የ2015 ዳይቨርሲቲ ቪዛ መርሃ ግብር (ዲቪ 2015) የማመልከቻ ወቅት ከትላንትና ማክሰኞ መስከረም 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት መጀመሩን፣ የሚጠናቀቀውም ቅዳሜ ጥቅምት 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት እንደሚሆን በኢትዮጵያ አሜሪካ ኤምባሲ ከትላንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ።
አመልካቾች ኤሌክትሮኒክ የዳይቨርሲቲ ቪዛ ምዝገባ ቅጹን በምዝገባው የጊዜ ገደብ ውስጥ በድረ-ገጽ አድራሻ dvlottery.state.gov መሙላት እና ማስገባት አለባቸው። የወረቀት ማመልከቻዎች ተቀባይነት የላቸውም። ሁሉም አመልካቾች የዲቪ ቅጹን ከሞሉ በኋላ ስለማመልከታቸው የሚሰጣቸውን ማረጋገጫ አትመው መያዝ አለባቸው። ይህም የማመልከቻቸውን ሁኔታ ለመከታተል ያስችላቸዋል። ማመልከቻዎች እስከምዝገባው የመጨረሻ ሳምንት ድረስ እንዳይቆዩ ኤምባሲው መክሯል። በዚያን ወቅት የሚፈጠር መጨናነቅ ድረ-ገጹን ሊያዘገየው ይችላል። ጥቅምት 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት በኋላ የሚገቡ ማመልከቻዎች ተቀባይነት አይኖራቸውም።
ከአሜሪካ ኮንግረስ በተፈቀደ ስልጣን የሚመራው የዳይቨርሲቲ ኢሚግራንት ቪዛ መርሃግብር በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስተዳዳሪነት፣ በኢሚግሬሽን እና የዜግነት ሕግ፣ በክፍል 203(ሐ) በተደነገገው መሰረት በየዓመቱ ይከናወናል። እ.ኤ.አ. በ1990 በወጣው የኢሚግሬሽን ሕግ በክፍል 131 የተቀመጠውና በኢሚግሬሽን እና የዜግነት ሕግ ክፍል 203 የተሻሻለው ድንጋጌ ዳይቨርሲቲ ኢሚግራንትስ በመባል የሚታወቁ ስደተኞችን ይመለከታል ኢሚግሬሽን እና የዜግነት ሕግ ክፍል 203 (ሐ) 55,000 ዳይቨርሲቲ ቪዛዎች የሕዝቦቻቸው ወደ አሜሪካ የመፍለስ መጠን አነስተኛ ከሆነባቸው አገራት ለሚመጡ ሰዎች እንዲደርሱ ይደነግጋል። በዚህም መሰረት 55 ሺህ ቪዛዎች ለዲቪ አመልካቾች ይመደባሉ፤ ሆኖም ከዲቪ 1999 ጀምሮ በየዓመቱ ከነዚህ ቪዛዎች 5,000 ያህሉ በኒካራጓ እና ማዕከላዊ አሜሪካ የዕርዳታ ሕግ መሰረት በጥቅም ላይ እንዲውሉ በኮንግረስ ተወስኗል።
በሕገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ለመግባት በመሻት ለማጭበርበር የሚሞክሩ ወይም ከአንድ በላይ ማመልከቻ የሚያስገቡ ሰዎችን መለየት የሚችል ልዩ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ስልቶች በስራ ላይ ውለዋል።
ዓመታዊው የዲቪ መርሃ ግብር ቀላል፣ ነገር ግን ጥብቅ የሆኑትን መመዘኛዎች ለሚያሟሉ አመልካቾች ወደ አሜሪካ ለመሄድ የሚያስችል ቪዛ ያስገኝላቸዋል። የዳይቨርሲቲ ቪዛ ዕድለኞች በኮምፒውተር በሚከናወን የሎተሪ ዕጣ አወጣጥ ስርዓት ይመረጣሉ። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የዳይቨርሲቲ ቪዛ ሂደትን ይበልጥ ቀልጣፋና አስተማማኝ ለማድረግ በማሰብ እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ የኤሌክትሮኒክ የምዝገባ ስርዓትን ተግባራዊ አድርጓል። በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ለመግባት በመሻት ለማጭበርበር የሚሞክሩ ወይም ከአንድ በላይ ማመልከቻ የሚያስገቡ ሰዎችን መለየት የሚችል ልዩ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ስልቶች በስራ ላይ ውለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ለተመረጡት ሰዎች ለዲቪ 2015 ዕድለኞች መመረጣቸውንም ሆነ የቪዛ ማመልከቻ እና ቃለመጠይቅ ስለሚያደርጉበት ሁኔታ የሚያሳውቀው በኢንተርኔት አማካኝነት ነው። አመልካቾች መመረጣቸውን ለማወቅ ከሚያዚያ 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በማመልከቻቸው ወቅት የተሰጣቸውን የማረጋገጫ ቁጥር dvlottery.state.gov ላይ በ Entry Status Check አማካኝነት ማወቅ ይችላሉ። የተመረጡ አመልካቾች ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ኢሚግራንት ቪዛ ስለሚጠይቁበት ሂደት የሚገልጽ መመሪያ ይደርሳቸዋል። የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጋብቻ አዋጅን በከፊል መሰረዙን ተከትሎ በኢሚግሬሽን አሰራሮች ላይ የተደረጉ ለውጦች በዲቪ- 2015 አመልካቾች ላይ ተፈጻሚ ይሆናሉ። የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች ከተመሳሳይ ጾታ ተጋቢዎች የሚቀርቡ የቪዛ ማመልከቻዎችን ከተቃራኒ ጾታ ተጋቢዎች ከሚቀርቡ ማመልከቻዎች ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ያስተናግዳሉ።
ለቪዛ ቃለመጠይቅ ቀጠሮ የሚያዘው በ Entry Status Check በኩል ነው። ስለማመልከቻ መስፈርቶችም ሆነ በዲቪ መርሃግብር ላይ በተደጋጋሚ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት የዲቪ-2015 መርሃግብር መመሪያዎችን፡-
በዲቪ-2014 መርሃግብር 3,500 የሚሆኑ ቪዛዎች መስፈርቶችን ላሟሉ ኢትዮጵያውያን የተሰጡ ሲሆን፤ ይህም በመላው ዓለም ከተፈቀደው ብዛት ከፍተኛው መሆኑን ኤምባሲው ገልጾአል።
ሰንደቅ ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment