Friday, March 22, 2013

ዶ/ር ያዕቆብን ጨምሮ 38 ሰዎች ታስረው ተፈቱ

ለፋሽስቱ ጄነራል ሩዶልፍ ግራዚያኒ መታሰቢያ እንዲሆን በጣሊያን ሀገር መናፈሻና ሙዚየም መሰራቱን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው የነበሩት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያምን ጨምሮ ሌሎች 38 ሰዎች ያልተፈቀደ ሰልፍ አድርገዋል በማለት ለሁለት ቀናት ከታሰሩ በኋላ ባለፈው ሰኞ በዋስ ተፈቱ።
ባለፈው እሁድ መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም ስድስት ኪሎ የካቲት 12 መታሰቢያ ሐውልት ዙርያ በመነሳት ወደጣሊያን ኤምባሲ ሊደረግ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በፖሊስ እና በደህንነት ኃይሎች እንዲበተን ከተደረገ በኋላ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትና ሌሎች ሰልፉን ሲያስተባብሩ የነበሩ ወጣቶች በመኪና ተጭነው ወደ አራዳ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ተወስደዋል። በፖሊስ ጣቢያው ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ አንድ ቀን እንዲያድሩ ከተደረገ በኋላ በመታወቂያ ዋስ ተፈተዋል።
ከታሰሩት አንዱ የሆኑት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ስለሁኔታው ሲናገሩ ‘‘ጠዋት በግምት ሦስት ሰዓት አካባቢ ሰልፉ ከሚጀመርበት የካቲት 12 ደረስን። ወጣቶች ቲሸርት ለብሰው ተሰላፊዎችን ያስተናግዱ ነበር። በግምት አንድ መቶ የምንሆን ሰዎች በተገኝንበት ሁኔታ አንድ ሲቪል የለበሰ ሰው ‘‘እዚህ ጋ መሰብሰብ አትችሉም’’ ሲለን ሕገ-መንግስታዊ መብታችን ነው። ሰልፉን ለማካሄድ ለሚመለከተው አካል አሳውቀናል ብለን ተጨማሪ ሰልፈኞችን መጠባበቃችንን ቀጠልን። በኋላም መኪና ይዘው በመምጣት እኔን ጨምሮ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያምና ሌሎች የሰልፉ አስተባባሪዎችን ወደ መኪና ካስገቡን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሰልፉ ወደ እስር ተለወጠ’’ ሲሉ ተናግረዋል።

አራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከተወሰዱ በኋላ ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርጎ ያለፈቃዳቸው ፎቶግራፍ እንዲነሱ መደረጉን፣ በመቀጠል በእስር ላይ የነበሩት ወጣቶች ‘‘ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻን ደም፤ ኢትዮጵያ ሀገሬ የደፈረሽ ይውደም’’ ሲሉ እዛው ፖሊስ ጣቢያው ውስጥ መዘመራቸውን፣ መዝሙሩን ፖሊሶቹ ሳይቀሩ መዘመራቸውን የሚገልፁት ኢንጂነር ይልቃል ከዚያ ውጪ በፖሊስ መምሪያው አሳፋሪ ተግባር ተፈፅሞ ነበር ይላሉ። የፓርቲው ፕሬዝዳንት ‘‘ቃል በሰጠንበት ወቅት ‘‘ብሔር’’ የሚለው መጠይቅ ላይ ብዙዎቹ ‘‘ኢትዮጵያ’’ እያሉ ሲሞሉ የግድ ጎሳችሁን ካልተናገራችሁ በሚል የደህንነት መርማሪዎቹ ድብደባ ፈፅመዋል። ቃል ሰጥተው ሲወጡ ፊታቸው ያበጠ እና ደም በደም የነበሩ ወጣቶች ነበሩ። ከነዚህም መካከል ብርሃኑ ተክለያሬድና ጌታነህ ባልቻ የተባሉ ደግሞ የፌስቡክ የሚስጥር ኮድ ቁጥራቸውን አምጡ በሚል መገደዳቸውን፣ በህገ-መንግስቱ የአንድ ሰው የግል ምስጢሮቹ ሰነዶቹ አይመረመሩም ቢልም በቀበሌ መታወቂያ ለሚወጣ ተራ ወንጀል የግል ምስጢር ካላመጣችሁ በማለት ድብደባ እስከመፈፀም ደርሰዋል’’ ሲሉ ነው የተናገሩት። ወደፊትም በደብዳቢዎቹ ላይ ክስ ለመመስረት ማስረጃ እየተሰበሰበ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።
‘‘የመንግስትን ተቋም ተጠቅመው ውንብድና የፈፀሙብን አካላት አሉ’’ ያሉት ኢንጂነር ይልቃል ‘‘ድርጊቱ አፈና ነው። አፈናው ደግሞ ከኢህአዴግ ሕገ-ወጥነትና ሀገሩን ማስተዳደር ካለመቻሉ ጋር የተያያዘ ነው። ኢህአዴግ የሰዎችን መብት እየጨፈለቀ እድሜውን ማራዘም ፈልጓል። ኢህአዴግ ዜጎች መብታቸውን እያረጋገጡ በሄዱ ቁጥር የውስጥ ባዶነቱ እየተጋለጠና ስልጣኑን የሚያጣ እየመሰለው የሚያደርገውን የማያውቅ ስርዓት ሆኖብናል’’ ሲሉ ተናግረዋል።
በቀጣይ ጉዳዩን በምንም መልኩ አንተወውም የሚሉት ኢንጂነሩ ‘‘የእሁድ ዕለቱን ሰላማዊ ሰልፍ ማን እንደከለከለን የምናውቀው ነገር የለም፤ የሆኑ ግለሰቦች መጥተው በጉልበት መጥተው አሰሩን እንጂ ማን እንዳሰረን ማን እንደፈታን አናውቅም። ህጋዊ የሚባል ነገር ሳናይ ነው የወጣነው’’ ብለዋል።
ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም በበኩላቸው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ለመገኘት መሄዳቸውን፣ የሰልፉም አላማ በጣሊያን ፍርድ ቤት የጦር ወንጀለኛ ሆኖ ተከሶ 15 አመት ለተፈረደበት የጦር ወንጀለኛ በተወለደበት አካባቢ ሐውልትና ፓርክ እየተቋቋመለት በመሆኑ፣ በጣሊያን ብቻ ወደ 23 ከተሞች ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ በመደረጉ፣ ግራዚያኒ ደግሞ ከማንም በላይ ኢትዮጵያውያንን በመጨፍጨፉ የየካቲት 12 ሐውልት መሰራትም ሕይወታቸውን በግፍ ላጡ እናቶቻችን፣ አባቶቻችን፣ አያቶቻችን ውርደት መታሰቢያ መሆኑን በማስታወስ በሰልፉ ለመሳተፍ መወሰናቸውን ዶ/ር ያዕቆብ የገለፁት።
የተቃውሞ ሰልፉን ለማካሄድ የሰልፉ አዘጋጆች ለሚመለከተው አካል ማሳወቃቸውን ገልፀውልኛል ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤ ህጉም የሚለው ማስፈቀድ ሳይሆን ማሳወቅ ስለሆነ በሕጉ መሰረት የሰላማዊ ሰልፉን እንዲያውቀው የተደረገው መንግስታዊ አካል በ48 ሰዓታት ውስጥ ምላሽ ካልሰጠ ሰልፉ እንደተፈቀደ ስለሚቆጠር ሰላማዊ ሰልፉ መካሄዱን ትክክለኛና ሕጋዊ እንደነበር አብራርተዋል።
በዚሁ ሕጋዊ መነሻ እሁድ መጋት 8 ቀን ስድስት ኪሎ አካባቢ ገና ጥቂት ሰልፈኞች እየተሰባሰቡ በነበሩበት ሁኔታ አንድ የኢህአዴግ ካድሬ ሮጦ መጥቶ ማንንም ሳያነጋግር ሞባይል መመንጨቅ፣ ካሜራ መንጠቅ፣ ሰውን በቦቅስ መምታት ጀመረ፤ አልፎ ተርፎ የተወሰኑ ተሰላፊዎችን እየገፈተረ መኪና ውስጥ እንድንገባ አደረገ። እኛም ከሄድን በኋላ ሌሎች ተሰላፊዎችን በመኪና እያመላለሰ በፖሊስ መኪና እየጫነ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ማጋዝ ጀመረ ሲሉ ዶ/ር ያዕቆብ ገልፀዋል።
‘‘ያደርንበት ፖሊስ ጣቢያ በጣም አሰቃቂ ነበር። ሰብአዊ ክብርን የሚደመስስ፣ ሰው በሰው ላይ የሚተኛበት ስለሆነ መጉላላት ደርሶብናል’’ ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ መንግስት ሰልፈኞቹን አስሮ ከማጉላላት በቀላሉ ውሃ በመርጨት መበተን ሲችል ወህኒ ቤት መውሰዱ አሳፋሪ ተግባር ነው ብለዋል። በቀጣይ በሚካሄድ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በድጋሚ እንደሚገኙና ተቃውሞ ማሰማቱ መቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት ጣሊያን አራተኛዋ የኢትዮጵያ ለጋሽ ሀገር ናት። የህዳሴውን ግድብ ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ያሉት በጣሊያን የኮንስትራክሽን ኩባንያ ሳሊኒ አማካኝነት መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን ዶ/ር ያዕቆብ የግራዝያኒ ተግባራት ምንጊዜም ተቃውሞ ሊቀርብበት የሚገባ ድርጊት ነው። ይሄንኑ ተቃውሞ መከላከል ግራዝያኒን በተዘዋዋሪ ከመደገፍ ተለይቶ አይታይም ብለዋል። ታሪክን በአግባቡ ያነበበ የግራዝያኒን ተግባር መቃወም ይገባዋል። የተቃውሞ ሰልፉ በአሁኑ ወቅት ያለውን የኢትዮጵያንና የጣሊያንን ግንኙነት የሚጎዳ አይደለም ሲሉ አጠቃለዋል።  
ፖሊስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል። ባለፈው ዘገባችን ላይ የአዲስ አበባ የሰላማዊ ሰልፍና ፈቃድ መስሪያ ቤት ሰልፉን ለማካሄድ የፈለጉ ሰዎች የማሳወቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውንና የሚመለከተውም አካል ጉዳዩን እንደሚያየው ምላሽ መስጠቱን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም።
በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በ1938 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግስት በፈረንሳይ ዋና ከተማ በፓሪስ ላይ ለተቀመጠው የሰላም ጉባኤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የደረሰው ጉዳት በማስመልከት በወጣው ሪፖርት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በፋሽስት ጣሊያን ተገድለዋል። ከ2000 በላይ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ንዋየ ቅዱሳትም በወራሪዎች ተዘርፈዋል። ከ14 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ እንስሳት ተዘርፈዋል፣ ተገድለዋል።
የግራዝያኒን ሐውልትና ፓርክ መሰራት በተመለከተ የተቃውሞ ሰልፉን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽ ኮሚቴ አባላትና ከባለራዕይ ወጣቶች ማህበርና ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር በመሆን ነበር።
የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት በአንቀፅ 30(1) ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት እንዳለው ይዘረዝራል።
በዘሪሁን ሙሉጌታ
ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment