Wednesday, October 30, 2013

የፖለቲካ ርዕዮተ አለም ህሳቤዎች ከሰበአዊ መብት አስተምሮት አንጻር ሲቃኙ __ (ክፍል አንድ)

በሸንቁጥ አየለ (shenkutayele@yahoo.com)
እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር አስተምሮት ባለ አዕምሮ የሆኑ የሰበአዊ ፍጥረታትን ነብስ ከአጽናፍ አስከ አጽናፍ መሳጭ በሆነ መግነጢሳዊ ሀይል የመሳብ ብሎም በተስፋ ዓለም የማማለል ጉልበትን የተላበሰዉ የሰበአዊ መብት ህግ አስተምሮት የፖለቲካ የርዕዮተ አለም ቀማሪዎችን እና ተግባሪዎችን ወገብ ግን አማራጭ በማሳጣት ሲያንቀጠቅጣቸዉ ይስተዋላል:: የሰበአዊ መብት አስተምህሮት ብሎም ተግባራዊ አፈጻጸም ዋና የጉሮሮ አጥንት ሆኖ የሚገኘዉ ጉዳይ ግን በአንዲት አገር ዉስጥ የዲሞክራሲያዊ መንግስት መኖር ጉዳይ ስለሆነ የአስተምህሮቱ አቀንቃኞች ራስ ምታት ሆኖ ይገኛል::

ጥቂት የሰበአዊ መብት አስተምህሮርት አቀንቃኞችም በአለም ዙሪያ ያሉ ኢዲሞክራሲያን : አንባገነን: ሁዋላቀር: እና የሰዉ ልጅ ፍጡር (ማለትም የሚገዙት ህዝባቸዉ) ከእኛ ስልጣን በታች ነዉ ብለዉ የሚያስቡ መንግስታት ተቆጥተዉ በዚህ የሰበአዊ መብት አስተምህሮት ላይ ፊታቸዉን አንዳያዞሩበት በመስጋት መሆኑ እስኪያሳብቅባቸዉ ሰበአዊ መብትን በአንዲት ሀገር ተግባራዊ ለማድረግ አንዲትን ሀገር የሚመራት መንግስት ዲሞክራሲያዊ መሆኑ ቅድመ ሆኔታ አይደለም እስከማለት ሲሄዱ ይስተዋላል:: ማጣፊያዉ ሲያጥራቸዉ የሚስተዋለዉ ግን ዲሞክራሲያዊነት በሌለበት ስርዓት ዉስጥ ሰበአዊ መብት በምን መልክ ነዉ ተግባራዊ የሚሆነዉ ተብለዉ ሲጠየቁ ነዉ::
ስለሆነም አጠቃላይ እዉነታዉ አንድ ነገር ሆኖ ቁልጭ ብሎ ይወጣል:: ይህም ሰበአዊ መብትን ተግባራዊ ለማድረግ ዲሞክራሲያው መብት ቅድመ ሆኔታ መሆኑ:: ይባስ ብሎም በአሁን ወቅት ዲሞክራሲ ቁንጮ ላይ ደርሰና በማለት የሚቀናጡ ሀገራትን የፖለቲካ ርዕዮተ አለም ሁሉ የሚፈታተን እና የሚገዳደር ሆኖ የወጣዉ የሰበአዊ መብት አስተምህሮት ለሁዋላ ቀሮቹና ለኢዲሞክራሲያን ሀገራትማ ምን ያህል የሚያበሳጭ አስተምህሮት እደሆን መገመት ይቻላል::
በአጠቃላይ አንዳንድ ሀገራት ዉስጠ ያሉና የሰዉን ልጅ ልኡልና ክቡር ፍጡሩነቱን የተቀበሉ ፖለቲከኞች ይሄንኑ የሰበአዊ መብት አስተምህሮት በተግባር ላይ ለማዋል በፖለቲካ ርዕዮታቸዉ ላይ ምርምርና ልዩ ልዩ ማስተካከያ ለማድረግ ሲደክሙ የሚስተዋሉትን ያህል ደፋር አንባገነኖች ደግሞ በግልጽ ከሰበአዊ መብት አስተምሮት ዉስጥ የምንቀበለዉ ይሄን እንጂ ይሄኛዉን ክፍል አይደለም በማለት ለፖለቲካ ርዕዮታቸዉ ቅድሚያ በመስጠት የሰበአዊ መብት አስተምሮትን በሁለተኛ ደረጃ ሲያስቀምጡት ይስተዋላሉ::
አንዳንድ ተንኮለኛና ብልጥ አንባገነን ቡድን የሚመራቸዉ ሀገራት ደግሞ ለማምታቻነት የሰበአዊ መብት አስተምሮትን እንዳለ በህገመንግስታቸዉ ዉስጥ ከተቀበሉ ብሁዋላ ወደ መሬት ሲያወርዱት ግን ተቃራኒዉን ኢሰበአዊ የሆነ መርህ የተከተል አካሄድ ሲያራምዱ ይስተዋላል:: ለምን ህገ መንግስቱን ትጥሳላችሁ ሲባሉም የአፈጻጸም ችግር ነዉ ወይም ደግሞ ይህ የሰበአዊ መብት አስተምሮት ከሚለዉ የወጣ ነዉ ወይም ይህ የእኛ መንስት የዉስጥ ኡዳይ ነዉ በማለት ብልጣብልጥ ብሎም ሁዋላቀር ማምለጫዎችን ለመደርደር ሲወላገዱ ይስተዋላሉ::
ሆኖም ዘር ቀለም እና ሀይማኖት ሳይለይ በመላዉ አለም ያሉ ባለ አዕምሮ የሆኑ የሰበአዊ ፍጥረታትን ነብስ ከአጽናፍ አስከ አጽናፍ መሳጭ በሆነ መግነጢሳዊ ሀይል እየሳበ ጽንሰ ሀሳባዊነቱን ብቻ ሳይሆን ተግባራዊነቱን ለማዬት የሚዋትቱ በርካታ አቀንቃኞችን ያፈራዉ የሰበአዊ መብት አስተምህሮት በአንድ ወቅት በአንባ ገነንነት የሚመሩትን ህዝብ ሀይማኖት ዘርና ጎሳ እየለዩ ህዝብ ሲያሳርዱና ሲያስጨፈጭፉ የነበሩ ምናምንቴ አዕምሮቢስ አንባገነን ሀይሎችን እንኩዋን ከፖለቲካ ጨዋታ በእነሱው መሰል ጡንቸኞች ሲባረሩ (ቀን ሲከዳቸዉ) የሚዘምሩለት ጉዳይ እንዲሆን አስገድዶአቸዋል:: ለማጣቀሻነት ሩቅ ሳንሄድ በእኛ ሀገር ቀድሞ ገዥ ዛሬ ደግሞ ተቃዋሚ የሆኑ ፖለቲከኞችን ማስተዋሉ በቂ ነዉ::
በጥቅሉም ይህ የሰበአዊ መብት አስተምህሮት አለም በዘመንች ቁጥር እድገቱ በፍጥነት እየጠለቀና እየሰፋ የመጣ ሀያል የአስተምህሮት ዘርፍ እየሆነ ሲወጣ ይስተዋል:: ለምሆኑ የሰበአዊ መብት አስተምሮት ምንድን ነዉ? በመላው አለም ያሉ የፖለቲካዉ ርዕዮተ አለም ህሳቤዎችንስ እንዴት ነዉ እየተፈታተነ ያለዉ? የሚሉትን ጉዳዮች በዚህ ዛሬ ባነሳሁት ርዕስ ስር (በክፍል አንድና በክፍል ሁለት) በደምሳሳዉ እንዳስሣቸዋለን::
ሰፊ አለማቀፋዊ ተቀባይነትን ያገኘዉ ሰበአዊ መብት በተለይም ከ1948 ዓም ጀምሮ በተባበሩት መንግስታ የራሱ ዘርፍ ተቁዋቁሞለት በስፋትና በጥልቀት እየተሰበከ ያለዉ የሰበአዊ መብት አስተምህሮት እንደሚያስተነትነዉ ሰበአዊ መብት የማይገሰስ መብት ነው:: ማንም ሰዉ በዘሩ : በብሄሩ: በዜግነቱ : በሀይማኖቱ እንዲሁም : የአንድ ቡድን ወይም ማህበረሰብ አባል በመሆኑ የሚያገኘዉ መብት ሳይሆን ሰዉ በሰበአዊነቱ ብቻ በእኩልነትና በማይገሰስ መልክ የሚጎናጸፈዉ መብት ነዉ:: ሁሉም ሰዉ ሰበአዊ መብቱን ያለመድሎና መገለል ሊጠቀምበትም ይገባል::
በመሆኑም የሰበአዊ መብት ዋና ዋና መለያ ባህሪያት ተብለዉ የሚዘረዘሩት ማንም ለማንም የሚሰጠዉ ወይም የሚነፍገዉ መብት ሳይሆን ሰዉ በሰበአዊነቱ ብቻ የሚጎናጸፈዉ መብት መሆኑ % ለሰዉ ልጆች ሁሉ እኩል የሚተገበር መብት መሆኑ % መብቱን የማስጠበቅ ግዴታ የሚተሳሰረዉ በአንዲት አገር ዉስጥ የሀገሪቱን ስልጣን ከጨበጠዉ ሀይል እንጅ ከግለሰቦች ጋር አለመሆኑ % ሰበአዊ መብት መጠበቅና ጥላ ከለላ ማግኘት ያለበት በህግ ማዕቀፍ መሆኑ% አንዲሁም ብቃት ያለዉ : ገለልተኛ : ነጻ ፍርድቤት ቀድሞ ህልዉ በሆነ ዝርዝር ግልጽ ህግ ብልም ህገ ስነስርት ላይ ተንተርሶ በእኩልነትና በፍትሃዊነት ለሁሉም ወገን ብይን መሰጠቱ ዋና ዋና መገለጫዎቹ ናቸዉ::
መሰረታዊዉ የሰበአዊ መብት ምንጩ የግለሰብ መብት በመንግስት እንዳይነጠቅ መጠበቅ ከሚል ህሳቤ ይመነጭ እና መንግስት መሰረታዊ የሚባሉትን የሰበአዊ ጥሰት ከመፈጸም መታቀብ አለበት በማለት ያስተነትናል:: በቀዳሚነትም ሰበአዊ መብት ክብር ያለዉ ሰበአዊ ህይወትን ለመምራት የመሰረት ድንጋይ ከመሆኑም በላይ ለሰዉ ልጆች ብልጽግና ቅድመ ሁኔታ ስለሆነ የህግ ሁሉ መሰረተና ቅድመ ሁኔታ ነዉ:: ይህም ማለት የማህበረሰብ : የመንግስት : የቡድኖች እንዲሁም የግለሰቦች የጋራ ግንኙነት መሰረት የሚቆመዉ በሰበአዊ መብት የህግ ህሳቤዎች ላይ ተነተርሶ ነዉ:: የማህበረሰብ : የመንግስት : የቡድኖች እንዲሁም የግለሰቦች የጋራ ግንኙነት መሰረት የሚቆመዉ በሰበአዊ መብት የህግ ህሳቤዎች ላይ ተነተርሶ መሆኑም የሚነግረን አንድ ነገር ቢኖር ሰበአዊ መብት በአንዲት ሀገር ዉስጥ ምን ያህል የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መሰረት ብሎም ምሰሶና ዋልታ መሆኑን ነዉ::
በሰበአዊ መብት ዙሪያ የተለያዩ ህሳቤዎች እና አመዳደቦች ያሉ ቢሆንም ሁሉም ሰበአዊ መብቶች አለም አቀፋዊ እና የተቆራኙ ብሎም ሁልም መብቶች እኩል ስለመሆናቸቸዉ የጋራ ስምምነት አለ:: ሁሉም መብቶች እኩል መሆናቸዉ እንዳለ ሆኖ ለዚህ ጽሁፍ ማስተንተኛ ይሆን ዘንድ ሰበአዊ መብትን በሶስት ዘርፍ ከፍለን ልንመለከተዉ እንችላለን:: ይሄዉም አንደኛ : ሁለተኛ እና ሶስተኛ ትዉልድ መብቶች ( First, second and third generation rights ) በማለት ::
የመጀመሪያ ትዉልድ መብት ማለትም የፖለቲካና የሲቪል መብት ሲሆን የሚያጠቃልላቸዉ መብቶችም በህይወት የመኖር መብት : የነጻነት መብት: የደህንነት መብት:ከግዳጅ አገልጋይነት እና ከባርነት ነጻ የመሆን መብት: ከኢሰብባዊ ቅጣትና ከቶርቸር ነጻ የመሆን መብት:በህግ ፊት እንደ ሰዉ እዉቅና የማግኘት መብት: በዘፈቀደ ያለመያዝ መብት: ከሀገር ያለመባረር መብት:በህግ ፊት እኩል ከለላ የማግኘት መብት : መፍትሄ የማግኘት መብት:የግል ህይወት ደህንነት መብት: የመንቀሳቀስና በሚፈልጉት ቦታ የመኖር መብት: የዜግነት መብት: የማሰብ ነጻነት መብት: የህሊናና የሀይማኖት መብት: የነጻነት መብት: ሀሳብን በጻነት የመግለጽ መብት: የመሰባሰብ መብትና የማህበር መብት:የንብረት መብት:በመንግስት ስርዓቱ ዉስጥ የመሳተፍ መብት ናቸው::
ሁለተኛ ትዉልድ መብቶች የኢኮኖሚ : የማህበራዊና የባህላዊ ምብቶች የሚባሉትን ያጠቃልላል:: የኢኮኖሚ መብት የሚባሉት የንብረት መብት: የመበልጸግ መብት:ስራን የመምረጥና የመስራት መብት: ፍትሃዊ ምንዳ የማግኘት መብት:ፍትሃዊ የስራ ሰአት የማግኘት መብት: የሰራተኛ ማህበራት መብት ናቸዉ:: የማህበራዊ መብት የሚባሉት ደረጃዉን የጠበቀ ኑሮ ለመኖር በቂና አስፈላጊ ነገሮች መኖር ማለትም የመጠላያ: የጤና: የምግብ: የማህበራዊ ደህንነት: የትምህርት መብት ሲሆኑ ባህላዊ መብቶች የሚባሉትም በማህበረሰቡ ባህል ዉስጥ የመሳተፍ:የሳይንሳዊ : የሞራላዊ:የቁሳዊ ፍላጎቶች የማሙዋላት መብት: በስነጽሁፍና ስነጥበብ የመሳተፍ መብቶችን ያካትታል:: ሶስተኛ ትዉልድ መብት ወይም ህብረተሰበአዊ መብት የሚባሉት ደግሞ የቡድን እና የጣምራ መብቶች :የልማት መብት : የሰላም መብት እንዲሁም በንጹህ አካባቢ የመኖር መበቶች ናቸዉ::
ከላይ የተዘረዘሩት የሰበአዊ መብቶች መንግስታትን እየተፈታተኑ እና አሉ የተባሉ የፖለቲካ ርዕዮተ አለሞችን ሁሉ ወገባቸዉን እያንቀጠቀጡ ይገኛሉ:: የዚህም ዋና ምክንያቱ እነዚህን ሁሉ አማላይ መብቶች ሁሉም ዜጎች ሊጎናጸፉዋቸዉ የሚገቡት ወይም ደግሞ መብቶቹ ሊጠበቁት የሚገባዉ የሀገሪቱን ስልጣን በጨበጠዉ አካል በኩል መሆኑ ነዉ:: በክፍል ሁለት ይሄንኑ ጉዳይ በዝርዝር እንሄድበታለን:: ለዛሬ ግን የሰበአዊ መብት ዘርፍ (የህብረተሰበአዊ መብት) የሆነዉ የልማት መብት እንዴት ለአንባገነን እና አጭበርባሪ መንግስታ ብሎም ለሚከተሉት የፖለቲካ ርዕዮተ አለማቸዉ ራስ ምታት እንደሚሆን በአጭሩ እንይ::
ይህ የልማት መብት ዘርፈ ብዙ : ይዘቱ ጥልቅና ስፋቱም ከአድማስ እስከ አድማስ የተንሰራፋ ነዉ:: የልማት መብት ፖለቲካዊ : ኢኮኖሚያዊ: ማህበራዊ: ህጋዊ: ተቁዋማዊ : ባህላዊ : ታሪካዊ : አካባቢያዊ ሌላዉ ቀርቶ የነገዉ ትዉልድን ጉዳይ ሁሉ አካቶ የሚጉዋዝ ጽንሰ ሀሳብ በመሆኑ አንዲት ሀገር ዉስጥ ያለ መንግስት የማህበረሰቡን የልማት መብት አስከብሪያለሁ/መልሻለሁ/ ሲል እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች ባቀፈ መልክ መሆን አለበት:: በተለይም አንባገነን መንግስታትና ልማታዊ መንግስት ነን የሚሉ መንግስታት ሁሉ ከሰበአዊ መብት አስተምህሮቶች የሚጠሉት መብት ቢኖር የልማት መብት የሚለዉን ቃል ነዉ::
ይህም የሆነበት ዋና ምክንያት እኛ አለማንህ : እኛ የልማት ምንጭ ሆንልህ : ያለኛ ልማት ሊኖር አይችልም እያሉ ማህበረሰቡን የሚያምታቱበት ጭንብላቸዉ ተገፎ መሳለቂያ የሚሆኑት ማህበረሰቡ ልማት ሰበአዊ መብቱ መሆኑን የተረዳ ዕለት ስለሚሆኑ ነዉ:: ሰበአዊ መብት ደግሞ መንግስት በግዱ ለማህበረሰቡ ሊፈጽመዉ : ሊያስፈጽመዉ : ሊያሙዋላዉ ብሎም ሊኖርለት የሚገባዉ ጉዳይ እንጂ አንዲት መንገድ አሰራሁ ወይም አንዲት ትምህርት ቤት አስከፈትሁ ብሎ ማህበረሰቡ ጉሮ ወሸባዬ ይባልልኝ ወይም ዘላለም እኔ ብቻ ልግዛ እያለ መፎከሪያ ሊያደረዉ የሚገባ ጉዳይ አለመሆኑ አለም አቀፋዊ ሀቅ ሆኖና ጎልቶ የወጣ ጉዳይ ነዉ::
ሁዋላቀረን : አንባገነን ብሎም አምታች መንግስታት ልማት የማህብረሰቡ ሰበአዊ መብት መሆኑን ከመናገርና ከማስረዳት ይልቅ እነሱ የሰጡት የበጎ ፈቃዳቸዉ ስጦታ ይመስል አጥብቀዉ ያምታታሉ:: እንዲያዉም ማህበረሰቡን ማልማት ግዴታቸዉ ሳይሆን ጥቂት ነገር አለማን ብለዉ በመናገራቸዉ ብቻ ማህበረሰቡ እንዲያጨበጭብላቸዉ ይወተዉታሉ::
ሚሊዮን ዜጎች በጎዳና ላይ ወድቀዉና በድህነት ታንቀዉ: ሚሊዮኖችን ሀብት ካፈሩበት ካፈናቀሉ ብሁዋላ ወደ ልመና በመግፋት የልማት መብታቸዉን: የኢኮኖሚ መብታቸዉን : የማህበራዊ መብታቸዉን: የፖለቲካና የሲቪል መብታቸዉን ብሎም ሁሉንም መብታቸዉን ከነጠቁ ብሁዋላ እዚህና እዚያ የተከሉዋትን ተብለጭላጭ ነገር እንደ ትልቅ ልማት እየቆጠሩ ማህበረሰቡ እንዲያጨበጭብላቸዉ አእምሮቢስ በሆኑ ካድሬዎቻቸዉ አጥብቀዉ ይሰብካሉ::
ሆኖም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር አስተምሮት ባለ አዕምሮ የሆኑ የሰበአዊ ፍጥረታትን ነብስ ከአጽናፍ አስከ አጽናፍ መሳጭ በሆነ መግነጢሳዊ ሀይል የመሳብ ብሎም በተስፋ ዓለም የማማለል ጉልበትን የተላበሰዉ የሰበአዊ መብት ህግ አስተምሮት እንዲህ አምታች የሆኑ አምባገነኖችን ብሎም በመላዉ አለም ያሉ የፖለቲካ የርዕዮተ አለም ቀመር ቀማሪዎችን እና ተግባሪዎችን ወገብ አማራጭ በማሳጣት ሲያንቀጠቅጥ ይስተዋላል::
ይሄ የሰበአዊ መብት አስተምህሮት ለምሆኑ በአለም ላይ ያሉ የፖለቲካ ርዕት አለም የሚባሉ ህሳቤዎችን በምን መልክ ነዉ ወገባቸዉን እያንቀጠቀጠዉ ያለዉ? በክፍል ሁለት በስፋት እንመለስበታለን::

No comments:

Post a Comment