Friday, February 15, 2013

ኢህአዴግ ከመቻቻል ይልቅ መጃጃልን መረጠ! የሐረካት ፊልም ድራማ ህዝቡን ያስተባብራል እንጂ አይለያይም!




ሰሞኑን ሁላችንም እንዳየነው ወጣት ሙስሊም ወንድሞቻችን ሕገ መንግስቱ የሰጠንን የእምነት ነፃነታችን ይከበር በማለት በሕጋዊ መንገድ መልስ እንዲሰጣቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ወደ ጎን በመተው በሓሰት ላይ የተመሰረተ ሓካት የሚል የፊልም ድራማ በኢትዮጵያ
ቴሌቪዥን ላይ ሲታይ መሰንበቱ ይታወቃል። የፊልሙ ይዘት በሶስት ነጥቦች ከፍሎ ማየት ይቻላል። 1. ፊልሙ ምን አዲስ ነገረ አለው? 2. የፊልሙ አላማ ምንድን ነው? 3. ፊልሙስ እንዳሰቡት ግቡን መቷልን? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ቀጥለን እንመልከት።

1. የሙስሊም ሐራካት የፊልም ድራ ምን አዲስ ነገር አለው?
ፊልሙ አዲስ ነገር የለውም። እንደዚህ ዓይነት በውሸት ላይ የተመሰረተ ማደናገሪያ ድራማ ማቅረብ የተለመደ፣ በተለይም ህወሓቶች ከተፈጠሩበት ቀን ጀምረው እስካሁን ድረስ በተለይም ምርጫ ሲቃራብ፣ የሚፈልጉትንና የሚጠረጡሩትን ሰው በእጅ አዙር
ለመምታት፣ የህዝቡን ቀልብ ለመቀየር፣ የፓለቲካ ተቃዋሚዎችን ለማስደንገጥና ወኔ ለመስለብ ሲሉ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀሙት የስነ ልቦና ጦርነትና ዘመቻ ነው። ለምሳሌ ወደ ዛሬው ድራማ ከመሄዳችን በፊት ህወሓቶች ስልጣን ከያዙ ጀምሮ እስካሁን ድረስ
ከፈፀሙት አሰቃቂ ድርጊቶች ውስጥ ቆንጥረን የሚከተሉትን እንመልከት፡-
_ ተቃውሞ ከህዝቡም ሆነ ከፓለቲካ ድርጅቶች እየበረታ ሲሄድ ከሚጠቀሙት ዘዴ አንዱ ድሮ የተረሳና ከአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ ምንም ተያያዥነት የሌለው ደኩመንት ከማሕደር እየመረጡ ከዘውዳዊ ስርዓት፣ ከደርግ ጭቆና፣ ከሻዕቢያ ወራር፣ ከሽብርተኝነትና
ከጦርነት ጋር የተያያዘ ፊልም አቀነባብረው ለዓይን እስከሚሰለች ድረስ ያቀርባሉ። መልእክቱም ቂማችን አልረሳንም ተጠንቀቁ ለማለት ነው።
_ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በምርጫ 97 እና በ2005ዓ.ም ዋዜማዎች ደጋግመው ሲያቀርቡ የነበሩት አስፈሪ ፊልሞችም ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን የሚገልፁ ናቸው። በትግራይ የአቶ ገብሩት አስራት ፎቶ ግራፍ ከኰሌኔል መንግስቱ ሀይለማሪያም በመቀላቀልና ጎን ለጎን በማስቀመጥ በትግርኛ ሌቪዥን ፕሮግራም ተደጋግሞ ሲቀርብ ዓይተናል። ፍርድ ቤት በነፃ የለቀቃቸው አቶ ስየ አብርሃን መልሶ ለማሰር ሲባል በአንድ ጀምበር ሕግ እንዳወጡ ሁሉ አቶ ስየ ከእስር እንደተለቀቁ በ2005ዓ.