Tuesday, December 2, 2014

ጠላት ጆሮው እየሰማ ዓይኑም እያየ ለክብራችን በአንድነት ጸንተን እንቆማለን!!!

ህወሃት ልዩነቶቻችንን አብዝቶና አርብቶ ክብራችንን አዋርዶ ረግጦ ሊገዛን ዘመኑን ሙሉ ሠርቷል። ለብዙ ግዜም አንዱን ህዝብ የአንዱ ጠላት አድርጎ ሲሰብክ ኑሯል። ይህንንም እውነት ለማስመሰል በበደኖ ፤በአርባ ጉጉ፤ በሃረርጌና በሌሎች ሥፍራዎች የብዙ ንጹሃን ዜጎችን ደም አፍስሶ ለርካሽ ፖለቲካ ፍጆታ አውሎታል። በደኖ ላይ አፈር ገፍቶ ይኖር የነበረ አማራ የተባለ ዘር የተጨፈጨፈው በህወሃት ፊታውራሪነት ነው። በአርባ ጉጉ ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ሰቆቃ አዛዥና አስፈጻሚው በመለስ ዜናዊ የሚመራው ህወሃት መሆኑን የምንዘነጋው ጉዳይ አይደለም። ልዩነታችን ውበታችን ሊሆን ሲገባው መጠቂያችን ሁኖ ጎድቶናል። በመለያየታችን ምክንያት ብዙሃኑ ለነጻነታቸው የሚያደርጉት ትግል ተዳከመ እንጂ አልጎለበተም። ጥቂቶች ብዙሃኑን ለመጨቆን አቅም አገኙ እንጂ አደብ አልገዙም። ተራርቀን በመቆማችን መለስ ዜናዊና ቡድኑ በክፍተቱ ተጠቀሙ እንጂ ነጻነት የተነፈገው ብዙሃኑ ያገኘው አንዳች በጎ ነገር የለም።

የመለስ ዜናዊና ቡድኑ ብርቱ ፍላጎት ኢትዮጵያዊያኖች የታሪክ እሰረኛ ሆነን ልዩነታችንን ማጥበብ ተስኖን ተከፋፍለን ተዳክመንና ተስፋ ቆርጠን እንድንኖር ነው።ይህን መፍቀድ ደግሞ ውረደት ነው።
በአገራችን ታሪክ ውስጥ በማወቅም ባለማወቅም ብዙ በጎ ያልሆኑ ነግሮች መፈጸማቸው እውነት ነው።ብዙሃኑ በጥቂቶች ተረግጠውና ተጨቁነው መከራቸው በዝቶ ዘመኑን ማሳለፋቸውም የሚካድ አይደለም።ጥንት ስህተት ተፈጽሟል። በዚህ ልዩነት የለንም። ብዙዎቻችን እንስማማለን።ልዩነታችን የሚሰፋው ያን ክፉ ስህተት መልሰን እንደግመዋለን በሚሉና ከስህተቱ ተምረን አንዲት ጠናካራ አገርን እንመስርት በሚባልበት ግዜ ነው።
ግንቦት ሰባት ጥንት የተፈጸሙ ክፉ ነገሮችን ለመደግም ፍላጎት የለውም።ያ ስህተት እንዳይደገም በርትቶ የሚሰራ ንቅናቄ ነው።ከጥንቱ ስህተት ልምድ ቀስመን ያን ስህተት ላንደግመው ቃል ገብተንና አብረን ለመታገል ቆርጠን ቆመናል። ከስልጡን ዜጋና ለመጪው ትውልድ ኃላፊነት ከሚሰማው ዜጋም የሚጠበቀው ይሄው ነው እንጂ ጥንት የተፈጸመውን እያመነዥኩ በጥላቻ ሰንሰለት ታስሮ ነጻነት እቀዳጃለሁ ማለት አይደለም።ጥንት እንዲህ ሆነናልና ዛሬ አብረን አንቆምም ማለት መለስ ዜናዊ የቆመለትን ዓላማ ከማስፈጸም ውጪ መከራውና ስቃዩ በዝቶበት ለሚኖረው ህዝባችን የሚፈይደው ከቶ ምን ይሆን?
እንደ ግንቦት ሰባት እምነት የታሪክ እሰረኛ ሁነን በጎ ነገር ሳንሰራ የምንቀረውም ከወደፊቱ ይልቅ የትናንቱን የታሪክ እንከኖች እያቦካን መኖርን ስንመርጥ ነው።የህወሃትም ህልምና ምኞትም የታሪክ እሰረኛ ሁነንና ተዳክመን እንድንኖር ነው እንጂ በአንድነት ቆመን ነጻነታችንና ክብራችንን እንድናስጠብቅ አይደለም። ከመቶ ዓመትና ከዚያ በፊት የተፈጸሙ ክፉ ነገሮች ለነገው ነጻነታችን እንቅፋት ሁነው እንዲቆሙ ማድረግ ነጻነቴን እፈልጋለሁ ከሚል ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም። ያለፈውን እያሰቡ የወደፊቱን ብሩህ ተስፋ ማጨለም ነቀፌታ በተለባሰው ታሪክ ውስጥ ራስን እስረኛ ማድረግ ነው። ነጻነቱን የሚፈልግ አስቀድሞ ከዚህ እስራት ራሱን ማስፈታት አለበት። ከዚህ እስራት ያልተፈታ የነጻነትን ጣእም አያውቃትምና ሌላውን ነጻ ሊያወጣ የሚችል የሞራል ብቃት ይኖረዋል ለማለት አይቻልም።
ግንቦት 7 ከእንዲህ ዓይነቱ እስራት የወጡ ዜጎች ስብስብ ነው። በዚህም ምክንያት ለነጻነታችንና ለክብራችን ስንል ጠላት ዓይኑ እያየ ጆሮውም እየሰማ ግንባራችንን ሳናጥፍ በአንድነት ጸንተን ጠላቶቻችንን ከመታገል ውጪ የቀረን ምንም ምርጫ የለንም ብሎ ያምናል። መለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹ ጠላቶቻችን ናቸው። ነጻነታችንን ነፍገው ክብራችንን አዋርደውና ረግጠው ሊገዙን የሚሞክሩ ኃይሎች ሁሉ ጠላቶቻችን ናቸው። የአገራችንን ድንበር አፍርሰው ዜጎችን አፋናቅለው ለም መሬቶቻችንን ለባእዳን የሚሰጡ ወይም ለራሳቸው መጠቀሚያ የሚያደርጉ ሁሉ ጠላቶቻችን ናቸው።ዜጎች በነጻነት እንዳያስቡ የዜጎችን የማወቅ መብትና ነጻነት የሚገደቡ ሁሉ ጠላቶቻችን ናቸው። ንጹሃን ዜጎችን በሃሰት ከሰው በሃሰት አስፈርደው ለስቃይ የሚዳርጉ በሙሉ ጠላቶቻችን ናቸው። የአገሪቷን ወጣቶች ከአገራቸው መሰደድና በየበረሃው ቀልጠው እንዲቀሩ ምክንያት የሆኑ ኃይሎች በሙሉ ጠላቶቻችን ናቸው። ይህን የመሰለ ህያው ጠላት እያለን ከሙታን ጋር ውጊያ ውስጥ መግባት ጅልነት ካልሆነ ሌላ ምን ሊባል ይችላል? የዛሬውን ህያው ጠላት ህወሃትን በአንድነት ሁኖ ለመታገል እምቢ ማለትስ የነጻነትን ትርጉም አለማወቅ ካልሆነ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?
