Tuesday, October 22, 2013

በትግራይ አንድ ቄስ ተገደሉ! ህወሃት ቤተ ክርስቲያንን እያሸበረ ነው

abraha-desta(አብርሃ ደስታ – ከመቐለ)
በትግራይ ክልል ክልተ አውላዕሎ ወረዳ (ጣብያ አይናለም) በቤተክርስትያን ግንባታ ምክንያት በህዝብና አስተዳዳሪዎች መካከል አምባጓሮ ተፈጥሮ አንድ ቄስ ተገደሉ። ቄሱ ህዝብና ቤተክርስትያኑ ወክለው ከመንግስት አካላት ጋር ሲከራከሩ የነበሩ ሲሆን በመንግስት ካድሬዎች የተለያየ ዛቻ ሲደርሳቸው ቆይቶ ማንነቱ ባልታወቀ ሰው በሌሊት ተገድለው ተገኝቷል። ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ተሰምቷል።
መንግስት ቤተክርስትያኑ እንዳይገነባ ያዘዘው ቤተክርስትያኑ ያረፈበት ቦታ አንድ የህወሓት ደጋፊ ባለሃብት ለኢንቨስትመንት ስለመረጠው ነው።

በተያያዘ ዜና በተምቤን ጣንቋ አበርገለ ወረዳ የመንግስት ካድሬዎች በቤተክርስትያን የፖለቲካ ስብሰባ እየጠሩ ምእመናን ስላስቸገሩ አንድ የቤተክርስትያኒቱ ቄስ በቤተክርስትያን የፖለቲካ ስብሰባ እንደማይፈቀድ ለካድሬዎቹ በመናገራቸው ቄሱ ለቀናት ታስረው መለቀቃቸው መረጃ ደርሶኛል።
ችግሩ ምን እንደሆነ ለማወቅ ቄሱ አናግሬያቸው፣ የመንግስት ካድሬዎች ተደጋጋሚ ስብሰባ እየጠሩ ብዙ ሰው ስለማይገኝላቸው ፀሎት ለማድረስ ወደ ቤተክርስትያን የሚሄድ ህዝብ እዛው በፀሎት ቦታ ህዝቡ መሰብሰብ ይሞክራሉ። ብዙውን ግዜ የስብሰባው አጀንዳ ህዝቡ ብድር እንዲወስድና ዕዳው እንዲከፍል ለማግባባት ያለመ በመሆኑ ህዝቡ አጀንዳው አይፈልገውም። እናም በቤተክርስትያን ስለሚሰበስቡት ህዝቡ ወደ ቤተክርስትያን መሄድ አቆመ። ቄሱም በቤተክርስትያን የፖለቲካ ስብሰባ እንደማይፈቀድ አወጁ። ካድሬዎቹም “ፀረ ዉድብና” በሚል ሰበብ አሰሯቸው።
አንድ በመቐለ ከተማ በሚገኝ ሀገረስብከት የሚያገለግሉ ካህን እንደነገሩኝ መንግስት የቤተክርስትያን አገልጋዮችና ሐላፊዎች የገዢው ፓርቲ አባላት እንዲሆኑ ያደርጋሉ። “ዉድብና” እያሉ እንዲናገሩ ይገደዳሉ። (ካህኑ ስማቸው እንዳይጠቀስ አደራ ብለውኛል)።

No comments:

Post a Comment