Monday, October 21, 2013

የቆሸሹ ቃላቶች

ከሙሉቀን ተስፋው
ቃል ይገድላል - ትርጓሜ ግን ያድናል፡፡ ቃላትን እንደ እኛ የውስጥ ፍላጎት የምንጠቀምባቸው ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህ ፍላታችን መሰረት ቅዱስ የነበሩ ቃላት የቆሸሹ፣ ክቡር የነበሩት የተናቁ ሆነዋል፡፡ ብዙ ነገሮች ጥንት በነበሩበት ትርጉም የማያስኬዱ ሆነዋል፡፡ 
ለዚህ ሀሳብ መነሻ የሆነኝን የሰሞኑ (የአመቱ) የአገራችን አብይ አጀንዳ የሆነው ‹‹የሀይማት አክራሪነት›› ነው፡፡ ወደ ሀይማኖት አክራሪነት ከመመለሴ በፊት አንዳንድ ‹‹የቆሸሹ›› ቃላትን እንመለከት፡፡ 
‹‹ሙስና›› የሚለውን ቃል 1980ዎቹ በፊት አማርኛ ቋንቋን የለመደ ሰው ‹‹ውበት፣ ደም ግባት፣ ላይህ›› በማለት ሊገነዘበው ይችላል፡፡ አሁን ግን የዚህን ቃል ትርጓሜ በዚህ መልኩ የሚተረጉመው ቀርቶ እንዲህ አይነት ትርጓሜ እንዳለው እንኳ የሚረዳ ሰው በጣም ውስን ነው፡፡
እድርና ሰንበቴ የመሳሰሉ ማህበራት መሪ ይመርጣሉ- ሙሴ ሲሉም ይሰይሙታል፡፡ እናም እንደነዚህ ያሉ ማህበራት ሀላፊ ወይም ሙሴ የመሆን ሂደት ‹‹ሙስና›› ተብሎም ይጠራል፡፡ ምናልባትም ሙስና የሚለውን ቃል መጀመሪያ የተጠቀመበት ሰው ‹‹ሀላፊ ጉቦኛ ነው›› ከሚል ግላዊ አስተሳሰብ የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ደግሞ ሙሴን የመሳሰሉ ታማኝና ቅን አገልጋዮችም ነበሩ፡፡ 

ያም ሆነ ይህ ዛሬ ሙስና የሚለው ቃል በስልጣን መባለግ፣ ጉቦኛ፣ ኪራይ ሰብሳቢነት የተጠናወተው ሰው፣ ስልጣንን መሰረት በማድረግ አላግባብ መጠቀም ወይም መጥቀም የሚለውን ትርጓሜ የያዘ ነው፡፡ ብዙዎቻችንም በዚህ መልኩ እናውቀዋለን፡፡
ሌላው ደግሞ ብሄር የሚለውን ቃል እንመልከት፡፡ ብሄር የሚለው ቃል ከግዕዝ ቋንቋ የተወረሰ ሲሆን ሀገር የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ ደግሞ ብዙ ቋንቋ ይነገራል፡፡ ማለትም የተለያየ አይነት ቋንቋ የሚናገሩ በርካታ ማህበረሰባት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አሁን ላይ ይህ ቃል የተምታታ ትርጓሜ ይዞ እናገኘዋለን፡፡ ብሄር አንዳንዴ ሀገርን ሲወክል ሌላ ጊዜ ደግሞ በሀገር ውስጥ የተለያየ ቋንቋ ተናገሪ ማህበረሰባትን እያንዳንዳቸውን ሲወክል ይታያል፡፡ ስለሆነም ብሄር የሚለው ቃል አሁን የተምታታ ትጓሜ ይዟል፡፡ አንዳንዴ ወደ ሀገር ከፍ ይላል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጎሳና ነገድን እስከ መወከል ይደርሳል፡፡ 
ድሮም ቢሆን ‹‹ዘብሄረ ቡልጋ፣ ዘብሄረ አክሱም፣ ዘብሄረ ዘጌ…›› እያሉ የሚጽፉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ‹‹ዘብሄረ አምሀራ ወይም ዘብሄረ ትግሬ›› እያሉ አልጻፉም፡፡ የነዚህ ሰዎች አጻጻፍ ሀገር የሚሉት የትውልድ ቦታቸውን ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊውን ‹‹ሀገርህ የት ነው›› ብሎ ቢጠይቀው ‹‹ቡልጋ፣ ሸዋ፣ ወሎ፣ ጅማ…›› ብሎ ሊመልስ ይችላል፡፡ ይህ አነጋገር የተለመደና የሚያመለክተውም የትውልድ ቦታና አካባቢን እንጅ ሌላ ሉዓላዊ አገርን አይደለም፡፡ ጠያቂው ሰው ራሱ ኢትዮጵያዊ መሆኑን በደንብ እያወቀ ነው አገርህ የት ነው ብሎ የሚጠይቀው፡፡ አንድ ቋንቋ እየተናገሩና እየተግባቡም ነውና፡፡
አንዳንድ የሀገራችን ፖለቲከኞች ብሄረሰብ እንጅ ብዙ ብሄር በአንድ ሀገር ውስጥ ሊኖር አይችልም የሚል እምነት የሚያራምዱ አሉ፡፡ ለምሳሌ ያክል ዶክተር ብርሀኑ ነጋ ‹‹የነጻነት ጎህ ሲቀድ›› በሚል መጽሀፉ አንድም ቦታ ላይ ብሄር የሚለው ቃል አልተጠቀመም፡፡ ቃሉን ሙሉ በሙሉ ‹‹ዘውግ›› በሚል ተክቶታል፡፡ አንዳርጋቸው ጽጌ ‹‹ነጻነትን የማያውቁ ነጻ አውጪዎች›› በሚል ድርሰቱ እንዲሁ ‹‹ዘውግ›› የሚል ቃል የተጠቀመ ሲሆን ‹‹በእኛ ሀገር ውስጥ ዘውግ እንጅ ብሄር የለም›› በማለት አስረግጦ ይደመድማል፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞች ጎሳ እና ነገድ የሚሉ ቃላት በደንብ ገላጭ ናቸው በማለት ይከራከራሉ፡፡ የእኛንም ሀገር የፌደራሊዝም ስርኣት ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም (Nation Based Federalism) ሳይሆን ጎሳ ተኮር (Ethnic Based Federalism) ነው ይላሉ፡፡ 
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ‹‹የክህደት ቁልቁለት በተባለ መጽሀፋቸው የተከራከሩት ‹‹አማራ›› የሚባል ብሄር የለም ብለው እንጅ ‹‹ብሄር›› በሚለው ቃል ላይ አይደለም፡፡ ስለሆነም ፕሮፌሰሩ ብሄር የሚለውን ቃል በሌሎች ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰባት ላይ መጠቀምን አልኮነኑም፡፡ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን አገላለጽ ሌሎች ብሄሮችና ብሄረሰቦች ግን አሉ ማለት ነው፡፡ ከእርሳቸው አባባል አንድ ግልጽ ያልሆነልኝ ነገር ግን ለሌሎች ቋንቋ ብሄረሰቦች ‹‹ብሄር ወይም ጎሳ›› ካላቸው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪው ‹‹ብሄሩ ወይም ጎሳው›› ምንድን ነው የሚለውን ነው፡፡ እርግጥ ነው ‹‹ለአማራው›› ከአማራነቱ ይልቅ ‹‹ሸዌ፣ ወሎዬ፣ ጎንደሬ፣ ጎጃሜ›› የሚሉት ቃላት የበለጠ ይገልጸዋል ይላሉ፡፡ ነገር ግን በየትኛውም አገላለጽ ሸዋ፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ጎጃም የቦታ እንጅ የጎሳ ስሞች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ 
የፕሮፌሰር ‹‹የአማራ›› ትርጓሜ ማለትም ‹‹አማራነትን ከክርስትና ሀይማኖት ጋር ማያያዙ›› እንዳለ ሆኖ የአማርኛ ቋንቋ ተናሪውን ህብረተሰብ የማንነት ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ግን አልመለሰም፡፡ ለትግርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሲዳምኛ፣…. ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰባት ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማየሚባል ‹‹ብሄር›› ካላቸው ለአማርኛ ተናጋውም ሊኖረው ግድ ነው፡፡ በዚህ በኩል ያሉት ስለሌለ መሞላት ያለበት ክፍተት ይመስለኛል፡፡
ወደ ተነሳሁበት ሀሳብ ስመለስ ብሄር /nation/ ሁለት ነገሮችን ለመግለጽ እየተጠቀምንበት ነው - ሀገርን ወይንም ጎሳን፡፡ አንድ መምህር ‹‹ብሄራዊ መዝሙሩን ዘምሩ›› ብሎ ተማሪዎቹን ቢያዝ በራሱ ገለጭ አይደለም፡፡ ‹‹የኢትዮጵያን ብሄራዊ መዝሙር›› ወይንም ‹‹የአማራን፣ የኦሮሞን፣ብሄራዊ መዝሙር›› ብሎ ማስተካከል አለበት፡፡ 
ከላይ ከመግቢያዬ ላይ ወዳነሳሁት ሀሳብ ስመለስ ደግሞ ‹‹የሀይማኖት አክራሪነት›› አገራችን አጀንዳ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፔንታ ጎን መንትያ ህንጻዎች በአልቃይዳ ከፈራረሱ በኋላ ችግሩ ለምዕራባውያኑ ከአሳሳቢም በላይ ሆኖ እስከ አሁን ቆይቷል፡፡ በተለያዩ የአለማች ክፍሎች በሀይማኖት ስም በተደራጁ ጽንፈኞች ብዙ ንብረት ወድሟል፤ የብዙ ሰው ህይወትም ጠፍቷል፡፡ በክርስትና ሀይማኖት ከተደራጁት ‹‹የጌታ ተዋጊ ሀይሎች›› (The Lord Resistance Army) በእስልምናው ደግሞ አልቃይዳ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በየትኛውም መልኩ ይደራጁ እነዚህ ቡድኖች ለሰው ህይወት መጥፋት፣ ለንብረት መውደም ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ንብረትንና የሰው ህይወትን እየቀጠፉ ‹‹ጽድቅ›› ሰራን ብሎ ማሰብ የጤነኛ አዕም ውጤት አለመሆኑን ለመገንዘብ ፊደል መቁጠርም አስፈላጊ አይደለም፡፡ እንደዚህ አይነት ቡድኖች እስካሉ ድረስ የትኛውም ሀገር መጠኑ ይለያይ እንጅ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠቂ ሊሆን ይችላል፡፡ 2010 የዓለም እግር ኳስን ካምፓላ ሆነው ሲመለከቱ በነበሩ ሰዎች ላይ በአሸባሪዎች በፈነዳ ፈንጅ ኢትዮጵያውን ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የፈነዳው ኡጋንዳ ቢሆንም የጥቂት ኢትዮጵያውያን ህይወት ጠፍቷል፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘመን ችግሩ አንድ ሀገር ብቻ ነው ብሎ መተው የሚገባ አለመሆኑን ማሳያ ይመስለኛል፡፡ 
ምንም እንኳ ይህ ችግር በእኛ ሀገር አለ የለም የሚለው ጥያቄ ሊያከራክር ቢችልም አንዳንድ አይን ያወጡ እውነታዎችን ግን መካድ አይቻልም፡፡ እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ ወንጀል ላለስራቱ አምላኩን ፈሪ ሰውን አክባሪ የሆነው አበሻዊ ጨዋነቱ ከህጉ በላይ ይገድበዋል፡፡ የእኛ ሀገር ሰው ሀይማኖተኛ ነው፡፡ ሀይማኖቱን አጥብቆ በመያዙ ግን ‹‹አክራሪ›› መባል የለበትም፡፡ አከረረ የሚለው የአማርኛ ቃል አቻ ፍች ‹‹አጠበቀ›› ነው፡፡ ሀይማኖቱን አጥብቆ የሚይዝ ሰው ወንጀል አይሰራም፡፡ ለኔ ይህ ሰው ወደ ፍጹምነት ደረጃ የተጠጋ ነው፡፡ ወደ ፍጹምነት ደረጃ የተጠጋ ሰው ደግሞ የሌሎች ደህንነት ያሳበዋል እንጅ በሌሎች ስቃይ አይደሰትም፡፡ ስለሌሎች ደህንነትና ስለ ሀገር ሰላም ይጸልያል፣ ይጾማል፡፡ በተቃራኒው ግን የሌሎችን ሰዎች ደህንነትና የአገርን ሰላም የሚነሳ ሰው በምንም መልኩ ሀይማኖታዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ጽንፈኝነት እንጅ ሀይማኖታዊ አክራሪነት አይደለም፡፡ በክርስትና ሀይማኖት ጳውሎስ ሲመክር ‹‹ቁሙ፣ በሀይማኖት ጽኑ›› ብሎ ነው፡፡ ጥብቅ ሀይማኖተኛ ሰው አክራሪ (Conservative) ሊሆን ይችላል፡፡ ወንጀለኛ ግን ሊሆን አይችልም፡፡ ወንጀለኛ የሚሆነው ጽንፈኝነትን (Extremism) ባህሪው ያደረገ ወገን ነው፡፡ አንድ ሰው ወይም ቡድን ጽንፈኛ ከሆነ ራስ ወዳድነት (Ego Centrism) ባህሪን ይላበሳል፡፡ ራስ ወዳድነት ደግሞ እርሱን (እነርሱን) ባልመሰሉ ወገኖች ላይ ጥላቻን ያበቅላል፡፡ ጥላቻው ወደ ድርጊት ይለወጥና ጥፋትን ያስከትላል፡፡ ጥፋቱ ደግሞ አንድም በንብረት አሊያም በሰው ህይወት ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ቡድኖች (ግለሰቦች) ወንጀለኛ ናቸው፡፡ ‹‹ሀይማኖታዊ አክራሪዎች›› ግን በምን መል ሊሆኑ ይችላሉ!! ልብ አድርጉ ሁለቱም ቃላት በጣም ቅዱስ ናቸው፡፡ ሀይማኖት (እምነት) የፈጣሪን ህልዎት በእምነት መቀበል እንጅ ወንጀለኛ መሆን አይደለም፡፡ አክራሪነትም ጥብቅ አማኝ መሆን እንጅ ወደ ጥፋት መሰማራት አይደለም፡፡
በቅርቡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹የሀይማኖት አክራሪዎች›› የተባሉ ቡድኖች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሲያቃጥሉ በየቀኑ አሳይቶናል (ምንም እንኳ ለእኔ ሰንደቅዓላማችን ያቃጠለው የመጀመሪያው ሰው ‹‹ባንዲራ ጨርቅ ነው›› ብሎ ፓርላማ ላይ የተናገረው ሰው ቢሆንም ቅሉ)፡፡ ስለዚህ ሰንደቅዓላማውን ማንም ያቃጥለው ማን ጥፋትን የሚያመጣ ሁሉ ጽንፈኛ አስተሳሰብ ያለው እንጅ ሀይማታዊ አክራሪ ነው ብዬ አላስብም፡፡
እንደ አጠቃላይ ግን የተቀደሱት ቃላት ሲረክሱ ስመለከት ይህን ጻፍኩት፡፡ ውበት ወደ ጉቦ (ሙስና) ሀገር ወደ ጎሳ (ብሄር) እንዲሁም ጥብቅ አማኝ ወደ አሸባሪነት (ሀይማኖታዊ አክራሪነት) ሲለወጡ የቋንቋና የስነ ልሳን ምሁራን ዝም ማለታቸው ግራ ሲያጋባኝ ጊዜ ይህን ከተብኩ፡፡ ቃላትን ትርጓሜ የመተንተን የቋንቋ ምሁራን ሚና ይመስለኝ ነበር፡፡ እነዚህ ምሁራን አሁን ላይ እየተጫወቱት ያለው ሚና ‹‹የፖለቲካ ካህናት›› የሚናገሩትን በመዝገበ ቃላት ላይ እያሰፈሩ ትርጓሜውን ለወቅቱ ፍጆታ ከማዋል የዘለለ አልሆነም፡፡ ማን ያውቃል ነገም ሌላ ቅዱስ ቃል ሲቆሽሽ እናስታውል ይሆናል!!
ሰላም!!

No comments:

Post a Comment