Friday, October 4, 2013

ይድረስ ለፕሬዚደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ

haile-and-girma
ይሄይስ አእምሮ
ክቡር ፕሬዚደንት ግርማ ሆይ፣
ኢትዮጵያንና “ሕዝቦቿ”ን የሚወዱ ከሆነ ቀጥዬ የምነግርዎትን ከልብ እንዲሰሙኝ በሚያምኑት እለምነዎታለሁ፡፡
ሰሞኑን በጡረታ ሊሰናበቱ እንደሆነ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ዜና ዘገባ ሰማሁ፡፡ በመጀመሪያ ሥራዎን ጨርሰው ለዚህ በመብቃትዎ እንኳን ደስ ያለዎ፡፡ ቀጥዬም በሥራ ዘመንዎ ምን እንደሠሩና እኛ በምናውቅልዎም ሆነ እርስዎ በሚያውቋቸው ምክንያቶች የተነሣ ምን ምን መሥራት ፈልገው ሊሠሩ እንዳልቻሉ “ፕሬዚደንታዊ የሥልጣን ዘመን”ዎን የኋሊዮሽ በማሰብ ከራስዎ ጋር በምልሰት ለመነጋገር የሚያስችል የማሰላሰያ ጊዜ በማግኘትዎ አሁንም በድጋሚ እንኳን ደስ ያለዎ – መልካም ዕረፍት፡፡ ነገር ግን ከስንብትዎ ጋር በተያያዘ የሰማሁት፣ ክፉኛ ያስደነገጠኝና ማመንም ያቃተኝ አንድ ጉዳይ ስላለ ይህን ማስታወሻ ልጽፍልዎ ተገደድኩ፡፡

ጡረታ ሲወጡ እንዲኖሩበት መንግሥት የተከራየልዎት ቤት በነዚሁ ሚዲያዎች እንደሰማሁት በርግጥም በወር ብር አራት መቶ ሺ ነው እንዴ???…(የመጀመሪያውና ባለ530 ሺው ቤት ምናልባትም “ስለተወደደ” ሊሆን ይችላል እንደተሰረዘ ሰምቻለሁ፡፡)
የሰማሁት ጉድ እውነት ከሆነ አሁኑኑ ተግባራዊ ሊያደርጉት የሚገባዎ አንድ ምክር ልለግሰዎ፡፡ ይህን የምለው በብዙ ምክንያቶች ነው፡፡ ዋናው ግን የራሴው ምክንያት ነው፡፡ ቤቴን ቢጎበኙ – እርግጠኛ ነኝ – “ይቅርብኝ በራሴው ቤት እኖራለሁ” ይላሉ፡፡
ውድ ፕሬዚደንት ግርማ፣
የኔ ደመወዝ ብር 4200 ነው፡፡ ተቆራርጦ በሚደርሰኝ ብር 3200 አካባቢ አራት ቤተሰቤን ከወር ወር ማድረስ እየተቸገርኩ ውጪ ሀገር ከሚኖሩ የቤተሰባችን አባላት የምደጎምበት ጊዜ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ልጆቼን ከፍዬ ማስተማር ስላቃተኝ ውለው እንዲመጡልኝ ብቻ በመንግሥት ትምህርት ቤት አስገብቻቸዋለሁ፡፡ ወሮችን እንዴት እንደማጋጥማቸው እኔና አንድዬ ብቻ ነን የምናውቅ፡፡ በመላዋ ሀገራችን የተንሠራፋው የኑሮ ውድነት እንኳንስ ከእጅ ወደ አፍ ልንኖር ከፍለን በማንጨርሰው ዕዳ ውስጥ ተነክረንም እንኳን ከአነስተኛ የምግብ አቅርቦትና ከትራንስፖርት ያለፈ ለሌላ ነገር የምናውለው ገንዘብ ሊኖረን አልቻለም፡፡
እንግዲህ ልብ ያድርጉ፡፡ እኔ ሀገሬን ከ30 ዓመታት በላይ በቅንነት አገልግያለሁ፡፡ በትምህርት ረገድም እስከዚህ ባያኮራም ሁለተኛ ዲግሪ አለኝ፡፡ እኔ መኖር አቅቶኝ እንግዲህ ከኔ ደመወዝ በግብር መልክ ለመንግሥት ገቢ ከሚደረግ አነስተኛ የሀገር ሀብት ለእርስዎ የቤት ኪራይ ብቻ ብር አራት መቶ ሺህ ወጪ ሲደረግ ይታይዎት፤ ይህ ድርጊት የግፎች ሁሉ የበላይ ሊሆን የሚገባውና ማሰብ የሚችል ኢትዮጵያዊን ጭንቅላት ሊያፈነዳ የሚችል አስነዋሪ ተግባር ነው፡፡ መንግሥትዎ ይህን ሲያደርግ የራሱ ዓላማ ሊኖረው ይችላል፡፡ ዐብዶም ሆነ ሰክሮ ሊሆን ቢችልም እርስዎ ግን ኃላፊነት ስላለብዎ ይህን ነገር በጭራሽ መቀበል የለብዎትም፡፡ ቢቀበሉት – እግዚአብሔር ምሥክሬ …read more
Via: Zehabesha

No comments:

Post a Comment