መስከረም ፳፪(ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በጋምቤላ ክልል ከ300 ሺ ሄክታር ያላነሰ መሬት በነጻ በሚባል ዋጋ የተረከበው የህንዱ የእርሻ ኩባንያ ካራቱሬ ፣ በተሰጠው መሬት ላይ የልማት ስራ አለማከናወኑንና የባንክና ሌሎች እዳዎችን ለመክፈል አለመቻሉን ሰንደቅ ጋዜጣ ዘግቧል።በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጠባባቂ የቢዝነስ ዴቭሎፕመንት የስራ ሒደት ባለቤት የሆኑት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ለጋዜጣው እንዳስረዱት ፣ ካራቱሪ ከባንኩ እ.ኤ.አ በዲሴምበር 2011 ወደ 62 ሚሊየን ብር ብድር ቢወስድም መክፈል በሚገባው ጊዜ ሊከፍል አልቻለም። ብድሩንም ለማስታመም የተደረጉ ተጨማሪ ጥረቶች ባለመሳካታቸው ጉዳዩ ወደህግ ክፍል መመራቱን ባለስልጣኑ ተናግረዋል። ባንኩ በአሁኑ ወቅት ይህ ብድር የተበላሸ ወይንም መመለስ የማይችል ነው በሚል ጉዳዩን ይዞት ለማስመለስ ወደ ሕጋዊ እርምጃ መግባቱን” አክለዋል።
የኩባንያው የምርት መሳሪዎች ዋና ክፍል ኃላፊና የሠራተኞች ተወካይ የሆኑት አቶ አለምሰገድ አያሌው ” ኩባንያው 300ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት ከግብርና ሚኒስቴር መሬት ተረክቦ የነበረ ቢሆንም ባለፉት አምስት አመታት ከ800 ሄክታር በላይ ለማልማት” አለመቻሉን ገልጸዋል።
ግብርና ሚኒስቴር ከአንድ ዓመት በፊት 200ሺ ሄክታር መሬት የነጠቃቸው መሆኑን አቶ አለምሰገድ አስታውሰው፣ ይህንንም ማልማት ባለመቻላቸው በአሁኑ ወቅት በእጃቸው የሚገኘው መሬት 10ሺ ሄክታር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱ 150 ያህል ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች እንዳሉት ለጋዜጣው የገለጹት አቶ አለምሰገድ የሰራተኞች ደመወዝ ክፍያ እስከ 45 ቀናት እንደሚዘገይ፣ ለጡረታና ለግብር ከሰራተኛው የሚሰበሰበው ክፍያ በአግባቡ ለሚመለከተው አካል እንደማይገባ አክለዋል።
የኩባንያው አመራሮች በውጪ ምንዛሪ የሚያስገቡዋቸውን ዘርና ማዳበሪያ በአገር ውስጥ እንደሚሸጡ፣ ከቀረጥ ነጻ ያስገቡዋቸውን ማሽነሪዎች በማከራየትና ለሶስተኛ ወገን በመሸጥ ያልተገባ ጥቅም እንደሚያጋብሱም አጋልጠዋል።
የጋምቤላ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ጆን ሾል የካራቱሪ የስራ አፈጻጸም እጅግ ደካማ መሆኑን ለጋዜጣው ገልጸዋል። ኩባንያው በተጨማሪም ለወረዳ መክፈል ያለበትን የመሬት ግብር ጭምር እንዳልከፈለ የጠቆሙት አቶ ጆን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የተበደረውን ባለመክፈሉ ባንኩ በመያዥነት የያዛቸውን ንብረቶች ወደማስከበር ስራ ፊቱን ማዞሩን ገልጸዋል።
ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የኔዘርላንድን የቆዳ ስፋት የሚያክል መሬት ለውጭ ባለሀብቶች በነጻ በሚባል ዋጋ መቸብቸባቸው ለከፍተኛ ትችት ዳርጎአቸው እንደነበር ይታወቃል። ኦክላንድ ኢንስቲቲዩት የተባለው አለማቀፍ ተቋም በድሀ አገሮች የሚደረገውን የመሬት መቀራመት ለማስቆም ሰፊ አለማቀፍ ዘመቻ ጀምሯል። ሂውማን ራይትስ ወችን የመሳሰሉ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችም ዜጎች ከመሬታቸው በሀይል እየተፈናቀሉ፣ መሬታቸውን በነጻ በሚባል ዋጋ ለውጭ ባለሀብቶች የመስጠቱን አሰራር ሲቃወሙ ቆይተዋል።
No comments:
Post a Comment