Wednesday, December 17, 2014

ከሞት በስተቀር ወደ ኋላ እሚመልሰን ምንም ሃይል የለም!

by Eyerusalem Tesfaw 
ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ በሚል ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ ዘጠኙ ፓርቲዎች በጋራ ያዘጋጁት የአንድ ወር መርሃ ግብር መቋጫው ህዳር 27 እና 28 እሚደረገው የአዳር ሰልፍ ነው ይህ የአዳር ሰልፍ ከተጠራ ወዲህ በወያኔ/ኢህአዴግ ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥ ተፈጥሮ እንደነበር በግልፅ ሲታይ የሰነበተ ነገር ነው እስሩ እንግልቱ እና ማዋከቡ ሰልፉ አንድ ሳምንት ሲቀረው ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን ከእሮብ ህዳር 24 ጀምሮ የነበሩትን ቀናት ላስታውሳችሁ ወደድኩ

በዚች ቀን በቅስቀሳ ላይ የነበሩ አባላቶቻችን ታሰሩብን በተለያየ አቅጣጫ ብዙ ሺህ ወረቀቶችን የበተኑ ሲሆን ብዙዎቹ በሰላም ሲመለሱ አምስት ልጆች በቁጥጥር ስር ዋሉ ወይኒ ንጉሴ እና ሚሮን አለማየሁ ማታ በመታወቂያ ዋስ የወጡ ሲሆን ማቲ ባህረ እና ሲሳይ በአሁን ሰዓትም ጉቶ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወረዳ 9 በእስር ላይ ይገኛሉ

ሐሙስ ህዳር 25 በህይወቴ ካሳለፍኳቸው እማይረሱኝ ቀናቶች አንዱ ነው አስጨናቂ አስፈሪ በመጨረሻም አስደሳች ዕለት ነበር ጌች አቤሎ ብሬ ዮኒ እያስ ፍቅር ሃይሌ ወይኒ እና እሙ ያች ቀን እንዴት ትረሳለች?

አርብ 26 ቢሯችን ቀን እና ለሊት ተከቦ ነው እሚያድረው እሚውለው ወደ ቢሮ እሚገባ እና እሚወጣ ሰው ተፈትሾ ነው እሚያልፈው እኛን ቢያግቱንም ከተማዋ ግን በቅስቀሳ ወረቀት አሸብርቃ ታድራለች ትውላለች ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት አካባቢ ወይኒ ንጉሴ እንደራሴ አካባቢ በደህንነቶች መያዟን ሰምተን ተሰባስበን ወደዛው አቀናን አገር ይያዝ አልን የሰማያዊ አርማ ያለበትን ቲሸርት በመልበሷ ነበር አፍነው ሊወስዷት ሲሉ የደረስነው ፖሊሰቹን ያፈናትን ደህንነት ይያዝልን አልን ፖሊሶቹ የኛ አባል ነው አሉን መታወቂያ ያሳይ ካለበለዚያ አንላቀቅም አልን ሰላዩ እሚናገረውን አልነበረውም በጣም ደንገጧል ፍቅረማርያም አርበደበደው በማንነትህ ስለምታፍር ነው መታወቂያ እማታወጣው አለው ከብዙ ንትርክ በኋላ ወይኒን አስመልሰን ተመለስን ከደቂቃዎች በኋላ ፍቅረ ሲወጣ እንደዛ ያርበደበደው ሰላይ በጣም ብዙ ፖሊሶችን ይዞ መጥቶ ምንም በሌለበት ድንጋይ ወርውሮ መታኝ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ ነገሮችን ለማረጋጋት ፍቅርን ይዘን ወደ ቢሮ ልንገባ ስንል ሁለት ሰላዮች አደባባይ ላይ በእጁ ምንም ያልያዘ ሰላማዊ ሰው ላይ ሽጉጥ አቀባበሉ ጌታነህ ሩጦ ሄዶ አንዱን ሰላይ የተቀባበለውን ሽጉጥ ከምንም ሳይቆጥረው እጁን ያዘው ፖሊሶቹ ገፈታትረው አስወጡት ፍቅረናም በግራ እና በቀኝ ሽጉጥ ደቅነው ይዘውት ሄዱ ረጅም ሰዓት ከፈጀ ንትርክ በኋላ ወደቢሮ ገባን
የነገረ ኢትዮጵያ ምክትል አዘጋጅ በላይ ማናየ እና ሳሙኤል አበበ ፍቅረ ማርያም እሚገኝበትን ለማወቅ በየእስር ቤቱ ለመፈለግ ወጡ ከቢሮአችን አቅርቢያ ያለው ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በቆጥጥር ስር እንደዋሉ ሰማን በዚቸ ቀን የመኢአድ ህዝብ ግንኙነት አቶ ተስፋሁንን ጨምሮ ብዙ አባላት ታሰሩብን የሁላችንም ስልክ በየአቅጣጫው ይጮሃል እከሌ ታሰረ እከሌ ታፈነ……. የጋዜጠኞቹ ቢሮ በዜና ተጨናንቃለች ወያኔ ከአቅሙ በላይ ሆነናበታል በዚህ ሰዓትም እሳት በሆኑት የሰማያዊ አባላት የስቃይ ማማ የሆነውን የማእከላዊ በር ጨምሮ አዲስ አበባ በቅስቀሳ ወረቀት ተጥለቀለቀች ደስታችን ወደር አልነበረውም ከሞት በቀር ምንም ነገር አያስቆመንም እያልን የተናገርነውን በተግባር እያሳየንበት ያለ ጊዜ ነበር ለሊት ስድስት ሰዓት አካባቢ እነ በላይ መጡ በራችን ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የመንግስት ቅጥረኞች መወረሩን ሰማን

በራችንን ቆልፈን ድምፃችንን ከፍ አድርገን እጅ ለእጅ ተያይዘን የሰማያዊ ፓርቲን መዝሙር በስሜት ስንዘምር አደርን ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነሳ ነበር ቁርስ የቀመስነው ማንም የርሃብ ስሜት አይሰማውም ነበር በዚህ አጋጣሚ ከኛ በላይ ሲጨነቁ ያደሩ አገር ውስጥም በውጭም ያሉ ወዳጆቻችንን ማመስገን እወዳለሁ በተለይ በውጭ አገር እሚኖሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጭንቀታቸው ያስጨንቅ ነበር በየደቂቃው ነበር እሚደውሉት ሁልጊዜም ከጎናችን በመሆን እያደረጋችሁ ያላችሁት ነገር ቀላል አይደለምና እናመሰግናለን

በራችንን ሰብረው ሊገቡ እንደሚችሉ እንጠብቅ ነበር ሆኖም ከበላይ ትዕዛዝ ስላልደረሳቸው ሰላም ከተባለ በሰላም አደርን እና ያቺ እኛ በጉጉት ወያኔ ደግሞ በፍርሃት እና በስጋት ሲጠብቃት
የነበረቸው ቀን መጣች

በራችንን ከፍተን ስንወጣ በሩ ላይ ተለጥፈው የነበሩት ወረቀቶች በሙሉ ተገንጥለዋል አሳፋሪ መንግስት ሰሞኑን በተከታታይ ስናዳምጠው የነበረው የሰማያዊ ፓርቲ ሁለተኛ መዝሙር እስከሚመስል ድረስ ሁሌ በቢሮአችን እሚከፈተው የአብነት አጎናፍር አያውቁንም እሚለውን ዘፈን ሞቅ አድርገን በመክፈት ግቢያችንን ሞቅ ሞቅ ማድረግ ጀመርን ገና በጠዋቱ የማፍያው መንግስት ወከባ ሳያስፈራቸው በዙ ሰዎች ወደቢሮአችን መምጣት ጀምሩ ሰልፉ በተለያየ አቅጣጫ እንደሚነሳ ተነግሮ ነበር የመጀመርያው ግሩፕ መስቀል አደባባይ እንደደረሰ መረጃ ደረሰን ወዲያው መስቀል አደባባይ የደረሱ ሰዎች በሙሉ በወያኔ ቅጥረኞች እየታፋኑ እንደሆነ ሰማን እንኳን እሚታወቁት የፓርቲ አባላት ይቀረና ለራሳቸው ጉዳይ መስቀል አደባባይ የተገኙት ሰዎች በተለይ ሙስሊሞች እየታነቁ ወደተለያየ ቦታ ይወሰዱ ጀመር

በቢሮ ያለን ልጆች ተሰበሰብን እና አሁም መውጣት እንዳለብን ተነጋግረን ባነሮችን የሰማያዊ አርማዎችን ይዘን ብርሃኑ ከፊት ሜጋ ፎኑን ይዞ መፈክር እያሰማ የጣይቱ ልጆች በመከተል ድምፃችንን ከፍ አድርገን እየጮህን አሰፍስፈው ወደሚጠብቁን ጅቦች በሚገርም ድፍረት ተጠጋን አጠገባቸው እስክንደርስ መታገስ አቃታቸው ያላቸውን ሃይል በሙሉ ይጠቀሙ ጀመር በቦክስ በርግጫ በአጣና እና በያዙት የፖሊስ ዱላ ካለምንም ምርጫ ሴት ወንድ ሽማግሌ ሳይባል የጭካኔ እና የጥላቻ በትራቸውን ያሳርፉብን ጀመር በመጀመርው ዱላ ወድቄ ነበር በዚህ ሁላ ስቃይ መሃል ዱላው ሲያርፍብኝ በጣም ሚነዝር ስሜት ይሰማኝ ነበር (እኔን ብቻ መስሎኝ ነበር ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሰው እንኳን ስጨብጥ ስለሚንዘረኝ አሁንም እንደዛ መስሎኝ ነበር ጓደኞቼን ስጠይቅ ግን በብዛት ይህ ስሜት እንደተሰማቸው ነገሩኝ) ጎበዝ ዱላው ተቀይሮ መሆኑ ነው እንግዲህ ከደቂቃዎች በኋላ ወደ ራሴ ስመለስ ንግስት አረ ሞተች ኡኡኡ እያለች ትጮሃለች በጣም ደንግጬ ቀና ስል ምኞት እራሷን ስታለች እንደዛ ወድቃ ኩላሊቷን ደጋግሞ ይረግጣታል ለመጮህ አቅም አነሰኝ በጣም አሞኝ ነበር በዚህ መሃል ንግስትን ከመሃከላችን ፀጉሯን እየጎተተ መሬት ለመሬት እያንከባለለ አወጣት በጣም ዘግናኝ ነበር ፀጉሯ እጁ ላይ ቀርቶ ነበር ባለን አቅም መጮህ ጀመርን ሌላ የከፋ ህመም አቤል በአፍ እና በአፍንጫው ደም እየጎረፈ አረፋ እየደፈቀ መሬት ለመሬት እየጎተቱ መኪና ላይ ጫኑት በሁሉም አቅጣጫ ጩኸት እና ዘግናኝ ነገር ነው እሚታየው በወደቅንበት ሆዳችንን ደረታችንን ይረግጡን ነበር ሰው እንዴት ወገኑ እንዲህ ይጨክናል?

ወዲያው መኪና መጣ ሴቶቹ እንድንወጣ አዘዙን ፒክ አፕ ነው መኪናው እርቦናል ደክሞናል አሞናል በዚህ ላይ ሁላችንም ወደ መኪናው ስንወጣ እንደበደብ ነበር ሴቶቹ ወጥተን ካለቅን በኋላ ይልቃልን እየደበደቡ አንተ ነህ እንዲህ ያደረከው እያሉ በጣም አፀያፊ ስድብ እየሰደቡ እኛ ላይ ወረወሩት በጣም አዘንኩ ኩራትም ተሰማኝ ከፊት ሆኖ መከራን እሚቀበል መሪ ማየት ብዙም አልተለመደምና ኮራሁበት መኪና ላይ ወጥተንም ዱላው አልቆመም በዙሪያችን የከበቡን ፖሊሶች ይመቱን ቀጠለ ምኙ ትንሽ ቀና ብላልናለች ጉዞ ካሳንችስ ወደሚገኘው ስድሰተኛ ፖሊስ ጣቢያ ይቀጥላል...

No comments:

Post a Comment