Monday, October 28, 2013

ይድረስ ለአቶ መስፍን አብርሃ

/ማኅሌት ሰለሞን ከጀርመን/
«መርዓዊና መንታ መንገዳቸው» በሚል ርዕስ የጻፉትን ተመለከትኩት። ገና ከጅምሩ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ የኮሎኝ ቅ.ሚካኤል ቤ.ክ ብቻ አስተዳዳሪ መሆናቸውን፥ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ.ክ ኃላፊነታችው ግን እንደተሻረ ነግረውን ማን እንደ ተሾመ ግን አልነገሩንም። ሊነግሩንም አይችሉም። የተሻረም ሆነ የተሾመ የለምና ።
ነሐሴ ፳፬ እና ፳፭ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በግብጾች ገዳም በተካሄደው ስብሰባ ላይ አቡነ ሙሴ በጀርመን መንበረ ጵጵስና አቋቁሜያአለሁ ያሉትን ይዘው ከሆነ በጀርመን ሕግ መሠረት የተቋቋመ ሀገረ ስብከት እያለ፧ መፍረስም ካለበት በሕጉ መሠረት ይፈርሳል እንጂ በቃል ሊፈርስ እንደማይችል፧ አባታችን ለሀገሩ/ለሕጉ/ እንግዳ፧ ለሰው ባዳ በመሆናቸው ባይረዱት/ምንም እንኳን የሀገር ቤቱን ሲኖዶስ አውግዘው በእንግሊዝ ሀገር የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ ያቀረቡ፧ ቆየት ብለው ደግሞ ያንኑ ሲኖዶስ ይቅርታ የጠየቁ አዲስ ሹመኛ መሆናቸው ቢታወቅም / እርሰዎ ግን ካፍ ነጥቀው ከሚያራግቡ ቀረብ ብለው ሊያስረዷቸው ይገባ ነበር ።

ቀጥለው የተቹት የ፴ኛ ዓመት ዝክረ ነገርን ነው በመጽሔቱ ላይ ምስጋና በዝቷል ፥ ስለ አሉ
ችግሮች አላነሳም ብለዋል ፴ ዘመን ሌት ተቀን ለደከሙት ቤተ ክርስቲያናችንን በጀርመንና በአውሮፓ እንድትስፋፋ ያለመታከት ለሠሩት ለሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀና ቤተሰባቸው የቀረበው ምስጋና ተገቢ ነው ከምስጋናስ ያነሰ ምን መደረግ ነበረበት ?
ችግርን በተመለከትም ሁሉንም ማቅረብ ባይቻልም ዋና ዋና የቤተ ክርስቲያናችን ችግሮች ተጠቃቅሰዋል በይቅርታም የተፈቱ ችግሮች እንዳሉ ፥ ቤተክርስቲያን ለማቋቋም በሚጥሩበት ወቅትም ከጀርመን መንግሥት ትብብር እንዳያገኙ የሃይማኖት ሰዎች ጭምር እንዳስቸገሩ፥ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ቤ.ክ ችግር ማለትም አቡነ ጳውሎስ አርፈው በነበረበት ወቅት ሌላ ፓትርያርክ ለመተካት ከመሯሯጥ ይልቅ የእርቁ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ፍጻሜው ከመታወቁ በፊት የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች እንዲገቱ ተሟግተዋል ሀሳብም አቅርበዋል ስለ ነገዋ ቤተ ክርስቲያን ስንል ዕድሉ ዛሬ ባያመልጠንስ ? እና ሐውልትና ቤተ ክርስቲያን /አቡነ ጳውሎስ በቁም ያቆሙትን ሐውልት አስመልክቶ/ የሚለውን ከዛው ከመጽሔቱ ላይ ይመልከቱ ። በገጽ ፲፩ ላይ ደግሞ ቋሚ ቤተ ክርስቲያን በመቋቋሙ የተከሰተ ችግር በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር ችግሮች ቀርበዋል ወይስ እነዚህን እንደችግር አልቆጠሯቸውም ? በውጭ ስላለን ሀገር ቤት ያለው የቤተ ክርስቲያንና የሃይማኖታችን ችግሮች አያገባንም ብለን እጃችንን አጣጥፍን እንቀመጥ ?... ደግሞ የሰላሳ ዓመቱን ጉዞ ለመተቸት ከመጣደፍ አስቀድሞ የ፴ኛ ዓመት ዝክረ ነገርን ብቻ ሳይሆን ቢያንስ የ፳፭ኛ እና የ፳ኛ ዓመት ዝክረ ነገሮችን ጨምሮ መመልከት ይገባ ነበር ። ችግርናቸው አልተካተተም ያሉት ሁሉ ቁልጭ ብሎ ቀርቦለዎታል።
ቀጥለው የነገሩን፧ ሁሉም አድባራት በሙስና የተዘፈቁ እንደሆነ ነው። እርስዎን የመሰለ ሙስናን ታጋይ ባለበት ደብር/ቤ.ክ/ ሳይቀር መሆኑ ነው ለነገሩ ከየትኛው ደብር እንደሆኑ አልነገሩንም ? የሚገርመው ግን ሁሉንም ሙስና ጠቅልለው ለሊቀ ካህንት አሸክመው ማለፍዎ ነው። ሙስናን ኮለን ሁንው ደቡብ/ ሰሜን ምስራቅ/ ምዕራብ ጀርመን ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን ፥ የሰንበት ት.ቤቶችንና የጽዋ ማኅበራትን እንዲቆጣጠሩልን ከፈለግን ስህተት አለያም የራስን ሸክም መሸከም ያለመቻል ደካማነት ነው። ሁላችንም በየአጥቢያችን መጠበቅና መቆጣጠር አለብን ። ለጊዜው ሙስና ያሉትን በዝርዝር ሲያቀርቡልን እመለስበት አለሁ። ለአሁኑ ግን የካርልስሩኸ የጽዋ ማህበር ወደ አጥቢያ ቤተክርስቲያንነት ከፍ እንዳለ ይታወቃል ነገርግን መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ በጀርመን ላለው መንፈሳዊ አግልግሎት ኃላፊ የሆነው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ካህናት ሳያውቅ ታቦትን ያህል የዕምነታችን መገለጫ
ከማይመለከታቸው ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር እንደ መቋሚያና ጸናጽል ፥ እንደ ከበሮና ጥላ… አምጥቶ ለ አቶ…. መስጠት ምን ያህል ሕገ ቤተክርስቲያንን መዳፈር እንደሆነ አልተረዱትም ?.... ወይስ እንደ ስህተትና ችግር አላዩትም ? ስህተቱንስ የፈጸሙት ደግሞ አንቱ የተባሉ አባት/አቡነ ሙሴ/ መሆናቸው አያሳስብም ? ለቤተ ክርስቲያን አሳቢና ተቆርቋሪ ከሆኑ የኸን ዓይን ያወጣ ችግር ጠቆም አርጎ አንኳን ለማለፍ አልሞከሩም የስንቱን ቤ.ክ ጉዳይ ሲፈተፍቱ ።
በኑረንበርግና በበርሊን ቤተ ክርስቲያን ለመስራት ወይ ለመግዛት ጥረት እንደሚደረግ በሙኒክና በፍራንክፈርት ደግሞ የገንዘብ ብክነትን በተመለከተ ጉዳዩ በሕግ ፊት ቀርቦ በሙኒኩ ካህን ላይ ሲፈረድባቸው የፍራንክፈርቱ ደግሞ ክሱ ውድቅ ሁኗል። በሕግ ያለቀን ጉዳይ እንደ አዲስ በየድረገጹ እየለጠፉ አንባቢን ከማሰልቸት፥ ወገንን ከማደናገር አለኝ የሚሉትን ማስረጃ ይዞ ይግባኝ ማለት ይሻላል።
በእሽቱትጋርት ከበላይ በነበረ ጫናና ግፊት ምክንያት ያለችሎታ ለቅድስት ልደታ ለማርያም ቤ.ክ የተመደበው ካህን ባለው ገንዘብ ላይ ለመጨመር ቀርቶ የነበረውንም ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ስለተጠቀሙበት አልቋል። ለምሳሌ የቤት ኪራይ የውኃና የመብራት ሳይኖሩበት ለብዙ ወር እየተከፈለ ማለት ነው። ቀጥሎም ምእመኑን ለሁለተኛ ጊዜ ከፋፍለው ስለበታተኑት ገንዘብ ጠፋ ተገኝቶ የነበረውንም የተሟላ ቤ.ክ ማስተዳደር ስለአልተቻለ ባለቤቷ የካቶሊክ ቤ.ክ መልሳ ወሰደችው ታላቁ ዕድልም እንደዋዛ አመለጠን ።
