Monday, November 11, 2013

“ዴሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ”

የመፀሃፍ ግምገማ
ደራሲ ብርሃኑ ነጋ
ግምገማ በጥላሁን አፈሣ
ብርሃኑን ከ ፳፭ አመታት ላላነሰ ግዜ በቅርብ የማውቀው ጓደኛየ ነው። ለሥራ ትጋቱ፣ ለቆመለት አላማ ፅናቱ፣ የማይረግበው የይቻላል መንፈሱ፣ ካወቅኩት ግዜ ጀምሮ ያልተለዩት መላያ ባህርዮቹ ናቸው። በእነዚህ አምታት ውስጥ፣ የአገሩን ጉዳይ በሚመለከት የተሳተፈባቸውንና ያከናወናቸውን መጠነ ሰፊ ተግባሮች መዘርዘር ይህ ቦታው ባይሆንም፣ በዚህ አጋጣሚ፤ እንደው በጥቅሉ ብርታቱን የሰጠው ግለሰብ መሆኑን በጨረፍታ ገልጬ ማለፍ እወዳለሁ።
ሌላው ቢቀር ፣ የራሱን የግል ነፃነት ተነፍጎ፣ የነፃነት ጭላንጭል በማይታይበት በቃሊቲ ወህኑ ቤት ነዋሪ በነበረባቸው በነዛ ሁለት ፈታኝ ዓመታት ውስጥ፣ “የነፃነት ጎህ ሲቀድ” በሚል ርዕስ በቁርጥራጭ ወረቀቶች ላይ ከትቦ ገና ከቃሊቲ ሳይሰናበት ለህትመት አብቅቶ ያቋደሰንን ከ ፮፻ ገፆች በላይ ያካተተውን መጸሃፉን በማንበብ ብቻ፣ በእርግጥም ብርታቱን የሰጠው ሰው መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። በተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ላይ ሆኖ በፃፋት በዛች ድንቅና ተስፋ ጫሪ መጽሃፉ መግቢያ ላይ፣ “ከአሜሪካ ኑሮዬ የተገነዘብኩት የነፃነት እና የኢኮኖሚ ብልፅግናን ጠንካራ ግንኙነት ነበር”፤ አገር ቤት ከተመለሰኩ በሗላ በጻፍኳቸው የተለያዩ ጽሑፎቼም “የዴሞክራሲ እና የኢኮኖሚ እድገት ትስስርን በሚመለከት በአጠቃላይና በተለይ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ብልፅግና የዜጎች ነፃነትና ዴሚክራሲያዊ ስርዐት አስፈላጊነትን መክሪአለሁ” በማልት በጽኑ የሚያምንበትን መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብ አስምሮበት አልፎ ነበር።
“ዴሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ” ብሎ በሰየማት በዚች ሁለተኛው መጸሃፉ ውስጥም እንዲሁ፣ “የአሜሪካን የፖለቲካ ስርዓት በገቢር በማየት የስርዓቱ የማዕዘን ድንጋዮች የህዝቡ የተለየ ጥሩነት፣ የፖለቲከኞቻቸው ልዩ ችሎታና ብስለት ሳይሆን ስርዓቱን ተሸክመው በያዙት ተቋማት ላይ መሆኑን አምኛለሁ። የተቋማት ጥንካሬ፣ የተቋማት ነፃነት፣ ከግለሰቦች ይልቅ ለተቋማት የሚሰጠው ክብርና ታማኝነት ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እውን ለማድረግ እጅግ አስፈላጊው መሳሪያ መሆኑን በፊት ከማምነውም የበለጠ ያለምንም ጥርጣሪ እንድረዳው አድርጎኛል” በማለት ገልጾልናል። ይህን መሰረታዊ እምነቱንም ነው በዚች መጸሃፉ ውስጥ በሰፊው በምክንያታዊ ትንተና የተደገፈ ሃተታ የሰጠበት።
ብርሃኑ ይህችን መጸሃፍ ለህትመት ከመብቃቷ በፊት፣ የመጀመሪያውን ንድፍ ልኮልኝ አስተያየቴን እንድሰጠው ጋበዞኝ ስለነበር፣ በኔ አስተያተት፣ መጸሃፏ ወቅታዊና መሰረታዊ በሆኑ የአገራችን ችግሮች ላይ ያነጣጣረችና የተለመችውን ኢላማ በብቃት የመታች መሆኑን ጠቁሜው በአስቸኳይ ለህትመት እንዲያበቃት ጎትጉቸው ነብር። ለህትመት ስትበቃም፣ በሽፋኗ ጀርባ ላይ ባጭሩ ከሰፈረው ስለመጸሃፏ ያለኝ አጠቃላይ አስተያየት ውስጥ፣ “የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ማንም ሰው ይህን መጽሃፍ በክፍት አዕምሮ ማንበብ ብቻ ሳይሆን አንብቦም ከሌሎች ዜጎች ጋር የምር ውይይት ማድረግ ይጠበቅበታል” የሚል ይገኝበታል። በዚች መጻጽፍም ፣ መጽሃፏ ካዘለቻቸው በዛ ያሉ ቁምነገሮች ውስጥ መሰረታዊ ናቸው ብየ ባመንኩባቸው ሁለት ነጥቦች ላይ አተኩሬ አስተያየቴን በማቅረብ አንባቢን ለውይይት እጋብዛለሁ። ወደ እነዚህ ሁለት ነጥቦች ይዤያችሁ ከመጓዜ በፊት ግን፣ የመጸሃፏን አጠቃላይ ይዘት አንባቢው እንዲረዳ፣ በአምስቱም የመጸሃፏ ምዕራፎች ሥር ደጋግመው ተንጸባርዋል የምላቸውን መሰረታዊ ሃሳቦች ባጭሩ እቃኛለሁ።
ብርሃኑ፣ የዚች መጽሃፍ አላማ፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ዴሚክራሲያዊ ካልሆኑ ስርዓቶች በሁሉም መስፈርት የተሻለ እንደሆነ ማስረዳት መሆኑን በዚች መጸሃፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ገልጾልናል። ይህንንም አወንታ፤ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታዎች ለናሙና እያቀረበና ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ከአካባቢ ጥበቃ ችግሮች ጋር እያዛመደ፣ ለአንባቢ በማይሰለች ብዕር፣ በሰፊው፣ በብቃትና በጥራት በመተንተን እንድንረዳ አድርጎናል። በዚህም ጉዞው፣ በመጀመሪያ የአምባገነን ሥርዓቶች መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው፣ ለአገር ልማትና ግንባታ የዴሞክራሲ መኖር ወሳኝ አለመሆኑን ለማሳየት የሚጠቀሙበትን መከራከሪያ ሃሳቦች በማቅረብ፣ የነዚህን ሃሳቦች ብኩንነት በወጉ እያገላበጠና እያደቀቀ በአምስቱም የመጸሃፉ ምዕራፎች ሥር በረድፍ በረድፉ አካቶ አመርቂ ትንታኔ አቅርቦበታል።
ብርሃኑ በዚች መጽሃፍ ላይ ያተኮረው፣ ለኢትዮጵያችን የሚያስፈልገው የትኛው አይነት የኢኮኖሚ ስርዓት ነው የሚለው ላይ ሳይሆን፣ የሚሻለውን ለመምረጥ የሚኬድበት ሂደት ላይ ነው። እንደብርሃኑ እምነት፣ ይህ “ደግሞ ባብዛኛው የሚመለከተው የፖለቲካ ሥርዓቱን” ስለሆነ፣ “በኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ላይ የሚደረግ ትርጉም ያለው ውይይት በመጀመሪያ መመለስ ያለበት ይህንን ጥያቄ ነው።” ስለዚህም ይመስለኛል፣ የመጀመሪዎቹን ከመቶ ገጾች በላይ ያካተቱ ሁለት ምዕራፎች በፖለቲካው ጥያቁዎችና ችግሮች ላይ እንዲያጠነጥኑ ያደረገው።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ሥር፣ አንድን የፖለቲካ ስርዓት ጥሩ የሚያሰኙትን ንጥረ ነገሮችና ከነዚህ ውስጥ የአገራችን የፖለቲካ ስርዓት አላሟላቸውም የሚላቸውን መስፈርቶች በሰፊው አትቶባቸዋል። እነዚህን የጥሩ ፓለቲካ ስርዓት አመልካች የሚላቸውን አምስት መሰረታዊ መስፈርቶች ለእያንዳንዳቸው ንዑስ ክፍል በመስጠት ሰፋ ያለ ትንታኔ አቅርቦማቸዋል። ይህን ምዕራፍ ሲያጠቃልልም፣ “ማህበረሰቡ ከጥቂት ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች ባሻገር ለሃገሩና ለፖለቲካ ስርዓቱ ታማኝ የሆኑና የባለቤትነት ስሜት የሚሰማቸው ዜጎችን በቀጣይነት ማፍራት የሚችለው” ሥርዓቱ እነዚህን ጥሩ የሚያሰኙትን መሰረታዊ መሥፈርቶች ሲያሟላ ብቻ መሆኑን አስምሮበት ነው። እነዚህን ዋቢ መስፈርቶች መጸሃፉን በማንበብ በሰፊው ልትተዋወቋቸው ስለምትችሉ፣ እዚህ መዘርዘር አስፈላጊ አይመሰለኝም።
የሁለተኛው ምዕራፍ ትኩረት፣ እነዚህን መሰረታዊ መሥፈርቶች ለማሟላት ሲፈለግ የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን መቃኘት ነው። በዚህ ምዕራፍ ሥር ፣ “የማንነት ፖለቲካ”በአገራችን ዲሞክራሲያዊ ሥርዐት ምሥረታ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ የችግሮቹ ሁሉ ቁንጮ ለመሆኑ ያለውን ግንዛቤ በሰፊው አትቶበታል። ይህን ትንተናውን ያካተተው ደግሞ “የታሪክ ጠባሳ” በሚሉ ሁለት ቀልብ ሳቢ ቃላት በሚጀምር ንዑስ ርዕስ ስር ነው። ታሪክ ትቶልን ያለፈውን “ጠባሳ” ከመግለጹ በፊት ግን፣ የመጀመሪያዎቹን አምስት ገጾች በመንደርደሪያነት በመጠቀም ታሪክ ምንድን ነው? የሚለውን መስቀለኛ ጥያቄ ይቃኝል። ይህን ቅኝት ተመርኩዞም፣ በታሪክ ላይ ተመስርቶ የዛሬውን የጋራ ህይወት ለመቅረጽ የሚደረግ ሙከራ ሁሌም ችግር ውስጥ የሚገባ ስለሆነ፣ የታሪክ ዘገባውን ለታሪክ ሰዎች ትተን፣ ለችግሩ የፖለቲካ መፍትሄ እንድንፈልግለት ይማፀነናል። ብዙም ሳይቆይ ግን፣ ይህንኑ የማንነት ፖለቲካ አሰመልክቶ በሁለት አቢይ ተዋንያን የህብረተብ ወገኖች የሚተረኩ ታሪኮች የሚላቸውን ይዞልን ይቀርባል። በዚህ ጊዜ ግን፣ እኛ እንድንሸሸው የተማጠነንን በታሪክ ላይ የተመሰረተ ዘገባ፤ እራሱ ማምለጥ የቻለ አልመሰለኝም። አስተያየቴን አቀርብባቸዋለሁ ካልኩት ሁለት መሰረታዊ ነጥቦች ውስጥ የመጀመሪያው በዚሁ የብርሃኑ የታሪክ ዘገባ ላይ ያጠነጠረ ስለሆነ፣ እመለስበታለሁና እዛው እስክደርስ አብራችሁኝ እንድትጓዙ በትህትና እጠይቃለሁ።
ብርሃኑ፣ በመጽሃፉ ሶስተኛ ምዕራፍ ሥር ፣ ጥሩ የሚባል የኢኮኖሚ ስርዓት ማካተት አለበት የሚላቸውን ንጥረ ነገሮችን በብቃትና በሰፊው ትንተና ያቀርብበታል። ይህን ሲያደርግም፣ ጥሩና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ስርዓት የትኛው ነው የሚለውን አከራካሪና ፍልስፍናዊ መልስ የሚሻ ጥያቄ ወደጎን ትቶ፣ በኢኮኖሚ ፍልስፍና ላይ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ሁሉ በጋራ ይሰማሙባቸዋል ብሎ የሚያምንባቸውን ንጥረ ነገሮች ብቻ በመቃኘት ነው። ብርሃኑ ይህን ስሌት የመረጠበትን ምክንያት ሲያስረዳ፣ መጽሃፏ በዋናነት እንድታነጣጥር የተለመበትን አቅጣጫ እንዳትስት ለማረግ መሆኑን ይገልጻል። በራሱ አባባል፣ “የተለያየ የግል ጥቅም ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥ” እና “በተለያየ መስፈርት ሲለኩ ብዙ አማራጭ መፍትሄዎች በሚኖሩበት ሁኔታ ጥሩውን እንዴት ነው የምንመርጠው? በሚለው የሂደት ጥያቄ ላይ እንድናተኩር ነው።” ይህን ምዕራፍ ሲቆጭም፣ የኢኮኖሚው ስርዓት እነዚህን መሰረታዊ ንጥረ ነገሮች ማካተቱ የሚለካው፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲው አወጣጥም ላይ ሆነ አተገባበር ላይ፣ የማህበረሰቡን አጠቃላይ ጥቅም የሚያስቀድም፤ ለማንም የተለየ ቡድን አድልዎ የማያደርግ መንግሥት መኖር ሲችል ብቻ ነው በማለት አሁንም የሂደት ጥያቄ በመጀመሪያ መመለስ ያለበት ወሳኝ ጥያቄ መሆኑን በጎላ ድምጽ በማሰማት ነው።
