Tuesday, March 12, 2013

“ተቃዋሚዎች ምርጫውን ከሚያሸንፉ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ---” - ሁጐ ቻቬዝ ቬኔዝዌላ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ አምባገነን ባለስልጣናት

“ ኧረ መልሱን ስጪኝ ዝምታው ምንድነው ቅድምም አሁንም የመረጥኩ አንቺን ነው” ባለፈው ማክሰኞ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቬኔዝዌላ ፕሬዚዳንት ሁጎ ቻቬዝ፤ በጣም ዝነኛ ነበሩ - ሰውን በመዘርጠጥና በመዝለፍ፡፡ በቀዳሚነት መዝለፍና መዘርጠጥ የሚቀናቸው የሥልጣን ተፎካካሪዎቻቸውን ተቃዋሚዎችን ነበር፡፡ በመቀጠል ደግሞ የአሜሪካን ፕሬዚዳንትና ካፒታሊዝምን እንደጉድ ሲዘረጥጡና ሲያብጠለጥሉ ኖረዋል (የነዳጅ ሃብታቸው በሰጣቸው የልብ ልብ!) ሁጐ ቻቬዝ እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም እጩ ፕሬዚዳንት ሳሉ አንዳንድ የተጠራጠሯቸው ወገኖች አጓጉል ጥያቄዎች አቅርበውላቸው ነበር፡፡ (ያውም እኮ በሥልጣን ዙሪያ!) “በአምስት ዓመት ውስጥ ሥልጣን ያስረክባሉ?” ተባሉ (አያችሁ ሠይጣን ሲፈትናቸው!) እሳቸውስ ምናቸው ሞኝ ነው! “እንዴታ! እንደውም ቀደም ብዬ ለማስረከብ ፈቃደኛ ነኝ” አሉና ቂብ አሉ - የሥልጣን መንበሩ ላይ፡፡

ከዚያማ ማን ወንድ ይምጣ - ከሥልጣን የሚያወርዳቸው፡፡ አምስት ዓመት ሳይሞላኝ እወርዳለሁ ያሉት ቻቬስ፤እንደሌሎቹ አምባገነን ባልንጀሮቻቸው ህገመንግስት እየሰረዙና እየደለዙ ቬኔዝዌላን ለ14 ዓመታት እንዳሻቸው ፈነጩባት (ፈነዱባት ይሻላል!) ፕሬዚዳንቱ ምርጫ በመጣ ቁጥር ተቀናቃኞቻቸውን ሙልጭ አድርገው በመስደብና በማንጓጠጥ ይታወቃሉ፡ (እንደኢህአዴግ “መጡም ቀሩም አይጠቅሙም አይጎዱም” ዓይነት እንዳይመስላችሁ!) አምባገነንነት ላይ የነዳጅ ዶላር ሲጨመርበት ምን እንደሚከሰት አስቡት! የማታ ማታ ግን ለሁለት ዓመት ያህል ከካንሰራቸው ጋር ሲታገሉ ቆይተው ህይወታቸው አለፈ - ከሥልጣን ሱሳቸውም ተገላገሉ፡፡ ሶሻሊዝም አቀንቃኝ የነበሩት የዓለማችን አወዛጋቢው ፕሬዚዳንት ቻቬዝ ስለካፒታሊዝም ሲናገሩ፤ “አዲስና የተሻለ ዓለም ለመገንባት ትክክለኛው መንገድ ካፒታሊዝም አይደለም ፤ ካፒታሊዝም በቀጥታ የሚወስደን ወደ ገሃነም ነው” ብለው ነበር፡፡
ለመሆኑ አሁን እሳቸው ያሉት የት ነው? ገነት ነው ገሃነም? (ገነትም ሆነ ገሃነም ያቺ የሚወዷት ሥልጣን ምድር ቀርታለች!) ስለቀድሞው የቬኔዝዌላ ፕሬዚዳንት እቺን ታህል ካወጋን ለጊዜው ይበቃናል (ለአምባገነን ብዙ የአየር ሰዓት ሰጠሁ እንዴ?) አሁን ደግሞ ወደራሳችን ገበና እንዝለቅ (አዲስ የኢቴቪ ድራማ እንዳይመስላችሁ!) ወደ ፖለቲካ ገበናችን ማለቴ ነው፡፡ እኔ የምላችሁ… በፓርቲዎች የአየር ሰዓት ድልድል ዙሪያ ሰሞኑን የተደረገውን ማሻሻያ እንዴት አያችሁት? መቼም ህውሀት/ወያኔ ቶሎ መስማት አይሆንለትም አይደል! (ጆሮው ስለሚኮራ እኮ ነው!) ዛሬ ያደረጋትን ማሻሻያ ፤ ባለፈው ምርጫ ወይም ከዚያ በፊት በነበረው ምርጫ ቢያደርገው እኮ ስንት ዲሞክራሲ ባዳነ ነበር! (“ለዲሞክራሲው ሲባል ነው” የሚል ነገር ሰምቼ እኮ ነው) በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ “መብቴን ወይም ነፃነቴን ውለዳት” ሲሉት አይወድም ፤ እልህ ውስጥ ይገባል፡፡
ክፋቱ ደግሞ ተቃዋሚዎቹም ከሱ ስለማይሻሉ በጥበብና በብልሃት አይዙትም (እልህን በእልህ ባይ ናቸው!) በነገራችሁ ላይ የሚያዝያውን ምርጫ አስመልክቶ ለፓርቲዎች የተደለደለው የአየር ሰዓት 9ሚ.ብር የሚገመት ነው ተብሏል (ለዲሞክራሲ 90 ሚሊዮንም አይቆጭም!) በኢቴቪ መግለጫ ሲሰጡ የሰማኋቸው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሃላፊ (“ፓርቲዎችን አላበላልጥም ፤ እንደ ልጆቼ ነው የማያቸው” ያሉትን ፕሮፌሰር ማለቴ ነው!) የአየር ሰዓት ድልድሉ ተቃዋሚዎችን በሚጠቅም መልኩ የተሻሻለው “ለዲሞክራሲው ሲባል ነው” ብለዋል (ለምንም ይሁን …ብቻ እንኳን ተሻሻለ!) አንድ ጥያቄ አለኝ ---- ለምንድነው የአየር ሰዓት ድልድሉ ለአሁኑ ምርጫ ብቻ ነው የተባለው? (“የአየር ሰዓትም” ከእነዎርልድ ባንክ በብድር እንጠይቅ ማለት ነው?) ቀደም ሲል የአየር ሰዓት ድልድሉ ፓርቲዎች በም/ቤት ባላቸው መቀመጫ ብዛት የሚከናወን እንደነበር ያስታወሱት ፕ/ር መርጊያ፤ “አሁንም ማቲማቲካሊ እንጂ ፕሪንሲፕሉ አልተቀየረም” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ (ነገር እንዳይመጣ ሰግተው እኮ ነው!) ከድፍረት አይቆጠርብኝና … አንዳንድ “ለዲሞክራሲው ሲባል” መሻሻል ወይም መለወጥ ያለባቸውን ነገሮች ብጠቁምስ? (በእልህ ሳይሆን በፒስ!) አሁን ለምሳሌ ባለፈው ጊዜ ኢህአዴግ ምን አለ? “መድረክ” የምርጫ ሥነምግባር ደንቡን ካልፈረመ አላናግረውም ብሎ ይኸው ዝም ጭጭ ተባብለው የለ - በአገር አማን!! እኔ የምለው ግን--- ደግሞ ለመነጋገር ምን ፊርማ ያስፈልጋል? (የሚኮራረፉ ፓርቲዎች ያላት ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ሳትሆን አትቀርም!) እናላችሁ --- ኢህአዴግ “እንደራደር” እያሉ ከሚወተውቱት ተቃዋሚዎች ጋር እሺ ብሎ ቢደራደር አሸነፈ እንጂ አልተሸነፈም (ፈርሙ አትፈርሙ የሚለውን ንትርኩን ወዲያ ትቶ!) ለምን መሰላችሁ ---