የቪዝባደኑን ካህን በተመለከተ በይቅርታና በንስሐ ከተመለሱ በኋላ የቀደመ ውሎአቸውንና ሥራቸውን እያነሱ መመናቸክ አያስፈልግም። እሱንማ እራሳቸውም ጠልተውት ጥለውት መጥተዋል ከእኛ የሚጠበቀው እጃችንን ዘርግተን እንኳን ደህና መጡ ብለን መቀበልና የጎደለውን መሙላት የጠመመውን ማቃናት እንጂ መናፍቅ ጴንጤ … እያልን በስድብ ካጣደፍናቸውማ ከቤ.ክይርቃሉ ከምእመናንም ይሸሻሉ ለመመለስ የሚፈልጉ ሌሎች ካሉም በዛው ጠፍተው ይቀራሉ። እርሰዎና መሰሎቼዎ የስድብ ናዳ እያወረዳችሁ ቤተ ክርስቲያንን የወላድ መካን እያደጋችኋት መሆኑን የተረዳችሁት አይመስልም። ለመረዳት ከፈለጉ ቅዱስ ፓትርያርኩ በጋዜጣዊ መግለጫቸው የተናገሩትን ልብ ብለው ይመልከቱ። እኝህ ካህን ወደ ሌላ ሂደው ቢሆን ኖሮ የሚደረግላቸው አቀባበል እንዴት ይሆን ነበር ? ብለንም መጠየቅ ይኖርብናል ።
ሚያዝያ 29 ቀን 2007 ዓ.ም ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የተፈረመው የማግደቡርግ የትብበር ሰነድ
1 . እንደገባኝ ከሆነ አንድ ግለሰብ ሃይማኖቱን ቢቀይር ደግሞ መጠመቅ ሳያስፈልገው በመጀመሪያ የተጠመቃት ጥምቀት ተከብራና ተቆጥራ የአዲሱ ሃይማኖት/ቤ.ክ/ ሙሉ አባል ይሆናል ። በአንዲት ጥምቀት እናምናለን /ጸሎተ ሃይማኖት/ የሚለውም ትርጉም ይኖረዋል ።
2. ስምምነት ባደርጉት አብያተክርስቲያናት በአንዱ የተሰጠን የጥምቀት፥የጋብቻ የምስክር ወረቀት ሁሉም አብያተክርስቲያናት ሕጋዊ አድርገው ይቀበሉታል ። የሚል ሥራን ለማቀላጠፍና የአብያተክርስቲያኑን ተቻችሎ የመኖር በእኩልነትና በመግባባት ላይ የተመሰረተ ወንድማማችነትም እንዲሰፍን የሚያግዝ የትብብር ሰነድ አንጂ የሃይማኖት አንድነት ስምምነት ውል አይደለም ።
ሌላው በጽሑፈዎ ላይ ጎልቶ የሚታይ ስህተት በትምህርትና በአገልግሎት ደክመው ያገኙት መጠርያ/ ሊቀ ካህናት ወይም ዶክተር የሚለው/ እያላቸው አንተ እያልክ አንጠልጥለህና ነጥልህ መጥራትህ ነው ይኸውም የእርሰዎን ተራነት እንጂ የሳቸውን ትንሽነት አያሳይም እሳቸውማ ።
የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ የሃይማኖቱም ተቆርቋሪ የዕድሜ ባለጸጋ ከመሆናቸው ጋር አንቱ የሚያሰኙ ሥራዎችን የሠሩ በመሆኑ ሁል ጊዜ እናከብራቸው አለን ። አንዳንዶቹን ልጥቀስለዎ ፧… በቅርቡ
የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ዮሐኪም ጋውክ ኢትዮጵያን ጎብኝተው ነበር በጉብኝታቸው ወቅት በደርግ የተገደሉትን የወንጌላውያን ቤ.ክ ኃላፊ የቄስ ጉዲና ቱምሳን የመቃብር ሥፍራ በመጎብኝት ጸሎት ሲያደርጉ፧ የአበባ ጉንጉን ሲያስቀምጡ በተመሳሳይ ሁኔታና ወቅት የተገደሉትን የኢትዮጵያ ኦ.ተ.ቤ.