Thursday, October 3, 2013

አፍንጫ ሲመታ የማያለቅስ አይን – አይን አይደለም

የአዉሮፓን ቅኝ ገዢዎች ጀርባና ፊት በአይኑ በፍጹም ያላየ የአፍሪካ ህዝብ ቢኖር የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ነዉ። አዎ! ኢትዮጵያ በቅኝ ገዢዎች ያልተገዛች አገር ብቻ ሳትሆን በቅኝ ገዢዎች ላይ አኩሪና አንጸባሪቂ ድል የተዳጀች የአለማችን ብቸኛ የጥቁር ህዝብ አገር ናት። የኢትዮጵያ ህዝብ በቅኝ ገዢዎች ያልተገዛዉ ቅኝ ገዢዎች ስላላዩት ወይም ኢትዮጵያ የግዜዉን ቅኝ ገዢዎች የማታጓጓ አገር ሆና አይደለም። አዉሮፓዉያን ወይም ቅጥረኞቻቸዉ የኢትዮጵያን ህዝብ አንበርክከዉ አገሩን መያዝ ያልቻሉት ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯ ሲደፈር እያዩ እቤታቸዉ ተኝተዉ የሚያድሩ ልጆች ሰለሌሏት ነዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ጀግኖች ልጆቹ በከፈሉት መስዋዕትነት የፖለቲካ ነጻነቱን ሳያስደፍር በሺዎች ለሚቆጠሩ አመታት የኖር ቢሆንም የአገር ዉስጥ አምባገነኖች ግን ለብዙ ዘመናት ቁም ስቅሉን ያሳዩት ሀዝብ ነዉ።በተለይ የዛሬዎቹ ዘረኛ አምባገነኖች ከዉጭ ቅኝ ገዢዎች ባልተለየ መንገድ የኢትዮጵያን ህዝብ ሰብዓዊ መብቶች ረግጠዋል። የጣሊያን፤ የእንግሊዝና የፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች ቅኝ በገዟቸዉ አገሮች አንዳደረጉት ሁሉ የዛሬዎቹ የአገር ዉስጥ ቅኝ ገዢዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ረግጠዉ መግዛት አንዲችሉ ህዝቡን በሐይማኖት፤ በዘርና በቋንቋ ከፋፍለዋል።
የአዉሮፓ ቅኝ ገዢዎች የአገር ዉስጥ ከሀዲዎችን መልምለዉ መናኛና ጥርስ የሌለዉ ሹመት እየሰጡ አገሬዉ ጸጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛላቸዉ አድርገዋል፤ የወያኔ አገዛዝም ይህንን መሰሪ የቅኝ ገዢዎች አሰራር አንዳለ ኮፒ በማድረግ ኦጋዴን፤አፋር፤ ኦሮሚያ፤አማራ፤ጋምቤላ፤ ቤንሻንጉልና ደቡብ ክልል ዉስጥ በራሳቸዉ አምሳል የክልል ምስለኔዎችን ፈጥረዉ ህዝብ አጎንብሶ እንዲገዛላቸዉ አድርገዋል።
