Tuesday, December 23, 2014

የህዝብ ታዛቢ ሆነው ከተመረጡት ውስጥ አብዛኞቹ የኢህአዴግ አባላት መሆናቸው ተገለጸ

ታህሳስ 12 ቀን 2007 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብ ታዛቢ ምርጫ አመራረጥ ሂደት ላይ የገዢው ፓርቲ አባላት በብዛት መመረጣቸውን የምርጫው ተሳታፊዎች ለሚሊዮኖች ድምፅ ገለፁ፡፡
2007 election
የምርጫ ታዛቢዎችን በማስመረጥ ሂደት ውስጥ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የሚኖሩ የሚሊዮኖች ድምፅ ያነጋገረቻቸው የምርጫው ተሳታፊዎች እንደገለፁት አስመራጮችም ሆነ ተመራጮች የቀበሌ አስተዳዳሪዎች መሆናቸውን ፣ የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ምንም ትኩረት እንዳልተሰጠው እና ለመራጩ ህዝብ በመገናኛ ብዙሃናት በቂ ጥሪ ያልተደረገለት መሆኑን ፣ ህዝቡ ስለምርጫው ምንም መረጃ ያልነበረው እንደሆነ ፣ የምርጫ ቦታዎችን ለማወቅ ነዋሪው ህዝብ እንደተቸገረና የምርጫ ቦታዎች እንዳይታወቁ መደረጉን ፣ የመስተዳድሩ ሀላፊዎችና የካቢኔ አባላት መድረኩን በመምራት ያሻቸውን ሲሰሩ እንደነበሩ የገለጹ ሲሆን በሁሉም ቦታዎች በቂ የምርጫ ተወካዮች አለመኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ አዳራሾቹም በገዢው ፓርቲ መፈክሮች መሞላታቸውን ከእነዚህም ውስጥ ከመሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ ጋር ለዘላቂ ልማት ወደፊት! የሚል እንደሚገኝበት አስታውቀዋል፡፡

የሚሊዮኖች ድምፅ ያነጋገረቻቸው የደብረሲና ነዋሪዎች እንደገለፁት በደብረሲና መድረኩን ሲመሩ የነበሩት የክልሉ አፈጉባኤ አቶ ፋቃዱ ሙላት መሆናቸውን እና የምርጫ ቦርድ ተወካይ አቶ ብስራት ታቼ ፣ ይህንን በማስመልከት ለተነሳላቸው ጥያቄ የምርጫ አስፈፃሚዎችን አሰልጥነን በበቂ ሁኔታ ስላልተመደቡ እንደ መንግስት እንዲረዱ መፍቀዳቸውን ገልፀዋል፡፡
በሌሎች የክልል ከተሞች ማለትም በሰሜን ሸዋ ፣ በጎንደር እና በቤንቺ ማጂ ዞን ሚዛን ተፈሪ በነበረው ታዛቢዎችን የመምረጥ ሂደት ላይ ተመሳሳይ ነገር መስተዋሉን የሚሊዮኖች ድምፅ ምንጮች ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ በተካሄደው ምርጫ ላይም በክልሎች የታየው ችግር መስተዋሉን የገለፁት ምንጮች ከእነዚህም መሃል ለነዋሪው ህዝብ በቂ ጥሪ ያለመደረጉን ፣ የምርጫ አዳራሾችን ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ፣ የተቃዋሚ አባላትን ክብር ያለመስጠትና በክትትል ማወከብ ፣ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች እንዳይገቡ መደረጉን ፣ የቀድሞ የምርጫ ታዛቢዎች በድጋሚ መመረጣቸውን ፣ የገዢው ፓርቲ የአንድ ለአምስት ጥርነፋ በስፋት መስተዋሉን በተለይም በወረዳ 12 እና 13 ይህ ነገር መታየቱን እንዲሁም የምርጫ ቦርድ ተወካዮች ማንነታቸውን የሚገልፅ መታወቂያ ለማሳየት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) አባላት ታዛቢዎችን በማስመረጥ ሂደቱ ላይ እንዳይሳተፉ መዳረጋቸውን እና ለተወሰኑ ሰዓታትም በእስር ለማሳለፍ እንደተገደዱ አስታውቀዋል፡፡
Source: ሚሊዮኖች ድምፅ

No comments:

Post a Comment