ክ ፓትርያርክ የብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስን የመቃብር ሥፍራ ግን ሳያዩ ይመለሳሉ። ሁኔታው ያሳዘናቸው ሊቀ ካህናት የቅሬታ ደብዳቤ ለፕሬዝዳንቱ ጽፈው ይልካሉ ፕሬዝዳንቱም በመልሱ የይቅርታ ደብዳቤ ጽፈውላቸዋል። ይህን ግን የማድረግ እንደምታውቀው ቀጥተኛ ኃላፊነት የነበረባቸው በሀገር ውስጥና በአውሮፓ ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት ወይም የፓትርያርኩ ጽ.ቤት ወይም የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አለበለዚያም በጀርመን የኢትዮጵያ ኢምባሲ ነበር… ።
ሌላው ደግሞ የውጭ ኃይሎች እንኳን ያልደፈሩትን የዋልድባ ቅዱስ ገዳም መንግሥት ሲያፍርስ መናኝ አባቶችን ሲያስርና ሲደበድብ፧ ንብረቱን ሲዘርፍ አባቶችም የድረሱልን ጥሪ ሲቀርቡ በጀርመን ያሉ ካህናትን፥ ምእመናንንና የገዳሙን ጥፋት የሚቃወሙ ዜጎችን፥ ጀርመናውያንንም ጭምር በማስተባበር ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ የዋልድባን አባቶች መከራና ግፍ የዓለም ኅብርተሰብ እንዲያውቀው አድርገዋል።
የኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች ጉዞ በማስተባበርም ተጕዋዡ ቅድስት ሀገርን እንዲያውቅና እንዲባረክ እግረመንገዱንም በጭቅጭቅና በችግር ላይ የሚገኘው/ የኢትዮጵያ ይዞታ የሆነው/ ዴርሡልጣን ገዳምና አባቶችንም እንዲረዳ እያደረጉ ነው ። ታዲይ እኝህን አባት በአክብሮት መጥራት እርሰዎንም ቢሆን ያስከብረዎታል መከባበር ደግሞ መልካም ባህላችን ነው ለወደፊቱ እርሰዎም አክብረው እንደሚከበሩ ተስፋ አደርጋለሁ።
በመጨረሻም መንታ መንገድ ያሉት ለሊቀ ካህናት አይሠራም አስተዳደራዊውንና መንፈሳዊውን አገልግሎት በተመለከተ ግንኙነታቸው ከሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ጋር ተባብሮ የመሠራት በመሆኑ። ምናልባት መንታ መንገድ ያሉት አንዳንዴ የሀገር ቤቱን ሲኖዶስ ሲተቹ የውጩን ደግሞ ጥሩ ሲሉ ሰምተው ከሆነ ሊቀ ካህናት በጨፍን አይደግፉም በጭፍንም አይቃወሙም በምክንያት እንጂ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ከጣሰ ሃይማኖት ካፋለሰ የውጭ በለው የውስጥ ሲኖዶስ ተገቢውን መልስ ያገኛል። በድጋፍም ይሁን በተቃውሞ መልክ ። እኛም ከሳቸው የተማርነው ይህንን ነው። የጅምላ ድጋፍና ተቃውሞውንማ ለእናንተ ትተነዋል።
አቶ መስፍን እኔም እነደ አንድ ምእመን ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀን የማውቀውን፧ ቤተ ክርስቲያንን የምቀርበውን ያህል እርሰዎ «መርዓዊና መንታ መንገዳቸው» በማለት ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ የምሰጠውን የግል አስተያዬቴን እዚህ ላይ እቋጫለሁ ።
እግዚአብሔር ሀገራችንንና ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅ አሜን !
ጥቅምት ፳፻፮ ዓ.ም ጀርመን

No comments:

Post a Comment