Saturday, March 23, 2013

ኢህአዴግ 9ኛ ጉባኤውን በባህርዳር ጀመረ


መጋቢት ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፭ (2005) ዓ/ም 

”በመለስ አስተምህሮዎች ጠንካራ ድርጅትና የልማት ሀይሎች ንቅናቄ ለህዳሴያችን በሚል” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ጉባኤ ዋና አላማ ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በሁዋላ እየተዳከመና  በውስጥ ሽኩቻ እየታመሰ የመጣውን ኢህአዴግን መልሶ ማጠንከር  ነው።ግንባሩ በስልጣን ሽኩቻ የሚታመሱት አባላቱ ድርጅቱ የመጣበትን ጉዞ መለስ ብለው እንዲያስታወሱ የሚያደርግ ተውኔት አዘጋጅቶ አሳይቷል። ኢህአዴግ ደርግን ለመጣል ያሰላፈውን ታሪክ፣ የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነት ለማስከበር የከፈለውን መስዋትነትና አባይ ለመገደብ የጀመረው ጥረት የሚያሳየው ተውኔት በቀጥታ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሰራጭ ተደርጓል።ግንባሩ ከ21 አመት በሁዋላ ተመልሶ ስለበረሀ ትግሉ ያቀረበው ተውኔት ነባሮቹ ታጋዮች የመጡበትን መንገድ ተመልሰው በማየት ለድርጅቱ ያላቸውን ታማኝነት እንዲያድሱ፣ ትግሉን ዘግይተው የተቀላቀሉት ወጣቶቹ መሪዎች ደግሞ የቆዩት መሪዎች የከፈሉትን መስዋትነት በማስታወስ ከበሬታ እንዲሰጡ  መልእክት  የሚያስተላልፍ ተውኔት መቅረቡን ጉባኤውን በመከታተል ላይ ያለው ዘጋቢያችን ገልጿል።ከመለስ ሞት በሁዋላ እያንዳንዱ የኢህአዴግ አባል ልዩነቱን እየፈታ በመቻቻል የድርጅቱን   ህልውና እንዲያስጠብቅ ተነግሮታል።በኢህአዴግ የጉባኤ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ” ድርጅታችንን እናድን፣ ድርጅታችንን እንጠብቅ” የሚለው መልእክት፣  ኢህአዴግ የገባበትን ቀውስ እንደሚያሳይ ዘጋቢያችን አክሎ ገልጿል።አቶ መለስ ዜናዊ ከሞቱ በሁዋላ ድርጅቱ አለመፍረሱ እንደ ትልቅ የድል ስኬት ተደርጎ ቀርቧል።አዲሱ የድርጅቱ ሊቀመንበር ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ድርጅታቸው ባለፈው ጉባኤ የወሰናቸውን ውሳኔዎች ለማስፈጸም እንዳልቻለ ገልጸዋል።የግብርናው መስክ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ምርቱን በእጥፍ ያሳድጋል ተብሎ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም አልተሳካም።የ2004 የግብርና ምርት እድገት ከታቀደለት አንሶ መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል ።የጥቃቅንና አነስተኛ የማምረቻ ተቋማት  በተፈለገው ፍጥነትና ጥራት ባለመቋቋማቸውና ባለመስፋፋታቸው ውጤት ማምጣት ሳይችሉ መቅረታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ኢንዱሰትሪው ኢኮኖሚውን መምራቱን ከግብርና ይረከባል ተብሎ የታቀደው በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሳካ አለመሆኑን ተናግረዋል።መንግስት የዘረጋቸው የመንገድ ፣ የባቡር ፣ የሀይል ፣ የስልክና የውሃ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የማስፈፀም አቅም ውስንነትና ዘርፉ ሰፊ የካፒታል አቅም መፈለጉ ፕሮጀክቶቹ እዲጓተቱ በማድረጉ ጉባኤው የመፍትሄ ሀሳብ እንዲፈልግ ተማጽነዋል።በኢህአዴግ የጉባኤ ታሪክ ባልታየ ሁኔታ ” የግብርናና የኢንዱስትሪ እቅዶች” እንዳልተሳኩ በሊቀመንበሩ መገለጹ ፣  የጉባኤው መንፈሳዊ መሪ ተደርገው የሚታዩት አቶ መለስ ዜናዊ ያወጡዋቸው እቅዶች የማይተገበሩ መሆናቸውን ያመላከተ መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጿል።አቶ ሀይለማርያም   ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቅ እያሉ የመጡት የአክራሪነት አስተሳሰቦች ከመሰረታዊ የአገሪቱ ህገ መንግስት መርህዎች ጋር የሚጋጩ ፣ የህዝቡን ዲሞክራሲያዊ አንድነትና እኩልነት ፣ የመንግስትን ከሀይማኖት ነፃ ሆኖ ሁሉንም በእኩልነት የማገልገል ሀላፊነቱን የሚፃረሩ መሆናቸውን ገልጸው ሁሉም ሊታገላቸው ይገባል በማለት ተማጽነዋል።የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ኢህአዴግ ለገባበት የአመራር ችግር፣ እንዲሁም ፈተና ለገጠመው የልማት እቅድ ጉባኤው የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ የሚጠይቅ ነው።ኢሳት ኢህአዴግ የጀመራቸውን የልማት እቅዶች ለማስፈጸም የገንዘብ እጥረት ማጋጠሙን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ለህዳሴው ግድብና ለሌሎች ስራዎች በቂ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ አለማድረጉ ለገንዘብ እጥረት መፈጠሩ አንዱ ምክንያት ነው። ከኢትዮጵያ እየተዘረፈ የሚወጣው ገንዘብ በእየአመቱ መጨመርም ሌላው የችግሩ ምክንያት ነው።9ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ለመጪው አምስት አመታት ግንባሩን የሚመሩትን ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል። አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በሊቀመንበርነት ድርጅቱን ለመምራት ሰፊ እድል አላቸው።በጉባኤው ላይ በቅርቡ ከህወሀት ስራ አስፈጻሚነትና ማእከላዊ ኮሚቴ እንዲነሱ የተደረጉት አቶ አርከበ እቁባይና አምባሳደር ብርሀነ ገብረክርስቶስም በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል።ሼክ ሙሀመድ አላሙዲንን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ሰዎች በጉባኤው ላይ ተሳትፈዋል። የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ተወካይ፣ የኤርትራ ተቃዋሚዎችም ፣ የሱዳን ልኡካንም በበአሉ ላይ ተገኝተዋል።


No comments:

Post a Comment