙባረክ ከሥልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ አዲስ አበባ የመጣው የግብፅ ‹‹ፐብሊክ ዲፕሎማሲ›› ቡድን ዋነኛ ዓላማ ቢቻል ኢትዮጵያ የጀመረችውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንድታዘገይ፣ ካልሆነም ለግድቡ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ በመመሥረት ቀዳዳ ለማግኘት እንደነበር ይፋ ባልሆነ መንገድ መወራቱ ይታወሳል፡፡

ግብፆች ከ30 ዓመታት በላይ አንቀጥቅጠው የገዙዋቸውን ሙባረክ ታህሪር አደባባይ ላይ ሆነው ካወረዱ በኋላ ትንፋሻቸውን መሰብሰብ ስለነበረባቸው የዲፕሎማሲውን መስክ መምረጥ ነበረባቸው፡፡ ምንም እንኳ በሚስጥር ከጎረቤት ሱዳን ጋር እያሴሩ ግድቡን ለማውደም እንቅልፋቸውን አጥተው እንደሚያድሩ ቢታወቅም፡፡ ሱዳን ግዛት ውስጥ የጦር አውሮፕላን መንደርደሪያ ቤዝ ከማግኘት እስከ የኮማንዶ ጦር ካምፕ ምሥረታ ድረስ ማሴራቸው በስፋት ይሰማል፡፡ በአፍሪካ እጅግ በጣም የተራመደውና በዓለም ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የግብፅ ጦር ኃይል ከሱዳን ባሻገር እነ ኢሳያስ አፈወርቂ ሠፈር ውስጥ ላለመክተሙስ ምን ማረጋገጫ ይኖራል? ኢትዮጵያ ድህነት ጠላቴ ነው ብላ በውኃ ሀብቷ ለመጠቀም ስትነሳና ሌሎች ደግሞ የህልውናችን ጉዳይ ነው ሲሉ ምን መደረግ አለበት? የዳተኝነትና የየዋህነት አስተሳሰብ ለጊዜው ገለል ተደርጎ የደኅንነት ሥጋቶቻችን በቅጡ ሊፈተሹ ግድ ይላል፡፡

ብሔራዊ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ካሉት አማራጮች መካከል አንደኛው ዲፕሎማሲ ነው፡፡ በበኩሌ በዲፕሎማሲው መስክ ያለን ብቃትና ዝግጅት ምን ያህል እንደሆነ ባላውቅም፣ የአስተማማኝነቱ ጉዳይ በጣም ያሳስበኛል፡፡ በዚህ መስክ የተሰማሩ ዲፕሎማቶቻችን ድምፃቸው ስለማይሰማ ለእኔ ብዙም ትርጉም አይሰጠኝም፡፡ ከዚህ ይልቅ የመከላከያ ኃይላችን አስተማማኝነት ልቆ ይታየኛል፡፡ እ.ኤ.አ በ1996 የህንድ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ ለብሔራዊ ደኅንነት የሰጠው ትርጉም ይማርከኛል፡፡ ብሔራዊ ደኅንነት በሰው ኃይል፣ በኢኮኖሚ ዕድገትና ብቃት፣ በተራቀቀ ቴክኖሎጂ፣ በፅኑ መሠረት ላይ በተገነባ ኢንዱስትሪ፣ በአስተማማኝ የተፈጥሮ ሀብትና በገዘፈ ወታደራዊ ኃይል ውህድ የሚከበር እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በኮሌጁ ትርጉም መሠረት ካሰላን ኢትዮጵያ ከ85 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር ነች፡፡ ከድህነት ለመላቀቅ ተፍ ተፍ እያለች መሆኗ ደስ የሚል ነው እድገቷ መቼ እንደሆን ይናፍቀናል፡፡ ዘመኑ ያፈራቸውን የተራቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመጠቀም ዕድሉ የተመቻቸላት ናት፡፡ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር መንገዱን ጀምራለች፡፡  በአፍሪካ ውስጥ ትልቅ ገበያና የኢንቨስትመንት መዳረሻ አገር መሆኗ ይታወቃል ፡፡ በወታደራዊ ቴክኖሎጂና አቋም የተሻለ ደረጃ ላይ ትገኛለች ተብሎ ይታሰባል፡፡ የዚህን ድምር ወጤት ስናይ ደግሞ ማንኛውንም የውጭ ጥቃት ለመመከት በምትችልበት ሁኔታ ላይ ያለች አገር እንዳለችን እናምናለን፡፡

ሰሞኑን ሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ውስጥ የሚገኝ አንድ ሚስጥራዊ የጦር መሣርያ ፋብሪካ በእስራኤል ጥቃት ተሰንዝሮበት ውድመት እንደደረሰበት እየሰማን ነው፡፡ ይኼንን የጦር መሣርያ ፋብሪካ ማንም ይሁን ማን ይደብድበው እጅግ በጣም አሳሳቢ የሚሆነው ምን ዓይነት ምርቶች ሲመረቱበት ነበር የሚለው ነው፡፡ የጦር መሣርያ ፋብሪካውን ደብድባዋለች የምትባለው እስራኤል ለህልውናዋ እንደሚያሠጋት ስማቸው በማይገለጽ ወታደራዊ ባለሥልጣናቷ አማካይነት እየገለጸች እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ ፋብሪካው ለሐማስና ለሒዝቦላህ ተላልፈው የሚሰጡ ሮኬቶችና ሚሳይሎች ይመረቱበታል ተብሏል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን (Drone) ይገጣጠምበታል የሚል መረጃም አለ፡፡ የሐማስና የሒዝቦላህ የሮኬት ጥቃት ያንገፈገፋት እስራኤል ረጅም ርቀት ተጉዛ በጦር አውሮፕላን ፋብሪካውን ማጋየቷ የብሔራዊ ደኅንነት ህልውናዋን ስለተፈታተናት ነው የሚል እሳቤ አለ፡፡

ምናልባት እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ ፕሮጀክቱ የሱዳንና የኢራን ሆኖ ዓላማውም ሐማስና ሒዝቦላህን ለማስታጠቅ ከሆነ እኛ ምን አገባን? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ጉዳዩ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ኢራን ይህ ፕሮጀክት ከእሷ ጋር መያያዝ እንደሌለበት ስትናገር፣ ሱዳን ደግሞ ባህላዊ መሣርያዎች የሚመረቱበት ተራ ፋብሪካ ነው ብላለች፡፡ ሰሞኑን የወጡት የሳተላይት ምስሎች ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩት እስከ 52 ጫማ ስፋት ያላቸው ስድስት ጉድጓዶች በድብደባው ምክንያት መፈጠራቸውን ነው፡፡ ከድብደባው በፊት በ40 ኮንቴይነሮች የተሞሉ የጦር መሣርያዎች ለመጓጓዝ ሲዘጋጁ ታይተዋል፡፡ ከድብደባው በኋላ ጉድጓዶቹ የታዩት ኮንቴይነሮቹ በነበሩበት ሥፍራ ላይ ነው፡፡ ወታደራዊ ኤክስፐርቶች ኮንቴይነሮቹ ከባድ ተወንጫፊዎች ሳይጫኑባቸው አልቀሩም ሲሉ፣ ከካርቱም ወጣ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ እንደ ሚሳይል የሚምዘገዘጉ ነገሮች አየር ላይ ሲፈነዱ ማየታቸው ተሰምቷል፡፡ የእስራኤል መንግሥት እስካሁን ፋብሪካውን ስለማጋየቱ ማስተባበያ ባይሰጥም ሱዳን የህልውናዬ ጠንቅ ናት ማለቱ ግን ታውቋል፡፡

በዚህ ፋብሪካ መጋየት ከማንም በላይ የተበሳጨችው ግብፅ ማንም ሳይጠራት ስትጮህ ግን እንዴት ብለን መጠየቅ የለብንም? እስራኤል ፋብሪካው በኢራንና በሱዳን ትብብር የተገነባ ነው ብትልም፣ ብዙዎች ግን ወደ ሐማስና ሒዝቦላህ መተላለፊያ የሆነችው ግብፅ ድርሻ ምንድን ነው ይላሉ፡፡ በዓባይ ወንዝ የተነሳ ከኢትዮጵያና ከሌሎች የተፋሰሱ አገሮች በስተጀርባ የሚካሄውን አመፅ የምትመራው ግብፅ እንደ ተራ የኮንትሮባንድ ዕቃ ሮኬትና ሚሳይል በግዛቷ ውስጥ ሲተላለፉ፣ የዚህ ፋብሪካ ባለድርሻ አይደለችም ብሎ ማሰብ በራሱ ችግር አለበት፡፡ ሱዳን ውስጥ የጦር አውሮፕላን መንደርደሪያና የጦር ማሳረፊያ ትፈልጋለች ወይም አግኝታለች የምትባለው ግብፅ ካልተጠረጠረች ማን ይጠርጠር? ይህ ጥርጣሬ ቅዥት የወለደው ሳይሆን ለዘመናት ከጀርባችን ሆና ስትፈጽመው የነበረው አሻጥር ነፀብራቅ ነው፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ ማንም አይንደውም ያሉትን ባድመ ውስጥ የተሠራውን ነገር ግን በመከላከያ ሠራዊታችን የተጣሰውን ምሽግ ማን እንደሠራው እኮ ነጋሪ አያስፈልገንም፡፡ ከኤርትራ ኋላ ሆነው አልሸባብን ሲያስታጥቁና ሲያደራጁ የነበሩት ሙባረክ እንደነበሩ ምስክር መቁጠርም አያሻንም፡፡

ሶማሊያ ደግማ ደጋግማ ኢትዮጵያን ስትወር ከጀርባ ሆነው ‹‹ጃስ›› የሚሉት እነማን እንደሆኑ አንረሳውም፡፡ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ለማልማት በዓለም ባንክና በአይኤምኤፍ ደጃፍ ላይ ቆማ ስትማፀን ማን የእልፍኝ አስከልካይ እንደነበረ የሚያውቀው ያውቀዋል ይህም የሆነበት ምክንያት መንግስት የተበደረው ገንዘብ በአግባቡ ያውላል ወይ ሲባል የምናውቀው ጉዳይ ነው !፡፡ ድህነት ያስመረረው ሕዝብ አገሩን በመገንባት ለብልፅግና ሲነሳ መንግስት የህዝብ ጠላት ሆኖ እያየን  ነው፡፡ ፡፡ በአንፃራዊ ሁኔታ ሰላሙ የተረጋገጠለት ሕዝብ ለዘመናት እንዲተኛ ከተደረገበት እንቅልፉ ተቀስቅሶ ወደ ልማት ሲሰማራ፣ ልክ እንደ ጦርነት ወደ ኋላ እንደሚያፈገፍግ የተረዱ ጠላቶች የሚያሾልኩት መረጃ ያስፈራቸው ወገኖች ሚስጥራቸው ማፈትለክ ጀምሯል፡፡ የመጀመርያው በዊኪሊክስ የተጋለጠው ሲሆን፣ የአሁኑ ደግሞ እስራኤል አጋየችው በተባለ የጦር መሣርያ ፋብሪካ ምክንያት ነው፡፡ ከካርቱም ደቡባዊ ምዕራብ 11 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያው አካባቢ በመኖርያ መንደር ውስጥ የዛሬ 16 ዓመት እንደተገነባ የሚነገርለት የጥይትና የቀላል መሣርያዎች ፋብሪካ የነበረው ‹‹ያርሙክ›› በመባል የሚታወቀው ሚስጥራዊ ተቋም ዛሬ ይዞታው ተቀይሯል ይባላል፡፡ በድብደባው ወቅት የተሰማው የጥይት መንጣጣት ሳይሆን አገር ምድር ያገላበጡ የሚሳይል ፍንዳታዎች ናቸው፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች የተናገሩትም አውሮፕላኖቹ ደብድበው ከሄዱ በኋላ የሰሙት መሬትን የሚያናውፅ ድምፅ የአነስተኛ መሣርያዎች ሳይሆን የከባድ ጦር መሣርያ ዓይነት ነበር፡፡ አንዳንዶች የአውሮፕላን ዓይነት ከባድ ድምፆችን ሰማን ሲሉ፣ ወደ አሸዋማው በረሃ የተወነጨፉት ሚሳይሎች ፍንዳታ ደግሞ የምፅዓት ቀን ይመስል ነበር ብለዋል፡፡

ከህዳሴው ግድብ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የጦር መሣርያ ፋብሪካ ያመርታቸዋል ከተባሉ ከባድ የጦር መሣርያዎች አንፃር ለብሔራዊ ደኅንነታችን አስጊ ነው፡፡ በዚህ ፋብሪካ ውስጥ የሚመረቱ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይሎች አገር አቋራጭ ሊሆኑ ይችላሉ መባላቸው ደግሞ በእጅጉ ሊያሳስበን የግድ ይላል፡፡ የዲፕሎማሲው ድርድር እንደተጠበቀ ሆኖ የአገራችን ህልውና በከፍተኛ ብቃትና ዝግጅት ማስጠበቅ ግን መቼም ቢሆን ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ በዓባይ ወንዛችን የሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ጥቅም ሳንጋፋ ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ መጠቀም አለብን፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿን በረሃብ ምክንያት ያጣች አገር የድህነት መጫወቻ ለመሆን ካሁን በኋላ ወደ ኋላ አትልም፡፡ መንግሥትም የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጎኑ አሠልፎ ወደ ብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ ሲያስቀጥል የብሔራዊ ደኅንነታችን አለኝታ የሆነውን የመከላከያ ብቃት ሊያስብበት ይገባዋል፡፡ ከዚህ በተረፈ አንዳንድ የዋሆች እንደሚሉት እየወጡ ያሉትን መረጃዎች አለመጠርጠር ተረታችን እንደሚለው ‹‹ያልጠረጠረ ተመነጠረ›› የሚለውን ያመጣብናል፡፡ የአል በሽር መንግሥትን ጉርብትናና የግብፆችን ብልጣ ብልጥ ግንኙነት እንደወረደ እየተቀበሉ የሚገኙትን ለጊዜው ትተናቸው፣ የአገራችንን ክንድ እናፈርጥም፡፡  በአገር ጉዳይ  ሁላችንም አንድ መሆን ነው ያለብን ልዩነታችን ወደ ኋላ ትተን ። ሁሌም ለብሔራዊ ደኅንነታችን መረጋገጥ በንቃት ዘብ እንቁም፡፡ በአገር ጉዳይ ድርድር የለምና !! ሁሌም ለብሔራዊ ደኅንነታችን መረጋገጥ በንቃት ዘብ እንቁም፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቃት!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!
                           ከዘካሪያስ

No comments:

Post a Comment