Friday, October 4, 2013

ዘመነ ፍዳው እንዲያጥር ለምትፈልጉ ወገኖች ሁሉ! – ከይነጋል በላቸው

ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከተሾመ የወንበዴ መንግሥት ፍትህንና ወገንተኝነትን መጠበቅ ቂልነት መሆኑን በ22 ዓመታት ያልተረዳ ዜጋ፣ የማይሆን ጥያቄ ጠይቆ የማይሆን መልስ ቢሰጠው ሊገረም አይገባውም፡፡ ከነተረቱ “ራሷ ሄዳ ጣፊያ የከለከሏት ‹ምላስ ሰምበር ላኩልኝ› አለች” ይባላል፡፡ ወያኔ ከመነሻው ሀገርንና ዜጋን ድራሹን ለማጥፋት መነሳቱንና ይሄ ሁሉ ሕዝብ በዓለም ዙሪያ እንዲበተን ያስገደደው ራሱ ወያኔ መሆኑን እየተገነዘብን በራሱ አምሳል የተቀረጹ ድፍን ቅል ወያኔዎች የተሰገሰጉባቸው ነጋዴና የቢዝነስ ሥራ አቀላጣፊ ኤምባሲዎች መልካም ሥራ ይሠራሉ ብሎ መጠበቅ ከመነሻው ሞኝነት ነው – የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የወያኔን እንጂየኢትዮጵያን ጉዳይ አይፈጽሙም፤ አያስፈጽሙም፡፡ የወያኔ ልጆችን የጦርና የቀለም ትምህርት ይከታተላሉ – መተካካቱ ችግር እንዳይገጥመው፡፡
የወያኔ የሀብት ክምችት እምከን እንዳይገጥመው የዲፕሎማሲ ሥራ ይሠራሉ … ፡፡ እርግጥ ነው ጋዜጠኛ ግሩም በመንታ በመንታ እያነባ የገለጠልን ሀገራዊ መራር እውነት በኢትዮጵያዊነታችን ፀንተን የቆየንና የሀገራችን ሰቆቃ የሌት እንቅልፍና የቀን የኅሊና ዕረፍት የሚያሳጣን ወገኖችን ማሳዘኑ፣ ማስለቀሱም አይቀርም፡፡ ይህ ስቃያቸውና ስቃያችን እንደራሔል የራማ ጩኸት በፈጣሪ ዘንድ ተሰምቶልን የባርነታችንና የስደታችን የመከራ ዘመን እንዲያበቃ ሁላችንም ሁሉም ነገር ለማይሳነው አምላከ ኢትዮጵያ በርትተን መጸለይ ይገባናል፡፡ ሙስሊሙም ለአላህ ይጸልይ – መንገዱ ቢለያይ መድረሻው አንድ ነውና ወይም ቢንስ አንድ እንደሚሆን በብዙዎች ይገመታልና ሁላችን ለየምናምንበት በመጸለይ ይህ የክፋት ዘመን ያለ ብዙ “ወጪ” ወደታሪክ መዝገብ እንዲካተት እንትጋ፡፡
ኢትዮጵያውያን በስደት ያልገባንበት ሀገር እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ከሶሎሞን ደሴቶችና(Solomon Islands) ከሲሼልስ እስከ አላስካና ሳይቤሪያ በሁሉም የዓለም ግዛቶች እንደጨው ዘር ተበትነን አሣራችንን እየበላን እንገኛለን – የውርደት ውርደት ተዋርደን ከሰውነት በታች እስከመቆጠር በደረሰ አሰቃቂ ሁኔታ ላይም እንድንገኝ ታሪክ አስጠሊታ ብያኔውን አስተላልፎብን በሰውና በእንስሳነት ደረጃ መሀል እንገኛለን – ባገር ቤት ከምንገኘውም ብዙዎቻችን አንገታችንን ደፍተን በገዢው ጎጠኛ ቡድን እንደተዋረድን መኖራችን ግልጽ ነው – በነገራችን ላይ ዜጎች ለስደት የመከራ ሕይወት እየተጋለጡ የሚገኙት ‹ከሀገር ቤቱ የሚብስ የለም› ከሚል ተስፋ መቁረጥ እንጂ የግንዛቤ ችግር ኖሯቸው እንዳልሆነ ልጠቁም እፈልጋለሁ፤ ሁሉም ስደተኛ ባይባልም አብዛኛው በህገወጥ መንገድ በረሃዎችን አቋርጦ በደላላዎችና በድንበር አሻጋሪዎች በኩል ሲሰደድ ምን ሊደርስበት እንደሚችል ያውቃል – ሊገጥመው የሚችልን ጠባብ መልካም ዕድል ተጠቅሞ ሰው ለመሆን ሀገሩን ጥሎ እግሩ ባወጣው ይሰደዳል እንጂ ሌላው የሚዘገንን ነገር ሁሉ ይቅርና የሰው ልጅ ለመለዋወጫነት ሳይቀር እየዋለ እንደሆነ በስፋት በየሚዲያው ስለሚነገር ብዙው ሰው ይህን አያውቅም ማለት አንችልም፡፡ ግን ምን ይደረግ? “ከወያኔ የሚብስ የለም!” በሚል ለዚህ ሁሉ ችግር መዳረጋችን ትልቅ የታሪክ ቅጣት ነው፡፡ የምንከፍለው ዕዳ ስላለብን ሊሆን እንደሚችል በሚያመለክት መልኩ አበሳችን በዝቷል(ይህ ነገር አያልፍም ማለት አይደለም – በሚገባ ያልፋል – ልክ እንደዮዲት ጉዲትና እንደሌሎቹም የታሪክ ጉድፎቻችን ሁሉ)፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ነገር አሰቃዮቻችንና አሳዳጆቻችን በመከራችን የሚደሰቱ መሆናቸው ነው፡፡ እሱም ብቻ አይደለም፡፡ አሳዳጆቻችን ከሀገራችን ሲያስወጡን የሚቀበሉን ሌሎች ‹የሰው ዘሮች› የበደልናቸው ሳይታወቅ በስቃያችን የሚደሰቱ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ በበርካታ የውስጥና የውጭ ኃይሎች የተቀነባበረ የሚመስል የስቃይ ዘመን ማብቃቱ ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም ለአሁኑ ግን ልናምነው የማንችለው ትንግርት ሆኖብናል፡፡ ከያቅጣጫው የምንሰማው ሀገራዊ ጉዳይ የሚያስደንቅና ከማስለቀስ አልፎ እንደማሽላዋ በእያረሩ መሳቅ በደረቁ እሚያስፈግግ እየሆነ ነው፤ አንገት ተቀልቶ ጭንቅላት ብቻውን እየተሸከረከረ ይስቃል እንደሚባለው መከራ በሚበዛ ጊዜ በትንሹም በትልቁም ሆድ ሲብሰን ክልብስ እያለ ጉንጮቻችንን የሚያርሰው ዕንባም ባቅሙ ይኮራብንና በምፀት እንስቃለን፡፡ የኛም ነገር ሁሉም ነገራችን ዕንቆቅልሽ ሆኖብን እንደዚያው ሆነናል፡፡ … አሁን ላይ ሆነን ግን ወያኔን መውቀስና