እለተ ሰኞ – ጥቅምት ሊሸኝ ህዳር ሊገባ የቀሩት ጥቂት ቀናት ብቻ ናቸው። በሳውዲ አረቢያ በህጋዊ መንገድ ገብተው ከአሰሪዎቻቸው ጋር ባለመግባባትና ፈርጀ ብዙ በሆነ ምክንያት መኖሪያ ፍቃድ የተበላሸባቸው ማደስ እንዲችሉ ፣ ከአሰሪዎቻቸው ጠፍተው ያለ ህጋዊ ሰነድ በግል ሲሰሩ ለነበሩ ፣ ከአምስት አመታት በፊት በህጋዊ መንገድ በሃጅ በኡምራ ገብተው ወደ ሃገራቸው ሳይመለሱ በህገ ወጥ መንገድ ያለ መኖሪያ ፈቃድ በሳውዲ የሚኖሩትን ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚቆጠሩ የተለያዩ ሃገር ዜጎች ህጋዊ ሰንዳቸውን እንዲያስተካክሉ የሚፈቅደው አዋጅ ተጠናቋል። የጭንቁ ቀን ቀርቧል!
የሳውዲ መንግስት ለሁለተኛ ጊዜ የሰጠው የምህረት ሲጠናቀቅ ህገ ወጥ ተብለው የተፈረጁ በሳውዲ የሚኖሩ የተለያዩ ሃገር ዜጎች ከተያዙ የሁለት አመት እስራት እና የሳውዲ ሪያል 100. 000 ( አንድ መቶ ሽ የሳውዲ ሪያል በግምት ግማሽ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር) ቅጣት እንደሚጣል አስታውቋል ! …የምህረት አዋጁ ማለቁን ተከትሎ ከፍተኛ ፍተሻ እንደሚደረግ መንግስት ጠንከር ጠንከር ያሉ መግለጫዎችን ሰጥቷል። የውጭ ዜጎች በብዛት የሚገኙባቸውን የሳውዲ ከተሞች እስከ ደንበር የገጠር መንደሮች በልዩ ልዩ ሞተር ሳይክሎች መኪኖች እና ሂሊኮፕተር ሳይቀር በመጠቀም ፍተሻውን እንደሚያጠናክር አስታውቋል ። መንግስት በዚሁ አሰሳና አፈሳ ስራ ተሳታፊ የሚሆኑ የመንግስት ሚኒስትር መስሪያቤት በዋናነት ከሰራተኛ ሚኒስትር ። በፖሊስ እና ከደህንነት በተውጣጡ ኮሚቴዎች ስልጠና ሰጥቶ ፍተሻውን እንደሚያከሂድ ያስታወቀበት ቀን ደርሷል ። በማስጠንቀቂያው ህገወጥ የተባሉትን ብቻ ሳይሆን ህገ ወጥ የተባሉተን ማስጠጋት በራሱ ከከፍተኛ ገንዘብ ቅጣት ከሃገር እሰከ መባረር የሚያደርስ እርምጃ ይወሰድበታል የሚል ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ በእርግጥም ከሰባት ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው የውጭ ዜጋ አስፈሪና አሳሳቢ ጉዳይ ነው!
በተፈራው ቀን ሰኞ ጅዳ ከወትሮው በተለየ ጸጥና ረጭ ብላለች ፣ ግህ እንደቀደደ በማለዳው ልጆቸን ይዠ ወደ ጅዳ የኢትዮጵያን አለም አቀፍ ትምህርት ቤት ተጓዝኩ። በትምህርት ቤቱ ስደርስ የምህረት አዋጁን ማብቃት ተከትሎ መምህራን እና ሰራተኞች ባለመምጣታቸው ተረዳሁ። ትንሽ ቆየት እንዳለኩ በስጋት ላይ የነበረው የ3000 ታዳጊዎች የትምህርት ማዕከል መማር ማስተማር ሂደት በትምህርት ቤቱ አስተዳደር፣ በኮሚኒቲና በመንግስት ተወካዮች የቅርብ ክትትልና ግልጽነት ያለው አካሔድ አለመከተል መኮላሸቱ አበሳጭቶ ቀኔን አጨልሞ ጀመረው! ከሃገረ ጀርምን ትናነት ምሽት ያረፉትን የምሰራበት ኩባንያ የስራ ባልደረቦቸን ፊቴ በርቶ እንዳልቀበላቸው ምክንያት የሆነኝን ትምህርት ቤት ልጆቸን ወደ ቤት ከመለስኩ በኋላ በትካዜ ወደ ቢሮየ አመራሁ…!
እለተ ማክሰኞ – ከአመት እስከ አመት ሞቅና ደመቅ ያለ እንቅስቃሴ በሚታይባቸው የጅዳ ፣ የመካ ፣ የመዲናና ዋና ከተማዋ ሪያድ ወትሮ የነበረው እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን የተወረሩ ከተማ መስለው መታየታቸው ተጠቅሷል። በመንግስት ጠንካራ ፍተሻ ግራ የተጋቡ ዜጎች በአፈሳና ፍተሻው ፍርሃቻ ከቤት ባለመውጣት ጊዜውን በማሳለፍ ላይ ሲሆኑ በውጭ ዜጎች ይንቀሳቀሱ የነበሩ ሱቆች እና አንዳንድ ግልጋሎት መስጫዎች በመዘጋታቸውም ከተሞቹ ጸጥና እረጭ እንዲሉ በማድረግ በንግድ ልውውጡ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደራቸውን መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር በመዘገብ ላይ ናቸው ። የምህረት አዋጁን በመጠቀም እንድም መኖሪያ ፈቃድ አለያም የመውጫ ሰነድ ማግኘት ያልቻሉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ ሃገር ዜጎች ለጉዳያቸው መጓተት ሰበቦች የሳውዲ መንግስትን መስሪያ ቤቶች የተቆላለፈ ቢሮክራሲያዊ አሰራር እና የየሃገራቸው ቆንስልና ኢንባሲ ጽህፈት ቤቶችንም ሰነዶችን በጊዜ አለማቅረብ እንደሆነ ገልጸውልኛል ። ይህም ለአሁኑ አፈሳውና መዋከቡ አደጋ እንደጣላቸው ተጨናንቀውና ተስፋ ቆርጠው በምሬት ሲናገሩ መስማት በራሱ ያማል …
የሳውዲ መንግስት ለወራት የሰጠውን የምህረት አዋጅ መጠቀም ካልቻሉት መካከል ቀዳሚ የሆንነው ኢትዮጵያውያን እንደ ቀረው ዜጋ ለፍተሻ ውክበቱና እስሩ ተጋላጭ ሆነናል ። በባህር አድርገው በህገ ወጥ መንገድ በየመን በኩል ወደ ሳውዲ የገቡትን ጨምሮ በአብዛኛው በግል የመኖሪያ ፈቃድ ገዝተው በአሰሪዎቻቸው ውጭ በተለያዩ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ተቀጥረው የሚሰሩ ፣ በአሰሪዎቻቸው እጅ አዙር ክፍያ በመክፈል በግል ሱቅ የከፈቱ ፣ በግል መኪና ገዝተው ኮንትራት ተማሪና ሰራተኞችን የሚያመላልሱና ፣ በአሰሪዎቻቸው ስም ጥቃቅን ንግድ ስራን ከፈተው በመስራት ይተዳደሩ የነበሩ በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የምህረት አዋጁ ካለቀበት ቀን ጀምሮ ከሞላ ጎደል ስራቸውን አቁመው የሚሆነውን በስጋት ቋፍ ላይ ሆነው በመከታተል ላይ ናቸው ።
ፍተሻው ተጠናክሮ ከመቀጠሉ አስቀድሞ አብዛኛው ህጋዊ እና ህገወጥ ተብሎ የተፈረጀው ነዋሪ ስጋት ከፍተሻው ጋር ሊፈጠር የሚችለው ማዋከብና ቤት ለቤት ፍተሻ ይደረጋል የሚለው የነበረ ቢሆንም በምህረት አዋጁ ማለቂያ ዋዜማ መንግስት በሰጠው መግለጫ ፍተሻው በኮሚቴ የተሚመራ በመሆኑ ማዋከብ የሌለበት እንደሚሆን በማሳወቅ “የቤት ለቤት ፍተሻ የለም!” የሚል መግለጫ በመሰጠቱ አፎይታን ፈጥሮ ነበር ። ይሁን እንጅ እለተ ሰኞ ምሽትና ማክሰኞ እስኪነጋጋ መንግስት የሰጠው መመሪያ ተጥሶ በሪያድ ነዋሪ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ሰምቻለሁ፣ አረጋግጨማለሁ! በተለይም በሪያድ ውስጥ ጩቤ እየታጠቁ እስከ መጋደል ባደረሰ እርምጃቸው የሃበሻውን ስም ያረከሱት “ባህር ሃይል ” በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩት ህገ ወጥ ዜጎቻችን መናህሪያ የሆኑ የከተማው ክፍሎች ቀደም ሲል በተደረገ ጥናት የመንግስ ኢላማ ሆነው ነበር ። በየመን በኩል በባህር የሚመጡት ኘእኒሁ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት መንፉሃ ደግሞ የመጀመሪያው የመንግስት የብረት ዱላ አረፈባት! “ለሃጣን የመጣ ለጻድቃን !” እንዲሉ ሁለት ኢትዮጵያንን ህይዎት እስከ መቅጠፍ እና በበርካታዎችን ላይ የአካል ጉዳት እስከ ማድረስ የደረሰ የቤት ለቤት ፍተሻ ተካሔዶ በሰላማዊና በህጋዊ የአካባቢው ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ላይ ቤተሰቦች ላይ ግፍ ተፈጸመ… መረጃው በደረሰኝ ቅጽበት ወደ ሪያድ ስልክ በመደወል ያነጋገርኳቸው ኢትዮጵያውያን እያነቡ የገለጹልኝን በትክክል ላመስቀመጥ ይከብደኛል … ብቻ የእኛ ዜጋ ተለይቶ ሲታደን ውሎ አደረ ….
ከጅዳ ከተማ አራት እና አምስት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት በመስክ ስራ ላይ ተሰማርቸ በምገኝበት የሰማዩ የከረረ ጸሃይና ከፊት ለፊቴ የተገጠገጠው በአሸዋ የተዋጠ በርሃ ወበቅ ሳያንገኛታኝ በሚጢጢዋ ከከምፒተሬ የፊስ ቡክ የውስጥ ገጽ እና በተንቀሳቃሽ ስልኬ የሚደርሱኝ በምስል የረደገፉ ሲያንገላቱኝ ዋሉ! እንዳልናገር ሊናገሩት የሚከብድ ፣ ዝም እንዳልለው ዝም የማይባል የወገን ጩኸት ነውና ይህን መረጃ አልሰሜ የሚሰማበትን መንገድ ሳፈላልግ ትናንት ረፋዱ ላይ ጋዜጠኛ ሽዋየ ለገሰ የላከችልኝን ማስታወሻ አስታወስኩና አትኩሮት ሰጥቸ አነበብኩት ” ነቢዩ ስለ ሳውዲ የምህረት አዋጅ ማለቅ መስራት የምትችል ከሆነ ዜና ሰርተህ ላክልን ፣ የማችል ከሆነ ግን ከዚህ እንድንሰራው የአንዳንድ ነዋረሀዎችን የስልክ አድራሻ ላክልን …” ይላል! ለሽዋየ ዜናውን እንደምሰራው ገልጨላት በቀጥታ ወደ ስራው ገባሁ! መረጃየን አሰባስቤ የምህረት አዋጁን ተከትሎ በሪያድ ኢትዮጵያውያነደ ላይ እና በጅዳ ትምህርት ቤት መዘጋትና በአደጋ ላይ መሆነደ ዙሪያ ዜናውን ለእለተ ረቡዕ ምሽት አደረስኩት …
የምሽቱ ዜና ሲተላለፍ እኔ ጅዳ እየገባሁ ነበር ፣ ዜናወ ተላልፎ እንዳለቀ እቤት ብደርስም ከድካም እረፍት የማይሰጡ መልእክቶች ይደርሱኝ ይዘዋል ….በሪያድ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ አምስት ማደጉን ፣ በርካታ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን መንገላታታቸውን ፣ “በመንፉሃ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው ግድያ ጩቤ ይዘው ለማጥቃት በመሞከራቸው ነው!” ፣ “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ !” እንደ ሚባለው በጅዳ ትምህርት ቤት ዙሪያ ለመምከር የጅዳ ቆንስል፣ የኮሚኒቲ እና የወላጅ ኮሚቴ ከፍተኛ ሃላፊዎች ስብሰባ መቀመጣቸውና ሌላም ሌላም መረጃዎች ደርሰውኝ አስተናገድኩ ….
አንድ ብርቱ ወዳጀ ስልክ ደውሎ እየሆነ ስላለው መረጃ ጠይቆኝ በሪያድ እየሆነ ያለውን ከፍቶኝ ከገለጽኩለት በኋላ የሰጠኝ ምክርና የእኔን ምላሽ የዛሬ ማለዳ ወጌ ማሳረጊያ ማድረጉን ፈቅጃለሁ. ..
በጥሞና መረጃውን ሰጥቸው እንዳበቃሁ ወዳጀ መናገር ጀመረ ” ነቢዩ ራስክን ጠብቅ! ለልጆችህ ኑርላቸው !” ሲል የወንድም የወዳጅና የአብሮ አደግነቱን ምክር መከረኝ …በአክብሮት ሰማሁት! አመሰገንኩትም! ግንስ ጥቂት ወረበሎች በፈጠሩት ሁከት ብዙሃን ሰላማዊ ነዋሪ ኑሮው ሲናጋ እየሰማሁና እያየሁ ፣ ወገን ልናገረው በሚከብደኝ አሰቃቂ ሁኔታ ግፍ የተፈጸመባቸው ጭብጥ መረጃዎች ይደርሱኛል! ከነ አሰቃቂው በብለት የተተለተለ የወገን ሬሳን ምስል እና በጥይት የተበሳሳና የተቆራረጠ ሰቅጣጭ መረጃ እየደረሰኝ እንዴት ራሴን መጠበቅ ይቻለኛል? አዎ ለልጆቸ እና እንድኖርላቸው ለሚፈልጉ ወገኖቸ ለመኖር ስል የወገንን የመከራ ጸአር ፣ የታፈነ የድረሱልኝ ጩኸት እየሰማሁ እና እያየሁ ዝም ማለቱ ለእኔ ከባድ ነው! እንዴትስ አድርጌ እንደኔ የሚፈልጋቸው ወላጅ ያላቸው ወገኖቸ እያነቡ እንባቸውን ባልጥርግ ለልጆቸ እና ለጠገብኩት የተንደላቀቀ ኑሮ ስል ዝምታን ልምረጥ ? እንዴትስ የህሊና እዳ ተሸክሜ ለልጆቸና ለሚፈልጉኝ ልኑር? እንዴትስ ይቻላል? አዎ ! ፈጣሪ ሁሉንም ያያል …የማይሳነው አምላክ አጥፍተን ከሚያዘንብብን ሰቆቃ ይታደገን ዘንድ በርትታችሁ ጸልዩ! ለእኔንም የፈራችሁ የሰጋችሁ ፣ አንድየ የታይታውን ሳይሆን የልቤን አይቶ እሱ ጽናት ብርታቱን ይስጠኝ ዘንድ ግን በርትታችሁ ጸልዩልኝ !
በጥሞና መረጃውን ሰጥቸው እንዳበቃሁ ወዳጀ መናገር ጀመረ ” ነቢዩ ራስክን ጠብቅ! ለልጆችህ ኑርላቸው !” ሲል የወንድም የወዳጅና የአብሮ አደግነቱን ምክር መከረኝ …በአክብሮት ሰማሁት! አመሰገንኩትም! ግንስ ጥቂት ወረበሎች በፈጠሩት ሁከት ብዙሃን ሰላማዊ ነዋሪ ኑሮው ሲናጋ እየሰማሁና እያየሁ ፣ ወገን ልናገረው በሚከብደኝ አሰቃቂ ሁኔታ ግፍ የተፈጸመባቸው ጭብጥ መረጃዎች ይደርሱኛል! ከነ አሰቃቂው በብለት የተተለተለ የወገን ሬሳን ምስል እና በጥይት የተበሳሳና የተቆራረጠ ሰቅጣጭ መረጃ እየደረሰኝ እንዴት ራሴን መጠበቅ ይቻለኛል? አዎ ለልጆቸ እና እንድኖርላቸው ለሚፈልጉ ወገኖቸ ለመኖር ስል የወገንን የመከራ ጸአር ፣ የታፈነ የድረሱልኝ ጩኸት እየሰማሁ እና እያየሁ ዝም ማለቱ ለእኔ ከባድ ነው! እንዴትስ አድርጌ እንደኔ የሚፈልጋቸው ወላጅ ያላቸው ወገኖቸ እያነቡ እንባቸውን ባልጥርግ ለልጆቸ እና ለጠገብኩት የተንደላቀቀ ኑሮ ስል ዝምታን ልምረጥ ? እንዴትስ የህሊና እዳ ተሸክሜ ለልጆቸና ለሚፈልጉኝ ልኑር? እንዴትስ ይቻላል? አዎ ! ፈጣሪ ሁሉንም ያያል …የማይሳነው አምላክ አጥፍተን ከሚያዘንብብን ሰቆቃ ይታደገን ዘንድ በርትታችሁ ጸልዩ! ለእኔንም የፈራችሁ የሰጋችሁ ፣ አንድየ የታይታውን ሳይሆን የልቤን አይቶ እሱ ጽናት ብርታቱን ይስጠኝ ዘንድ ግን በርትታችሁ ጸልዩልኝ !
ይቅርታ የምክራችሁ ምንጩ ፍቅርና አክብሮት እንደሆነ ጠልቆ ቢገባኝም ቅሉ “ለልጆችህ ለወገኖችህ ኑር ! ” ብላችሁ ግን አትምከሩኝ ! መስዋዕቱን እኔው ልቀበለው ስለቆረጥኩ እውነቱን በመናገሬ ለሚደርስብኝ ስቃይ መከራ የተዘጋጀሁ ነኝና ስለእኔ አትፍሩ ፣ አትዘኑ ! ልጆቸን ለማሳደግ እና የእለት እንጀራየን ለማግኘት ደፋ ቀና ከማለቱ ጎን ለጎን ባለችኝ ውሱን ጊዜ ህሊናየ ፈቅዶት ማድረግ ያለብኝን እያደረግኩ እስከ ወዲያኛው እዘልቃለሁ! በግል ጨካኝ አውሬ ፣ ሰላቢ ምቀኛ ፣ ሆዳም አድርባይ ፣ ዋሾ አስመሳይ ቀጣፊ ልሆን ብቸልም በአረብ ሃገር ኑሮ ከከተምኩ ጀምሮ በአደባባይ የምሰጣችሁ መረጃ ከተጨበጠ አሁን አሁን በግላጭ እየታየ ከመጣው ሰቆቃ ሰብዕና የማይጎዳውን እየመረጥኩ ከሞላው እየጨለፍኩ ያቃመስኳችሁ መሆኑን ታምኑኝ ዘንድ ልማጸናችሁ ግድ ይለኛል! አዎ ወገን ሲገፋ ፣ ሲበደል መረጃ በማቀበሌ መስዋዕትነት መክፈል ካለብኝ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ! ይህ ቂል ሆኝ አለያም ራሴን ለመኮፈስ ወጥኘ የኝረጨው ከንቱ ፉከራ እንዳይመስላችሁ! እናም ቃሌን ልድገመው እየሆነ ስላለው ነግ በየግል ቤታችን ስለሚገባው መከራ እሰቡ እዘኑ እንጅ ስለእኔ አትዘኑ … ! ደግሞም መፍትሔ ሃሳብ ከመረጃየ ባታገኙ አይድነቃችሁ … መፍትሔ ይፈልጉ ዘንድ ህዝብና ሃገር ለመጠበቅ ቃል ገብተው ሃገር የሚያስተዳድሩትን በርትታችሁ ጎትጉቱ! መፍትሔው የወገንን መብት የሚከበርበትን መላ ይፈልጉ ዘንድ እስኩሰሟችሁ ጩሁባቸው! እኔ እስክጠፋ መረጃ ከማቀበል የሚያሸሽ ህሊና አጥቻለሁ ! እናም ስለእኔ በፍጹም አትዘኑ ! ቢቻል ማለት ካለባችሁ እንደ መለኩሴዋ እናቴ ” ለእውነት ግንባርክን ስጥ ፣ ዋጋህን ከባለእግዚአብሔር ታገኘዋለህ! ” ብላችሁ ጽናትን ተመኙልኝ ፣ ፍርሃትን ፈርቸው በተገላገልኩት መባቻ ፍርሃትን አታስተምሩኝ ! እውነትን አፍኘ ለልጆቸና ለሚወዱኝ የመኖር አባዜው ትርጉሙ እየኖሩ አለመኖር ነውና ግንባሬን ሊደርስ ከሚችልብኝ የጨካኞች ኢላማ የማሸሸት ሞራሉ የለኝም ! ጠባቂየ እውነትን ስበኩ የሚለው አንድ አምላክ እንጅ እኔ አይደለሁም! ልጆቸም የሚጠበቁት በአንድ ፈጣሪ እንጅ በእኔ አይደለም ! እሱ ሁላችንን ይጠብቀን ! በቃ የእኔ ምላሽ ይህ ነው ! ቸር ያሰማን!
አክባሪያችሁ
ነቢዩ ሲራክ
No comments:
Post a Comment