ም በተወለዱባት የተምቤን አውራጃ ለምርጫ በተወዳደሩበት ወቅትም “የህወሓት ታጋዮች ሰማእታት አደራ በልቶ ከአማራ ትምክሕተኞች ጋር የተሰለፈ ነው” በማለት በአካባቢው የተወለደው የህወሓት ታጋይ የነበረው “አሞራ” በሚል የትግል ሜዳ ስም የሚታወቀው በጦር ሜዳ ህይወቱን ያለፈ ታጋይ ፊልሙ ተደጋግሞ እንዲታይ ተደርገዋል። የፊልሙ መልእክትም “ስየ” የአሞራ አደራ የሰበረ ከዳተኛ ስለሆነ እንዳትመርጡት” የሚል ሲሆን ለሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ “ በደማችን ያመጣ ነው ለውጥ ማንም ሊነጥቀን እንደማይችል እርማችሁን አውጡ፣ ልካችሁንም እወቁ” የሚል እንደነበር ልብ ብሎ ለመተመለከተው ሰው በግልፅ ያስረዳል።
_ በምርጫዎቹ አካባቢ በወዲ ባሌማ የሚመራ አራት አባላት ያሉት ከፍተኛ የህወሓት አመራር ቡድን በአሜሪካ በዋሽንግተን ዲሲ ርእሰ ከተማ ለትግራይ ተወላጆች ብቻ ሰብስበው በሚያነጋጉርበት ጊዜም በነ “አቶ ገብሩ አስራት የሚመራው ዓረና የሚባለው የፓለቲካ ድርጅት የትግራይ አልካይዳ ናቸው” ብለው በንቀት በመናገራቸው ህዝቡ ስብሰባቸውን ጥሎ ደፍርሶ በመውጣት ተቃውሞውን በመግለፁ የሐፍረት ሸማቸውን ተከናንበው ወደ መጡበት እንደተመለሱ የሚታወስ ነው።
_ የግንቦት 7 እና የኦነግ ስም እየተለጠፈባቸው በየጊዜው በእስር ቤት ታጉረው እውነቱን አውጡ ወይም ውሸት ተናገሩ እየተባሉ በኤለክትሪክ የሚጠበሱ ወገኖቻችንም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። በወህኒ ቤት አስገዳጅ ምርመራ ዓይናቸውን የጠፋ ጀነራል፣ቤት ንብረታውን ሲወረስ ተበሳጭተው ከግንብ ጋር ራሳቸውን በራሳቸው አላተሙ በሚል ዛቻና ማስተባቢያ ጭንቅላታቸው የተፈጠፈጡ እስረኛ፣ “ወንጀል ሰርተናል እያላችሁ ተናገሩ” እየተባሉ በአካላቸውም ሆነ አእምሮዋቸው እንዲኰላሹ የሚደረጉ ወገኖቻችን ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ በውል እንረዳለን።
_ የህዝብ ድምፅ ይከበር በማለት አደባባይ ወጥተው ድምፃቸው ያሰሙትን ወጣቶች ባንክ ሲዘርፉ አገኘናቸው በማለት ደማቸውን በአዲስ አበባ አስፋልት የተጥለቀለቀውን 193 የሚሆኑ ዜጎች የምናስታውሰው ነው። በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከያሉበት
ከእናታቸው ጉያ እየተለቀሙ በጭነት መኪናዎች እየታፈሱ እንደ ድንች በላዩ ላይ ተደራርበው ወደ ዴዴሳና ብር ሸቀለቆ ተወስደው የወያነ ጥይት፣ የወባ በሽታና የዱር አራዊት ሲሳይ በመሆን ወሬ ነጋሪ እንኳን የሌላቸው ደብዛቸው ጠፍቶ እንደወጡ የቀሩት ወጣቶች ቤቱ ይቁጠረው።
_ አፍ ላፊ ተብላ ዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባት በብቸኝነት በጨለማ ቤት ታጉራ ፍዳዋን ስታይ የቆየችው የእህታችን ብርትኳን ሜዲክሳ ሁኔታም ስናስታውስ በዘመናችን ከተፈፀሙት አሳዛኝና አሳፋሪ ክስተቶችም አንዱ ነው። በመጨለማ መታጎርዋ ብቻ አይደለም “ከልጄና ከአረት እናቴ በላይ ሀገሬ ይድማል” ብላ የከፈለቺውን መስዋእትነት በማንቋሸሽ
“የታሰርኩት በራሴ ስህተት ነው ብለሽ ተናገሪ” በማለት በተደረገላት ተፅዕኖ በሐሰተኛ ወረቀት በመፈረም በህዝብ ፊት የሞራል ሀፍረት እንዲሰማት ለማድረግ የተደረገ ሙራና ርካሽና ሰይጣናዊ ድራማም ከቶውኑ ከህዝብ አእምሮ አይፋቅም።
_ ሕገ መንግስት የሰጣትን መብት ተነፍጋ በሐሰት ውንጀላ ወህኒ ቤት እንድትገባ የተደረገቸው እርጉዝ እናት የዋስና የመታከም መብትዋን ተነፍጋ በእስር ቤት እንድትወልድ የተገደደቺው ኢትዮጵያዊት እናትም በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለማችን ታይቶ
የማይታወቅ ፋሽሽታዊና የአፓርታይድ ተግባር መሆኑን በግልፅ ዓይተናል።
_ ሌላ ቀርቶ ያንተ ነፃ አውጪ ነን እያሉ በሙና በደሙ የሚነግዱበት የትግራይ ህዝብም ከዚህ አሰቃቂና አውዳሚ ሰለባ የወጣ አይደለም። ሌላውን ትተን ለፌደራል ዕጩ ሆኖ ለምርጫ ቀርቦ በነበረው በአቶ አረጋዊ ገብረዮሐንስ ላይ የተፈፀመው ተወዳዳሪ
የሌለው ግፍም የስርዓታቸው ጨካኝ ባህርይ አመላካች ነው። አቶ አረጋዊ ገብረሐንስ በዓይነ ቁራኛ ሲከታተሉት ቆይተው በመጨረሻ እንደ በግ በቤቱ አጋድመው ማረዳቸው ብቻ አይደለም። ገና የሐዘን ድንኳኑን ሳይፈርስ 7 ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የፍርዱን ሂደት በመጨረስ ተከራካሪ ቤተሰብም እንዳይኖር ሚስቱ በድንጋጤ አንድ ወር ሳትቆይ ሞተች። ስድስት ልጆቹንና ወንድሞቹንም ጭምር በፍርሃት ሀገር ለቀው በመሄድ በአሁኑ ጊዜ በጎረቤት ሀገር በስደት ላይ ይገኛሉ። ይኸው ነው ህወሓት ላለፉት 40 ዓመታት ወንድሞቹን በጠመንጃ እያሳደደ ስለገደለ ብቻ ከናንተ የበለጥኩ ጀግና ነኝ እያለን የሚገኘው።ታዲያ!! የሰሞኑን በሙስሊም ወንድሞቻችን ላይ ሐራካት በሚል ስያሜ የተሰራውን አስቂኝና አሳዛኝ ድራማ ከላይ ከተጠቀሱት አስነዋሪ ድርጊቶች የተለየ ነው ብላችሁ ታስባላችሁን? አይመስለኝም። በዚሁ አሳፋሪ ድርጊት የሚደሰቱና የሚያንጨበጭቡ የሰው ልጅ ነፃነትና ክብር የዶሮን ያህል ግምት የማይሰጡ የስርዓቱን ሰው በላ ካድሬዎችና ለፍርፋሪ ያደሩ ከሃዲዎች ካልሆኑ በስተቀር በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና የአብሮነት ባህል ታንፆ ያደገ ሰው በገዛ ወንድሙ ላይ ያን ያህል ይጨክናል ብዬ አላምንም።በመሆኑም ባለፉት ጥቂት ቀናት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተለቀቀው በሙስሊም ሕብረተሰብ ላይ ያነጣጠረው የፊልም ዘመቻ
በውሸት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሚያመላክቱ ብዙ ጭብጦች ለማቅረብ ሌላ ምርምርና ፍልስፍና አያስፈልገውም። ራሱ ፊልሙ በግልፅ ይናገራል። እሱም የሚከተሉትን በመጠኑ መጥቀስ ይቻላል፡-
- በፊልሙ መልካቸውን በመቀያየርና በመቀባባት ኢሰብኣዊ በሆነ አካኋን ዲያብሎስ አስመስሎ ያቀረባቸው ሰዎች ከመሪዎቹና ከአጠቃላይ ጥያቄው ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውና የኮሚቴው አባል ያልሆኑ ናቸው።
