Thursday, December 13, 2012

የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ሊፈነዳ ደርሷል !!



በአንድ አገር ዕድገትና ልማት የሚመጣው በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ተሳትፎ ጭምር ነው፡፡ ሕዝብ ለራሱ ምን እንደሚፈልግ ወይም ምን እንደሚጠቅመው የሚወስነው ራሱ ነው እንጂ መንግሥት አይደለም፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ሚና (ድርሻ) ዲሞክራሲን በተከተለ ሥርዓት የሕዝብ ፍላጐት ማስፈጸም ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፉት21 አመታት የገዥ መደቦች መራራ ጭቆናና የአስተዳደር በደል ያሳለፈ ሕዝብ ነው፡፡


ኢሕአዴግ ለዲሞክራሲ፣ ለመልካም አስተዳደር፣ ለሕግ የበላይነትና ለሰብዓዊ መብቶች እንደማይቆረቆር ቢታወቅም፣  የዜጐች ሰብዓዊ መብቶችን ሲጣሱና ሲረገጡ ያያል፤ ይሰማልም፡፡

ኢሕአዴግ የዜጐችን ክብር፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲን ለማምጣት ለ17 ዓመታት ታግያለው ቢልም፤ መስዋዕትነትም ከፍያለው ቢልም፡፡ ሆኖም የዜጐችን ሰብዓዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት በጽናት አላከበረም፡፡ የአስተዳደርና ፍትሕ አካላትም በከፍተኛ ሙስና ተዘፍቀዋል፡፡ የሚነዱት መኪናና የሚኖሩበት ቤት ማሳያ ነው፡፡ በዚሁ ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዜጐች ላይ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እየተፈጸሙ ይታያሉ፤ ተፈጽመዋልም፡፡


ለዚህም ዋነኛነት ሱማሌ ክልል መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህ ክልል የሚኖሩ የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተፈጸመባቸው ያለው የመብት ረገጣ አንድና ሁለት የለውም፡፡ ሥር የሰደደ ነው፡፡ ተዘርዝሮ አያልቅም  እንዲሁም በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚደርሰው ግፍ ምን እሱ ብቻ በአማራው ህዝብ ላይ የሚደርሰው በደል ‹‹ኧረ የመንግሥት ያለህ›› እያስባለ ነው፡፡ 

በክልሉ ጅጅጋ ከተማ የተመደበ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቅርንጫፍ ቢሮውን ቆልፎ ከመመለከት በስተቀር የሠራው ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም በሱማሌ ክልል ባለሥልጣናት የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ከሰፊው በአጭሩ ይህን ይመስላል፡፡ 

አንደኛ በደርግ መንግሥት የተወረሱ በቀበሌና በኪራይ ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሥር ያሉና የኪራይ ተመናቸው በደርግ መንግሥት ከአምስት እስከ መቶ ብር የነበሩ ቤቶች፣ አሁን በየትኛውም ክልል ባልተደረገና ለከተማው ዕድገት ገቢ በሚል ሰበብ የዜጐችን አቅምና ችግር ባላገናዘበ መልኩ ቤቶቹ ከ200 እስከ 700 ብር የኪራይ ክፍያ እንዲደረግባቸው እየታቀደ ነው፡፡ ነዋሪዎችም ይህንኑ ሲሰሙ አሁን ካለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት አንፃር የሚላስ የሚቀመስ በሌለበት ሁኔታ ይህንን ክፈሉ ብንባል መሞት እንጂ ለማን አቤት እንላለን እያሉ እምባቸውን እየረጩ በጭንቀት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከክልላችን ውጡልን ከሚል መልዕክት ሌላ ትርጉም የለውም በማለትም በምሬት መንግሥትን በማማረር ላይ ይገኛሉ፡፡ 

ሁለተኛ ጅጅጋ ታይዋን በተባለ ንግድ ቦታ ይሠሩ የነበሩ የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ ነጋዴዎች ንብረታችሁን አውጡ ተብለው መደብሮቻቸውን በጠራራ ፀሐይ በመቶዎች በሚቆጠሩ ወታደሮች እንዲያወጡም ተደርጓል፡፡ በሚሊዮን ብር የሚገመቱ ንብረቶቻቸውም ወድሟዋል፤ ተወርሷልም፡፡ 

ሦስተኛ ለበርካታ ዓመታት በቀበሌና በኪራይ ቤቶች አስተዳደር የነበሩ ቤቶችን የተከራዩ ዜጐች መተኪያ ባታ፣ ካሳና መቆያ ሳይሰጣቸው ቤቱን ለባለሀብት ይሰጣል ውጡ እየተባሉ ንብረቶቻቸው በቀበሌ ወታደሮች ሲወረወሩ ተስተውሏል፡፡ ቤተሰቦቻቸውና ልጆቻቸው አውላላ ሜዳ ላይ እንዲወድቁ ተደርጓል፡፡ ይህንን የተመለከቱት ነዋሪዎች ምን መጣብን እያሉ በምሬት አልቅሰዋል፤ አዝነዋል፡፡ 
በመላው ኢትዮጵያ እየተፈፀመ ያለው በደል ቤት ይቁጠረውና!                              

ስለዚህ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚመራ መንግሥት ይህንን የመሰለ መጠነ ሰፊ የዜጐች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሲፈጸም ዝም ብሎ መመልከትና ማየት በእጅጉ የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን ድርጊቱ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ሥርዓት የዜጐች ሰብዓዊ መብቶችንና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው እያለ በጐን በዘር፣ በጐሣ፣ በሃይማኖት ልዩነት እያደረጉ ዜጐችን ከቤት ንብረታቸው በማፈናቀል ለመከራ፣ ችግርና ስቃይ እንዲጋለጡ እየተደረገ ነው፡፡ ይህም መጨረሻው ወንጀል ነው፡፡ በመሆኑም የኢሕአዴግ መንግሥት በጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ ካላደረገለት መቋጫ ወደማይገኝለት አደጋ የሚሄድ ነው እላለሁ፡፡
ህዝቡ ከዚህ በላይ ምንም ማድረግ ስላልቻለ ሊፈነዳ ደርሷል ውጤቱ የከፋ ይሆናል!
               ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!
                               ከዘካሪያስ

No comments:

Post a Comment