ምእራፍ ፬ ጥሩ የኢኮኖሚ ስርዓት በአገራችን ለመገንባት ያሉብንን መሰረታዊ መዋቅራዊ ችግሮች በአራቱም የጥሩ ኢኮኖሚ መለኪያ መስፈርቶች አኳያ በመመዘን ይፈትሽና በነዚህ መሥፈርቶች ስትለካ ሀገራችን ፍጹም ሗላ የቀረች መሆኗ ብዙ የሚያከራክር ጉዳይ አለመሆኑን ያስረዳል። እነዚህ ዘርፈ ሰፊ የአገራችን ችግሮች፣ መንግሥት ስለተቀየረና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት ስለተመሰረተ በቶሎ የሚጠፉ ስላልሁኑ፣ ለማንኛውም አይነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥርዓት ፈታኝ እንደሚሆኑና አመርቂ መልስ የሚሹ መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል ሲል ያሳስበናል። አሁንም ለብርሃኑ ዋነኛው ቁምነገር፣ ከብዙ የፖሊሲ አማራጮች ውስጥ፣ የፖለቲካ ስርዓቱ የትኛውን መፍትሄ እንዴት ይመርጣል የሚለው የዚያን የፖለቲካ
ኢኮኖሚ ምንነት የሚያሳይ አይነተኛ ገላጭ መሆኑን መገንዘብ መቻላችን ነው። በአመራረጥ ሂደቱ ላይ ያልተስተካከለ የመወዳደሪያ ሜዳ፣ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ውጤት ሲተነትንም ውጤቱ በሙስና ግዙፍ ጫና የተቀፈደደ ጭንጋፍ ኢኮኖሚ እንደሚሆን ለአንባቢ መረዳት ዳገት ባልሆነ ትንተና አስረድቶናል። በዚሁ ምዕርፍ ሥርም፣ ስለ እድገት/ልማትና የልማታዊ መንግሥት ከአርሶ አደሩና ከአርቢው መደብ መሬት መፈናቀል በሰፊው ዘክሮበታል። ይህን ምዕራፍ ሲያጠቃልልም፣ የኢኮኖሚ ችግሮቻችን ብዙ ቢሆኑምና እነዚህን መጠነ ሰፊ ችግሮቻችንን መፍታት ቀላል ባይሆንም ቅሉ፣ ሂደቱን በጥንቃቄ ካዘጋጀነው መፍትሄው ከችሎታችን ውጪ አንዳይደልና ተስፋችንን ጨለምተኛ እንዳናደርገው ምሁራዊ ምክሩን በመለገስ ነው።
ብርሃኑ በምዕራፍ ፭ ስር የአካባቢ ጥበቃ ችግሮቻችንን አስመልክቶ፣ የህዝብ ብዛት፣ የአየር ፀባይ መቀየር፣ የደን መመናመን፣ የመሬት መሸርሸር/መከላት የሚያመጡትን ችግሮች አገሪቷ ካለችበት ሁኔታ ጋር አዛምዶ አሁንም ሰፋ ያለ ትንተና አቅርቦበታል። በብርሃኑ እምነት፣ እነዚህ መጠነ ሰፊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ተቀባይነት ያለው እቅድ መንደፍ የሚቻለው፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እራሳቸው በመረጧቸው ወኪሎቻቸው አመካኝነት በሰጥቶ መቀበል ሂደት ተወያይተውበትና ተከራክረውበት ለብዙሃኑ የሚበጀውን ውሳኔ መስጠት ሲችሉ ብቻ ነው። ይህንን ምዕራፍ የሚደመድመውም፣ መፍትሄው ላይ ከመድረሳችን በፊት፣ ዋናው ጥያቄ ወደመፍትሄው የምንጓዝበት ሄደት መሆኑን ለአንድ አፍታም መዘንጋት እንደሌለብን በመጠቆም ነው።
ይህችን አጭር ግምገማ በወጉ ያነበበ ሁሉ ሊረዳው እንደሚችለው፣ ብርሃኑ፣ ሳይሰለች በአምስቱም ብዕራፎች ሥር ደጋግሞ የነገረን መሰረታዊ እምነቱ፣ ለጥያቄዎቻችን በዛ ያሉ ተወዳዳሪ መልሶች፣ ለችጎሮቻችን ብዙ አማራጭ መፍትሄዎች በሚኖሩበት ሁኔታ፣ መፍትሄውን ለመፈለግ የምንጓዝበት ሄደት ዴሞክራሲያዊ መሆን ወሳኝነት እንዳለው ነው። መፀሃፉን አጠቃሎ በማሳረግ የተሰናበተንም፤ “ከእወነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውጪ ማህበራዊ ልከኛ የሆነ መፍትሄ ሊሰጠን የሚችል ሌላ የፖለቲካ ስርዓት የለም። ይህን ስርዓት በኢትዮጵያ መመስረት ለሁሉም አይነት ማህበረሰባችን ችግሮች የመፍትሄው መጀመሪያ ብቻ ሳይሆን፤ የመፍትሄው ዋና ቁልፍ ነው” በማለት ነው። የሁለተኛው ትዝብታዊና ጥያቄ አዘል አስተያየቴም፤ ብርሃኑ መሰረታዊ እምነቱ መሆኑን ሳያሰልስ ባስታወቀንና እኔም እሰየው ብየ በምቀበለው የዴሞክራሲያዊ ሂደትን ወሳኝነት ከሚያረጋግጠው ንጥረ ሃሳብ ጋር የተያያዘ ይሆናል። አሁን በቀጥታ ወደ አስተያየቶቼ ይዣችሁ ላዝግም።
“በማንነት” ጥያቄ ላይ
ብርሃኑ፣ የ “ማንነት”ን ጥያቄ አሰመልክቶ ያቀረበውን ትንተና ያካተተው “የታሪክ ጠባሳ” በሚሉ ሁለት ቀልብ ሳቢ ቃላት በሚጀምር ንዑስ ርዕስ ስር መሆኑን ቀደም ብየ ጠቁሜያለሁ። በኔ አስተያየት፣ የብርሃኑ የታሪክ አተረጓጎም ችግር የሚጀምረው ከዚህ ነው።