- “ለዲሞክራሲው ሲባል” ነው! ከ“ዝነኛው” የ97 ምርጫ ማግስት ጀምሮ ጠበበ እንጂ ሰፋ ተብሎ የማይታወቀው የፖለቲካ ምህዳር ለምን በደንብ አይሰፋም? (ለዲሞክራሲው ሲባል“ ማለቴ ነው) ተቃዋሚዎች የፓርቲ ልሳናቸውን የሚያሳትሙበት ማተምያ ቤት፣ ስብሰባ የሚያካሂዱበት አዳራሽ ወዘተ--- ለምን አይመቻችላቸውም? (ያው “ለዲሞክራሲው ሲባል”!) የመጨረሻ ጥያቄ አለኝ ---- በ21 ዓመት የኢህአዴግ የሥልጣን ዘመን በጉጉት ጠብቀን ጠብቀን “ሲያምራችሁ ይቅር” የተባልነው አንድ ነገር አለ፡፡ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ! እናም “ለዲሞክራሲው ሲባል” የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ ይፈቀድልን ዘንድ ህገመንግስታዊ መብታችንን እንጠይቃለን (በእልህ ሳይሆን በፒስ!) እስከዚያው ግን ለ“ልማታዊው ፓርቲያችን” ለኢህአዴግ የተፈራ ካሳን ዜማ እንመርጥለታለን፡፡
ኧረ መልሱን ስጪኝ ዝምታው ምንድነው ቅድምም አሁንም የመረጥኩ አንቺን ነው--- የሚለውን፡፡ እኔ የምላችሁ… ኢህአዴግ በቅርቡ በባህርዳር ለሚያካሂደው 9ኛው ጉባኤ 15 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከውጭ አገራት እንደጋበዘ ሰማችሁ አይደል? (የአገር ቤት ፓርቲን ትቶ ከውጭ “መቀላወጥ” ምን ይሉታል?) በጣም እኮ ነው የሚገርመው ---- ኢህአዴግ ከአገር ውስጥ አንድ ፓርቲ እንኳን ሳይጋብዝ አስራምናምን ከውጭ? (የፓርቲ ጉባኤ ድንኳን ሰበራ እንዳይጀመር ሰጋሁ!) ቆይ ግን--- ይሄ ጉደኛ ፓርቲ እነዚህን ሁሉ የፓርቲ ባልንጀራዎች መቼ ነው የተዋወቃቸው? እዚህ ከአንድ ተቃዋሚ ጋር በተጣላ ቁጥር ውጭ ካለ አንድ ፓርቲ ጋር ባልንጀርነት ሲመሰርት ነበር ማለት ነው? የኢህአዴግ ቃል አቀባይ አቶ ሴኮ ቱሬ (የስማቸውን ፍቺ ባውቀው ደስ ይለኝ ነበር) ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ የኢህአዴግ ዘጠነኛ ጉባኤ ፓን አፍሪካኒዝምን ያንፀባርቃል ብለዋል፡፡
(በአገር ውስጥ ባለው የፓርቲዎች ግንኙነት አኩሪ ታሪክ ባይኖረውም ማለት ነው!) አንድ ነገር ግን መዘንጋት የለበትም፡፡ ምን መሰላችሁ--- ለሌሎች ሃሳባችንንና መስመራችንን ስናጋራ ልዩ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ሁሉ ነገራችንን ዘርግፈን መስጠት የለብንም፡፡ ለምን መሰላችሁ --- አንዳንዴ እንጠቅማለን ብለን ልንጎዳ እንችላለን፡፡ አያችሁ ---
