በፀጋው መላኩ
የ20/80 ነባር የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ40ሺ ቤቶች እጣ በዚህ አመት ለማውጣት እቅድ የተያዘ ሲሆን ከዚያ በፊት ግን አንድ ሰው በአንድ የቤት ፕሮግራም ብቻ መመዝገቡን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን የጣት አሻራ ለመውሰድ የሚያስችለው ማሽን ግዥ እየተካሄደ ነው። በዚሁ ዙሪያ ለሰንደቅ ማብራሪያ የሰጡት የቤቶች ልማት አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግስቱ የጣት አሻራ መስጠቱ ሂደት ሳይቀደምና ዳታ ቤዙን የማናበቡ ሥራ ሳይካሄድ እጣውን በተድበሰበሰ መልኩ ማውጣቱ አግባብነት የሌለው መሆኑን አመልክተዋል።
የጣት አሻራውን በመውሰዱ በኩል ኃላፊነቱን የተረከበው የመረጃ ደህንነት ኤጀንሲ የጣት አሻራን ለመሰብሰብ የሚያስችለውን ማሽን ግዢ በማከናወን ላይ መሆኑ ታውቋል። እንደ አቶ መስፍን ገለፃ ቀደም ሲል በተቀመጠው አሰራር መሠረት መመሪያው ተመዝጋቢው በአካል ተገኝቶ አሻራ መስጠት አለበት ቢልም ተመዝጋቢ ዜጐች ከአዲስ አበባ ውጪ በተለያዩ ሥራ ተሰማርተው የሚገኙበት ሁኔታ ስለሚኖር በዚህ በኩል ያለውን ችግር ለማቃለል ማንም ዜጋ ባለበት አካባቢ ሆኖ የጣቱን አሻራ በስካነር በመላክ ወደ ዳታቤዝ እንዲገባ የሚያደርግበት አሰራር እንዲኖር ዝግጅት እየተደረገ ነው።
የጣት አሻራ መስጫው ጊዜ በትክክል ባይታወቅም እንደ አቶ መስፍን ገለፃ ምንአልባትም ህዳር አካባቢ ሊሆን ይችላል። የጣት አሻራ መስጠቱ ሂደት የዘገየበት ዋናው ምክንያት በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ቤት ተመዝጋቢዎች መንግስት በሚያስቀምጠው አሰራር መሰረት አዲሰ አበባ ሳይመጡ በየአካባቢያቸው የጣት አሻራ እንዲሰጡ ለማድረግ መሆኑ ታውቋል።
የጣት አሻራ ስካነር ማሽኑ ግዢ ተጠናቆ የጣት አሻራው የመሰጠቱ ሥራ ካበቃ በኋላም የዳታቤዝ ማናበቡ ሂደት ተጠናቆ የቤቶቹ ሁኔታ ለከተማው የሥራ አመራር ቦርድ ቀርቦ ውሳኔ እንደተሰጠበት እጣው የሚወጣ መሆኑ ታውቋል።
በአሁኑ ሰዓት ለነባር 20/80 የቤት ተመዝጋቢዎች እጣ ይወጣባቸዋል ተብለው ግንባታ እየተካሄደባቸው ካሉት ሳይቶች ውስጥ አራት ኪሎ፣ የካ አባዶ፣ የካ ጣፎ፣ ቱሉ ዲምቱ፣ ቂሊንጦ እና ገላን የሚገኙበት መሆኑን አቶ መስፍን ገልፀዋል። በአሁኑ ሰዓት የቤቶች ግንባታ ሲታይ 80 በመቶ የደረሱ እንዲሁም የተጠናቀቁም ያሉ መሆኑ ታውቋል።
በተጨማሪም 95ሺ ቤቶች በግንባታ ላይ መሆናቸው ታውቋል። የቤቶች ግንባታን ቀደም ሲል ሲደረግ እንደነበረው በመሀል ከተማ በመልሶ ማልማት ፕሮግራም ለማካሄድ የመሬት ዝግጅቱና የሚነሳውን ነዋሪ መልሶ የማስፈሩ ሂደት ከፍተኛ ወጪን እየጠየቀ በመምጣቱ ለጊዜው ቤቶቹ በከተማዋ የማስፋፊያ ቦታዎች ላይ እየተገነቡ መሆናቸውንና አቶ መስፍን ጨምረው ገልፀዋል።
No comments:
Post a Comment