- ኩሩና ታጋይ ወንድሞቻችን “ሕገ መንግስት የሰጠን የእምነት ነፃነት ይከበርልን” ብለው የማያወላውል አቋማቸው መሆኑን በሚሊዮኖች ተከታዮቻቸው ፊት የተናገሩትን በመደበቅ በወህኒ ቤት ጓሮ በአፈ ሙዝ ተገደው በሉ የተባሉትን ብቻ እንዲቀር የተደረገ ስነ ምግባርና ሃላፊነት የጎደለው መሆኑን በግልፅ ያሳያል።
- ከፊልሙ በስተጀርባ ያለው ምስልና እንቅስቃሴም ፈሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያልታየና ያልነበረ፣ ሆን ተብሎ የዋሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ለማሳሳትና ለማደናገር ሲባል ከሱማሊ የአልሸባብ፣ ከናይጀሪያ የባኮ ሐራም፣ ከየመንንና ከሌሎች ሀገሮች የአልቃይዳ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ቅንጭብጫቢ ለቃቅመው የለጣጠፉት መሆኑንም በግልፅ ያሳያል።
- ከአጠቃላይ በፊልሙ ከተጠቀሱት ዝባንኬዎች ውስጥ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንድትተላለፍ የፈለጉዋት ቃል “አላማችን ከመንግስት ጋር ተዋግተን በመገልበጥ በምትኩ የእሰላም መንግስት ለማቋቋም ነው” የምትለዋ ሐረግ ናት። ይቺ ደግሞ የከሰረች አባባል ናት።
ምክንያቱ ወጣቶቹ ከመታሰራቸው በፊት አላማቸው ለሰፊው ህዝብ ግልፅ አድርገዋልና። ከፊልሙ እንደታየውም በሉ ተብለው ተገደው የተናገሩት እንጂ እምነታቸው እንዳልሆነ ከፊታቸው ይነበባል፣ የከንፈራቸው እንቅስቃሴና ድምፁ ይለያያል፣ እንዲሁም ዓይናቸው ምንና ማንን እየተመለከቱ እየተናገሩ እንደሆነ ያስታውቃል። በአጠቃላይ ፍርሃት፣ ድንጋጤና ሀፍረት እየተሰማቸውና እየተሸማቀቁ እየተናገሩ እንደሆነ ከሁኔታቸው በግልፅ መረዳት ይቻላል።
2. የሙስሊም ሐራካት የፊልም ድራማ አላማው ምንድን ነው?
_ መንግስት ሙስሊም ወጣቶቹ በሰላም የጠየቁትን ጥያቄ በሰላም ከመመለስ ይልቅ የፊልም ድራማ መስራት የመረጡበት ዋና አላማ የህዝቡን አንገት ለማስደፋት ነው። ወጣቶቹ በግልፅ ከመንግስት ጋር በሰላም ለመነጋገር እንፈልጋለን እያሉ በአደባባይ ይጨኹ እንደነበር ይታወሳል። ነገር ግን ህወሓት/ኢሕአዴግ ልዩነት ይዞ ከሌላውን ወገን ማለት ተቃዋሚ ከሚላቸው ወገኖች በግልፅ ለመነጋገር ፍረትና የሞራል መሰረት እንደሌለው ሁሉ ጊዜ ተደጋግሞ ተገልፀዋል። የስርዓቱን ህልውና በማጭበርበር፣ ህዝብ ለህዝብ በማጋጨትና በማለያየት፣ በሙስናና በዝርፊያ፣ በማሸበርና በውሸት ላይ የተመሰረተ ስርዓት ስለሆነ በአደባባይ ቆሞ ለመከራከርና በህዝብ ዘንድ ለመዳኘት ባህሪውንና ተፈጥረውን አይፈቅድለትም። በሰለጠነ መንገድ ከመቻቻል ይልቅ መጃጃል የመረጠበት ዋና ምክንያትም ለዚሁ ነው።
_ ሌላው ዓቢይ ምክንያት ከመለስ ሞት በኋላ ሌላ ቀርቶ ላመነበት ጉዳይ እንኳን ደፍሮ ለመናገር የሚችል ሰው የለም። ሁሉም ማለት ይቻላል በሙና ተዘፍቀው መለስ የፈቀደላቸውን ስኳር እየቃሙ በአንድ ሰው ጭላት ሽፋን ተጠልለው የኖሩ መሆናቸውን ከራሳቸው በላይ ሌላ ምስክር የለም። እነርሱ ራሳቸው በአደባባይ እንደ መሰከሩት ሁሉ ሀገር ማለት መለስ፣ ኢሕአዴግ ማለት መለስ፣ ስርዓት ማለት መለስ፣ ፓርላማ ማለት መለስ፣ ሕግ ማለት መለስ ብቻ እንደነበር አሜን ብለው በመቀበል እንደ በሬ መንጋ በአንድ ሰው ሲነዱ የነበሩ ናቸው። ከመለስ ሞት በኋላም ሕብረተሰቡ ይንቃቸዋል ብቻ ሳይሆን
እነሱም ራሳቸው በራሳቸው የማይተማመኑ ከመሆናቸውም በላይ እሆ ዛሬ በድንጋጤ ተውጠው የፈሪ ዱላ ስር ነው እንዲሉ ህዝብን እየበጠበጡ ይገኛሉ።እንዲያውም ከመለስ ሞት በኋላ መንግስት አለን ወይ በማለት አጣያያቂ ሆኖ ይገኛል። እውነት ለመናገር ከሆነ በአሁኑ ጊዜ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ሀገሪትዋን እያስተዳደረ ያለው መከላኪያ ሰራዊት ነው ቢባል ውሸት አይሆንም። ለዚህም ነው ፈሪ ጨካኝ ነው እንደሚባለው ሁሉ ጡንቻቸውን ለማሳየት ሲሉ በአሁኑ ጊዜ ህዝቡን በማሳርና በማንገላታት ላይ ተጠምደው ይገኛሉ።
ቀደም ብለው የፈሪ ዱላቸውን ጥቃት የጀመሩትም በትግራይ ህዝብ ላይ ነው። ትግራይን በቅድሚያ ሰጥ ረጭ አድርገው ካልገዙና ካላረጋገጡ በሌላ አካባቢ ተቀባይነት እንደሌላቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። አሁን በሙስሊሙ ሕብረተሰባችን ላይ የተከፈተው የጥፋት ዘመቻም መነሻው ፍርሃትና መደናገጥ ነው። የሐራካት የውሸት ድራማ አላማም ህዝቡ እኔን አይተህ
ተቀጣ በሚል ሌላውን ወገን በፍርሃት በሽብር ለመግዛትና መንግስት መስለው ለመታየት እየተደረገ ያለው እኩይ ስራ የወለደው መሆኑን ግልፅ ነው።
3. የሙስሊም ሐራካት የፊልም ድራማ አላማው እንዳሰቡት ተሳክቷልን?
በተሌቪዥን ተደጋግሞ የተላለፈውን የፊልም ድራማ እነሱ እንዳሰቡት አልሆነም። እንዳሰቡት አልተሳካላቸውም የምንልበት ምክንያቶችም የሚከተሉት ናቸው።
_ ፊልሙ ውሸት መሆኑን ገና በቴሌቪዥንና በሚዲያ ከመለቀቁ በፊት ነው የታወቀው።
_ ፊልሙ ጋሃድ ያደረገው ነገር ሙስሊሙ ወጣቶቹ ሽብርተኛ መሆናቸው ሳይሆን በይበልጥ ማንነታቸውን በጉልህ ያጋለጠው የህወሓት/ኢሕአዴግ መሪዎች እነርሱ ራሳቸው ያወጡትን ሕግ የማያከብሩ ጋጥ ወጥና ከሕግ በላይ መሆናቸውን ነው።
_ ፍርድ ቤት ያገደውን ነገር በጉልበታቸው እንዳወጡት በብዙ መልኩ ተጠቅሰዋል። ይህ ድርጊት ደግሞ የሚያሳየው የኢትዮጵያ ህዝብ የሕግ ዋስትና የለውም ማለት ብቻ ሳይሆን ሃላፊነት የሚሰማውና በሕግ የሚገዛ ኢትዮጵያዊ መንግስት እንደሌለውም በግልፅ አሳይቷል።
_ ይህ ተግባር ከሁሉም በላይ የሚያሳየው በህዝብ ላይ ያላቸው ንቀትና ማንአለብኝነት መሆኑን አያጠያይቅም። ነገር ግን እነሱ እንዳሰቡት ህዝቡን አንገንት አስደፍተውና ለያይተው ለመግዛት ቀርቶ እንዲያውም በሕብረተሰቡ ዘንድ ከመቸው በላይ እንዲተባበርና እንዲነሳሳ አደርገው እንጂ አልተሰካላቸውም።
ትግሉን ያቀጣጥላዋል እንጂ አንገት አያስደፋንም!!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!
             ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment