Friday, October 25, 2013

የጌታነህ ትሬዲንግ ባለቤት ራሳቸውን በሽጉጥ ገድለው እንዲሞቱ የተደረገበት ምስጢር ከ4 ዓመት በኋላ ወጣ

(አራጣ አበዳሪው ከተማ ከበደ እኚህ ናቸው)
(ዘ-ሐበሻ) አንድ ሰሞን በአዲስ አበባ በዋጋ ቅናሽ የሆኑ ልብሶችን በማስመጣትና ትላልቅ ሱቆችን “ጌታነህ ትሬዲንግ” በሚል ከፍተው እየሰሩ ከፍተኛ ታዋቂነትን እና ተወዳጅነትን ካተረፉ በኋላ ወዲያውኑ ራሳቸውን አጠፉ ተብሎ በ2009 ዓ.ም ተነግሮላቸው የነበሩት የዚህ ትልቅ ድርጅት ባለቤት አቶ ዮሐንስ ጌታነህ ከ4 ዓመት በኋላ የአሟሟታቸው ምክንያት ይፋ ሆነ።

“አቶ ዮሐንስ ጌታነህ የጌታነህ ትሬዲንግ ባለቤት ሲሆኑ፣ ምን እንደሆነ ባልታወቀ ምክንያት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ራሳቸውን በሽጉጥ ገድለው ተገኝተዋል።” በሚል በወቅቱ አሟሟታቸው ተሸንፎ የነበሩት እኚሁ ግለሰብ ለሞት ያበቋቸው አሁን በነ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ በሙስና ተከሰው የሚገኙት 10ኛው ተከሳሽ  አቶ ከተማ ከበደ አስገልጥ መሆናቸውን አቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ላይ መረዳት ተችሏል።
አቶ ዮሐንስ ጌታነህ ኢትዮጵያ ውስጥ በከፈቱት ፋብሪካ የተለያዩ ልብሶችን በአነስተኛ ዋጋ እያመረቱ ለገበያ ያቀርቡ የነበረ ሲሆን፣ ለተለያየ ምርት የሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎችንም ያቀርቡ ነበር አቶ ዮሐንስ ሕይወታቸውን ካጠፉ 4 ዓመት ያለፋቸው ቢሆንም መንግስት ለሞታቸው የነበረውን ምክንያት እያወቀ በአቶ ከተማ ከበደ ላይ አሁን ክስ መመስረቱን አንዳንድ ሰዎች በፖለቲካ አለመስማማት የተፈጠረ ነው ይሉታል። እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ታዋቂው አራጣ አበዳሪ አቶ ከተማ ከበደ ከመንግስት ጋር ባይጣሉ ኖሮ እንዲህ ያለ የተደበቀ ምስጢር አይወጣም ነበር ይላሉ።
በአቶ ከተማ ከበደ ላይ የተመሰረተው ክስ የሚከተለው ነው፦
23ኛ ክስ
በ10ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ
ወንጀሉ
በ1996 ዓ.ም የወጣውን የገንዘብና የባንክ አዋጅ ቁጥር 83/1986 አንቀጽ 59(1) (ሸ) ስር የተደነገገውን በመተላለፉ፣
የወንጀሉ ዝርዝር
ተከሳሹ አሜሪካ አገር ከምትኖረው ትእግስት ከተማ ከበደ ከተባለች ልጁ ውክልና በመውሰድ ጌታነህ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ሥራ አስኪያጅ ለሆኑት አቶ ዮሐንስ ጌታነህ ካሳ ጥቅምት 1 ቀን 1998 ዓ.ም በተፃፈ የብድር ውል ስምምነት ብር 40,000,000 (አርባ ሚሊዮን ብር) ብድር በመስጠት ለባንኮችና መሰል የፋይናንስ ተቋማት ብቻ የተፈቀደውን የባንክ ስራ በህገወጥ መንገድ እንደ ንግድ ስራ ሲሰራ በመገኘቱ በፈፀመው ወንጀል ተከሷል።
24ኛ ክስ
በ10ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ
ወንጀሉ
በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 715(ሀ) እና (ሐ) ላይ የተደነገገውን በመተላለፉ፣
የወንጀሉ ዝርዝር
ተከሳሹ አቶ ዮሀንስ ጌታነህ ካሳ የተባሉ የግል ተበዳይን የገንዘብ ችግር መሰረት በማድረግ ከንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አክስዮን ማህበር ጣና ቅርንጫፍ እና ከአቢሲኒያ ባንክ ነጋድራስ ቅርንጫፍ ከ1998 እስከ 2001 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከግል ተበዳይ ድርጅት በተለያዩ ቀናት በተፃፉ የተለያ ቼኮች በልጁ ትእግስት ከተማ ከበደ፣ በእራሱ በተከሳሹ እና ኬኬ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በተባለ በእራሱ ድርጅት በህግ ከተፈቀደው ወለድ በላይ ብር 111,705,397.83 (አንድ መቶ አስራ አንድሚሊዮን ሰባት መቶ አምስት ሺህ ሶስት መቶ ዘጠና ሰባት ብር 83/100 ሳንቲም) አራጣ በማስከፈል በግል ተበዳይ ላይ የሀብት መራቆት እንዲደርስበትና እራሱን እንዲያጠፉ በማድረጉ በከባድ ሁኔታ አራጣ ማበደር ወንጀል ተከሷል።

No comments:

Post a Comment