ጠባሳ የደረቀን ቁስልን አመልካች ነው። ይህ አባባል፣ ብርሃኑ በዚህ ምዕራፍ ሥር ያተኮረበት የወቅቱን የኦሮሞ ብሄረሰብ ጥያቄ በተመለከተ ፣ የሚሰጠው ፍቺ የታሪክ ቁስላችሁ ደርቋል የሚለውን ነው። የኦሮሞ ብሄረተኞች ፣ ቁስላችን አልደረቀም ብቻ ሳይሆን፣ እያመረቀዘ ያለ ሰለሆነ፣ በወቅቱ መድሃኒት ካልተተኘለት ከጊዜ በሗላ መላ ፖለቲካዊ ሰውነታችንን ወሮና አጠቃላይ አገራዊ ህልውናችንን ሸርሽሮ ሊገነጣጥለን የሚችል ሞገደኛ በሽታ ነው የሚሉት። ኦሮሞ ያልሆንነውንና “ዴሞክራሲያዊ“ ሃገራዊ ብሄረተኞች ነን የምንለውን የሚጠይቁት፣ ቁስላችው እንዲሰማን አይመስለኝም። እኔ እስከተረዳሁት ድረስ፣ እየነገሩን ያለው፣ ቁስላችን አሁንም ድረስ ይሰማናል ስንላችሁ ስሙን እንጂ። መሠማማት የሚቻለውና መሥማማት ላይ የሚደረሰው፣ በመጀመሪያ መሥማት ሲቻል ነውና አስቀድማችሁ ጆሯችሁን ለግሱን ነው የሚሉን የሚመስለኝ ። በኔ ግምት፣ ብርሃኑ ቃሉን በገላጭነት የተጠቀመበት ትርጉምን ሳያውቅ ቀርቶ ሳይሆን፣ በዚህ ጥያቄ ላይ እራሱ ለሚተርከው ታሪክ ጠባሳ ከቁስል የተሻለ ቅርበት ያለው መግለጫ ሆኖ ስላገኘው ይመስለኛል። ይህን ያልኩበትን ምክንያት ላስረዳ። ለዚህ እንዲረዳኝ፣ በመጀመሪያ ብርሃኑ የተዋንያኖቹን ማንነት የገለጸበትን ስሌት ልመዝግብ።
በብርሀኑ አገላለጽ፣ አንደኞቹ “የኦሮሞ ማህበረሰብንና ይህን መህበረሰብ እንወክላለን የሚሉ ብሄረተኛ የፖለቲካ ድርጅቶች” ሲሆኑ፣ ሁለተኞቹ ደግሞ “ጭፍን የሆኑ ሀገራዊ ብሄረተኞች” ያልሁኑ፣ “ለዴሞድራሲያዊ ስርዓት መመስረት ከልባቸው የሚያምኑ ምክንያታዊ ‘ዴሞክራሲያዊ ሀገራዊ ብሄረተኞች’“ ናቸው። በኔ አስተያየት፤ ይህ አገላለጽ፣ በአንፃራዊነት ሲታይ፣ ያልተመጣጣነ ስለሆነ ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱ አይቀሬ ነው። ይህ አገላለፅ ቢያንስ ለኔ የሰጠኝ እንድምታ፣ ብሄረተኛ ድርጅቶች የጎሳ ድርጅቶ ስለሆኑና ሃገር አቀፍ ራዕይ ስለማያራምዱ፣ “ዴሞክራሲያዊ”፣ “ምክንያቲዊ”፣ “ለዴሞክራሲያው ስርዓት መመስረት ከልባቸው የሚያምኑ” ሊሆኑ አይቹሉም የሚለውን እንድምታ ነው። ይህን እንድምታ ደግሞ፣ እነዚህ አቆላማጭ ቅጽሎች የተለጠፈልባቸው “ሀገራዊ ብሄረተኞች” በአብዛኛው እንደሚደግፉት ለማወቅ ሳያቋርጡ በተለያዩ ድህረገፆች ላይ የብሄር ጥያቄን አስመልክቶ የሚወጡትን መጣጥፎች ይዘት በመቃኘት ብቻ መገመት አያዳግትም። ለዚህም ነው፣ እኛ ሃገራዊ ብሄረተኞች ነን የምንለው፣ ከብሄር ድርጅቶች ጋር እንኳን መሰማማት መተያየት ያቃተን። ለዚህም ነው፣ ግማሽ ምዕተ ዓመት ሊሞላው በተቃረበው ዘመናዊው የብሄር ጥያቄ ሳብያ እስካሁን ቀፍድዶ የያዘንን ችግር ማርገብ ተስኖን እያከረርንና እያጦዝን የምንገኘው። በሁለት አቢይ ተዋንያን የህብረተብ ወገኖች የሚተረኩ ታሪኮች ብሎ ያቀረበው የብርሃኑም የታሪክ አተረጓጎምም ይህን ችግር ለማርገብ የሚችል እንዳልመሰለኝ ልግለጽ።
ብርሃኑ በመጀመሪያ፣ ባጭሩ ፣ አንድ ገፅ ብቻ ፈጅቶ፣ የኦሮሞን “ማህበረሰብ እንወክላለን በሚሉ ብሄረተኛ የፖለቲካ ድርጅቶች ዘንድ የሚነሱ ታሪክ ነክ ጥያቄዎች” የሚላቸውን “ለአብነት” ያቀረበው ሲጨመቅ ይህ ነው፦
የኦሮሞ ሕዝብ በታሪክ የደረሰበት መጠነ ሰፊ ግፍ ከታሪክነት ባሻገር ፣ የባህል ፤ የሞራል፤ የስነልቦና አልፎም የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች በኦሮሞ ብሄር ህዝቦች ዘንድ ትቶ አልፏል። ለዚህ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው የኦሮሞ ህዝብ ያለምንም ጣልቃ ገብነት የራሱን እድል በራሱ ለመወሰን ሲችል ነው። ይህ ደግሞ ሊተገበር የሚችለው፣ የኦሮሞ ህዝብ የራሱን የተለየ የፖለቲካ ማህበረሰብ (አገር)ሲፈጥር ወይንም ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር የሚያስችለው በቂ የሆነ ራስን የማስተዳደር መብትና ባጠቃላይ በማህበረሰቡ ዘንድ ደግሞ ተገቢውን ቦታውን ሊያስይዘው የሚችለው አዲስ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ሲፈጥር ነው።
ቀጥሎም፣ በ “ዴሞክራሲያዊ ሀገራዊ ብሄረተኞች” በኩል፣ በማንነት ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ለሚያነሷቸው ታሪክ ነክ ጥያቄዎች የሚሰጠውን በታሪክ አተረጓጎም ላይ የተመሰረተ ምላሽ በየሚላቸውን አሥር ገፆች ያህል በመለገስ ሰፋ አርጎ ይዘረዝራል። ይህን ሰፊ ዘገባ፣ እንደ ላይኛው በአጭሩ ጨምቄ ማቅረብ ባልችልም፣ በጣም አጨናንቄ ብሰበስበው ከሞላ ጎደል የሚመስለው የሚከተለውን ነው፦
በሚንሊክ መስፋፋት፣ ከባላባቶችና ከወታደሩ ክፍል አልፎ የአማራው ህዝብ አላተረፈም። ይህ ቢሆን እንኳ፣ ከመቶ ዓመታት በፊት ለተደረገ ድርጊት በዛሬ ላይ ያሉ የአማራ ህብረተሰብ ክፍሎች ተጠያቂ የሚሆኑበትና በአያቶቻችው ወንጀል ካሳ ከፋይ የሚሆኑበት ምክንያት መኖር የለበትም። የኦሮሞ ባላባቶችና ንጉሶችም አሸናፊ በነበሩበት ዘመን በተሸናፍው ህዝብ ላይ ተመሳሳይ ግፍ ፈጽመዋል። ቋንቋ ላይ በተመሰረተ ፌደራላዊ አወቃቀር ስሌት፣ ቢያንስ ሰማንያ ስድስት (86) የሚሆኑ ግዛቶች ሊመሰረቱባት በምትችለው ኢትዮጵያችን ውስጥ፣ ይህን አወቃቀር ቁምነገር ብሎ የሚወስድ ብዙ ሰው አለ ለማለት ያስቸግራል። ለምንስ ነው ለፌደራላዊ አወቃቀር፣ቋንቋ ትንግርታዊ መስፈርት ሆኖ የሚቀርበው።