የግድያው መዘዝ ትላንት ከቀትር በኋላ ዲሲ በሚገኝ አንድ የሐበሻ ሬስቶራንት ምሳ እየቀማመስን ነበር። መግቢያ በሩን አልፎ ወደ ውስጥ የዘለቀው ሰው ትኩረታችንን ሳበው፤ ጥቁር አሜሪካዊ ይመስላል። ፀጉሩ ተንጨባሯል፣ ባዶ እግሩን ነው፣ ፂሙ ተንዥርጓል፣ ያጠልቀው የነተበ ጃኬትና የተቀዳደው ሱሪ ..ለረጅም ጊዜ ከላዩ ላይ ወልቀው እንደማያውቁ እንዲሁም ውሃ በገላው ከፈሰሰ አመታት እንደተቆጠሩ ሁኔታውን በማየት መረዳት ይቻላል።..በዝግታ ተራምዶ.. የምግብ ቤቱ ባለቤት ፊት ደርሶ ቆመ። ባለቤቱም « አንድ ግዜ ቆየኝ..» ብሎ በአማርኛ ሲናገር እየተመገበ የነበረው ሰው ሁሉ ትኩረቱ ወደ እዚህ ሰው ተሳበ። የሁላችንም ጥያቄ « ኢትዮጲያዊ ነው እንዴ?» የሚል ነበር። ..ከተቀመጥኩበት ተስፈንጥሬ በመነሳት ላናግረው ሞከርኩ፤ ግን አልተሳካልኝም። የሬስቶራንቱ ባለቤት « ማንንም አያናግርም፤ ከማንም ምግብና ሳንቲም አይቀበለም፤ አትድከም።» አለኝና በምን ምክንያት እንዲህ የአእምሮ በሽተኛ ሊሆን እንደቻለ ሲጠይቀው፥ « አሜሪካ ከ15 አመት በፊት ነበር የመጣው፤ ከአራት አመት በፊት በጣም የሚወዳት እህቱ በጥቁሮች በብዙ ጥይት ተደብድባ ስትገደል ተመለከተ። አንድ እህቱ እንዳዛ በጭካኔ ስትገደል በአይኑ በማየቱ ወዲያው አእምሮ ተነካ። ምንም አይነት ሱስ የለበትም። በጣም ጨዋና ጎበዝ ሰራተኛ ነበር። » አለኝ። …እነሆ ይህ ወገን በየጎዳናው ሲያድር የኢትዮጲያ ኮሚኒቲ ዞር ብሎ አለማየቱ አሳዛኝ ነው። ..ይህን እያብሰለሰልኩ እያለ አንዱ ኮሚኒቲ ማህበር ከሰሞኑ ለሃበሻው የበተነው የጥሪ ወረቀት እንዳጋጣሚ አገኘሁ፤ በደብዳቤው መግቢያ ከሰፈሩት ቀዳሚው፥ « ሕክምና፣ መጠለያ፣ ስራና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች በማጣት የሚንገላቱትን ወገኖች መርዳት..» ይላል። ..ይህ የማህበሩ “አላማ” መሆኑ ነው። ግን በወረቀት ላይ የሰፈረ፣ በተግባር ግን ያልተደገፈ..ለመሆኑ ማረጋገጫው ይህ የአእምሮ በሽተኛ ወገንና በየጎዳናው ወደቀው የሚታዩ ሓበሾች ናቸው። ..ሐበሻ በየአገሩ ስቃይና መከራ እጣ ፈንታችን ሆነ ማለት ነው!? (በፎቶው አእምሮው የተነካው ሃበሻ…)
No comments:
Post a Comment