ኢህአዴግ ለአፍሪካውያን የሚያጋራው በጎ በጎ ነገሮች እንዳሉት ቢናገርም ሁሉንም ፈጽሞ ማጋራት የሌለበት አሉታዊ ነገሮችም እንዳሉት ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት!! እስቲ አስቡት…የፓርቲውን የ“ምስጢራዊነት” ባህል ለሌሎች አፍሪካውያን ቢያጋራ ምን ዓይነት ችግር ላይ እንደሚወድቁ! (ለራሱም እኮ አልጠቀመውም) “እኔ ብቻ ነኝ የአገር መድሃኒት” የሚለውንም ጎጂ ባህሉን ለአፍሪካ ወንድሞች ማጋራት የለበትም (ትርፉ ዕዳ ነዋ!) የፍረጃ ልምዱንም (ኪራይ ሰብሳቢ፣ የሻቢያ ተላላኪዎች፣ ጥገኞች…ወዘተ) አጋራለሁ ብሎ እንዳያስብ እንመክረዋለን (እንዴ ማፈሪያ ይሆናላ!) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢህአዴግን ሲበዛ ባተሌ መሆን ለአንድ ሁነኛ ባልንጀራዬ ሳወያየው ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ… “ኢህአዴግ የተባለ ሁሉ (አመራር፣ ካድሬ፣ አባል ወዘተ…) ከምርጫው በኋላ ቫኬሽን ይወጣል” “ኧረ ይገባቸዋል…ግን ለምን ያህል ጊዜ ነው?” ጠየቅሁት፡፡ “እስከቀጣዩ ምርጫ!” “እስከ ቀጣዩ ምርጫ? እስከ 2007 ማለትህ ነው?” “አግኝተኸኛል … ያኔ ምርጫ ሲቃረብ ደግሞ ስብሰባ፣ ውይይት፣ ብሶት መስማት … የኮንዶሚኒየም እጣ ማውጣት፣ የልማት ዲስኩር … መቀወጥ ይጀምራሉ … ምርጫው ሲጠናቀቅ እንደገና ቫኬሽን …” “ቆይ እነሱ ቫኬሽን ሲወጡ ማነው የሚመራው … ማለቴ … የሚያስተዳድረው?” “እነሱው! ካሉበት ሆነው በሞባይል ያስተዳድሩናል … በሞባይል ያዛሉ … በሞባይል ቅሬታ ይሰማሉ … በሞባይል ደንብና መመሪያ ያወጣሉ … ቀላል ነው … ለምደውታል” “ምኑን?” “ቫኬሽን ላይ ሆኖ አገር መምራቱን!” ትንሽ ቆዘምኩ፡፡
ትንሽ አሰብኩ፡፡ አሰላሰልኩ፡፡ በኋላ እንዲህ አልኩ - ለራሴ፡፡ “እነሱ ቫኬሽን ሲወጡ እንኳን ለምን ለተቃዋሚዎች አይሰጧቸውም?” (አገር መምራቱን ማለቴ ነው!) እኔ የምለው ግን ---- ኢህአዴግ ወተት በየቤታችን በቧንቧ ያስገባልናል ብለን ስንት ስንኩራራ እንዲህ ያሳፍረን! (ውሃውም ጠፋ እኮ!) አንድ ለልጃቸው ሠርግ ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩ እናት አንዴ መብራት፣ ሌላ ጊዜ ውሃ እየጠፋ ሲቸገሩ ምን አሉ መሰላችሁ? “ይሄንን ጠላ ጅቡቲ ሄጄ ካልጠመቅሁት ጠላም አይሆን!” አሁን ደግሞ ስለ ቻቬዝ ትንሽ እናውጋ፡፡ አንዴ ስለአገራቸው ተቃዋሚዎች ምን አሉ መሰላችሁ? “ተቃዋሚዎች አስቂኝ ስለሆኑ ማታ ማታ ልጆቻችንን ያዝናኑልናል” (እንደኛ አገር ተቃዋሚ ከሆኑ በጨጓራ በሽታ ይቃጠላሉ!) እ.ኤ.አ በ2002 ዓ.ም ለአጭር ሰዓታት የዘለቀ ኩዴታ ተሞክሮባቸው የነበሩት ቻቬዝ፤ የሞት ሞታቸውን እንዲህ የሚል መግለጫ ሰጥተው ነበር- “በእስረኝነት የተያዝኩ ፕሬዚዳንት ነኝ እንጂ ሥልጣን አለቀቅሁም” (ይሞታል እንዴ!) እ.ኤ.