Wednesday, October 2, 2013

ኢዴፓ በመጪው እሁድ በአክሱም ሆቴል ጠቅላላ ጉባኤ ሊያካሂድ ነው

በመስከረም አያሌው

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በመጪው እሁድ መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን በአክሱም ሆቴል ሊያካሂድ ነው።
የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ጠቅላላ ጉባኤው የሚካሄደው በፓርቲው ደንብ መሠረት የስራ አስፈፃሚ የስራ ዘመን መጠናቀቅን አስመልክቶ ምርጫ ለማካሄድ ነው። ማዕከላዊ ኮሚቴውን ጨምሮ ስራ አስፈፃሚው አካል ከተመረጠ ሁለት አመት በመሙላቱ በጉባኤው ላይ የተተኪ አመራር ምርጫ ይካሄዳል። ከዚህ በተጨማሪም ከጠቅላላ ጉባኤው ቀደም ብሎ ማዕከላዊ ኮሚቴው ቅዳሜ በሚያደርገው ስብሰባ እጩዎችን ያሳውቃል።
ከጠቅላላ ጉባኤው እና ከምርጫው ቀደም ብሎ ፓርቲው አባላቱ በሁለት አመታት ውስጥ ሲያደርጉት የነበረውን እንቅስቃሴ ገምግሞ እጩዎችን ያቀርባል። ለስራ አስፈፃሚ የሚመረጡት አመራሮች ሙሉ ለሙሉ አዲስ ሊሆኑ ይችላሉ፤ አሊያም የነበሩት ሊቀጥሉ ይችላሉ ያሉት አቶ ሙሼ ‘‘በእርግጠኝነት የምናገረው ግን እኔ በፕሬዝዳንትነት እንደማልቀጠል ነው’’ ብለዋል። በፓርቲው አመራር ደረጃ ለ15 አመት ገደማ መስራታቸውን የገለፁት አቶ ሙሼ፤ አሁን ግን ፓርቲው አዲስ አመራር መርጦ እንዲቀጥል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
በጉባኤው ላይ ከስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ በተጨማሪም የፓርቲው የሁለት አመታት የስራ ሂደት፣ ፓርቲው የደረሰበት ተጨባጭ ሁኔታ እና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ግምገማ ይካሄዳል። በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ከመላው የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጡ ከ200 እስከ 250 የሚደርሱ የፓርቲው አባላት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም ዝግጅት እንዲያደርጉ ቀደም ብሎ ለአባላት የተነገራቸው ሲሆን፤ አስፈላጊው ነገርም እየተመቻቸላቸው ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ለማግኘት ከፍተኛ ችግር ገጥሞት እንደነበርም ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል። በርካታ ሆቴሎች እና አዳራሾች ለፓርቲው የስብሰባ አዳራሽ ለመፍቀድ ፍርሃት ይታይባቸው እንደነበር የገለፁት አቶ ሙሼ በተለይ ራስ ሆቴል አዳራሹን ፈቅዶ ከተስማማ በኋላ ደብዳቤ እና ክፍያ ይዘው ሲሄዱ ምክንያቱን እንኳን በአግባቡ ሳያስረዳ ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልፆላቸዋል። በመቀጠል ወደ እየሩሳሌም ሆቴል በማምራት ተስማምተው ክፍያውን ከፈፀሙ በኋላ ሆቴሉ ስምምነቱን በማፍረስ ገንዘቡን ተመላሽ አድርጓል።
የአዳራሽ ጥያቄውን ይዘው ወደ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ቢያቀኑም ሆቴሉ ‘‘ፈቃድ እንኳን ይዛችሁ ብትመጡ እኛ የተለያየ ተፅእኖ እየደረሰብን ስለሆነ አናስተናግድም’’ የሚል መልስ እንደሰጣቸው ጨምረው ገልፀዋል። በመጨረሻም ወደ አክሱም ሆቴል አምርተው መስማማታቸውን እና ክፍያ ፈፅመው የጉባኤውን እለት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ሙሼ፤’’ ሆቴሎቹ አዳራሾቻቸውን ለመፍቀድ ከፍተኛ የሆነ የፍርሃት ስሜት እንዳለባቸው ተገንዝበናል’’ ብለዋል።

No comments:

Post a Comment