ግንቦት ሰባት የነጻነት፤ የዴሞክራሲና የፍትህ ንቅናቄ ከትላንትናው በደል ይልቅ የዛሬው በደል ያንገበግበዋል። ከጥንቱ ጉድፍ ይልቅ የመጪው ትውልድ እጣ ፈንታ ያስጨንቀዋል። የዛሬው በደል ያንገበገባቸው ኢትዮጵያዊያን ስጋና አጥንታቸውን ከመቁጥር አልፈው ከአራቱም አቅጣጫ ተጠራርተው በአገራችን ውስጥ ፍትህ ነግሶ፤ ነጻነት ሰፍኖ፤ ህዝቦቿ በሠላም በፍቅርና በአንድነት እንዲኖሩ ለማየት ብርቱ ፍላጎት ባላቸው ወንዶቾና ሴቶች የተቋቋመ ንቅናቄ ነው። የግንቦት ሰባት ጠላቱ የዛሬው ህወሃት እንጂ የትላንትናዎቹ ፊውዳሎች ወይም ደርጎች አይደሉም። እነርሱ ዛሬ የሉም። ጠላታችን በእነርሱ መቃብር ላይ የቆመው ዘረኛውና ዘራፊው ህወሃት እንጂ በዛሬውና ነጌው ህይወታችን ላይ ቅንጣት ታክል ተጽዕኖ መፍጠር የማይችሉ የትናትናዎቹ ሙታኖች አይደሉም።
ህወሃትን የመሰለ ዘረኛና ዘራፊ ቡድን በራሳችን ላይ ተጭኖ እርሱን በአንድነት ሆነን ከመታገል ፈንታ “እንዲያና እንዲህ” ሁነን ነበር እያሉ ማላዘን ጥቅም የለውም። ጥቅም አለው ከተባለም የሚጠቅመው ህወሃትን እንጂ ነጻነቱን ተነፍጎ የኖረውን ህዝብ አይደለም። ነጻነትን ለመቀዳጀት የፈለገ እርሱ የጠላት ጆሮ እየሰማ አይኑም እያየ እጅ ለእጅ ተያይዞ ጠላትን ለመፋለም መዘጋጀት አለበት። አዎን አማራጫችን አንድ ሆነን ህያው የሆነውን ጠላታችንን መታገል ነው። አንድ ሆነን አንታገለም ማለት ጠላት ህዝባችንን እስከ ልጅ ልጆቻችን እንደጨቆነ ይዝለቅ ከማለት ውጪ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም።
ህያዊያን ጠላቶቻችንን በጋራ ለመዋጋት ከልብ የምናቀርበውን ጥሪ የሚጠራጠሩና ከሙታኖች ጋር የገጠሙት ጦርነት ያልበረደላቸው ወገኖቻችን ሊያውቁት የሚገባው አንድ ቁምነገር ቢኖር፤ ግንቦት ሰባት ምንም የተደበቀ አጀንዳ የሌለው መሆኑን ነው። የንቅንቄያችን አጀንዳ ለሰው ሁሉ የተገለጸ እንጂ የተሰወረ አይደለም። አጀንዳችን ነጻነት፤ ፍትህ፤ እኩልነት እና ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር ተገንብታ ማየት ነው። ይህንን ለማስፈን አሉ የሚባሉ መንገዶችን ሁሉ እንጠቀማለን። ከሁሉም ነጻነት ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን ጋር አብረን እንሰራለን።ሊረዱን የሚፈልጉ ወዳጆችን ርዳታ ሁሉ እንደአስፈላጊነቱ እንጠቀማለን። ይህን ሁሉ የምናደርገው ለስልጣን አለመሆኑን አሁንም ደግመን ደጋግመን እንናገራለን። የምንታገለው አገራችንን ከጥፋት ማዳንና በዚያችም አገር ውስጥ ስልጣን ላይ የሚወጣበትን ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍጠር ነው። ይህንን ደግሞ ጠላት ዓይኑ እያየ ጆሮውም እየሰማ እናደርገዋለን።
ድል ለነጻነት ታጋዮች በሙሉ !!!!

No comments:

Post a Comment