አዉሮፓዉያን ቅኝ በገዟቸዉ አገሮች ዉስጥ ሁሉ የህዝብን ቅስም ሰብረዉ የሦስተኛዉን አለም ህዝቦች አንበርክከዉ በቅኝ ገዢነት ለብዙ አመታት እንዲቀጥሉ ያስቻለቸዉን ከፍተኛ ሠራዊትና ሰላይ ያገኙት ከዚያዉ ቅኝ ከሚገዙት ህዝብ መኃል ነዉ እንጂ ከአዉሮፓ ይዘዉ የሄዱት ሠራዊት እጅግ በጣም ትንሽ ነዉ። በአምስት አመቱ የጣሊያን ወረራ ግዜ መረጃ በማቀበል በተዋጊነትና የጣሊያን ፋሺስቶችን መልካምነት በመናገር የኢትዮጵያ አርበኞችን ትግል እጅግ በጣም አድካሚ ያደረጉት ኢትዮጵያዉያን ባንዳዎች እንደነበሩ የታሪክ ማህደራችን በግልጽ ይናገራል። ኢትዮጵያ በህይወታቸዉ ቆርጠዉ ጣልያን ጓዳ ድረስ ዘልቀዉ ገብተዉ አገርን ከዉድቀት ትዉልድን ደግሞ ከዉርደት ያዳኑ ባሻ አዉዓሎምንና ሸዋረገድ ሐይሌን የመሳሰሉ ጀግኖች እንደነበሯት ሁሉ ኢትዮጵያን በሻንጣ ጠቅልለዉ ለጣልያን ለማቀበል ብዙ የደከሙ የባንዳዎቹ የነ ኃይለሥላሤ ጉግሳም አገር ናት።
ባለፉት አምስት አመታት ግንቦት ሰባት የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለህዘብ ይፋ ባደረገዉ የተለያዩ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎች መሠረት ወያኔ አይወክልም አንጂ እወክላለሁ ብሎ የሚናገረዉ ወይም የወያኔ የፖለቲካ ኃይል ምንጩ የትግራይ ክልል ነዉ። የትግራይ ክልል ህዝብ ደግሞ ብዛቱ ከ4.5 ሚሊዮን ብዙም አይበልጥም። ታድያ እንዴት ሆኖ ነዉ ከዚህ ከአገራችን ህዝብ ብዛት 6 በመቶ ብቻ ከሆነዉ ከትግራይ ክልል የመጡ ጥቂት የፖለቲካ ሊቃቂቶች 94 በመቶ የሚሆነዉን የኢትዮጵያ ህዘብ እጅና አግር አስረዉ እየቀጠቀጡ መግዛት የቻሉት? እንዴት ሆኖ ነዉ የእነዚህ ጥቂት ከሃዲዎች ቡድን በፖሊስ፤ በድህንነት፤ በጦር ኃይሎች፤በኤኮኖሚና በሌሎችም የተለያዩ ዘርፎች ዉስጥ የራሴ የሚላቸዉን ሰዎች አስቀምጦ አገራችንን እንዳሰኘዉ ማድረግ የቻለዉ? መለሱ ቀላል ነዉ። ኢትዮጵያ ትናንት እንደነበሩባት ሁሉ ዛሬም ኃ/ሥላሤ ጉግሳና መሰል ጓደኞቹ አሏት። አዎ! ትናንት የነጭ ፋሺችቶችን ጠመንጃ ተሸክመዉ የገዛ ህዝባቸዉን ደም እንደ ጎርፍ ያፈሰሱ ባንዳዎች፤ እራስ ወዳዶችና የአዕምሮ እዉራን እንደነበሩን ሁሉ ዛሬም የጥቁር ፋሺስቶችን ጠመንጃ ተሸክመዉ የራሳቸዉን ወገኖች ካለ ርህራሄ የሚጨፈጭፉ ጨካኝና አረመኔ ኃይሎች አሉ። ከእነዚህ ከህዝብ አብራክ ወጥተዉ የተሰጣቸዉን ጠመንጃ ቃታ ከመሳብ ዉጭ ሌላ ምንም ህዝባዊ አደራና አገራዊ ስሜት ከማይሰማቸዉ ጨካኝና ግዑዝ ኃይሎች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ ፌዴራል ፖሊስ በመባል የሚታወቀዉ ስብስብ ነዉ።