ቋንቋ ባህልን የሚያመለክት ከሆነ ከቋንቋ በላይ የባህል መግለጫ የሆኑ ብዙ ቁምነገሮች አሉ። ለምሳሌ ሀይማኖት። ይህ፣ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የበላይነትን የያዘው የማንነት መስፈርት ከሌኒንና ከእስታሊን አስተምህሮት የተቀዳ፣ ነገር ግን በተግባር ብዙም የማያስኬድ እርዕዮተ አለማዊ መፍትሄ ነው ብዮ አምናለሁ። የማንንት ጥያቄ ካለ ደግሞ ፣ የግለሰብ መብትን ማዕከል ባደረገ ሥርዓት ሥር በሚደረግ የሽግግር ወቅት፣ ለተወሰነ ጊዜ የወል ስብስቦችን የጋራ ጥያቄዎች የሚያስተናግድበትን መንገድ በድርድር ማስተናገድ ይቻላል። ዞሮ ዞሮ ግን የዜጎችን ግለሰባዊ መብትና ግዴታ የተንተራሰ ዘላቂ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትሲገነባ ይህ ጥያቅ እየከሰመ የሚሄድ ጥያቄ ነው።
በብርሃኑ አባብል፣ እነዚህ ከላይ የተቀመጡት መልሶች “ጭፍን በሆኑ ‘ሀገራዊ ብሄረተኞች’በኩል ሳይሆን ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት ከልባቸው በሚያምኑ ምክንያታዊ ‘ዴሞክራሲያዊ ሀገራዊ ብሄረተኞች’ በኩል” የተሰጡ ናቸው። ብርሃኑም ይህን በራሱ ብዕር የተዘከረውን የዚህን የህብረተሰብ ክፍል የታሪክ አተረጓጎም እንደሚጋራ መጸሃፉን ላነበበ ግልጽ ነው።
ባይሆን ኖሮ፣ የማይሰማማባቸውን ነጥቦች በጠቆመን ነበር። በአንጻሩ ደግሞ፣ “ጭፍን” በሆኑ “ሀገራዊ ብሄረተኞች” በኩል የሚሰጡት መልሶች ምን እንደሆኑ ብርሃኑ አልነገረንም። ይህን ቢነግረን ኖሮ፣ የጭፍኖቹ ታሪክ አተረጓጎም ጭፍን ካልሁኑት የሚለይበትን ማመዛዘን እንድንችል በረዳን ነበር። እንደኔ ከሆነ፣ እነዚህ መልሶች፣ ጥያቄውን ለማራከሻና በወጉ ላለመስማት የሚቀርብ ምክንያቶች እንጂ፣ በእርግጥ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት ከልባቸው በሚያምኑ ምክንያታዊ ‘ዴሞክራሲያዊ ሀገራዊ ብሄረተኞች’ መስጠት ያለባቸው መልሶች አይመስሉኝም። በኔ ግምት፣ ይህን አይነቱ የታሪክ ግንዛቤም ነው፣ እራሳችንን ሀገራዊ ብሄረተኞች ብለን የምንጠራው የህብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ ግድፈት።
የኦሮሞ ብሄረተኞች የሚሟገቱት አያቶቻቸው ለሰሩብን በደል የአሁኑ የአማራው ብሄረሰብ ትውልድ ህዝቦች ካሳ ይክፈሉን በማለት አይመስለኝም፤ የራሳችንን እድል በራሳችን የምንወስንበት መሰረታዊ የሆነ መብታችን ይታወቅልን ብለው እንጂ። ይህ መሰረታዊ የሆነ የህዝቦች መብት፣ ከአርባ አምስት አመታት በፊት በተባበሩት መንግትሥታት ማህበር ሁለት ስምምነቶች የተደነገገው፣ እስታሊንና ሌኒን አምነውበት ነበር በማለት አይደለም፤ የጊዜው መስረታዊ የሆነ የህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ጥያቄ መሆኑ ታምኖበት እንጂ። ብርሃኑ፣ በዚህ ትተናው ላይ እንዳስቀመጠው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት በዛ ያሉ ብሄረሰቦች ውስጥ፣ “በጣም ትልቅ ቁጥር ያለው“ የኦሮሞ ብሄረሰብ ነው። የዚህ ብሄረሰብ ህዝቦች፣ አንድ የሚያደርገንን ቋንቋችንን ማዕከል አድርገን በፌደራላዊ አወቃቀር በምትገዛ ኢትዮጵያ ውስጥ በክልላችን እራሳችንን ማስተዳደር እንፈልጋለን ቢሉ፣ “ለምንስ ነው፣ ለፌደራላዊ አወቃቀር፣ ቋንቋ ትንግርታዊ መስፈርት ሆኖ የሚቀርበው” ብሎ ሙግት ውስጥ መግባት ትርፉ ምንድን ነው? በአገሪቷ ውስጥ 86 ቋንቋዎች ኖሩ አልኖሩ፣ ሌሎቹን 85 ቋንቋዎች የሚናገሩት ህዝቦች በቋንቋችን ዙሪያ ተሰባስበን እራሳችንን እናስተዳድር አሉ አላሉ፣ እኛ የኦሮሞ ብሄረሰብ ህዝቦች የምንፈልገው ግን ይህን ነው ማለታቸው፣ ዴሞክራሲያዊ ነኝ ለሚለው ሀገራዊ ብሄረተኛ የማይዋጥለት ምክንያት ምንድን ነው? ጥያቄያችሁ፣ የግለሰብ መብትን ማዕከል ባደረገ ሥርዓት ሥር በሚደረግ የሽግግር ወቅት፣ ለተወሰነ ጊዜ መስተናገድ ይችላል ማለት ትርጉሙስ ምንድን ነው? የኦሮሞ ብሄረተኞች ጥያቄ እኮ በተወሰነ ጊዜ የተከለለ የሽግግር ወቅት መስተንግዶ ይደረግልን አይመስለኝም፤ በዘላቂነት እራሳችንን በራሳችን የምናስተዳድርበት መሰረታዊ የሆነ ዲሞክራሲያዊ የወል መብታችን ይጠበቅልን እንጂ። ብርሃኑ ቋንቋን አስመልክቶ በተጠቀመበት የአጠያየቅ ስሌት ፣ “ለምንስ ነው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዐት መመስረት፣ የግለሰብ መብት ብቸኛ ማዕከልነት ትንግርታዊ መስፈርት ሆኖ የሚቀርበው?” ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ምን ሊሆን ነው? በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ሥር፣ ለግለሰብ መብት ከወል ስብስቦች መብት የበለጠ እውቅና መሰጠት አለበት ብሎስ የደነገገው ማን ነው? “ከስታሊን ቀኖና” በተላቀቅን ማግስት፣ በቅጡ ሳንመረምር በዛው ፍጥነት የተነከርንበት የኔዮሊበራል ቀኖና ይሆን?
እኔ እንደሚመስለኝ፣ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ የአንድ ብሄረሰብ ህዝቦች በድምጽ ብልጫ ተጠቅመው፣ ቋንቋቸውን ማዕከል ባደረገ አወቃቀር ሥር ተሰባስበው፣ እራሳቸወን በራሳቸው ሊያስተዳድሩ የሚችሉበትን መብት አይጻረርም። የኦሮሞ ብሄረተኞች፣ ይህን ፣ በፌደራል አወቃቀር ስር እራሳችንን የማስተዳደር መስረታዊ መብታችንን ሀገራዊ ብሄረተኛ ነኝ የሚለው ክፍልና በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት አንቀበልም ካሉ፣ የቀረን አማራጭ “የኦሮሞ ህዝብ የራሱን የተለየ የፖለቲካ ማህበረሰብ (አገር)” እነዲፈጥር የሚያስችለንን ሁኔታ እስክናገኝ ድረስ ሳናቋርጥ መታገል ነው ቢሉ፣ የዚህ እምነታቸው ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ምኑ ላይ ነው?
ብርሀኑ፣ “አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከሃያ አመታት በላይ፣ ቋንቋን ማዕከል ባደረገ ማንነት ከፍሎ የዜግነት መግለጫ ሁሉ የነዚህ ማንነቶች ውጤት አድርጎና አገሪቷን አዋቅሮ” እንደሚገዛ ነግሮናል። በዚህም ምክንያት፦ “ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ክፍል ይህንን የማንነት መግለጫ ከምር ወስዶና ከዚህ ጋር አብሮ የመጣውን ፌደራላዊ አስተዳደር እንደአሁኑ ለይስሙላ ሳይሆን በእውን ተግባራዊ እንዲሆን አድርጎና ለወደፊትም ጠብቆ ለማቆየት ይፈልጋል”ብሎናል፣ ብርሃኑ በመቀጠል። ይን አባባል ከሞላ ጎደል ትክክል ይመስለኛል። በኔ አስተያየት የጎደለው ነገር ቢኖር፣ ቋንቋን ማዕከል ያደረገ ፌደራላዊ አወቃቀር በረጅም ትግላችን ያገኘነው የትግል ፍሬ እንጂ፣ በሕወሃት እንካችሁ ተብሎ የተለገሰን ስጦታ አይደለም ለሚለው የኦሮሞ ብሄርተኞች እምነት፣ አነሰም በዛ እውቅና አለመስጠቱ ነው።
የኦሮሞ ብሄረተኛ የፖለቲካ ድርጁች፣ ቢያንስ ኦነግ፣ በባሌ የኦሮሙያ ክልል ውስጥ በ1950ው አስርተ ዓመት አጋማሽ ላይ ከአራት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ የዘውዱን አገዛዝ በረጅም የትጥቅ ትግል የተፋለሙበት የትግል ዘመን የራሳቸውን እድል በራሳቸው
ለመወሰን የሚችሉበትን አስተዳደር ለመፍጠር እንደነበር በየጊዜው ማስረዳታቸው አልቀረም። እንደ ሻቢያና ሕውሃት በለሱ ባይቀናውም፣ ኦነግም የደርግ አገዛዝ ከጀመረ እስከ ወደቀበት ዘመን ድረስ በትጥቅ የወታደራዊው መንግሥትን ይታገል እንደነበር ግልጽ ነው። ደርግ በወደቀበትም ወቅት፤ ኦነግ በአብዛኛው የኦሮሞ ክልል ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ እንደነበረውም አይታበልም። ብዙ ሳይቆይ፣ ሕወሃት ጦሩንና በምስሉ የፈጠረውን ኦህዴድን ተጠቅሞ ኦነግን ከውድድር ውጭ እንዲሆን ያደረገውም፣ ይህው የህዝቡ ድጋፍ ስላስደነገጠው መሆኑ ብዙ አያጠያይቅም ። በኔ ግምት፣ አሁንም ቢሆን የኦሮሞ ብሄረተኛ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚታገሉት፣ ቋንቋቸውን ማዕከል ያደረገ ፌደራላዊ አስተዳደር ፣ “እንደ አሁኑ ለይስሙላ ሳይሆን በእውን ተግባራዊ እንዲሆን” ይመሰለኛል። ብርሃኑ እንደጠቆመው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ይህን አጥብቀው የሚቃወሙ በዛ ያሉ ሃገራዊ ብሄረተኞች አሉ። በብርሃኑ አባባል፣ ይህ ልዩነት ሊታረቅ ወይም ሊፈታ የሚችለው፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማቋቋም በምንጓዝበት ወቅት “በመጀምሪያ በሰጥቶ መቀበል ድርድር ቀጥሎም በዚህ ድርድር የሚደረስበት ውጤት ቀስ በቀስ ተግባራዊ ሲሆንና በተግባራዊነቱም የማህበረሰቡን ተጨባጭ ድጋፍ ቀስ በቀስ እያገኘ ሲሄድ ብቻ ነው።” እኔም፣ እነዚህ ሃገራዊው ብሄረተኞች መሰረታዊ ለሆነ የብሄር ጥያቄ የሚሰጡት መልስ፣ በመልስነት የተገደገ፣ እንኳን ለመወያየት ለመታያየት የማያስችል እረጅም አጥር ነው ብየ ባምንም፣ መፍትሄው ላይ የሚደረስብት ሂደት፣ መሠማማትን፣ መነጋገርንና መደራደርናን የሚያካትት እስከሆነ ድረስ ቅሬታ አይኖረኝም።
በዚሁ “የማንንት” በብሄር ጥያቄ ላይ ብርሃኑ በመጸሃፉ ያሰፈራቸውን እኔም ከላይ አስተያየቴን የሰጠሁባቸውን ነጥቦች አስመልክቶ፤ ከሌላ አኳያ በሰላ ብዕር መነደፍ መጀመሩን ይህችን መጣጥፍ በመጫጫር ላይ እያለሁ፣ በተስፋዬ ደምመላሽ “የግንቦት ሳባት ፓለቲካና የዛሬው የለውጥ ትግል” በሚል ርዕስ የተጣፈች ጦማር በማንበብ ተገንዝቤያለሁ። የተስፋዬን ትችት ምን ያህል እኔ ካቀረብኩት አስተያየት እንደሚለይ አንባቢ እንዲገነዘው ያህል፣ ከጽሁፉ ውስጥ በአንድ አንቀጽ ሥር የተካተቱ ሶስት አረፍተነገሮች መዝዤ ላቅርብላችሁ። አረፍተነገሮቹ ፣ ብርሃኑ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲል፣ እነዚህን የጎሳ ፖለቲካ ፈጣሪዎች እየተሞዳሞደ እንዳለ የሚጠቁሙ ሲሆኑ፣ ሰለመጸሀፉ የሚለው እንዲህ ነው፦
አቀራረቡ የዘር ፖለቲከኞችንና ሊህቃንን በሃሳብና በውይይት ከመፈታተንና የአንድ አገራዊ ለውጥ ትግል አመራር ወይም አካል ለማድረግ ከመጣር ይልቅ እነዚህን ግለሰቦችና ወገኖች ከነጎሳ ፖለቲካቸው መሳብና በነሱ ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት ማግኘት ላይ ማተኮር፣ “ለቅንጅት” ማባበል ነው። ለምሳሌ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የዘር ብሔረተኞችን ሃሳቦች በተገቢ ትንተና ከመፈተሽ ይልቅ የነዚህን ታሪክ በድሎናል ባይ ወገኖች “ጭንቀቶች” በውይይት “ማረጋጋት” እና “ማለሳለስ” አስፈላጊነትን ያጎላል። ብሔረተኝነታቸው የታነጸበትንና የተማከለበትን ስታሊናዊ ቀኖና የኢትዮጵያ ታሪክ ትንተና መሣሪያቸው አድርጎ አይቶ ያልፈዋል።
ትንሽ ወረድም ብሎ፣ ይህ አይነት አቀራረብ የሚያሳየው ብርሃኑ የሚመራው እንቅስቃሴ “አገር አዳኝ ብሔራዊና ስልታዊ ራዕይ” አለማዳበሩን ነው ይልና አገር አዳኝ ራዕይ “ለአገር ከፋፋይ የዘር ፖለቲካ ምንም ቦታ የሌለው” መሆኑን ሰፋ አርጎ ያብራራል።
ተስፋየ ይህን አቋም በጽናት ማራመድ የጀመረው ቢያንስ የደርግ ዘመን ማገባደጃ ከባቢ እንደነበር አውቃለሁ። በአጋጣሚ ተስፋዬም፣ ብርሃኑም፣ እኔም በመስራችነት እንሳተፍባት በነበረችው የ “እምቢልታ” መፅሄት የመጀመሪያ እትም ላይ “የብሄራዊ ማንነትና ልዩነት ፖለቲካዊ ቋንቋና አይዲዮሎጂ” (ትርጉም የኔ) በሚል ርዕስ በጻፈው ጽሁፍ ሥር ይህው አቋሙ ተንጸባርቆበት ይገኛል። በዚሁ ጥያቄ ላይ፣ ይሄንኑ አቋሙን ሳያሰልስ በየጊዜው በጽሁፍ ማቅረቡን እስካሁን አላቋረጠም። እኔ ከብርሃኑ በስተግራ ቆሜ፣ በመጸሃፍህ ውስጥ የኦሮሞ ብሄረተኞችን ለውይይት የሚያበቃ እውቅና አልሰጠሃቸውም ብየ ስከራከር፣ ቁስላችን ገና አልደረቀም ሲሉህ የለም ሽሮ ጠባሳ ሆኗል ማለትህ በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት የሚለውን የአበው ተረት ያንጸባርቃል ብየ ስሟገት፣ ተስፋየ በሩቁ ከቀኝ ሆኖ ፣ ጎሰኞችን ምን “ማባበል”፣ ምን “ማረጋጋት”፣ ምን “ማለሳለስ” ያስፈልጋል፤ በማለት ይሟገታል። “የታነጻችሁበትንና የተማከላችሁበትን ስታሊናዊ ቀኖና” አውልቃችሁ ጥላቹሁ፣ የእኛ ሃገራዊ ብሄረተኞች አንድ አካል አንድ አምሳል ሆናችሁ ትግሉን እስካልተቀላቀላችሁ ድረስ እዛው በጠበል መባል አለባቸው የሚለውን ከሃያ አመት በላይ ይዞት የቆየውን የራሱን “ቀኖና” ለጥያቄው መልስ እንደሆነ አርጎ ያቀርብልናል።
ይህችን የተስፋዬን ፅሁፍ ሳነብ፣ እንዲህ አይነቱን ቅስፍ አርጎ የሚይዝ “አገር አዳኝ ራዕይ” የዛሪ ሃያ አመት አካባቢ በሰፊው ሲስተጋባ በቅጡ የተመለከተው ደረጀ አለማየሁ ፣ አንባቢ እንዳይስተው ለማድረግ ሁኔታውን አጩሆ የገለጸበት አንድ አባባል
ትዝ አለኝ። ቃል በቃል ባይሆንም፣ ይህ አይነት ራዕይ ታላቅ ፍቅርን ለማሳየት ሲል አጥብቆ በመሳም አፍኖ የሚገለውን የወዳጅ አይነት ነው በማለት ነበር ደረጀ የገለጸው። ይህችን የተስፋዬን ጽሁፉ እንዳነበብኩም ፣ ብርሃኑን ለቀቅ አድርጌ ከተስፋየ ጋር ሙግት መግጠም ዳድቶኝ ነበር። ይህ ደግሞ ከተነሳሁበት ውሱን አላማ ያዋጣኛልና፣ አልገፋሁበትም። እንደውም፣በብርሃኑም መጽሃፍ ላይ ቢሆን በዚህ ነጥብ ዙሪያ በበቂው ሃሳቤን አቅርቤበታለሁና፣ ብርሃኑንም ተወት አርጌ በሁለተኛው ነጥብ ላይ ወዳለኝ አስተያየቴ ይዣችሁ ልሂድ።
በዴሞክራሲያዊ ሄደት ላይ
የሁለተኛው ትዝብታዊና ጥያቄ አዘል አስተያየቴ፤ ብርሃኑ መሰረታዊ እምነቱ መሆኑን ሳያሰልስ ባስታወቀን የዴሞክራሲያዊ ሂደትን ወሳኝነት በሚያረጋግጠው ንጥረ ሃሳብ ጋር የተያያዘ ነው። ብርሃኑ፣ የዴሚክራሲ ሥርዐት መኖር ለማንኛውም አገርን ነክ ፖሊሲ አነዳደፍ፣ አጸዳደቅም ሆነ አተገባበር ሂደት ትክክለኛነት ወሳኝ መሆኑን በመጸሃፉ ግልጽ አድርጎልና። ለዚህ ሌላ አቋራጭ መንገድ የለውም። የዴሞክራሲ ሥርዓት በሌለበት አገርም፣ ይህን ስርዓት ለመመስረት የምንረማመድበት የትግል ሂደት የዴሞክራሲያዊ መስፈርቶችን ካላሟላ ውጤቱ ስኬታማ አይሆንም። ከመጸሃፉ ይዘት አጠቃላይ መልእክት ተነስተን፣ ይህ መሰረታዊ ሃሳብ ለብርሃኑ አልፋ ኦሜጋ ነው ለማለት እንችላለን።
በተጨማሪ ደግሞ፣ ብርሃኑ ከምሁርነት ሥራውና ሙያው ባሻገር፣ የፖለቲካም ንቅናቄ መሪ መሆኑ ግልጽ ነው። ብርሃኑ የሚመራው የግንቦት 7 ንቅናቄ የሚከተለውን የትግል ስልት የትጥቅ ትግልንም ይጨምራል። እኔ እንደምረዳው፣ የትጥቅ ትግል ግቡን እንዲመታ፣ እንደ ሰላማዊ ትግል ስልት “እየሞቱ ነው ትግል” ብሎ አያቆምም፤ “እየገደሉ ነው ድል” ማለትንም መጨመር ይኖርበታል። እየገደለ ድል የተቀዳጀ ስልጣን ሲይዝ ደግሞ፣ በትንቅንቁ ወቅት በተሰዉበት ጓዶቹ ሥም በበቂ የደም ካሳ ሳይሰበስብ ስልጣኑን እንደማይለቅ ታሪክ ይነግረናል። ትግሉን ሲጀምር፣ ከድል በሗላ በትረ ሥልጣኑን ለህዝብ የማስረከብ ሃሳብ ቤኖረው እንኳን፣ በስልጣን ላይ እያለ የደም ካሳው ስብሰባ ምርኮኛ/ሱሰኛ ሆኖ የመቅረት እድሉ ከፍተኛ ስለሆነ ከጊዜ በሗላ እንደኔ ባሩድ ያሸተተ በጠመንጃ ታግዞ እስካላስለቀቀኝ ድርሰ ወይ ፍንክች ማለቱ አይቀሬ ነው። ደም አፍሶ ስልጣን የያዘ፣ በኮሮጆ ውስጥ በታጨቀ ወረቀት ተሸንፎ ሥልጣን በፍቃዱ ለህዝብ ሲያስተላልፍ ታሪክ አሳይቶን አያውቅም። በሕዝብ ግፊት ምርጫ ለማካሄድ ቢሞክር እንኳ፣ እንደማያዋጣ ሲያውቀው ኮሮጆውን መድፋቱ አይቀሬ እንደሆነ ለመረዳት፣ ታሪክ ፍለጋ ካገራችን ውጭ መጓዝ አያስፈልገንም።
ይህን አወንታ ብርሃኑ መረዳት የሚሳነው ማይሆንም ቅሉ፣ የትጥቅ ትግልን እንደ አመራጭ ለመጠቀም የወሰነ ንቅናቄ በመምራት እየተንቀሳቀሰ ነው። ከላይ እንዳስረዳሁት፣ ብርሃኑ በመጸሀፉ የዴሞክራሲ ሥርዐትን ለመመስረት የምንረማመድበት የትግል ሂደት የዴሞክራሲያዊ መስፈርቶችን ካላሟላ ውጤቱ ስኬታማ እንደማይሆን በማያሻማ ትንታኔ አቅርቦልናል። የትጥቅ ትግል ሂደትደግሞ፣ በተፈጥሮው የዴሞክራሲያዊ ሂደት መስፈርቶችን ማሟላት አይችልም። በኔ እምነት፣ የትጥቅ ትግልና የሰላማዊ ትግል ስልቶች ባመዛኙ ተጻራሪዎች እንጂ ተደጋጋፊዎች አይደሉም። የብርሃኑ ድርጊትና ቃል ለየቅል የሆኑትም በዚህ ላይ ይመስለኛል። ብርሃኑ፣ ይህንን በመጸሃፉ በብቃትና በጥራት ያስረዳንን እምነቱን፣ ከትጥቅ ትግል መሰረታዊ ጸባዩ ጋር እንዴት ሊያጣጥም እንደቻለ በምክንያታዊነት ላይ የተመረኮዘ ትንታኔ ሊሰጥበት እስካልቻለ ድረስ፣ በመጸሃፉ ላይ ያሰፈረውን መሰረታዊ እምነቱን በርግጥ እራሱው እንደሚያምንበት ሙሉ ለሙሉ በቀበል ያዳግታል ባይ ነኝ።
መደምደሚያ
በመጸሃፏ የሗላ ሽፋን ላይ ባጭሩ በሰፈረው ስለመጸሃፏ ያለኝ አጠቃላይ አስተያየት እንዳሰቀመጥኩት፦
ብርሃኑ፣ በዚች መፀሃፉ ውስጥ በተደጋጋሚ የመዘገባቸው ነጥቦች ቢኖሩ፣ መጸሃፉ መሰረታዊ በሆኑ ሶስት ችግሮች ላይ ብቻ በማተኮርና በነዚህ ችግሮች ላይ የጨረፍታ እይታዎቹን በማንፀባረቅ፣ የአጠቃላይ የአገሪቷን ችግሮች ውስብስብነት ለማሳየትና በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት ለመክፈት ያለመ እንጂ ሁሉንም አይነት የአገሪቷን ችግሮች ለማካተት ያልከጀለ መሆኑን ነው። ይህችን መጸሃፍ አንብቤ ስጨርስ
የተረዳሁትም፣ ከመመጻደቅ በነፃ፣ በኔ አውቅልሃለሁ ምሁራዊ ግብዝነት ባልታጀለ የአፃፃፍ ስልትና ይዘት፣ የተለመውን ውሱን አላማ በብቃት እንዳሟላ ነው።
ብርሃኑ፣ እነኝህን ችግሮች ለመፍታት የሚቀርቡ የመፍትሄ አመራጮችን በዝርዝር በመመልከት፣ ችግሮቹን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት ባይቻል እንኳ፣ በተቻለ መጠን ለመቅረፍ፣ ከነጉድለቱም ቢሆን፣ ዲሚክራሲያዊ ስርዐት ለምን ምትክ የሌለው ብቸኛው መንገድ እንደሆነ የሚያስረዳበትን የመከራከርያ ሃሳብ በሁለተኛው የመጸሃፉ ክፍል ይዞልን እንደሚቀርብ አስቀድሞ አብስሮናል። እኔም እሰየው እያልኩ፣ ይህ አላማው እንዲሳካለት፣ ብርታቱንና ፅናቱን ባልጠራጠርም፣ ጤንነቱን እንዲሰጠው እመኝለታለሁ። በዚች ግምገማየ ላቀረብኳቸው ሂስ አዘል ጥያቄዎችም ሆነ በሌሎች አንባቢዎችም ለሚሰነዘሩበት ተጨማሪ ሂሶችና ጥያቆውች በሁለተኛው የመጸሃፉ ክፍል አመርቂ መልስ እንደሚሰጥበቸው እተማመናለሁ።
የዛ ሰው ይበለን!

No comments:

Post a Comment