አብርሃም ደስታ
ቆይ ግን እኔ የምኒሊክ ‘አድናቂ’ ነኝ እንዴ? ባጋጣሚ ስለ አፄ ምኒሊክ ጥሩም መጥፎም ፅፌ አላውቅም። ግን ብዙ የህወሓት ደጋፊዎች የምኒሊክ አገዛዝ እንደምደግፍ አድርገው ለህዝብ ይነግራሉ። የፌስቡክ ጓደኛዬ ዳንኤል ብርሃነም “የምኒሊክ ቲፈዞነትህ ለማስቀጠል ከፈለክ የሱ ወራሾች የሆኑ ‘አንድነቶች’ (ፓርቲው መሆኑ ነው) አሉልህ፤ ከነሱ ጋር ተቀላቀል” የሚል መልእክት ያለው አስተያየት ሰጠኝ።
የህወሓት ደጋፊዎች ከምኒሊክ ጋር የሚያገናኙኝ ምናልባት ህወሓት ስለምቃወም ይሆን? ወይስ እንደነሱ ‘ሸዋ አማራ ጠላታችን ነው’ ብዬ አለመፃፌን ነው? ህወሓትን መቃወም ከምኒሊክ አገዛዝ… ጋር ምን ያገናኘዋል? ግን’ኮ ህወሓቶች በስልጣን ለመቆየት የሚጠቀሙት ስትራተጂ ‘ከፋፍለህ ግዛ’ ነው።
‘እኛና እነሱ’ ብለው ይከፋፍላሉ። በዚህ መሰረት ‘ህወሓት ከተቃወምክ የሸዋ ፖለቲከኞች ትደግፋለህ ማለት ነው’ ይሉሃል። ቆይ የሸዋ ፖለቲከኞች ሳንደግፍ ህወሓትን መቃወም አንችልም ማለት ነው?
በዚህ አጋጣሚ ስለ ምኒሊክ ስርዓት ያለኝ አመለካካት ላካፍላቹ። (ፖለቲከኛ ጠንቃቃ መሆን አለበት ይባላል፤ ግን እኔ ፖለቲከኛ ነኝ እንዴ? የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆነ ሁሉ ፖለቲከኛ ነው ብዬ አላምንም)። በኔ መነፅር የምኒሊክ ስርዓት እንደማንኛውም ዘውዳዊ አገዛዝ ነው። በንጉሳዊ ስርዓት ‘ዙፋኑ ይመለከተናል’ የሚሉ መሳፍንት ሁሉ ዘውዱን ለመጫንና ግዛቶችን ለማስፋፋት ጥረት ያደርጋሉ። ለግል ስልጣናቸውና ግዛታቸው የሚያግዛቸው ተግባር ሁሉ ያደርጋሉ። ከህዝቦች ነፃነት በላይ ስልጣናቸው ያስቀድማሉና። ሁሉም ለስልጣንቸው አደጋ የሚደቅን ግለሰብ ምህረት የላቸውም (የፈለገ ዘመድ ቢሆን)። በዚህ ልክም ሀገራዊ ራእይ የነበራቸውም አይጠፉም።
ሁሉም መሳፍንትና ነገስታት ዘውዱን ለመጫን ብዙ ግፍ ፈፅመዋል። ያለፈ የንጉሳውያን ታሪክ እያስታወሱ መወቃቀስ ላሁኗ ኢትዮዽያ አይጠቅምም የሚል እምነት አለኝ። ‘ዮሃንስ እንዲህ አለን፣ ምኒሊክ እንዲህ አደረገን’ እየተባባልን ግዜያችን ባናጠፋ (ለዚህም ነው ስለነዚህ ታሪክ መፃፍ የማልፈልገው)።
አንዳንድ የሚፃፉ ነገሮች ግን ይገርሙኛል። ‘ምኒሊክ ለትግራይ እንዲህ አለ፣ ለኦሮሞዎች እንዲህ አደረገ’ ሲባል … እና ምን? ምኒሊክ የሰራው ነገር ለስልጣኑ ሲል ነው። ዮሃንስም እንዲሁ፣ ቴድሮስም እንዲሁ። ለስልጣናቸው ሲሉ መጥፎ የሰሩትን ያህል ጥሩ ነገርም ሰርተው ይሆናል። በስልጣን ሽኩቻ ምክንያት መዓት ችግሮች ሰርተው ይሆናል። ግን ምኒሊክ ለሰራው ነገር አሁን ላሉ የሸዋ አርሶ አደሮች፣ ዮሃንስ ለሰራው የአሁኑ ተምቤኖች፣ ቴድሮስ ለሰራው የአሁኑ ጎንደሬዎች፣ ህወሓት ለሰራው የአሁኑ ትግራዮች ተጠያቂ ሊሆኑ አይችሉም።
ምኒሊክ የዮሃንስን ዘውድ ለመያዝ የተጠቀመው ስልት (ጥሩም መጥፎም) በመጥቀስ የሸዋ ሰዎች ለትግራይ ሰዎች መጥፎና ጠላቶች ማረጋገጫ አድርገን መፃፍ ተገቢ አይደለም። አፄ ቴድሮስ የጎጃም መሳንፍት ጠራርጎ ሲያባርር አንድም ለስልጣኑ አልያም ደግሞ ለሌላ ጥሩ ነገር ነበር እንበለው። በዚህ ጉዳይ እርግጠኞች መሆን አንችልም። መከራከር ቢቻልም። ስለ አንድ ነገር ግን እርግጠኞች መሆን አለብን፤ ቴድሮስ መሳፍንቱን ሲያባርር መሳፍንቱ ትግሬ ወይ ኦሮሞ ወይ አማራ ወይ ሌላ ሰለነበሩ አይደለም።
ዮሃንስም የቴድሮስን ዙፋን ለመጨበጥ የተለያዩ ስልቶች ተጠቅሞ ይሆናል። ለምን አደረገው ብለን ብንጠይቅ … ለስልጣኑና ለሌላም ሊሆን ይችላል። አንድ ሓቅ ግን አለ። ዮሃንስ ቴድሮስን ስልጣን መቀማት የፈለገው ቴድሮስ ጎንደሬ ስለነበር (ወይ ትግራዊ ስላልነበረ) ግን አይደለም። በተመሳሳይ መልኩ ምኒሊክም እንደማንኛውም ንግስና ፈላጊ የዮሃንስ ዙፋን ለመውረስ የተለያዩ ስልቶች ተጠቅሞ ይሆናል (የተጠቀመው ስልት ጥሩ ወይ መጥፎ ሊሆን ይችላል፣ እንደ አመለካከታችን ይለያያል)። ግን ምኒሊክ ይሄን ነገር ሲያደርግ ስልጣኑንና ፖለቲካዊ ዓላማውን እያሰበ እንጂ ብሄር እየቆጠረ አይመስለኝም። ምክንያቱም ነገስታት ለንግስናቸው ሲሉ የራሳቸው ብሄር ተወላጆችም ሲገድሉ ነበር።
በዚህ መሰረት ቴድሮስ ከትግራይ ቢሆን ኑሮ ዮሃንስ የዙፋን ተቀናቃኝ አይሆንም ነበር ማለት አንችልም። የትግራይ መሳፍንት’ኮ እርስበርሳቸው ተፋጅተዋል። ዮሃንስ ከሸዋ ቢሆን ኑሮ ምኒልክ ለዮሃንስ ጥሩ ይሆን ነበር ብትሉኝ አላምናችሁም። ቆይ! በላይ ዘለቀ በሃይለስላሴ የተገደለው ትግሬ ስለነበረ ነው እንዴ? ደርግ የሃይለስላሴን ስርዓት የተቃወመው ትግሬ ስለነበረ ነው እንዴ? ህወሓት ኢዲዩን ያጠፋው ኢዲዩ የሸዋ ስለነበር ነው እንዴ? አይደለም።
እኔም ህወሓት የምቃወመው ህወሓት ከትግራይ ስለሆነ ወይ ስላልሆነ አይደለም፤ የምኒሊክ ስርዓት ናፋቂ ስለሆንኩም አይደለም። ከህወሓት አገዛዝ የተሻለ ሌላ ስርዓት ማየት ስለምፈልግ ነው። ስልጣን ወደ ህዝብ ወርዶ ማየት ስላማረኝ ነው።
ሁሌ ህዝብና ፖለቲከኞች ለያይተን ማየት ይኖርብናል። ምኒሊክ ለዮሃንስ የስልጣን ተፎካካሪ (የስልጣን ጠላት) ስለነበረ የትግራይና የሸዋ ሰዎች ጠላት መሆን አለባቸው በሚል ሓሳብ አልስማማም። ምኒሊክ ሌላ የሸዋ ህዝብ ሌላ፤ ህወሓት ሌላ የትግራይ ህዝብ ሌላ።
It is so!!!
No comments:
Post a Comment