አ በ2012 ለትንሳኤ በዓል በተሰበሰበ ምዕመን ፊት እያለቀሱ የታዩት ቻቬዝ፤ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ኢየሱስ፤ መስቀልህን አምጣ ልሸከም … ገላዬ እንዲደማም የእሾህ አክሊልህን ስጠኝ … ግን መኖር እፈልጋለሁ … ለዚህ አገርና ህዝብ ብዙ የምሰራው አለኝ … ሩጫዬን ገና አልጨረስኩምና እንዳትወስደኝ” (ሥልጣን አልበቃኝም ቢሉ ይሻላቸው ነበር) መቼም ቻቬዝ ---እንደ አሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ የሚጠሉት ሰው አልነበረም ፤ እናም በተደጋጋሚ ሰድበዋቸዋል፡፡ አንዴ ራሳቸው በሚያዘጋጁት የቲቪ ቶክ ሾው ላይ “የአልኮል ሱሰኛ፣ ሰካራም፣ ውሸታም፣ የነቀዝክ … አዕምሮህ የተነካ በሽተኛ!” ሲሉ ሞልጨዋቸዋል፡፡ የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትር የነበሩት ቶኒ ብሌርም ከመሞለጭ አልዳኑም “የኢምፔሪያሊዝም ታጋች ነህ … ገሃነም ግባ!” ብለዋቸዋል፡፡ ቻቬዝ የካፒታሊስት አገራት መሪዎች ቀንደኛ ጠላት የነበሩትን ያህል የሶሻሊስቶቹ ወዳጅ እንደነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም ኩባ ሄደው የነበሩት ሁጐ ቻቬዝ፤ፊደል ካስትሮን ሲያደንቁ “በዚህች አህጉር የተካሄዱ አብዮቶች አባት ነህ፤ የኛም አባት አንተ ነህ” ብለዋቸዋል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከካንሰር ህመማቸው ጋር ክፉኛ እየታገሉ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተወዳደሩት ቻቬዝ፤ ተቃዋሚዎቻቸውን ተስፋ ለማስቆረጥ ጉልበት አላጡም ነበር፡፡ (ኢህአዴግም አንዳንዴ ይነሳበታል እኮ!) ለማንኛውም እሳቸው ያሉት እንዲህ ነበር “ተቃዋሚዎች ምርጫውን ከሚያሸንፉ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይሻላል” ይሄ አባባል ለኛም ይሠራል እንዴ? (ቢያንስ በአሁኑ ምርጫ!) ሥልጣን የሌለበት አገር የሄዱት ቻቬዝ (ቢኖርም የሚሰጣቸው የለም!) ስለ ሶሻሊዝምና ካፒታሊዝም በተናገሩት አባባል የዛሬ ፖለቲካዊ ወጋችንን እንቋጭ - “ካፒታሊዝም የሰይጣንና የብዝበዛ ሥርዓት ነው - የመጀመርያው ሶሻሊስት ነው ብዬ በማስበው በኢየሱስ ክርስቶስ ዓይን ነገሮችን ማየት የምትሹ ከሆነ እውነተኛ ህብረተሰብ መፍጠር የሚችለው ሶሻሊዝም ብቻ ነው” ምንም እንኳን ቻቬዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እቺን ዓለም ቢሰናበቱም በተለይ በካፒታሊዝምና በአሜሪካ መሪዎች ላይ በተናገሯቸው የዘለፋ ቃላት መታወሳቸው አይቀርም (ባያኮራም!)
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment