Wednesday, December 17, 2014

የኢትዮጵያን ዲሞክራሲ ለመዉለድ ስንት ዘመን ይፈጃል? (ከ ቶፋ ቆርቾ)

ከ ቶፋ ቆርቾ
የምርጫ ወግ
electionምርጫ ደርሷል አይደል? ለዛ መሆን አለበት በአንድ በኩል EBC ‘ምርጫ ቦርድ ለምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና ሰጠ … ኮሮጆ አሰራጨ’… ሌሎች መገናኛ ብዙሃን ደግሞ ‘ምናምን የሚባል ፓርቲ ሰልፍ ጠራ’ … ‘የነእከሌ ፓርቲ ትየንተ ህዝብ በፖሊስ ሃይል በሃል ተበተነ’ ….. ዱዱዱዳ…እንዲያም እንዲህም የሚሉ ወሬዎች መስማት ከመሰንበቻዉ የተለመደ ሆኗል፡፡
እኛ ሃገር ስለምርጫ አምስት ዓመት እየጠበቁ ማዉራት የተለመደ ተከታታይ ድራማ (series TV show) ይመስላል… የመጪዉ ግንቦት አምተኛዉ ምእራፍ (Season 5) መሆኑ ነዉ ማለት ነዉ? ቂቂቂቂ….! እኔ የምለዉ ግን ለይመሰል ብቻ ምርጫ ማድረግ ምን ይጠቅማል? መጨረሻዉን ቀድመዉ ያወቁትን ፊልም ማየት ወይ ‘ልብ አንጠልጣይ’ የተባለ ልብ ወለድ መፃፍ ማንበብ ጊዜ ማሳለፊያ አልያም የደራሲዉን ችሎታ ለመገምገም ካለሆነ በቀር ምኑ ይነሽጣል? እሺ አንድ ሁለቴ እያወቁ መሸወድ ያለ ነዉና ምን አይደል እንበል…. አመስቴ ስሆንስ? አራዶቹ  ቢሰሙ ‘አይከይፈፍም’ ይሉናል ከምር ኩሸት ይሆናል! ልጆች ሆነን ‘ክስክስ’ የምንለዉ አይነት አክሽን ፊልም ስናይ ‘አክተሩ’ አይሞትም ምናመን ብለንና አምነን አሳምነን ፊል ማየት እንጀምራለን እዉነትም ፊልሙ ሲገባደድ አክተሩ ጠላቶቹን ያሸንፋል በቃ አይሞትም…. የኛም ሃገር ምርጫም ልክ እንደዛዉ ነዉ….. መሪ ተዋናዩ የማይሸነፍበት አክሽን ፊልም! ልየነቱ በሚሊዮነች የሚቆጠሩ መሪ እና አጃቢ ተዋንያን የሚሳተፉበት መሆኑና ለወራት የሚወራለት መሆኑ ብቻ ነዉ! የሆነዉ ሆኖ አሸናፊዉና አጃቢዎቹ ቀድሞ ዉጤቱ የታወቀበትን ምርጫ የሚባል ድራማ መሰል ነገር ማካሄድ ለምን አስፈለጋቸዉ? ቃለ ተዉኔቱን… ዝግጅቱን… ቀረፃዉን…. ዳኝነቱን አንድ አካል ብቻዉን በተቆጣጠረበት ቲያትር ዉስጥ መግባት የሚያስገኘዉ ትርፍ ይኖረዉ ይሆን?
ይመሰለኛል አለዉ…. ባይሆን ኖሮ አጃቢዎቹ ስለምን ይሄን ያህል መፈራገጥ ያስፈለጋቸዉ ነበር? ብዬ እጠይቀለሁ… በርግጥ መልሱን እነሱ ያዉቁታል!  የትወና ብቃትን ለማሳደግ ብቻ የሚያደረጉት ከሆነም ከልብ ያስገርማል …. ይቺ ይቺ በጣም አደገኛ ‘አድቬንቼር’ ነች!  የምሬን ነዉ ያለገባኝ ነገር እንዳለ አላዉቅም ግን ደግሞ እንደዉ አጉል ጉንጭ ከማልፋት… ሰዉም ከማስቸገር ምርጫ የምንለዉ ጉዳይ እዉነተኛ የፉክክር መድረክ እስኪሆን ተወት ብናደርገዉስ? ባይሆን መሰራት ያለባቸዉን መሰረታዊ ጉዳዮችን በርትተን እንስራ….፡፡
የዲሞክራሲ ሂደት?
የሆነዉ ሆነና እቺ ዲሞክራሲ የሚሏት “ዛር” ኢትዮጵያ ዉስጥ ምች ሆን ሞልቶላት የምትቆመዉ? ብትለመን ብትለምን አልወርድ አለች አይደል? ለነገሩ ብቅ ስትል ገና አስደንብረዉ እያባረሯት በየት በኩል ትምጣ? ይልቅዬ ‘ዲሞከራሲዊነት ሂደት ነዉ’ የሚባለዉ ተረት ተረት አብሮን ሊያረጅ ነዉ አይደል? ከምር 10 ዓመት ሆነዉ እኮ….! እናማ መቶ አመት እስኪሞላዉ ልንጠብቅ ነዉ ማለት ነዉ?
በነገራችን ላይ የዚህ ‘ሂደት ነዉ’ የሚሉት ማሳበቢያን ፅንሰ-ሃሳብ ከየት ይሆን ያገኟት ብዬ ሳስብ ድንገት እንግሊዝያዊዉ የኢኮኖሚክስ ሊቅ አዳም ስሚዝ ‘The Wealth of Nations’ የሚለዉ መፃሃፉ ዉስጥ ቶሸንቅሮት ኖሮ አገኘሁትና ‘እነኚ እንግሊዞች ተኮለኞች ናቸዉ….’ የሚሉት ስንኝ ወዲያዉ ትዉስ አለኝ፡፡ ለነገሩ ስሚዝ ስለዲሞክራሲ አስቦ የተናገረዉ ሳይሆን ስለእድገት ሲያወራ ያነሳዉ ሃሳብ ነዉ፡፡ እንደ ሰዉየዉ አባባል የሃገራት የኢኮኖሚ እድገት ተፈጥሮላዊ ሂደቱን ጠብቆ የሚመጣ ዝግመታዊ ለዉጥ (the natural progress of opulence) የሚለዉ አይነት ነዉ፡፡ እንዲህ ማለት ደግሞ ዛሬ የበለፀጉት ሃገራት የደረሱበት የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ ዕዉደቱ ይተበቅ ከተባለ ለታዳጊ ሃገራት ከመቶ አመት በላይ ሊፈጅ ነዉ፡፡ ሃሳቡን ብዙ ሙሁራን ፉርሽ ያደረጉት ጉዳይ ቢሆንም እኛ ቤት ሲመጣ ታዲያ ዲሞክራሲዊ ለዉጥ በሂደት የሚገኝ ነዉ ከሚባለዉ ማስመሰያ ጋር መሳ ለመሳ የሆነ ይመስላል፡፡ ለምን ቢባል ይሄዉ ሃያ አራት አመታትን አስቆጠርን ያየነዉ መሻሻል የለም … እናም መቶዋን ልነደፍን ነዉ ማለት ነዉ?
ነገሩማ የሚመስለዉ ወደኋላ መመለስ የጀመርን እንጂ ወደፊት መንቀሳቀሱ ሲያምራችሁ ይቀር የተባልን ነዉ፡፡ ወደ ኋላ መንሸራተት እንደ ሃገርና እንደ ስርዓት ትልቅ ኪሳራ ነዉ… ‘የዲሞክራሲ ውርጃ’ አይነት ነገርም ይመስላል፡፡ …. ከምር እንዴት ቁልቁል እንወርዳለን? እዚህ ላይ ፖላንዳዊዉ የምጣኔ ሃብት ሙሁሩ ፖል የተናገረዉን መጥቀስ የተገባ የሆናል…. ‘ሰዉ ከሆንን ምን እንደ ዉሻ ወደ ትፋታችን ይመልሰናል ይልቁንስ የተሻለ ሁኔታን እንፈጥራለን እነጂ’… ያላትን አይነት ሽንቆጣዉን ያስታዉሷል (if we were to emerge alive, we should not return to previous status quo but … form a better world)….. እናማ በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን ተስፋችን ምን ይሆን? ይሄ መከረኛ ትወልድ ያሰበዉን ሳይናገር… የፈቀደዉን ሳይመርጥ… አቛሙን እዳሻዉ ሳይገልፅ ዘመናትን ጠብቆ ያሰበዉ ሳይሳካ ሊያለፍ መሆኑ አሳዛኝ ነዉ፡፡
‘እና ምን ይሁን?’ የሚሉ ጠያቂዎች አይጠፉምና ለማለት የተፈለገዉን ማስረዳት ይገባል፡፡ ጉዳዩ እንግዲህ ኢንዲህ ነዉ….. ዲሞክራሲያዊ ሂደቱን የጠበቀ ለዉጥ ለማየት የግድ ዘመናትን በናፍቆት መጠበቅ የለብንም…. ሂደት ነዉ እያሉ መቀለዱን አቁመን ዛሬዉኑ መደረግ ያለበትን ማደረግ የሁሉም ወገን ሃለፊነት መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ምርጫ ማካሄድ በራሱ ግብ አይደለም! ይልቁን ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ከሚጠበቁ  ግብዐቶች መካከል አንዱ ብቻ ነዉ:: ኢትዮጵያ ዉስጥ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓትን እንገነባለን የሚባለዉ ለተፈላጊዉ ስርዓት መታጣት ተግዳሮት የሆኑ ነገሮችን ምንነትን ከስር መሰረቱ አጥርቶ ሳይለዩ ከላይ ከላይ በመጋለብ ነዉ:: ዋናዉን የስርዓቱን በሽታ መርምሮ ከለዩ በኌላ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የተያዘዉ ምልክቶችን ማስታመምና ግባዐቶች ላይ መረባረብ ነዉ:: እንደ ሚታወቀዉ ሃገሪቱ ሊፈቱ የማይችሉ የሚመስሉ ቅራኔ ዉስጥ ሰምጣ ገብታለች…. ታፍና ከመሞቷ በፊት የነፍስ አድን ስራዎች መሰራት አለባቸዉ፡፡
መድሃኒቱ
ቀዳሚዉና ዋንኛዉ ጉዳይ፡- ለታሪክ ቅራኒዎቻችን መፍትሄ ማበጀቱ ነዉ፡፡ በአንድ ወቅት… በወዲኛዉ ዘመን በበርካታ ቤሔርና ቤሔረሰቦች ላይ የደረሰ በደል አለ ይባላል፡፡ ይህም የመታገያ አጀንዳ ከሆነ ከአራት አስርት ዓመታት አለፉ:: እርግጥ ነዉ ኢትዮጲያ ዉስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ሁሉ እከሌ ከከሌ ሰይባል በጭቆና ዉስጥ ነበሩ… (ምናልባት ዛሬም ያ ሁኔታ የተለወጠ አይመስልም)፡፡ እናም በተለየ መንግድ የበደል ገፈት ቀማሽ የነበሩ ቤሔሮች፣ ቛንቛ ተናጋሪዎችና የእምነት ተከታዮች ነበሩ፡፡ የዝሆን ጆሮ ይሰጠኝ አልሰማሁም ወይም አይኔን ግንባር ያደርገዉ አላየሁም ብሎ ሽምጥጥ አድርጎ ለመካድ ካልሆነ በቀር ታሪክ የመዘገባቸዉ እዉነታዎች አሉ::  በሚኖሩበት ስፍራና ቀየ ስንክሳር ያዩ… በማንነታቸዉ እንዲያፍሩና እንዲሸማቀቁ ተደርገዉ የነበሩ የህበረተሰብ አካላት ነበሩ ምናልባተም ዛሬም ቅርፁን ይለወጥ እንጂ በዚህ ሁኔታ ዉስጥ የሚያለፉ ህዝቦች አሉ፡፡ በሌለላ አነጋገር የአማራና የትግራይ ተወላጅ ያለሆኑ እንዲሁም የኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታይ ያልነበሩ ህዝቦች ላይ በተለየ መልኩ የደረሰ በደልና ስቃይ ነበር፡፡ የአፄ ሚንሊክ የግዛት ማስፋፋትና ትልቛን ኢትዮጲያን በመፍጠር ሂደት ዉስጥ የፈጠረዉ ጠባሳ ያለተፈቀ ሃቅ ነዉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሁኔታ ሆን ተብሎ በተፈጠረ የማጋጋያና የማጋነኛ የፈጠራ ንግርቶች ታጅቦ በህዝቦች ማካከል በጋህድ የሚታይ ቅራኔን ፈጥሯል፡፡ በዉጤቱም ግልፅ የሆኑ መናናቆችና መጠላለፎች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በአሁኑ ወቅት እየታዩ ነዉ፡፡ ዛሬ በርካታ አስደንጋጭ  ሁነቶች እየተሰተዋሉ ነዉ …. በፊዉዳሉ ዘመን ለጋብቻ አጥንት ይቆጠር እንደነበረዉ ሁሉ በኛም ዘመን ለሁለት ጥንዶች መጋባት መፈላለጋቸዉና ማፋቀራቸዉ ብቻ በቂ አልሆነም ዘርን ማስተካከልም ተቀዳሚ ጉዳይ ሆኗል ፡፡ ይሄ ደግሞ በከተሞች ጭምር የሚያጋጥም ጉዳይ ነዉ፡፡ በግለሰቦች ደረጃ ያለዉን ማንሳቱ በህዝቦች ማካከል የቱን ያህል ስር የሰደደ የመጠፋፋትና የበቀል ስሜት እያደገ እንደሆነ የሚያመላክት አይነተኛ ሁነት በመሆኑ ነዉ፡፡ ቁምነገሩ ይህን እያወራን እና እያራገብን እስከ መቼ እንዘልቃለን የሚለዉ ነዉ፡፡ እዉነተኛዉ አደጋ አይኑን አፍጥጦና ጥርሱን አግጦ እኪመጣ ከዚያም እኪያጠፋን እተጠባበቅን ያለን ነዉ የምንመስለዉ፡፡ አሳዛኙ ጉዳይ ታድያ ይህ ሁሉ ዐደጋ በዚህና በመጪዉ ትዉልድ ላይ የተደቀነዉ ትዉልዱ በግል ላልፈፀመዉና ላልደረሰበት በደል ነገር ግን ያለፈዉ ትዉልድ ያወረሰዉ ስንክሳር መሆኑ ነዉ፡፡ የዚህን ማለቂያ የሌለዉን የመካሰስ ወጥመድ ሰብሮ መዉጣት የሁሉም ወገን ሃላፊነት መሆን ይኖርበታል:: ለዚህ ደግሞ  ድፍረት ይጠይቃል… እዉነተኛ እርቅና የወገናዊነትን መንፈስ ለመፍጠር ከበዳይም ከተበዳይም ወገን ተወላጅ የሆንን ሁሉ ደፍረን ልንቀበለዉ ጨክነን ልንጋተዉ የሚገባ እዉነታ አለ፡፡
ተወደደም ተጠላ በአንድ ሃገርና አከባቢ እንድንኖር ተፈጠሮ ግድ ብላናለች…ምንም ባንፈላለግ እንኴን ልንነጣጠል አንችልም… ይህ ቀዳሚዉ ሃቅ ነዉ፡፡ ሌላኛዉ ትላነት ለደረሰዉ ጥፋትና በደል የዚህ ትዉልድ ሰዎች ቀጥተኛ ተሰታፊዎች አይደለንም፡፡ ይሄን ታሳቢ አድርግን ቀጣዩን እርምጃ መዉሰድ ተገቢ ይሆናል:: ስለሆነም ለዚህ የዉርስ ፀብ መፍትሔ ማበጀት አለብን፡፡ ሃቁ ይህ ነዉ… አፄ ሚኒሊክና ጦራቸዉ አደዋ ላይ ወራሪዉን ጠላትን አሳፈሮ በመመለስ በሰሩት ገድል የኢትዮጲያ ብቻ ሳይሆኑ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ጀግና እደነበሩት ሁሉ በሌላዉ ገፅታቸዉ ደግሞ ግዛት ለመስፋፋት በደረጉት ዘመቻና በተከቱሉት ፖሊሲ ኢሰባዉነት የተሞሉ ጨፍጫፊ ነበሩ፡፡ በተለይ በአርሲ፣ በባሌ፣ በሐረር፣ በቦረና፣ በወላይታ፣ በከፋና በሌሎችም አከባቢዎች የደረሱ ዘግናኝ ጥፋቶች የማይረሱ የሃያኛዉ ክፍለ-ዘመን የታሪካችን መጥፎ ገፅታ አንዱ አካል ነዉ፡፡ ለዚህ ጥፋት የኦሮሞ ህዝብ እና ሌሎችም ቤሔሮች ብቻ የሚቆጩበት… የአማራ ህዝቦች ብቻ ለዘመናት የሚወቀሱበት ጉዳይ ሊያቆም ይገበዋል፡፡ የድርጊቱ ፈፃማዎች በዚያ ዘመን የነበሩ የስርዓቱ ጠበቂዎች ሲሆኑ በደሉ የደረሰዉ ግን በሁሉም ኢትዮጵያዉያን ላይ እንደሆነ ሊታሰብ ይገባዋል፡፡ ስለሆነም ሚኒሊክ መወገዝ ካለባቸዉ በጋራ እናዉግዝ … ለችግሩ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች መታሰቢያ ማድረግ ካለብን በጋራ ስንዘክራቸዉ እንኑር…! ይህን ጉዳይ መቛጨት የሚቻለዉ ሃያት ቅደመ ሃያቶችህ በድለዋል የሚባሉት የአማራ ተወላጆች ሃያት ቅድመ ሃያቶቻችን መከራን ተቀብለዋል ለሚሉ ለሌሎቹ ቢሔሮች ሃዘናችሁ ሃዘናችን ነዉ … ያለፈዉ ትዉልድ ስራ ተገቢ አይደለም ብሎ በደፈናዉ ይቅር በመባባል ብቻ ከሆነ ማድረግ ነዉ፡፡ ተበድለናል የሚሉ ወገኖችም ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል:: ይሄ ጉዳይ መፍትሄ ሳይበጅለት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንገነባለን ብሎ መነሳቱ አለያም ለዉጥ እናመጣለን ማለት የህልም እሩጫ ከመሆን አያልፍም::
ሁለተኛዉ ጉዳይ፡- ከመጀመርያዉ ሃሳብ ጋር የተያያዘና ተቀዋሚ ነን ብለዉ የቆሙ ሃይሎችን ይመለከታል:: ከትዉልድ ትዉልድ የተሸጋገረዉ ተቃርኖ መፍትሄ ሊበጀለት ባለመቻሉና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መስማማት ባለመፈለግ አንድ ኢህዲግን ለመገዳደር ዘጠና ምናምን ፓርቲዎች ተፈጥረዋል:: ብዙዎች ስለምን በሃገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች የጋራ ተቀናቃኝ የሚሉትን ሃይልን ለመታገል ሲሉ መስማማት እንኳን ይሳናቸዋል የሚለዉ ጥያቄ መልስ የሚያጡበት ጉዳይ ነዉ:: መልሱ ግን ቀላል ግልጽ ነዉ::አንደኛዉ ያለፈዉ ታሪካዊ ተቃርኖ የጋራ ግብ እንዳይኖራቸዉ አድርጔቸዋል…. የጋራ ግብ ቢኖራቸዉ እንኳን ተቀራርበዉ ለመወያየትና ከልብ የሆነ ጥምረትም ይበሉት ጅኒ ቁልቋል ለመፍጠር አልተቻላቸዉም:: ትልቁ የሙግት መከፈቻና የስጋት ምንጭ ሊሆን የሚችለውም እነዚህ ገዢዉን ግንባር እንቃወማለን የሚሉ ሃይሎች እርስ በርስ መቀዋወማቸዉ ብቻ ሳይሆን በጠላትነት ስሜት መተያየታቸዉ ጭምር ነዉ::ስለተመሳሳይ ጉዳይ በተለያየ መድረክ በተመሳሳይ ቌንቌ እየተናገሩ በህብረት ግን መስራት ሲሳናቸዉ ሲታይ የሚገርም ትይንት የሚሆነዉ ያኔ ነዉ::  ሌላኛዉ ጉዳይ ስለመጪ ጊዜ ያላቸዉ አተያይ ጉራማይሌ መሆኑ ነዉ:: አይበለዉና ይህ የከፋዉና የመረረዉ ህዝቡ ነግ በግብታዊነት ተነስቶ ለዉጥ እንፈልጋለን ብሎ በሌሎች ሃገራት እንደታየዉ ስልጣን ላይ ያለዉን ሃይል ቢያባርረዉ ተቃዋሚ ነን የሚሉት ሃገሪቷን በየትኛዉ ፍኖተ ካርታና ፕሮግራም ሊመሯት ይሆን? ይህን የመሰለለዉን ተቃርኖ መፍታት ሳይቻላቸዉ በሰላማዊዉ መድረክም ሆነ በሌላ ዘዴ የስርዓት ለዉጥ እናመጣለን ብለዉ የተነሱ ሃይሎች ሃገሪቱን እና ህዝቡን ወደሌላኛዉ አዙሪት ዉስጥ ያስገቧታል የሚለዉ ስጋትን የምንጋራ ጥቂቶች አይደለንም:: ዋናዉ ጉዳይ ተቃዋሚዎች ላለመስማማት የተስማሙበትን ባህል ቀይረዉ መቀራረብና በጋራ መስራት ካልተቻላቸዉ  ስልጣንን እደንደተመኛት ሳይወርሷት እኛም ዲማክራሲን እንደናፈቅናት ሳናገኛት በምድረ በዳ መቅረታችን የምር ይመስላል::
ሦወስተኛዉ ጉዳይ ከላይ ከተጠቀሱት አበይት ሃሳቦች ጋር በቀጥታ የሚያያዝና መዳረሻ ሊሆን የሚገባዉ ነዉ::ይሄዉም ለዘመናት የተቆለሉ ፖለቲካዊ ቅራኔዎችን በሰከነና በሰለጠነ መንግድ መፍትሄ እዲያገኙ የማደረግ ሂደት ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር ከመቸዉም ጊዜ በበለጠ ስለ ቤሔራዊ እርቅና ስለ ሃገራዊ መግባባት መሰራቱ የተሸለ መሆኑን መረዳት የተገባ ነዉ፡፡ በርግጥ ይህን ሃሳብ ብዙዎች ያዝ ለቀቅ ሲያደርጉት ይስተዋላል፡፡ የሆነዉ ሆኖ ሁሉም መንታ ልብ መሳይ ናቸዉ፡፡ ለምን ቢባል ሲገፉበት አይታይም…. ዛሬ ስለ እርቅ በተናገሩበት አንደበት ነገ ሲያወግዙና ሲፈርጁ ይታያሉ፡፡ እረቀ ሰላምን ለማስፈን ቀዳሚዉ ጉዳይ እዉቅና መስጠትና መከባበር ነዉ፡፡ እዉቅና መስጠት እዉነታን ከመቀበል ይጀምራል፡፡ያለፈን ታሪክ ተቀብለን መፍትሄ እንደምንሻለት ሁሉ የዛሬዉንም ነባራዊ ሁኔታ በቅጡ መረዳት የተገባ ይሆናል:: ተወደደም ተጠላም ባለንበት ዘምንም ሆነ በመጪዎቹ አመታት አሁን ስልጣን ላይ ያለዉ ሃይል ባሻዉና በፈቀደዉ ምንገድ ሃገሪቱን እየመራ የመቀጠሉ ነገር  እዉን ይመስላል፡፡ ይህን ሃይል ያገለለ የእርቅ ሃሳብም ሆነ ሌላ አይነት እንቅስቃሴ መድረሻዉ የትም ነዉ፡፡ ስለሆነም ለማዉገዝና ለማጥላለት የሚያስንፈዉ ሃሳበችን ስልጣን ላይ ያለዉን ሃይል እንደ መንግሰት ተቀብሎ ያስገኛቸዉን ዉስን ነገር ግን ነባራዊና አዉንታዊ ለዉጦች ወይም እድገቶች አክብሮ እዉቅና መስጠት ተቀዳሚዉ እርምጃ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የዚህ አይነቱ አቀራረብ ተንበረካኪ.. ተለጣፊ… ሌላለም ሌላም ነገሮችን ሊያስብል እንደሚችል ይገመታል፡፡ ይሁን እንጂ እዉነት ስለሆነ በዚህ መንገድ መጔዙ ግድ ይለናል፡፡ ፈረንጆቹ walk the talk እንደሚሉት የምናወራዉን ልንተገብረዉ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ለማለት የተፈለገዉ ጠላትነትን ብቻ ግብ ያደረገ ዘለቄታ የሌለዉ አካሄድ ስለሚሆን መደረግ ያለበትን ሁሉ አድርጎ እርቅና ድርድር ለመፍጠር የሚቻለባትን በር ክፍት አርጎ ቢያንስ መጠባበቁ የተገባ ነዉ::
እንደ መዉጫ
ከላይ የተዘረዘሩት ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ዲሞክራሲ … መብት… ለዉጥ …ትግል ቢባል እመኑኝ የትም አንደርስም፡፡ ቢሞከር እንኴን ከዚህ ቀደም እደታዩት የታሪክ አጋጣሚዎች ታጥቦ ጭቃ ከመሆን ፈቅ እንደማንል ለመተንበይ ነብይ ሞን አያሻም፡፡ ስልጣን ላይ ያለዉ ሃይል በታዓምር ዲሞክራያዊ ሊሆን እንደማይፈልግ እየታወቀ… ሰልፍ ቢወጣ… ባምርጫ ላይ ምርጫ ቢደረደር እንደዉ አጉል መፈራገጥ ለመላላጥ የሚሉት አይነት ካልሆነ በቀር ጠብ የሚል ነገር ይኖራል ማልት ቂልነት ከመሆን የሚያለፍ ነገር የለዉም፡፡ ዲሞክራሲያዊነት ደግሞ ለድርድር መቅረብ የለለበት የለዉጥ መንገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሌላ ዙር ጦርነትና ወይም ሌላ ምዕራፍ አብዮት ለሃገሪቱም ሆነ ለህዝቡ የሚበጅ አይሆንም፡፡ ስለሆነም የምንፈልገዉን አይነት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እዉን ለማድረግ የሚቻለዉ የዘመናት የታሪክ ቅራኔዎችን በቅንነት አይቶ መፍትሄ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ተቃዋሚዎች እርስ በእርስ ከመቀዋወም ሲዎጡና በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ተግባብተዉ ለለዉጥ አብረዉ መስራት ሲችሉ ነዉ::የነኝህ ሁለት መሰራታዊ ጉዳዮች እዉን መሆን ወደ ሶስተኛዉ ግብ የሚያንደረድረን ይሆናል:: ይኄዉም ከገዢዉ ሃይል ጋር ለመደራደርና መገባባት ላይ ለመድረስ የሚያስችል አቅም የሚፈጥር ሁነኛ መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ ይቻላል:: ያኔ ሁሉንም ወገን ያሳተፈ ስርዓት መመስረት ሲቻል የምንፈልገዉ የሰዎች መብት መከበር፣ ሰላም፣ እኩልነት፣ ነፃነት፣ እድገት ብልፅግና በምንወዳት ሃገራችን እዉን ማድረግ እንችላለን:: ይሁንና ይህን ህልም የሚመስል ምኞት እዉን ለማድረግ ስንት ዘመን ይፈጅብን ይሆን? ተምኔቱን ተጨባጭ ማደረግ የሁሉም ዜጎች ሃላፊነት ሊወሆን ይገበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

No comments:

Post a Comment