Monday, December 22, 2014

አገሬ! (ብሌን ከበደ)

poor
የኔነት መለያ ~ የናት ያባቴ አገር ~ የተወለድኩባት፣
ስረ መሰረቴ ~ ቅርንጫፍ ሀረጌ ~ እትብቴ ያለባት፣
ተስፋዬ : ውጥነኔ ~ ህልሜ ሚፈታባት፣
ሀገሬ የኔ ናት~ ፣
ሀገሬ እርስቴ ናት~።
አፈሩን ፈጭቼ ፣
ውሀ ተራጥቼ ፣
ዘልዬ ቦርቄ ~ ያደኩበት መንደር ፣
በሀሳብ በርሬ ~ በምናብ ከንፌ~ የማርፍባት ሰፈር ፣
የማንነቴ ምንጭ ~ መመኪያ አገሬ፣
አድባሬ አውጋሬ ፣
የዘወትር ህልሜ ~ የድካሜ እፎይታ ~ ማረፊያዬ ጎጆዬ፣
የትም የትም ዞሬ ~ ማሳረጊያ ቤቴ ~ አንገት ማስገቢያዬ፣
አገሬ እማማዬ ።

ቀየሩት ይሉኛል ~ አፈረሱት አሉኝ ~ ለወጡት ባዱኛ፣
የኛ ሰፈርማ ፣
ሜዳው ሸንተሩ ~ መቦረቂያ መስኩ ~ አሁን የት አለና፣
ተሸጠ ለሌላ ~
የነሱን ኪስ ሞላ።
ይህው በቀደም ለት ፣
ደውዬ ልጠይቅ ~ የወዳጅ ደህንነት፣
ስልኩ ጠርቶ ጠርቶ ~ “• • • ጥሪ አይቀበልም” ~ የምትል ሴት አለች፣
ያውም ባባቴ ቤት ~ በተወለድኩበት ~ ደሞ ይቺ ማነች?
ብዬ አጠያይቄ ~ ጭራሽ መልስ ባጣ፣
ሳወርድ ሳወጣ፣
ኔት ወርክ ስለሌለ ~ የሚል ምላሽ መጣ።
ኔት ወርክ ስለሌለ?
መብራት ስለሌለ?
ውሀ ስለሌለ?
የት ገባ ተባለ?
የምናየው ልማት፣
በ’ኢቲቪ’ መስኮት?
አረንጓዴ ለብሶ ~ አውድማው አሽቶ፣
እህል ተትረፍርፎ ~ ህዝብ ጠግቦ በልቶ፣
በአየር በምድር ~ መንገድ ተዘርግቶ፣
ከተማው ተውቦ ~ ህንፃው ሰማይ ነክቶ፣
ስልጣኔ ገኖ ~ ቴክኖሎጂው በዝቶ፣
እኔን ግራ ገባኝ • • •?
ማንስ ነው `ሚነግረኝ?
የሚወራው ሌላ የሚታየው ሌላ፣
አረ ለመሆኑ ~ ‘ኢቲቪ’ የሚባለው
የምስኪኗ አገሬ ~ ወይስ የሌላ ነው?

No comments:

Post a Comment