መሳደብ ኋላቀርነት ማለትም ጊዜ ያለፈበት ይመስለኛል፡፡ የራስን ሥራ ሳይሠሩ ተፈጥሮው ወንጀልና ግፍንንና በደል መፈጸም ብቻ የሆነን አንድ አካል መልካም እንዲሆን ዘላለሙን መመኘት ከንቱነት ነው፡፡ ወያኔ መልካም የመሆን ተፈጥሮ ቢኖረው ኖሮ ባሳለፋቸው 40 ዓመታት ገደማ ባሕርይውን በለወጠና ኢትዮጵያን ከተደጋጋሚ ውድመት ሊታደጋት በተቻለው ነበር፡፡ አሁን አሁን ሳስበው ብዙዎቻችን እየጣርን ያለነው ድንጋይ ዳቦ እንዲሆን ወይም የእባብ ዕንቁላል እርግብ ሆኖ እንዲፈለፈል ነው፡፡ የማይሳካ ነገር ስንመኝ ጥቂት የማይባሉ ወርቃማ ዐሠርት ዓመታት ላይመለሱ ነጎዱ፤ በዚህ ሂደት ግን መከራችንና ስቃያችን ጠርዝ እየለቀቀ በዓለም ፊት ውርደታችን እየከፋ መጣ፡፡ እንደሰማሁት ሶማሊያውያን ሳይቀሩ በ‹መንግሥታቸው‹ና በራሳቸው መብትን የማስከበር ቆራጥነታቸው ሲከበሩ እኛ ብቻ በማንም እንደተዋረድን፣ እንደጠፍ አህያም ማንም የፈለገውን እንደጫነን አለን – ለዚህ ዘግናኝ ሀገራዊና ማኅበራዊ ሕይወት የዳረገንም በዋናነት ብዙዎቻችን በጥቅምና በዓላማ መለያየታችን እንዲሁም በሌሎች እየደረሰ የምናየው ችግር በእኛ ላይ ላለመምጣቱ እርግጠኞች የሆንን ያህል የወገኖቻችንን ችግር እንደራሳችን አድርጎ ያለማየት ወያኔያዊ ልክፍት ያሳደረብን አሉታዊ ተጽዕኖ ነው፡፡ ከዚህ በላይ አሣፋሪና አስደንጋጭ ዘመን ከአሁን በፊት የደረሰብን ለወደፊቱም የሚደርስብን አይመስለኝም፡፡ ገና ለገና በህጋዊ መንገድ አልወጣችሁም ተብሎ ይህን ያህል የወንጀለኞች አባሪና ተባባሪ የሆነ የኤምባሲ ሠራተኛ ሊኖረን የቻለው እቤት ያለው ‹መንግሥት› ፀረ-ኢትዮጵያ በመሆኑ እንጂ እነዚህ የኤምባሲ ሠራተኞች ቅንጣት ታህል የወገንተኝነት ስሜት ቢኖራቸው ኖሮ ችግራችን በአሣፋሪነቱ ያን ያህል ጎልቶ ሊወጣ የሚችል አልነበረም – በታሪክም በስመጥርነትም መቼም ከሱዳንና ከጅቡቲ አንሰን አይመስለኝም፡፡ ድሃ መንግሥታት ዜጎቻቸው ይሰደዳሉ፤ ሠርተውም ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለሀገራቸው ገቢን ያስገኛሉ – ህንድና ቻይና ሌሎችም የኤዥያ አህጉር ሀገሮች በዚህ ረገድ በጣም ይታወቃሉ፡፡ የኛ ግን መንግሥት ተብዬውና ተሰዳጁ ወገን ዐይጥና ድመት ወይም በሬና አራጁ በመሆናቸው የመንግሥት ተጠሪዎች ለዜጎች ስቃይ መበርታት ደፋ ቀና ይላሉ እንጂ የዜግነት ይቅርና የሰብኣዊነት ስሜት ፍጹሙን የላቸውም – ይህ ልዩነት የተፈጠረው የሌሎች ሀገሮች ባለሥልጣናት ዜጎቻቸውን – በህግም ሆነ አለህግ ቢሰደዱ – እንደዜጋ ሲቀበሉ ‹የኞቹ› ታሪካዊ ተልዕኳቸውን አይረሱምና ከሕዝቡ ጋርም ውኃና ዘይት መሆናቸውን ከጥንት ከጧቱ ይገነዘባሉና ማንም ተቀቀለ ወይ ተጠበሰ ምናልባት እንደባሕርይ አባታቸው እንደአቶ መለስ ዴቭላዊ ከመደሰት በስተቀር ደንታቸው አይደለም – መሬት የሚንከባለልን ኳስ ለማንሳት ያጎነበሰን የ12 ዓመት ሕጻን በተቃዋሚነት ፈርጆ ግንባሩን በጥይት ከሚበረቁስ አረመኔ ቅኚ ገዢ የወያኔ መንግሥት የተላኩና የጠባብ ብሔርተኝነት ደዌ የሚያሰቃያቸው ዕብድ ውሾች ለወገን ይቆረቆራሉ፣ ለሀገር ስምና ዝናም ያስባሉ ብሎ መጠበቅ፣ ምናልባትም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁሮች በጥቁሮች ላይ ያወጁትን ይህን በሀገራችን ግዘፍ ነስቶ የምናየውን ልዩ አፓርታይድ የሚያራምዱ ደናቁርት ወገኖችን የተለዬ ተፈጥሮ መዘንጋት ነው፡፡
‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ደግሞ ባለ ዕዳ አይቀበለውም›ና የነሱን ልበ-ደንዳናነት የተመለከተ የውጭው በተለይም በአጋንንታዊ መንፈስ የተነጠቀው ገንዘብ አምላኪ ዜጋ የነሱን መስመር ተከትሎ ያሰቃየናል፤ ያንገላታናል – እነዚህ ወገኖች ለተገፉና በበደል ጅራፍ ተገርፈው ከሀገራቸው ለሚሰደዱ ረዳት መሆን ሲገባቸው ከእንስሳነት ባሕርይም ወርደው የለዬላቸው አውሬዎች መሆናቸው ይበልጥ ያሳምማል – ቅጣት በየፈርጁ ሆነብን – “አንበሣን ፈርቼ ዛፍ ላይ ብወጣ ነብር ጠበቀኝ” እንዲሉ ነው – ግዴለም – ሊነጋጋ ሲል ይጨላልማልና ሁሉም ሸምቀቆዎች እንዲህ እንዳሁኑ መጠባበቃቸው ለበጎ ሳይሆን አይቀርም ብለን ተስፋችንን በፈጣሪ እናድርግ፡፡
ግሩም ተ/ሃይማኖት እንዳለው በስስ የአካል ክፍሎቻችን የጋለ ብረት እየሰደደ በስቃያችን እስከመደሰት የደረሰ የሰው ዘር መኖሩን እየሰማን ነው፡፡ በመንፈሳዊነት ዐይን ስናየው ይህ ሁሉ ከንቱነትና ጭካኔ የክፉ መንፈስ አምላኪነትንና ተከታይነትንም የማሳያ መንገድ ነው – በኛ መግነኑ ሆድ ያስብሳል እንጂ የዚህ ዓይነቱን ነገር መስፋፋት ከዱሮውም የምናውቀውና የምንጠብቀውም ነበር (ማቴ. ፳፬፣ የጳውሎስ መልእክት ወደ ሮሜ ሰዎች ፩ – ከቁጥር ፲፰ ጀምሮ)፡፡ ክርስቶስ “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ የጸለየላቸው ዓይነቶቹ እነዚህ የውጭና የሀገር ውስጥ አሳዳጆቻችንና አሰቃዮቻችን የመጨረሻውን ዋጋቸውን የሚያገኙበት ጊዜ በብርሃን ፍጥነት እየተወረወረ መምጣቱን ብንረዳም እስከዚያው ግን በተለይ በውጭ የሚገኙ የተቃዋሚ ኃይላትና ታዋቂ ግለሰቦች ሊያደርጉት የሚገባቸው ነገር መኖሩን መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ ኅሊናየ ጠቁም ያለኝን ስጠቁም ጥቆማየን ለሚመከተው በማድረስ ረገድ ሚዲያዎች የተለመደ ትብብራቸውን እንደማይነፍጉኝ በማመን ምሥጋናየን ከወዲሁ አቀርባለሁ – ለነገሩ ማመስገን አለብኝ እንዴ? አዎ፣ ትግራይኦንላየን ይህችን ጦማር ካተመልኝ ማመስገን ሳይኖርብኝ አይቀርም – because it is a matter of being a reborn Ethiopian; nevertheless, um, one must be naive to expect such a U-turn, a radical move now; perhaps it is too early, or perhaps it will never happen due to ethnically oriented sociopathic infliction upon the structure of their seemingly dysfunctional brain. … ይህ ድረገፅና አምሳያዎቹ ‹ዕድገታቸውን ጨርሰው› ከመክሰማቸው በፊት ነፍስ ማወቅ ከጀመሩ በርግጥም እሰዬው ነው ሊወደሱም ይገባቸዋል፡፡… (አይ ይሄ ሆድ! ስንቱን አሳየን! የዋናዎቹስ ይሁን ግዴለም፤ እነገነት ዘውዴንና ክፍሌ ወዳጆን የመሰሉ አጋሰስ የተጋቦት ወያኔዎችን የጥፋት ተባባሪነት ታሪክ ስንታዘብ ስንትና ስንት ጉድ እኮ ነው እምናይ? ብርሃኑ ዘሪሁን በአንደኛው ገጸ ባሕርይው አማካይነት “ሆዳችን እንኳንስ ከኋላችን አልሆነ፤ ገፍቶ ገደል ይከተን ነበር!” ያለው እንዴቱን ያህል ትክክል ነው!? አሁን ሽመልስ ከማል አያሳዝናችሁም? – ለወያኔ ዕድሜ መርዘም ሲል ሆዱን ተመርኩዞ የሀሰት ምሥክርነቱንና ማስተባበያውን ለመስጠት እንዲህ ሲቅመደመድ ለታዘበው አንጀትን ይበላል – አይበላም? ቅን አሳቢ እንሁን – ይበላል፡፡ ከወያኔዎች በልጠው ወያኔን የሆኑ ሁሉ ስለሆዳቸውና ለሆዳቸው ሲሉ እንዲህ ሲሆኑ ስናይ ከምናዝንባቸው ይልቅ እናዝንላቸዋለን – ነገን የማየት ዕድላቸው በአንድ በኩልና በትንሹ በማፈርና ባለማፈር ተፈጥሯዊ ባሕርያቸው መካከል የተሸጎጠ በመሆኑ ምናልባት በጊዜ ሂደት አንጎላቸው በትክክል መሥራቱን የሚጀምር ከሆነ እንደግርማ አይገብሩ ወይም እንደ ንጉሤ አስገልጥ በዝጉብኞች ውስጥ በብርጭቆ ግርዶሽ ተደብቀው በሥነ ልቦናዊ ቀውስ እየተንገላቱ ቀባሪ እስከሚያጡ ድረስ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን አሰቃይተው በሞት እንዳይለዩን ከመጨነቅ ነው እንዲህ የምላችሁ – ቀዳሚውን አንድ ቢያውቅም፡፡ በሌላም ወገን አሁን በሚሠሩት ጠያፍ ነገር በህግም ሆነ በግንፍልተኝነት(ይህኛው ማንም ተበዳይ ነኝ የሚል ወገን ሊያስበው የማይገባ መጥፎ ነገር ነው!) ምን ሊደርስባቸው ከመገመት ውጪ ብዙዎቻችን የምናውቀው ነገር ባለመኖሩ ይህም ከአሁኑ እንድንንሰፈሰፍላቸው ያስገድደናል፡፡) በዐረብ ሀገራት የሚሰደዱ ወገኖቻችን የሚገኙበት አስቸጋሪ ሁኔታ ግልጽ ነው፡፡ ጊዜም የማይሰጠው ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ብናደርግ ጥሩ ነው፡፡
በውጪ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ኅብረት ፈጥረው አንድ የዲፕሎማሲ ቡድን ይመሥርቱ፡፡ ይህ ቡድን በተለይ የዜጎቻችን ችግር አይሎ በሚታዩባቸው የዐረቡ ዓለም ጠንካራና ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ያላቸውን ተወካዮችን ይላክ፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገሪቱን ጥቅምና የዜጎችን መብት የማያስጠብቅ መሆኑን፣ ይልቁንም በተቃራኒው የሚሠራ ፀረ-ሰው መንግሥት መሆኑንና የሀገሪቱን ዘላቂና ቋሚ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅሞች ማስከበር የሚቻለው በሕዝብ የሚመረጥ መንግሥት ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በማስረዳት የእነዚህ ሀገራት መንግሥታትና ዜጎች በዚህ ክፉኛ እየተገፋ ባለ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ ግፍና በደል እንዳይሠራ የተቻላቸውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከሃይማኖትም ከሌሎች ማኅበራዊና ታሪካዊ ዳራዎችም በመነሳት የግንዛቤ ማሰጨበጫ ሥራ ይሠራ፡፡ የሀገሪቱ ሕዝብ እንደ አሁኑ ባለቤት እንደሌለው ሆኖ ለዘላለም እንደማይኖርና ባለቤት በሚኖረው ጊዜ መቀያየምን የሚፈጥር ጥቁር የታሪክ ነጥብን ትተው እንዳይነጉዱ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች በጥንቃቄ እንዲያስቡበት በግልጽ ይነገራቸው፡፡ ሰዎች በፈጣሪ ፊት እኩል መሆናቸውንም እንዲያውቁት ጥረት ይደረግ፡፡ የሰው ግርድና ምርት እንደሌለው እንዲረዱ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ይከናወን፡፡ በዚህ ረገድ ታዋቂ ኢትዮጵያውያንም የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ያድርጉ፡፡ ዝምታችን እያስጨረሰን ነውና በየፊናችን እየጮኸን ለወገኖቻችን ያለንን ፈጥኖ ደራሽነትና አለኝታነት እንግለጥ፡፡ ይህን ብናደርግ በታሪክም በፈጣሪም ዘንድ እንከበራለን፡፡ ባናደርግ እንወቀስበታለን፡፡
በትጥቅ ትግል ላይ ነን የሚሉ አገር በቀል ድርጅቶች በዚህ ዙሪያ ትልቅ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤ ይቻላቸዋልም፡፡ ሁላችንም እንደምንገነዘበው ሀገር ማለት ተራራና ወንዝ ብቻ ማለት አይደለም፤ ሀገር ማለት ዛፍና ቅጠል ማለት ብቻም አይደለም፤ ሀገር ማለት ሁሉንም ያጠቃለለ ቢሆንም፣ ሕዝብ ግን ዋናውን ደረጃ የያዘ የሃገር ማንነት መገለጫ አዎንታዊ ክፍል ነው፡፡ ለሕዝብ ቆሜያለሁ የሚል አርበኛ ደግሞ በቅድሚያ መገንዘብ የሚኖርበት ከጠላት ጋር የሚዋገበት የጦር አውድማ የጦር መጠለያ ጣቢያ ሲሆን፣ ከእባብ ዋሻ የጦር ተገኑን አስፍሮ እባብን እዋጋለሁ የሚል አርበኛ ካለ የፀረ እባብ ጭንብሉን አጥልቆ ጠላትን በአንድነት ቢዋጋና ለአገር ነጻነት መስዋትነትን ቢከፍል ታሪክ ሥራውን ሲያስበው ይኖራል። ግን ተከፋፍሎ ለመጓዝ ከቆረጠ ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ይልቅ የራሱን – ምናልባትም ከሥልጣን ጋር የተያያዘ – ጥቅምና ፍላጎት አስቀድሟል ማለት ነውና ከሕዝብ ልብ እየወጣ ይሄዳል – ያም ዱሮውን ገብቶ ከሆነ ነው፡፡ ሕዝብ በማንኛውም ረገድ እንጦርጦስ ወርዶ፣ ሀገር የእፉኝቶች መፈንጪያ ሆና፣ ዘረኝነት ድሩን አድርቶ ጥቂቶች አለሀፍረትና አለአንዳች ይሉኝታ በብዙዎች ላይ የሚምነሸነሹበት አስከፊ ሥርዓት ተፈጥሮ፣ የኑሮ ውድነቱ አብዛኛውን ሸማች ከገበያ አውጥቶትና ለከፋ ድህነት ዳርጎት፣ በተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ሥውርና ግልጽ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ታውጆ፣ የሙያ ማኅበራትና የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ድራሻቸው እንዲጠፋና በምትካቸው የወያኔ ሥሪት የሆኑ ኮንዶማዊ ድርጅቶች አገር ምድሩን በሸፍጥና በተንኮል ሥራ አጥለቅልቀው በማይረቡ ጥቅማ ጥቅሞች በትምህርት ያልገፉ ድሃ ዜጎችን እያማለሉ፣ ቄስ መስቀሉን ኢማሙ ክታቡን ኅሊናን ለሚያሳውር የዘረኝነት ዓላማና ለሆዳቸው ሲሉ ሸጠው ለውጠው፣ አማኑኤል ሆስፒታል በፖለቲካውና በኑሮ ብስጭት በሚያብዱ ዜጎች ከአፍ እስከገደፉ ጢም ብሎ እየሞላና በድንኳን እየተስተናገዱ፣ የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾችና ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ዘብጥያ እየወረዱ ወይም እየተገረፉና እየተገደሉ ሀገር ማቅ ለብሳ፣ ከሞላ ጎደል ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች በሞራልም በሃይማኖትም ሙልጭ ወጥተው ሆዳምነትና ስግብግብነት እየተንሰራፋ እንዲሄድ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ሀገር ወደባድማነት እየተለወጠች በምትገኝበት አደገኛ ሁኔታ በጎጥና በዘር ተደራጅቶ ይህን ሥር የሰደደ ጠላት ራሱ በመጣበት መንገድ አሸንፈዋለሁ ብሎ መነሣት የሚያዋጣ አይደለም ብቻ ሣይሆን ይህን ድጥ የበዛበት መንገድ መሞከሩ ራሱ የሕዝብን ችግር ከማባባስ ባሻገር የፈየደው ነገር እንደሌለ ከልምድ መረዳት ዐዋቂነት ነው – አሁን ዘግይቶም ቢሆን፡፡ አልበርት አነስታይን እንዳለው አንድን ችግር ለመፍታት ችግሩ በተፈጠረበት የአስተሳሰብ ጎዳና መጓዝ የሚያዛልቅ አይደለም፤ የተሻለ አስተሳሰብንና የላቀ አስተዋይነትን ይዞ መገኘት ይጠይቃል፡፡ መጽሐፉም ይላል፡- ‹ብዔል ዘቡል ብዔል ዘቡልን አያስወጣም›፡፡ ስለዚህም በትጥቅ ትግል የተሰለፉም ይሁኑ ሌሎች ተቃዋሚዎች በአንድነት ሆነው በመታገል የዚህን ሕዝብ ሰቆቃ ማስወገድ ይገባቸዋል – አለበለዚያ እነሱም ከወያኔ ባልተናነሰ በችግራችን መራዘምና እየገዘፈ መሄድ በኃላፊነት የሚጠየቁበት ጊዜ ይመጣል፤ ይህን አጠቃላይ እውነት ሁሉም ወገን ሊገነዘበው ይገባል – እየመሰለን እንጂ ከታሪክ ፍርድ ማምለጫ የማሳበሪያ መንገድ በጭራሽ የለም፡፡ ለአሁኑ አጣዳፊ ችግር ደግሞ በአንዳንድ ሀገራት – ለምሳሌ በየመን – የጋራ ግንባራቸውን ተወካዮች በመመደብ ለወገናቸው ያላቸውን ፍቅርና ቅን አሳቢነት ማሳየት አለባቸው፤ የተበተኑ ወገኖቻችንም አለኝታ እንዳላቸውና እንደወያኔው ያለ የሚሸጣቸው የቀን ጅብ ሣይሆን ተቆርቋሪ ወገን እንዳላቸው ማሳወቅ ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ነገር ለነገ የሚያሳድሩት ጉዳይ ሳይሆን የዲፕሎማሲው ሥራ ዛሬውኑ መጀመርና ልዩ ትኩረት አግኝቶ ተግባራዊ መሆን ይገባዋል – እርግጥ ነው – ድርጊት የንግግርን ያህል ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ግን ይሞከር – እንዲሁ በየስብሰባውና በየቃለ መጠይቁ ‹ሕዝብ፣ ሕዝብ› ወይም ‹ኢትዮጰያ፣ ኢትዮጵያ› ማለት ብቻውን ጉንጭን ማልፋት ነው፤ የወገን ፍቅር ይኑረን – ያንንም በተግባርና ለማስመሰል ሣይሆን ከእውነት እናሳይ፤ አናቱን የሚያሳክከውን እግሩን ብናክለት ኅሊናችንም ታካኪውም ይታዘቡናልና በአፋጣኝ እንለወጥ፤ በሞተ ሕዝብ ላይ ለመንገሥ ከምንራወጥ የሚሞተውን ሕዝብ ጠላቶቻችን ናቸው ብለን ከፈረጅናቸው ወገኖች ጋርም ቢሆን “ተመሳጥረን” እናድነው፤ ከወገን ጋር ተባብሮና ተመሳጥሮ ሕዝብን ከመግደል ይልቅ ከጠላት ጋር ተባብሮ ሕዝብን ማዳን በፈጣሪም በታሪክም ታላቅ ዋጋ አለውና አሁን ለአቃቂርና ለወሬ ስለቃ ጊዜ እንዲኖረን ፈቃዳችን አይሁን፡፡ ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ደግሞ ሁሉም ወገን መተባበር አለበት፡፡ ወገን እየተሰቃዬ፣ እየተሰደደ፣ አካሉ እየተቆራረጠና ለመለዋወጫነት እየተሸጠ … ባለበት የሚዘገንን ሁኔታ በድሎትና በቅንጦት መኖር፣ ገንዘብንም በአልባሌ ሥፍራና ለአልባሌ ተግባር ማዋል በእግዚአብሔር ዘንድ በኃጢኣተኝነት ባይሆንም እንኳን በነውረኝነት ሳያስፈርጅ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ እናም ከዚህ አንጻር ብዙዎቻችን ብዙ መሥራት፣ ራሳችንንም በጥሞናና በተመስጦ መፈተሸ ይጠበቅብናል፡፡ በተለይም እዬዬም ሲደላ ነውና ሕዝባችን ላይ የተሰኩትን እሾሆች ለመንቀል ምንም ጥረት ሳናደርግና ፈቃደኝነት ሳይኖረን እርስ በርስ በነገር ጦር ብንጠዛጠዝ ታሪክ ምሮ አይምረንም፡፡
በመሠረቱ ሕዝብ ሲባል ያ ደንቆሮ የወያኔው የየመን ኤምባሲ ሠራተኛ እንደተናገረው በገረድና በአሽከር ወይም በባለሥልጣንና በከበርቴ የሚመደብ ሳይሆን ውሻና ድመትም እንኳን ቢሆኑ በኢትዮጵያ አፈር፣ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የተፈጠረ ሁሉ በየፈርጁ ክብርና ሞገስ ያለው ፍጡር መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ክርስቶስ አለ፡- እኔ የመጣሁት ለጻድቃን አይደለም – ለኃጥኣን እንጂ፡፡ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ኃላፊ ዜጎችን ባለውና በሌለው፣ በተማረና ባልተማረ፣ በቀላና በጠቆረ፣ ባጠረና በረዘመ፣ … እንዲሁም በዚህና በዚያ ሃይማኖትና ፆታ ተመሥርቶ እያዳላ የሚፈርድ ወይ የሚያስተዳድር ከሆነ ያ ሰው ‹ሰው ነኝ› ባይል ይሻለዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር በፈጣሪም ህግ በዓለምም ህግ የተወገዘ ኃጢኣትና ወንጀልም ነው፡፡ ዜጋህን እንዴት ‹ለገረድ አልመጣንም› ትላለህ? ምን ዓይነት ልበድፍንነት ነው? እንዲህ ዓይነት ደደብ ዜጎች በኃላፊነት ብቻ ሣይሆን በተራ ዜጋነት በሚገኙባት ሀገር መፈጠር ራሱ አያስጨንቅም ትላላችሁ? ጋዜጠኛ ግሩም ይህን ጽሑፍ ካነበብክ እባክህን የዚህን ሰውዬ ስምና መለያዎች መዝግበህ ያዝ፤ የሕዝብ ጊዜ ሲመጣ ለፍርድ አቅርበን ለምንና ለነማን ወደየመን እንደተላከ እናስጠይቃለን፡፡ ይህን የምለው የበቀለኝነት ስሜት ተጠናውቶኝ እንዳይመስላችሁ – በፍጹም – ግን ሁላችንም በምንሠራው ሥራ መለካትና መዳኘትም ስለሚኖርብን ነው – ከሞትን በኋላም ቢሆን፡፡ ለምሳሌ በጉጉት ከምንጠብቀው ነጻነት በኋላ አቶ መለስን ለመክሰስ ከተዘጋጁ ሰዎች መካከል እኔ አንዱ ነኝ፡፡ – ጣሊያን ሀገር እንዲህ ሆነ አሉ፡- አንድ ሕጻን እየተጫወተ ሳለ ለውሃ በተቆፈረ 36 ሜትር ጠባብ ጉድጓድ ውስጥ ይገባል፡፡ የአካባቢው ሰዎችና ባለሥልጣናት ያን እምቦቀቅላ እንዴት እንደሚያወጡት እየተጨነቁ ሳለ የሀገሪቱ መሪ (ፕሬዝደንት ወይ ጠ/ሚ) ከተፍ ይላል፡፡ ለካንስ ወሬውን በዚያው ቅፅበት በተባራሪ ሰምቶ ኖሯል፡፡ ይህ የሀገር መሪ እንደሕዝቡ እየተጨነቀ፣ እያለቀሰና እያጽናና ሸሚዙን ሰብስቦ በላብ እየተጠመቀ አብሮ ሰው የሚሠራውን ሥራ መሥራቱን ይቀጥላል – ከልቡ፡፡… የዜግነት ግዴታ፣ የመሪነት ግዴታ፣ የሰብኣዊነት ግዴታ፣ የአለኝታነት መንፈስ … ማለት እንዲህ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆን ኖሮስ? ‹እኔ ለአንድ ሕፃን አልተሾምኩም!› ሊባል ነው? ወይንስ እንደፔፕሲ ማስታወቂያ ‹ተጨማሪ ይጠይቁ› ይሉን ይሆን? የምንገርም ሕዝብ ከሚገርሙ መሪዎች ጋር! አይደል? መበታተን ይነሰን ታዲያ? ለወገኑ የማያስብና ከፋፋይ ዘረኛ እንዴት ባለሥልጣን ሊሆን ይችላል?
እግዚአብሔር ሆይ ሰው ሹምልን – ሰው አማረን፤ ሰው ናፈቀን፡፡ እንደሰው የሚያስቡና ጠረናቸው ሰው ሰው የሚል ሰዎች እንዲመሩን ወደሥልጣን አምጣልን፡፡ ጅቦችና ዓሣማዎችን ከላያችን አንስተህ፣ ዘረኞችንና ማይም ሆዳሞችን ከጫንቃችን አውርደህ፣ ሀገራዊና ወገናዊ ስሜት የሌላቸውን በጮማና ዊስኪ የደነዘዙና የደነበሹ ባለሥልጣኖችን በቃችሁ ብለህ ለወገንና ለሀገር የሚቆረቆሩ፣ ሕዝባችን ተራበ ተራቆተ ብለው ሌት ከቀን የሚጨነቁ እውነተኛ የሀገር መሪዎችን ስጠን፡፡ከሚገባን በላይ ተቀጥተናልና አሁንስ ምሕረትህን ላክልን፤ እንደቸርነትህ እንጂ እንደሥራችን ግን አይሁንብን፡፡ የጥንቱን መተሳሰብና ፈሪሃ እግዚአብሔርንም መልስልን፡፡ አሜን፡፡
በየኤምባሲዎች የምትገኙ የወያኔ ባለሥልጣናት ደግሞ እንዲህ አድርጉ፤ በግልጽ ለወገን መቆርቆራችሁ ከተደረሰበት ከሥራ ልትታገዱ ወይም የከፋ የቂም በቀል እርምጃም ሊወስድባችሁም ይችላል – በመበቀል ወያኔን የሚስተካከል የለምና፡፡ ስለዚህ ሥቃይ ላይ የሚገኙ ወገኖቻችሁን በድብቅና በእጅ አዙር ለመርዳት ሞክሩ፡፡ በዚህ የተቀደሰ ተግባራችሁ ቢያንስ ትውልዳችሁን – የራሳችሁን ልጆችና የልጅ ልጆች – ከቅጣት ትታደጋላችሁ፡፡ እንደምታውቁት እነመለስ ልጅ አልወጣላቸውም፡፡ ይህም የሆነው የእርጉማን ልጆች በመሆናቸው እንጂ የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ጥራት ስለጎደላቸው እንዳይመስላችሁ – ራሳቸው እነመለስም ቢሆኑ አብዛኞቹ የባንዳና የጠላት አሽከር ልጆች በመሆናቸውና በዚያም ምክንያት የሀገራዊና ሕዝባዊ እርግማን ተረካቢዎች በመሆናቸው ያገኙትን ዕድል ለነሱና ለሀገራቸው በሚጠቅም መልኩ አልተጠቀሙበትም – ዕድለቢስነታቸው ያሳዝናል፤ ወደውና ፈቅደው እንዳልሆነ ግን ዕንወቅላቸው፡፡ እግዚአብሔር አንድን ሕዝብ ሊቀጣ ሲፈልግ ጨካኝ ንጉሥ እንደሚሾም ቀድሞውን በመጽሐፍም የተጠቆመ ነውና በነዚህ የእፉኝት ልጆች ሰበብ የእኛም የብዙኃኑ የቀደመ ኃጢኣት ታጠበ፤ የቀረን የንስሓው ጊዜ ነውና ከየተዘፈቅንበት … አረንቋ እየወጣን ኅሊናችንን በማጽዳት ወደነጻነት አምባ ለመውጣት እንሞክር – እግዚአብሔር እንደማይረሳን በፍጹም ልባችን እንመን – አንድ እርምጃ ወደርሱ እንቅረብና እርሱ ወደኛ ዐሠርና ሃያ እርምጃዎችን እንደማይመጣ እንታዘበው – ‹በኔ ይሁንባችሁ› አልላችሁም – እኔም ምንም አይደለሁምና – ለትህትና አይደለም – ባይሆን በወደድኩ – ምክንያቱም በሀገራችን አንድ ሎጥ እንኳን ቢገኝ ኖሮ ምን ያህል የእግዚአብሔር ፀጋ እንደሚበዛልን እረዳለሁና – ሁላችን እንደጠፋን የማምን ነገር ግን ወደርሱ ብንመለስ ትንሣኤያችን በቅጽበት ውስጥ እውን ሊሆን እንደሚችል የምገነዘብ ኃጢኣተኛ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ አለበለዚያ … ምዕመናን … ነገር አለ! … ፈጣሪ ከተጨማሪ የደም ባሕር ይሠውረን፡፡ በነገራችን ላይ እርግማን ትውልድን እንደሚመትር ወይ እንደሚያመክን ብዙ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ማስረዳት ይቻላል፡፡ የበረከትን፣ የስብሃትን፣ የሰዓረን፣ የተፈራን፣ የ‹ሐጎስ›ን፣ የ‹አብረኸት›ን ልጆች ብታዩዋቸው ትገረማላችሁ፤ ታዝኑማላችሁ፡፡ ለካንስ እርግማን ያለዘር የማስቀረት ኃይል አለው? ብላችሁ ትደመማላችሁ፡፡ የወያኔ ባሪያዎች ግን ባለቻችሁ አጭር ጊዜ ጥሩ ሥራ በመሥራት ከዚህ ሕዝባዊና ሀገራዊ እርግማን ነጻ ልትወጡ ትችላላችሁ፡፡ መልካም ዕድል በደጃችሁ አለች፡፡
ለድረ ገፆች የሚላኩትን አንገብጋቢ ጉዳዮች የማያወጡና በሌላ በኩል ግን ሌላ አዘናጊ ፍሬ ፈርስኪ የሚለጥፉ ዘበናይ ድረገፆች መኖራቸውን በቁጭት ተጠቁሟል፤ ይህን እኔም በሚገባ አውቃለሁ – ሊያውም በአግራሞት፡፡ አሁን በዚህ በጭንቅ ቀን በነዚህ ዓላማቸው የተለያዬ – ምናልባትም የወያኔ ተቀጥላ ሊሆኑ በሚችሉ የሚዲያ ተቋማት ላይ መዝመቱ ጊዜንና ጉልበትን በከንቱ ማባከን ስለሚሆን እንጂ በብዙዎቹ ላይ ብዙ ነገር መናገር በተቻለ ነበር፡፡ ለጊዜው ግን ቆም ብለው ቀልብ እንዲገዙ እንመክራቸዋለን – ለቀለብ ብለው ቀልብን አጥተዋልና፡፡ ሰው በወደደው እንደሚቆርብ እነዚህ ጤናማነታቸው የሚያጠራጥር ሚዲያዎችም የፈለጉትን የመሆን መብት አላቸው፡፡ ቢችሉ ግን የሀገሪቱንና የሕዝቡን ችግር ቢያሳውቁ ለነሱም የወደፊት ግለ-ታሪክ ይበጃል፤ ከተወቃሽነት ከመዳን አልፈው ትውልዳቸው በነሱ የአሁን ቅሌት አንገቱን ከመድፋት ይድናል፤ ትውልድን አንገት ማስደፋት በነመለስ ይብቃ፡፡ አለበለዚያ ሕዝቡ ያላሳከከውን የሚያኩለት ከሆነና የጠላቱ ተባባሪዎች እንደሆኑ መቀጠል ከፈለጉ የሚያግዳቸው የለምና በጌታቸው አነጋገር ‹መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው›(ልብ በሉ – የመለስ ጉልበትና የዕብሪት ምንጭ ከምንም ያላዳነውና ቡችሎቹንምከምንም የማያድናቸው ሰው ሠራሽ ጠመንጃ ነው – የኛ ግን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለምሥኪኖች ሊዘረጋላቸው ያዘጋጀው የመጨረሻው ዱላ መለኮታዊ ወገናዊነት ነው)፤ መታወቅ ያለበት አንድ ዋና ነገር በሚዲያም ሆነ በሌላ መንገድ ከወያኔ ጋር የሚተባበሩና የጭቁኖችን የነጻነት ቀን በማዘግየት ረገድ አሉታዊ ሚና የሚጫወቱ ወገኖችም ቢሆኑ ቢያንስ ቢያንስ እየቆዬ ከሚሸነቁጣቸው የኅሊና ፍርድ ሊያመልጡ የማይችሉ መሆናቸው ነው – ይህን ይረዱ፡- ዛሬ ነጭን ጥቁር፣ ጥቁርን ነጭ ማለት ይቻላል – ቀላልም ነው፤ ነገር ግን እንዲህ የማይባልበትም ቀን መምጣቱን ሁሉም ሊገነዘብና ራሱን በማስተካከያው ቀን ሊያስተካክል ይጠበቅበታል – ያም ቀን ዛሬና አሁን ነው፡፡ በኋላ ማፈር አለ፤ በኋላ መደበቅ አለ፤ በኋላ መፍራትም አለ፤ በኋላ ለ‹በኋላ› ለራሱ የመትረፍ ዕድልን አለማግኘትም አለ – የመመለሻ ጊዜዎች ገደብ እንዳላቸው አለማወቅ ግብዝነት ነው – The door of repentance and atonement is not indefinitely open to any one in any given circumstance. There are times during which golden opportunities are denied if once missed. Remember what Jesus said with regard to Judas’ betrayal after he sold Him for thirty pieces of silver. ቅድስት ኢትዮጵያን በሚመከት የመመለሻው ወቅት አሁንና አሁን ብቻ ይመስለኛል – አይምሰልህ የምትል በሚያዋጣህ የጥፋት ጎዳና መትመምህን ቀጥል – የጌታህን ቃል በድጋሚ ላስታውስህና ‹መንገድህን ጨርቅ ያድርግልህ› ልበልህ፤ አሽሙረኛው መለስ በተቃዋሚዎች ላይ ሲዘባበት ‹እናንተ እኛን ለመዋጋት ያብቃችሁ እንጂ ቁምጣ እናሰፋላችኋለን› ያለውን እዚህ መድገም ነውር ነው – እንዲህስ የትምና እንዲህም አይባልም – የቀደመውንም ለቀልድ እንጂ ለምር አላልኩትም – መጽሐፉ ‹ትዕቢትሰ ፀሩ ለክርስቶስ› ይላልና በምንም ነገር መመፃደቅ ግብዝነት ነው – ደግሞም ቅዱሱ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡- ‹ኢይድኅን ንጉሥ በብዝኃ ሠራዊቱ – ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም›፡፡ መለስ በግብዝነቱና በሰይጣናዊ ዕውቀቱ ተጎዳበት – ተቀሰፈበት – እንጂ አልተጠቀመበትም፡፡ የሚሠሩትን የማያውቁት ወያኔዊና ወያኔ-ቀመስ ድረገፆችም ይሁኑ ሌሎች ማስተዋል የተሣናቸው ኃይሎች ሁሉም ነገር እንዲህ እንደደፈረሰ የሚቀር ከመሰላቸው ተሳስተዋል፡፡ በዚያም ላይ የኢትዮጵያ ችግር ሚዲያ ኖረም አልኖረም መወገዱ አይቀርም፤ ትርፉ ትዝብት ብቻ ነው እንጂ የታሪክን እሽክርክሪት በሬዲዮ ጋጋታም ይሁን በቴሌቪዥን ጩኸት የነጻነት ባቡሩ እንዳይመጣ ለሴከንድ አናዘገየውም ወይም ቶሎ እንዲደርስ አናፈጥነውም፤ የእኔም መጣጥፎች እንዲሁ ናቸው – ለመተንፈስ ብቻ፡፡ የወያኔ ቲቪና ተቀጥላው ተቃዋሚ መሰል ድረገፅ ኢትዮጵያ አረንጓዴ በአረንጓዴ ሆናለች፤ ዕድገቱ 333 በመቶ ደረሰ፣ ግሽበቱ ወደ 0.005 ወረደ፤ ኢሕአዴግ በ‹እንከን የለሽ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ› 99.99 ከመቶ በሆነ ውጤት ‹ተቃዋሚዎች›ን በዝረራ አሸነፈ… ቢባል መሬት ላይ ካለው እውነት ጋር ዐይንና ናጫ ስለሆነ የፈጠጠው ገሃድ እውነት ይህን ውሸት መገንዘብ ለሚፈልግ ሚዛናዊ ሰው ከመገንዘብ አይገታውም – ምድረ ወያኔ አለቃውን እየተከተለ እንደጣቃ በውሸት ቢተረተር፣ ገበሬን ሚሊዮኔር አደረግሁ ተብሎ እየተደሰኮረ በቤቱ ይቀምሰውና ይልሰው ምናምኒት በሌለው ጭቁን ሕዝብ ላይ ቢቀለድ እውነቱ ባለበት ስላለ ሲነጋ ለማፈር ካልሆነ የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ አይለውጥም፡፡ ኤፍኤሞቻችንም በወሲብ ወሬ፣ በጫትና በሀሽሽ የምርቃና አይሬ ዘፈን፣ በድሪያና እንቶፈንቶ ቱማታ እንዲሁም በአርሰናልና ቼልሲ ባዕዳን የእግር ኳስ ጨዋታ ትንታኔ በተለይ ወጣቱን ሲያደነቁሩት ውለው ሲያደነቁሩት ቢያድሩም አሁንም አስደንጋጩ እውነት ካለበት አንድ ጋት እንኳን ወደፊት ንቅንቅ አይልም፡፡ ኮብል ስቶንና አስፋልትም ግፋ ቢል ከጭቃ ይገላግሉን እንደሆነ እንጂ እንደእሳት የሚጋረፍን ርሀብ ለማስታገስ ወደ ሆድ ጠብ የሚል ነገር አያስገኙም – ሊያውም በባቡር መስመር ዝርጋታ ምክንያት በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ትርምስመሷ ስለወጣ ጉዟችን ሁሉ እንደጉዞ ፍትሃት ሆኖኣል – በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባን አለማየት ነው፡፡ ሕንጻውና ፋብሪካውም ለወያኔዎችና ለነሱው ጥገኛ ኢንቬስተሮች የአላግባብ ብልጽግና ምንጭ ከመሆን በዘለለ ጭቁኖችን አልጠቀሙም – የተመሰቃቀለና ለመግለጽም የሚያዳግት ሁኔታ ነው ያለው በሀገራችን፡፡ … በነገራችን ላይ … አይ ይቅርብኝ ተውኩት፡፡
ለማንኛውም ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ልብ ብሎም ብዙም ሳይረፈድ ወደኅሊናቀው ይመለስ፡፡ የሚታየኝን አላውቅም – ግን የነጻነት ቀን በእጅጉ መቅረቧ ይሰማኛል፤ ብዙ ተሰቃይተናልና ይገባናልም፡፡ እምልላችኋለሁ – ከኅያው እግዚአብሔር በስተቀር የምተማመነው ሌላ ምድራዊ ኃይል በኢትዮጵያ ሕዋ ውስጥ በምናብ እያየሁ አይደለም እንዲህ በልበ ሙሉነት ነጻነታችን ቀርባለች የምለው – እርሱን ያመኑ አያፍሩም፡፡ በእስካሁኑ አካሄዳችን በሰው መተማመን ብዙ የኅሊና ቀውስ ውስጥ እንደከተተኝ ስለምረዳ በሰው መተማመኔን እርግፍ አድርጌ ትቻለሁ – ይህንንም ስል እግዚአብሔር ራሱ ወርዶ አንድን ሕዝብን ነጻ እንደማያወጣ አውቃለሁ – በመረጣቸው ሥራውን ይሠራል እንጂ፡፡
ሰው በተለያዬ ምክንያት ከአውነት መንገድ ሊወጣ ይችላል – እስከወዲያኛው ጭንቅላቱን ለሆዱ ወይም ለሸውራራ አስተሳሰብና ለጠማማ እምነት ካዋለ በቋሚነት እንደዋሸ ይኖራል – እውነትን ለመረዳት ተወነባብዶ ወይም እውነታው ከሀሰቱ ተሳከሮበትም ከሆነ በማስረጃና መረጃ የተጠናከረ የጠራ ግንዛቤ እስኪይዝ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ የውሸት ሰለባ እንደሆነ ሊቆይና ወደእውነቱ ሊመለስ ይችላል – ያኔ እንደገና ተወለደ፡፡ በዋናነት በዘረኝነት ልክፍት፣ በይሉኝታ፣ ከሰው ጋር ላለመቀያየም፣ በ‹ከነገሩ ጦም እደሩ› የሰነፎች ይትበሃል፣ በትውውቅና በመሳሰለው ሰዎች ዐይናቸውን ጋርደው ከእውነት አደባባይ በመሠወር ወደሀሰት ሽርንቁላ ሊወተፉ ይችላሉ፡፡ … ለነገሩ አሁን እኔን በዚህ ጉዳይ ምን ጥልቅ አደረገኝ! አሃ፣ ያገባኛል እንጂ፡፡ እናሳ? ምን ላደርግ እችላለሁ? ማድረግ የምችለው – እግዚአብሔር ከ‹ጨለማ ወደ ብርሃን ያውጣቸው› ብሎ መጸለይ ነው፡፡ እኔስ የትኛው ውስጥ ነው የምኖር? ከግምት ባለፈ አላውቅም፡፡ ግን የሚቃወሙኝ ሊጸልዩልኝ ይችላሉ – ‹ከጨለማ ወደ ብርሃን ያውጣህ› ብለው፡፡ እንጸላለይና መሀል መንገድ ላይ እንገናኝ፡፡ ያኔ ሰማይና ምድር ይታረቃሉ፤ ያኔ ማንም የማንንም ድቀትና ሞት አይመኝም፡፡ ያኔ የዲያሎስ ቀንድ ይሰበራል – ክንፉም ይረግፋል፡፡ በቃ፡፡
ይነጋል በላቸው

No comments:

Post a Comment