ፌዴራል ፖሊስ ወያኔ አዲስ አበባ ገብቶ አብሮ በኖረ ህዝብ መኃል የዘርና የጎሳ አጥር ከሰራ በኋላ የክፋቱ ማራመጀና የተንኮል ዕቅዱ ማስፈጸሚያ እንዲሆነዉ ከፈጠራቸዉ ተቋሞች ዉስጥ አንዱ ነዉ። ፌዴራል ፖሊስ አመሰራረቱም ሆነ የቀን ከቀን ስራዉ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅምና ፈላጎት ጋር በምንም መልኩ የተገናኘ አይደለም። ፌዴራል ፖሊስን የፈጠረዉ ወያኔ፤ የሚመራዉና የሚቆጣጠረዉ ወያኔ፤ ፌዴራል ፖሊስ በሚወስዳቸዉ ጸረ ህዝብ እርምጃዎች ዋነኛዉ ተጠቃሚም ወያኔ ብቻ ነዉ።የፌዴራል ፖሊስ ከተቋቋመበት ግዜ ጀምሮ የወሰዳቸዉን ጸረ ህዘብና ጸረ አገር እርምጃዎች አንድ በአንድ ስንመለከት ይህ ተቋም በሚወስዳቸዉ እርምጃዎች የሚጎዳዉ የገፈቱ ቀማሽ የሆነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የፌዴራል ፖሊስ አባላት እራሳቸዉም ቢሆኑ በግልና በቡድን የራሳቸዉ እርምጃ ሰለባዎች ናቸዉ። ታድያ ለምንድነዉ ፌዴራል ፖሊስ ከ20 አመት በላይ እሱን እራሱንና እናቱን፤ አባቱን፤ እህቱንና ወንድሙን የሚጎዳ እርምጃ የሚወስደዉ? የታጠቀ ኃይል ማለትም ፖሊስ፤መከላከያ ሠራዊትና ህዝባዊ ሚሊሺያ ለአዛዦቻቸዉ መታዘዝ እንዳለባቸዉ ከማንም የተሰወረ አይደለም፤ ሆኖም መታዘዝ አንዱ ሀቅ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ትዕዛዝ ሰጪዉ ወያኔ በጥላቻና በዘረኝነት የተነከረ ኃይል ነዉ። ታድያ የወያኔ ጥላቻና ዘረኝነት ጧትና ማታ የሚፈራረቁበት ፌዴራል ፖሊስ እነዚህ ዘረኞች ሂድና ወገኖችህን ግደል ብለዉ ሲያዙት ለምንድነዉ ትዕዛዛቸዉን አልቀበልም የማይለዉ?
ለመሆኑ ይህ ወያኔ ሰራሽ የሆነዉ ፌዴራል ፖሊስ የፊዉዳል ኃ/ሥላሤን ስርዐት ለመደምሰስ በተካሄደዉ ትግል ዉስጥ በፊዉዳሉ ስርዐት መቃብር ላይ የመጨረሻዉን ችንካር የቸነከሩት የፖሊስ ሠራዊት፤ የጦር ኃይሎችና የብሔራዊ ጦር አባላት መሆናቸዉን ያዉቃል? ደርግን ለመጣል በተደረገዉ የሞትና የሽረት ትግል ዉስጥም ቢሆን መሳሪያ የታጠቁ አማጽያንን እየሄዱ በመቀላቀል ደርግን የተዋጉት ደርግ እራሱ ያሰለጠናቸዉ የፖሊስ ሰራዊትና የመከላከያ ሠራዊት አባላት መሆናቸዉንስ ያዉቁ ኖሯል? ታድያ ምነዉ የዛሬዎቹ ፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላት እያረረ የሚስቅ ማሽላ ሆኑ? እዚህ ላይ ወያኔ በየክልሉ ህዝብን እንዲገድሉ ያሰማራቸዉን የፌዴራል ፖሊስ አባላት አንድ የምንጠይቃቸዉ ጥያቄ አለ፤ እሱም በታጠቁት መሳሪያ በነጋ በጠባ የሚገድሉት ህዝብን ከሆነ ከአደጋና ከጥቃት የሚጠብቁትስ ማንን ነዉ?
በ2011 ዓም ጣሂሪር አደባባይ ላይ የተሰበሰበዉ የግብፅ ህዝብ ላይ የሙባረክን ትዕዛዝ ተከትሎ የግብፅ ጦር እርምጃ ወስዶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የአረቡ አለም አብዮት ተብሎ የሚጠራዉና ከ150 ሚሊዮን በላይ አረቦችን ከአምባገነኖች ያላቀቀዉ ትልቁ የዘመናችን ክስተት እንደተራ ነገር ተረስቶ ይቀር ነበር። አስተዋዩ የግብፅ ጦር ግን መኃላዉ ለሙባረክ ሳይሆን ለህዝብና ለአገር መሆኑን ስለሚረዳ በዚያ ክፉ ቀን ሙባረክን ከድቶ ከህዝብ ጋር ቆመ። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘረኝነትንና አምባገነንነንተን አሽቀንጥሮ ጥሎ ነጻነቱን እንዳያዉጅ ደንቃራ ሆነዉ ያስቸገሩት ግደሉ ሲባሉ ተሽቀዳድመዉ የሚሄዱት የአግአዚ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ከኢትዮጵያ ግፉዓን አብራክ የወጣዉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ጭምር ናቸዉ። ይህ የሚያሳየን ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የሚገድሉት የኢትዮጵያን ህዝብ ብቻ ሳይሆን የነገ ተስፋዉን ጭምር መሆኑን ነዉ።
ወታደራዊ ትዕዛዝ መቀበል አንድ ነገር ነዉ፤ የዘረኞችን ትዕዛዝ ተቀብሎ በነጋ በጠባ የንጹሀን ዜጎችን ደም ማፍሰስ ግን ሂሊና ካለዉ ከማንም ሰዉ የሚጠበቅ ተግባር አይደለም። የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስም ቢሆን አንዴ፤ ሁለቴ፤ ወይም ሦስቴ የበላዮቹን ትዕዛዝ ተቀብሎ ህዝብን የሚጎዳ እርምጃ ይወስድ ይሆናል ግን ፌዴራል ፖሊስ ምን አይነት ጨካኞች የተሰበሰቡበት ስብስብ ቢሆን ነዉ እሱን እራሱንና ወገኖቹን በዘር፤ በቋንቋና በሐይማኖት ከፋፍሎ እንደ እንሰሳ እየረገጠ የሚገዛን ኃይል እየታዘዘ ሃያ አመት ሙሉ ወንድሞቹንና አህቶቹን የሚገድለዉ? የወያኔ ዘረኞች መሳሪያ አስታጥቀዉ እንዲጠብቃቸዉ ያሰለጠኑትንም ኃይል ቢሆን በዘርና በቋንቋ ከፋፍለዉ ነዉ የሚገዙት፤ ወያኔ በፌዴራል ፖሊስ፤ በመከላከያ ሰራዊትም ሆነ በደህንነት ዉስጥ ከትግርኛ ተናጋሪዎች ዉጭ የአዛዥነቱን ቦታ ሌላ ለማንም እንደማይሰጥ በግልጽ ይታወቃል። ታድያ ፌዴራል ፖሊስ መቼ ይሆን ከዚህ የቀን መኝታዉ ነቅቶ ሌላ ቢቀር የራሱን መብት፤ ነጻነትና እኩልነት የሚያስከብረዉ? መቼ ነዉ ፌዴራል ፖሊስ የታጠቀዉን መሳሪያ ወገኖቹ ላይ ሳይሆን ወደ ዘረኞችና ወደ ህዝብ ጠላቶች ላይ የሚያዞረዉ?
የኢትዮጵያ ህዝብ ሰኔ 1997ና ህዳር 1998 ዓም አግአዚና ፌዴራል ፖሊስ ተጋግዘዉ ያደረሱበትን በደል አሁንም አልረሳዉም። አግአዚ ኢትዮጵያዉያንን ለመግደል ሆን ተብሎ የተቋቋመ ኃይል ነዉና ግደል ሲባል ጥያቄዉ “ለምን ልግደል” ሳይሆን ስንት ልግደል ነዉ፤ ከዚህ በተጨማሪ አግዓዚ እሱ ከሚናገረዉ ቋንቋ ዉጭ የሚናገሩ ኢትዮጵያዉያንን በመግደል የሚደሰት በጭራቅ የሚመሰል ጦር ነዉ። አዛዦቹም እንደዚሁ ልክ እንደነሱ ትግርኛ የማይናገር ኢትዮጵያዊ ሞት ሞትም አይመስላቸዉም። ለዚህ ነዉ እነሱ ከሚያስቡት ዉጭ የተለየ አስተሳሰብ ያለዉን ኢትዮጵያዊ ሁሉ እሰሩ፤ደብድቡ ወይም ግደሉ እያሉ የሚያዝዙት። ታድያ የትግራይ ክልልን ጨምሮ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተመልምሎ የመጣዉ ፌዴራል ፖሊስ ምን አይነት ጭካኔ ቢያስተምሩት ነዉ መብቴን አክብሩልኝ ብሎ ሰላማዊ ሠልፍ የወጣዉን የራሱን ወገን ልክ እንደ ጦር ሜዳ ጠላት ደረት ደረቱን በጥይት እየመታ የሚገድለዉ? በተለይ ፌዴራል ፖሊስ ባለፈዉ በሐምሌ ወር ማለቂያ አካባቢ በኮፈሌና በአካባበቢዋ የማምለክ መብቴ ይከበርልኝ ብሎ የጠየቀን ህዝብ መኖሪያ አካባቢዉ ድረስ በመሄድ በግፍ የጨፈጨፈዉ ለምንድነዉ? ለመሆኑ ፌዴራል ፖሊስ በሱና ሆነ በወገኖቹ ላይ የሚፈጸመዉ ግፍና በደል ተሰምቶት ከወገኖቹ ጎን የሚቆመዉ መቼ ይሆን?
አግዓዚ ጦር የተቋቋመዉም የሚኖረዉም የወያኔን ስልጣንና ክብር ዘለአለማዊ ለማድረግ ነዉ። ፌደዴራል ፖሊስ ግን ሌላ ቢቀር ስሙ ፌዴራል ነዉና ተቀዳሚ ተግበሩ መሆን ያለበት በፌዴራል ኢትዮጵያ ድንበር ዉስጥ የሚኖረዉ ህዝብ ዘሩና ቋንቋዉ ሳይለይ መብቱ፤ ነጻነቱና እኩልነቱ ተከብሮ እንዲኖር ማድረግ ነዉ። ዛሬ በተግባር የምናየዉ ግን አግአዚ ጦርም ሆነ ፌዴራል ፖሊሰ የኢትዮጵያን ህዝብ ልክ እንደዉጭ ጠላት ሲጨፈጭፉ ነዉ። አግአዚ መግደል ብቸኛ ሙያዉ ነዉና ግደል ተብሎ ሲገድል ይነድደናል ወይ ያሰቆጨናል እንጂ አይገርመንም። የሚገርመን፤ የሚያስቆጨን፤ የሚያንገበግበንና ወያ ነዶ የሚያሰኘን ህዝብን ለመጠበቅ ከህዝብ ዉስጥ ተመልምሎ የሰለጠነዉ ፌዴራል ፖሊስ በወገኖቹ ገንዘብ የተገዛዉን ጠመንጃ እዛዉ ወገኖቹ ላይ ሲያዞር ነዉ።
የ1997ቶቹን ነቢዩ ኃይሌን፤ ኀብታሙ ቶላንና ሽብሬ ደሳለኝን ከሰሞኑ እንደ ቅጠል ከረገፉት ደግሞ ሀቢብ ዋቢን፤ አደም ጀማሎንና ወንድማማቾቹን ገመቹ ተኪንና ታከለዉ ተኪን ስናስብ ኢትዮጵያዊነት በፍጹም ያልጎበኘዉ የፌዴራል ፖሊስ ጭካኔና አረመኔነት ይገርመናልም ያንገበግበናልም። እኛ ኢትዮጵያዉያን የጥንትም ሆነ የዘመኑ ታሪካችን የሚነግረን እህቶቻችን “ወንድም ጋሻ” ድረስ ሲሉን ልማዳችን በፍጥነት ደርሰን እህቶቻችንን መታደግ ነዉ እንጂ የእህቶቻችንን አንገት በጥይት ቀንጥሰን መጣል አይደለም። ታድያ ይህ ትናንት የሽብሬ ደሳለኝን አንገት ቀንጥሶ የጣለዉና ዛሬ ደግሞ ጡት ያልጨረሰች ህጻን ልጅና እናቷን በአንድ ጥይት ያጋደመዉ ፌዴራል ፖሊስ ዬት የበቀለ ትዉልድ ነዉ? ለመሆኑ ፌዴራል ፖሊስ ወገንና ጠላት ለይቶ ለዘረኞችና ለስልጣን ሱሰኞች ሳይሆን ለህገመንግስት የሚገዛ ኃይል ነዉ ወይስ እንደጨበጠዉ ጠመንጃ ግዑዝ የሆነና ተኩስ በተባለ ቁጥር ማንም ላይ የሚተኩስ ተንቀሳቃሽ ሮቦት ነዉ? ከመቼ ወዲህ ነዉ ኢትዮጵያዊ ኃይል በፀረ ኢትዮጵይ ኃይሎች እየተመራ ኢትዮጵያዉያንን በግፍ መግደል የጀመረዉ? ጡት የሚጠባ ህጻን ልጅ እሬሳ በጥይት የተመታች እናቱ ደረት ላይ ተጋድሞ ማየት አንድ ኢትየጵያዊ ዜጋን ቀርቶ ኢትዮጵያዉያንን ሊገድል የመጣ የጠላት ወታደርንም አንጀት የሚበላ እጅግ በጣም አሳዛኝ ክስተት ነዉ። የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ግን በዚህ አይነቱ ዘግናኝ ተግባር የሚያዝኑ መሆናቸዉ ብቻ ሳይሆን እነሱ እራሳቸዉ ናቸዉ ይህንን ሂትለር በአይሁዶች ላይ የፈፀመዉን አይነት ታሪካዊ በደል በወገኖቻችን ላይ የሚፈጽሙት።
ህይወታቸዉን መምራት የሚችሉበት ሌላ አማራጭ አጥተዉ ፌዴራል ፖሊስ የገቡና እንዲሁም የገቡበት ቦታ ጨንቋቸዉና በህዝብ ላይ የሚፈፅሙት ግፍ አንገፍግፏቸዉ መዉጪያ ቀዳዳ የሚፈልጉ አያሌ የፌዴራል ፖሊስ አባላት አሉ። በእኛ ግምትና እምነት መሳሪያ በእጁ የጨበጠ ሰዉ መዉጫና መግቢያ ፈልጎ ማግኘት አያቅተዉምና እነዚህ በፌዴራል ፖሊስ ዉስጥ የሚገኙ አገርና ወገን ወዳድ ኢትዮጵያዉያን የነጻነት ኃይሎችን ለመቀላቀል ከአሁን የተሻለ ግዜና አጋጣሚ የሚያገኙ አይመስለንም፤ ስለሆነም በግልም ሆነ በነጠላ እራሳቸዉን እያደራጁ የነጻነት ኃይሎችን እንዲቀላቀሉ እያሳሰብን የኢትዮጵያን ትንሳኤ በማፋጠን የበደሉትን ሀዝብ እንዲክሱ አገራዊ ጥሪ እናቀርብላቸዋለን። ይህንን ጥሪ የማይቀበልና በተለይ ከወያኔ ዘረኛ አገዛዝ የሚሰጠዉን የግደል ጥሪ እተቀበለ የገዛ ወገኖቹን የሚገድል የፌዴራል ፖሊስ አባል ይህ የበሰበሰ ስርዐት መዉደቂያዉ ሩቅ አይደለምና ከህዝብ ቁጣና ፍርድ እንደማያመልጥ ደግመን ደጋግመን ልናሳስብ እንወዳለን።

No comments:

Post a Comment