በተክሉ አባተ
ባህል ብዙ ትርጉም ይኖረዋል:: ለእኔ ግን የአንድ ኅብረተሰብ የአስተሳሰብ: የጠባይና: የባህርይ መገለጫ ወይም ምልክት ነው:: በተፈጥሮ (በዘር ውርስ) የማይገኝና በሰው ብርቱ ጥረት የሚፈጠር ስለሆነ እያንዳንዱ አገር የራሱ የሆነ ልዩ ባህል አለው:: ለልጅ ልጅም በትምህርትና በተሞክሮ ያስተላልፋል:: በጊዜ ብዛትና በተለያዩ ብሄራዊ: ክልላዊና: ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች የተነሳ ባህል ሊከለስ ሊዳብር ሊለወጥም ይችላል:: ያም ቢሆን ግን አገራት በባህላቸው ልዩ የሆኑ ናቸው (የዓለም ህዝቦች የሚጋሩትም ባህል እንዳለ ሳንረሳ):: በአጠቃላይ ባህል የኅብረተሰብን ምንነትንና ማንነትን ገላጭ ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም::
ዳሩ ግን ሁሉም ባህሎች ጠቃሚ ወይም ገንቢ ላይሆኑ ይችላሉ:: እንዲያውም በባህል ስም ‘ገዳይ’ የሆኑ አስተሳሰቦችና ምግባራት ሊስተዋሉ ይችላሉ አሉም:: ለግለሰብ እድገት ጤናና ሰላም እንዲሁም ለአገር መሻሻል ልዩ አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ባህሎች እንዳሉ ሁሉ ባለንበት እንድንሄድ እንዲያውም ባላንስ እንዳጣ መኪና ወደኋላ እንድንሸራተት የሚያደርጉ ባህሎችም አሉ:: እነዚህን ወደፊት እንድንሄድ የማያግዙ ወይም ወደኋላ የሚጎትቱንን ጎጅ ባህሎች ብያቸዋለሁ:: ቆም ብለን ማሰብና መገንዘብ መመርመር ከፈለግንና ከቻልን ጎጅ ባህሎችን መለየት እንችላለን:: እንዲህ ማድረግ ከቻልን ደግሞ ጠቃሚ ባህል ግንባታ ላይ እናተኩራለን:: ለግል ህይወታችንና ለአገራችንም ጠቀም ያለ ለውጥ ባጭር ጊዜ ማምጣት እንችላለን:: በመሆኑም በዚህና በቀጣይ ጽሁፎች ለኛ ለኢትዮጵያውያን ጎጅ ናቸው ብዬ የማስባቸውን የምንነታችንንና የማንነታችንን መገለጫ የሆኑ ባህሎቻችንን ለመለየት እሞክራለሁ::
ጎጅ ባህል ስል ግን ሁሌ አሰልቺ በሆነ መልኩ በሚዲያ የሚለፈፉትን አይነት ማለቴ አይደለም:: ለእኔ ጎጅ ባህል ግግ ማውጣትን: እንጥል መቁረጥን: የሴት ልጅ ግርዛትን: ያለእድሜ ጋብቻን: ያለአቅም ድግስን: እጅ ሳይታጠቡ መመገብን: ወዘተረፈ አይመለከትም:: ምንም እንኳን እነዚህ ተግባራት ጎጅነታቸው የማያነጋግር ቢሆንም ለእኔ ግን በአሁኑ ጊዜ አሳሳቢ ሆነው አይታዩኝም:: ትኩረቴ የሚሆነው አስተሳሰባችንን ጠባያችንንና ምግባራችንን ማእከል ባደረጉ ደካማ ባህሎቻችን ላይ ነው:: እነዚህ ባህሎች ላለፉት በርካታ ዓሥርት ዓመታት ባለንበት እንድንረግጥ እንዲሁም በአንዳንድ የህይወት ዘርፎች ወደኋላ በፍጥነት እንድንጓዝ ያደረጉን ናቸው ብዬ አምናለሁ:: ለብሄራዊ ድቀታችን ግንባር ቀደም ተጠሪውና ተጠያቂው መንግስት ቢሆንም እንደህጻን ልጅ ተንከባክበን የያዝናቸው አንዳንድ ባህሎቻችንም ቀላል ያልሆነ አስተዋጽዖ አድርገዋል:: በግል ህይወት በቤተሰብ በጎረቤት በጓደኛ በመስሪያ ቤትና በብሄራዊ ደረጃ እንቅስቃሴያችን ጥራትና ዋጋ እንዳይኖረው የሚያደርጉ ብዙ ጎታቾች አሉን::
በተከታታይ የምዘረዝራቸው ባህሎች በተወሰነ መልኩ ደካማ ጎኖች ተብለውም ለፈረጁ ይችላሉ:: ለእኔ ግን ደካማ ጎን የግለሰብን ችግር አመላካች ስለሚሆን ቃሉን በዚህ ጽሁፍ እምብዛም አልጠቀመውም:: ጽሁፌን በደንብ እንድትረዱልኝ ግን በቅድሚያ ማሳሰቢያዎቼን ልጥቀስ:: አንድ: በጅምላ የኢትዮጵያ ባህል ገዳይ ወይም ጎጅ ነው እያልኩ አይደለም:: ለቁጥር የሚያዳግቱ የትም አገር የማይገኙ ወርቅ ባህሎች ሞልተውናል:: ለመሻሻል እንዲረዳን በጎጅዎች ላይ ብቻ ማተኮሬ እንጅ:: ሁለት: ቀጥዬ የምጠቅሳቸው ጎጅ ባህሎች ሁሉም ሰው ጋር አሉ የሚባል ባይሆንም ብዙዎቻችን ግን የምንጋራቸው ይመስላሉ:: ለማንኛውም እያንዳንዱ አንባቢ የየትኛው ጎጅ ባህል ሰለባ እንደሆነ ራሱ ይመርምር:: ሥስት: ይህ ጽሁፍ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በተሰበሰበ መረጃና ማስረጃ ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን ከማህበራዊ ሚዲያዎች የተመለከትኩትንና
በማህበራዊ ህይወት የታዘብኩትን መሰረት ያደረገ ነው:: አራት: ጎጅ ባህሎች በፖለቲካው ዘርፍ በሃይማኖት ተቋማት በስራ ቦታ በጓደኝነት ህይወት በቤተሰብ እንዲሁም በትዳር ህይወት ውስጥ እንደልብ ይገኛሉ:: አምስት: ባህል ሊተች የማይችል ቅርስ ነው ወይም እኛ ኢትዮጵያውያን ጎጅ ባህል የለንም ብሎ የሚያምን ሰው ካለ ቆም ብሎ አስተሳሰቡን ይፈትሽ:: ይህ አስተሳሰብ ራሱ የጎጅ ባህሎች ቁንጮ እንደሆነ ይረዳ:: ስድስት: የሚዘረዘሩት ጎጅ ባህሎች አዲስ ናቸው እያልኩም አይደለም:: በአንድም በሌላም መልኩ በተለያዩ ተችዎች ተነስተው ይሆናል:: ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በቀጣይነት መወያየት በእጅጉ ይጠቅማል በሚል እሳቤ ለማቅረብ ወሰንኩ:: ችግሮች እስኪጠፉ ድረስ አብዝቶ መወያየት ጥሩ ነው:: ሰባት: በዚህ ጽሁፍ የሚቀርበው ጎጅ ባህል ብሄራዊና ፖለቲካዊ አንደምታ ያለው ነው::
መሪ-መራሽ የለውጥ ትኩሳት
በብሄራዊ ደረጃ ፖለቲካዊ እምርታ ሳናስመዘግብ የቀረነው በበርካታ እንቅፋቶችና ምክንያቶች ነው:: በእኔ እይታ ግን መሪን ያማከለ እንቅስቃሴ ወይም ትግል በተደጋጋሚ ማድረጋችን ለውድቀታችን ዋና መንስኤ ነው:: መሪዎች ለውጥ እንዲመጣ የማይናቅ ድርሻ ማድረግ እንደሚችሉ የማይካድ ቢሆንም እኛ ግን ከሚገባው መጠን በላይ መሪዎችን እንደአጥቢያ ኮኮብ ያለምንም መጠራጠር ስንከተል በተደጋጋሚ ጉድ ሆነናል:: የመሪዎች መሰደድ ወይም መታሰር ወይም መሞት ድንገት እንደነጋበት ጅብ ክፉኛ አስደንግጦናል:: መሄጃም አሳጥቶናል ልንወድቅም ተፍግምግመናል እየተፍገመገምንም ነው::
ለማስረጃ ያህል ብዙ ማለትይቻላል:: ጃንሆይ እግዚአብሔር የቀባቸው ታላቅ መሪ ናቸው ብሎ ብዙው ሰው ያምን ስለነበር በወቅቱ የተከሰቱ አስተዳደራዊ ችግሮችን ለመፍታት አልተቻለም:: ኢትዮጵያ ማደግ የምትችለው በሳቸው ሥራ ብቻ እንደሆነ ታመነ:: በአጠቃላይ ንጉሡ አንዳች ነገር ሰርተው ለውጥ እንዲያመጡ ለዘመናት ተጠበቀ:: መጨረሻ ላይ በመሪ- ተኮር ለውጥ ባህል መያዝ ያልፈለጉ የወጣቱና የጦሩ ክፍል ተነሳና ሌላ ምዕራፍ ተጀመረ:: በኋላም ጓድ መንግስቱ ለውጥና እድገት እንዲያመጡ ለዘመናት ተመኘን:: መሪው ሲኮበልሉ ጅምሮች ሁሉ እንዲጠፉ ተደረገ:: የኢሕአፓ ትንታግ መሪዎችን በማየት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ተስፋ ተጣለ:: ወጣቱም ንቁ ተሳታፊ ሆነ:: መሪዎቹ ሲሰደዱና ሲታሰሩ እንዲሁም ሲሞቱ የተሰነቀው ተስፋ የማይጨበጥ እንደሆነ ግልጥ ሆነ:: ከዚያም መለስ ዜናዊ አገሪቷን በመዳፋቸው ስር አደረጉ:: በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ (ደጋፊውም ተቃዋሚውም) ለውጥ የሚመጣ ከሆነ በሳቸው ብቻ እንደሆነ አሰበ:: ድንገት ሰውዬው ሲሞቱ ድርጅታቸውም አብሮ ሞተ:: ተከታዮቻቸውና ተቃዋሚዎችም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ባለማወቅ ግራ ተጋቡ:: መሞታቸውንም ለመቀበል የተቸገሩ ደጋፊዎች ነበሩ:: ግን ሁሉም ሰው በብዙ ጎጅ ባህሎች የተጠቃ ስለሆነ ያለተቀናቃኝ መልሰው የፖለቲካውን መዘውር ጨበጡት:: ቅንጅት መንፈስ ነው እስኪባል ድረስ በፍጥነት በህዝብ ልብና ህሊና ውስጥ ገባ:: መሪዎች እንዳልሆነ ሲሆኑ እንደብረት ግሎ የነበረ ትግል እንደ በረዶ ቀዘቀዘ:: የአገር መሪዎችን እንደ ምሳሌ አነሳሁ እንጅ መሪ የማምለክ አባዜ በሁሉም የኑሮ ደረጃና ዘርፍ ይታያል:: በመስሪያ ቤት አለቆች ብቻ ለውጥ እንዲያመጡ በንቃት እንጠብቃለን:: ሌላው ቀርቶ በሥራ ቦታ የተፈቀደልን መብት ሲጣስ ዝም ብለን እናልፋለን:: ሌላ ሰው እንዲከራከርልን እንጠብቃለን:: ስብሰባ ላይ ከአለቆች የተሻለና የተለየ ሃሳብ እያለን አንናገርም ተከራክረን ጥሩ ውሳኔ እንዲተላለፍ የበኩላችንን አስተዋጽዖ አናደርግም::
በጓደኝነትም ችግሩ እንዲሁ ነው:: ብዙ ጊዜ አንዱ በሃሳብ ወይም በሌላ ነገር ከፍ ብሎ ይታያል:: እሱ ያለው ካልሆነ ጓደኝነት ሊሰረዝ የሚችል ኮንትራት ነው:: ሌላኛው ጓደኛ ይህን ስለሚያውቅ የጓደኛው ተለጣፊ ሆኖ ይኖራል:: ሲሳሳትና መጥፎ ሥራ ሲሰራ ለማስተካከል አይጥርም:: የመናገርና በነጻነት የመኖር መብቱን ቀስ በቀስ ለጓደኛው ያስረክባል:: የሚዝናኑባቸው ቦታዎችና ቀኖች እንዲሁም የመወያያ ርዕሶች የሚመረጡት በአንደኛው ወገን ነው:: ሌላኛው ወገን ግን ሳያውቅ የበታችነት ስሜት እየተሰማው ቁጥብነት እያጠቃው ይኖራል:: እንዲህ አይነቱን ሰው ለብሄራዊ ለውጥና ለእድገት ለማሳተፍ አዳጋች ነው እሱን ንቁ ተሳታፊ ከማድረግ እድገት እራሱን ማምጣት ይቀላል:: የመሪና የተመሪነት ባህል በትዳርም ውስጥ ልዩ ቦታ አለው:: ባል ወይም ሚስት እንደፈርዖን የሚፈሩበት ቤት ሞልቷል:: ብዙ ጊዜ ባል አምባገነን ነው ይባላል ሊሆን ይችላል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሚስቶች ወሳኝና አደገኛ የሆነ አካሄድ ጀምረዋል:: ለመብታቸው መቆማቸው የሚበረታታ ነው:: ዳሩ ግን የነሱ የበላይነት ደግሞ አይጣል ነው:: የወንድን ጭቆና በሴት ጭቆና ለመተካት የሚደረግ ፍልሚያ እንጅ በእኩልነትና በመተሳሰብ የሚደረግ የለውጥ ጉዞ አይመስልም:: ጨቋኝ ባል ወይም ሚስት ሆይ የራሳችሁን መብት ለመጠበቅ የሌላውን ሰው መብት ማፈን ያለባችሁ አይመስለኝም:: በሃይማኖቱም በኩል ችግሩ ፈርጥሟል:: ቄሱ: ፓስተሩ: ሼኩ: ብለዋልና ፈቅደዋልና እያለ ሰብአዊ መብት ሲረገጥ መንፈሳዊ ህይዎት ሲቀጭጭ ዝም ብሎ የሚያየው እኮ በጣም እየበዛ ነው:: ዝምታው ስለበዛ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች እኮ ምድርን ገነት ሳይሆን ሲዖል እያደረጓት ነው:: ሴቶችን የሚደፍሩና ትዳር የሚበትኑ አሉ:: በሙስናና በዘር ግንድ የተጠመዱ ሞልተዋል:: የሰውን አእምሮ ሃይማኖታዊ በሚመስል ግን ባልሆነ ትምህርት አስንፈዋል:: የለውጥ ማዕበልን አፍነዋል:: ይህ ሁሉ የሆነው እነሱን ፍጹም መሪ አድርጎ ያለማስተዋል የሚንጋጋ መንጋ ስላለ ነው:: ይህ ጎጅ ባህል ነጻ ናቸው በሚባሉ የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ሥር መሰረቱን ዘርግቷል:: ሃይማኖቶች የሚያዝዙትን ከማወቅና ከማገናዘብ እንዲሁም ከመፈጸም ይልቅ መሪዎች የሚለፍፉትን በየቤቱ በተናጥል የሚሰሩትን መጥፎ ድርጊት መደግፍና መሸፋፈን እንደጽድቅ ሥራ እየተቆጠረ ነው:: ይህ ሲባል እውነተኛ የሃይማኖት መሪዎች የሉም ማለት አይደለም ቁጥራቸው ግን እጅግ ውሱን ነው::
ይህን ሁሉ ያነሳሁት መርህን ሳይሆን መሪን ያማከለ ትግል ዋጋ እንደሌለውና ጎጅ ባህል እንደሆነ ለማሳየት ነው:: ጃንሆይን: መንግስቱን: መለስን: ኢሕአፓን: ቅንጅትን የሃይማኖት ሰዎችን መሪና የለውጥ ሐዋርያ አርገን ተከተልናቸው:: ግባቸውን ዓላማቸውን እስትራቴጅያቸውንና ታክቲካቸውን በደንብ ሳናውቅና ሳናምንባቸው መሪዎችን አመንባቸው:: በጭፍንም ተከተልናቸው:: የነሱ እንቅፋት እኛንም ክፉኛ አደናቀፈንና ወደቅን:: በመሆኑም በዓለም ላይ ካሉ አገሮች በሁሉም የእድገትና የለውጥ መለኪያዎች አንሰን ተገኘን:: ወገኖቻችን በባዕድ አገር እንደአውሬ በመሳሪያ ይታደናሉ: በአደባባይ ይገደላሉ: በአረብ እስር ቤቶች የሰውነት ክፍላቸው ለገበያ ይቀርባሉ:: እንደዚህም ሆኖ ችግራችንን የሚፈታ አንዳች መሪ እንዲመጣ ቁጭ ብለን እንመኛለን:: ራሳችን ለውጥ ማምጣት እንደምንችል አናምንም:: ሌላው ቀርቶ የራሳችንን የግል ሰብአዊ መብቶች መሪዎች እንዲያስከብሩልን በትዕግስት እንጠብቃለን: ታዲያ ከዚህ የከፋ ምን ጎጅ ባህል አለ? ማንኛውንም ገንቢ አስተያየት በteklu.abate@gmail.com ይላኩ!

No comments:
Post a Comment