* ምርጫ ቦርድ “ሆደሰፊ” እየሆንኩ ነው ብሏል (እንመነው እንዴ?) ዛሬ ከናንተ ምን እንደምፈልግ ታውቃላችሁ? የኢህአዴግን “ትዕግስት” እና የምርጫ ቦርድን “ሆደሰፊነት” ብቻ! (ራሳቸው ሲናገሩ ሰምቼ እኮ ነው!) ሁለቱ አለን የምትሉ ከሆነ ግን በነፃነት ማውጋት፤ አዳዲስ ምስጢሮችን መለዋወጥ፤ ፖለቲከኞችን ማማት፤ ባለሥልጣናትን “መቦጨቅ” (ማስረጃ ባይኖረንም በመረጃ) እንችላለን፡፡ እንዳልኳችሁ እናንተ ብቻ ትዕግስቱና ሆደ ሰፊነቱ ይኑራችሁ፡፡ እኔ የምለው ግን--- ሰሞኑን ምርጫ ቦርድ “ሆደሰፊነቱን” በኢቴቪ ሲናገር ሰምታችኋል? (የአበሻ ይሉኝታ አያውቅም ልበል?) ከኢህአዴግ ጋር የፓርቲዎች ምክር ቤት አባል የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የእጩዎች ማስመዝገቢያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው ጠይቀው፤ በአስር ቀን አራዘምኩ ብሎ እኮ ነው “ሆደ ሰፊ ነኝ” ያለው (ሆደ ሰፊ አያውቅም ማለት ነው!) ባለፈው ሳምንት የኢህአዴግ ፅ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን ከምርጫው ጋር በተገናኘ ስለተቃዋሚዎች ያሉትን ሰምታችኋል አይደል? (ኢህአዴግ ግን አሳዘነኝ!) በምርጫው ይሸነፋል ብዬ እንዳይመስላችሁ! ቢሆንማ አድርጎት ነው! (መታሰቡስ!) በነገራችሁ ላይ አንድ ፖለቲከኛ ወዳጅ አለኝ --- ሁሌ ምርጫ ሲቃረብ “አስማተኛ ፓርቲዎች ካልተፈጠሩ በስተቀር ኢህአዴግ በምርጫ አይሸነፍም!” ይለኛል (የሚያውቀው ነገር ቢኖር ነው) አስማቱን ትተን ወደ ነባራዊው እውነታ ስንመጣ --- አቶ ሬድዋን ምን ነበር ያሉት? “የተቃዋሚዎች በምርጫው መሳተፍና አለመሳተፍ ትርፍም ኪሳራም የለውም” በዚህ አነጋገራቸው የበሸቀ ሌላ ወዳጄ “የሳቸውም ንግግር ያው ነው!” አለኝ - በንዴት ጨሶ (ትርፍም ኪሳራም የለውም ማለቱ እኮ ነው!) አንድ ታዋቂ የአገር ውስጥ የፖለቲካ ተንታኝ በሰጡት አስተያየት ደግሞ “ንግግሩ ለሃያ አንድ ዓመት በሥልጣን ላይ ለቆየ ፓርቲ አይመጥንም” ብለዋል፡፡
ደግነቱ ይሄን አስተያየት በሰጡ ማግስት ነፃ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ አሜሪካ መብረራቸውን ሰምቻለሁ (አሜሪካ የመሸጉ ፖለቲከኞቻችን ስንት ደረሱ ይሆን?) እኔ የምለው ግን--- ኢህአዴግ መቼ ይሆን ዲፕሎማት የሚዋጣለት? (ከዚህ በኋላማ ተስፋ የለውም-- አረጀ እኮ!) አሁን እንግዲህ ለየት ወዳለው የዛሬ አጀንዳችን ብወስዳችሁ ሳይሻል አይቀርም፡፡
የአሁኑ ዘመን ትውልድ ራሱ ከልጅነት ሳይወጣ ልጅ አሳዳጊ መሆኑን ይወቅስና፣ የሰው ልጅ 40 ዓመት ሳይሞላው በፊት ወላጅ መሆን አይገባውም በማለት ልጆችን ማሳደግ የሚገባቸው አያቶች እንደሆኑ ይጠቁማል፡፡
በአገራት መካከል ሁልጊዜም አለመስማማት መኖሩ አይቀርም፡፡ አለመስማማት ችግር የለውም፡፡ እያንዳንዱ አገር ልዩ መሆኑን የሚያሳይ ጤናማ ምልክት ነው፡፡ አለመስማማትን በኃይል መፍታት ግን ከፍተኛ ያለመብሰል ምልክት ነው፡፡ በዓለም ላይ የሃይል መፍትሄ የማይወገድበት ምክንያት የለም፣ አገራቱ ለማስወገድ ፈቃደኛ እስከሆኑ ድረስ ነው ታዲያ፡፡ አንዳንዶች በገፍ የሚሞቱት ሰዎችና የሚጠፋው ህይወት ይሄንን ፈቃደኝነት ለማምጣት በቂ ነው ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ኋላ ቀር ባህል ለሰፈነበት እንዳንተ ያለው አገር ግን ነገሩ እነሱ እንደሚያስቡት አይደለም፡፡ ሙግት ማሸነፍ እችላለሁ ብለህ እስካሰብክ ድረስ መሟገትህ አይቀርም፡፡ በጦርነት ማሸነፍ እችላለሁ ብለህ እስካሰብክ ድረስም ትዋጋለህ፡፡ ለዚህ ታዲያ መፍትሄው ምንድነው?መፍትሄ የለኝም፡፡ ምልከታ እንጂ! --- የአጭር ጊዜ መፍትሄ የሚሆነው አንድ የዓለም መንግስት መመስረት ነው - አለመግባባቶችን የሚፈታ የዓለም ፍርድ ቤት ያለው! (አሁን እንዳለው ዓለማቀፍ ፍ/ቤት ውሳኔው ችላ የማይባል መሆን ግን አለበት) የትኛውም አገር የቱንም ያህል ጉልበት ቢኖረውና ተፅዕኖ ማሳረፍ ቢችልም ሌላው አገር ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝር ዋስትና የሚሆን አንድ የዓለም ሰላም አስከባሪ ኃይል ሊመሰረት ይችላል፡፡
በዚህ መንገድ ብቻ ነው በዓለም ላይ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው፡፡ ያኔ --- የትናንሽ አገራት ዕጣ ፈንታ በትላልቅ አገራት መልካም ፈቃድ ላይ የተመረኮዘ መሆኑ ይቀራል፡፡ በራሳቸው ሃብት ላይ መደራደራቸው ያቆማል፡፡ ቁልፍ መሬታቸውን ለውጭ ወታደራዊ ሃይል (ቤዝ) አሳልፈው አይሰጡም፡፡ … አንድ አገር ብትወረር 160ዎቹም የዓለም አገራት በተቃውሞ ይነሳሉ፡፡ --- ትላልቅ አገራት የዓለምን የሃብት ክምችት ለብቻቸው መቆጣጠርና ማከማቸታቸውም ይቀራል፡፡ ይልቁንም ሃብቱን ለሌሎች አገራት እኩል እንዲያካፍሉ---ይገደዳሉ፡፡ የመላው ዓለም መንግስትም የጨዋታውን ሜዳ ለሁሉም እኩል ያደላድላል፡፡
(ደራሲውና አንባቢው ስለዘመኑ የትምህርት ሥርዓትም የጦፈ ክርክር አድርገዋል፡፡ ቀንጨብ አድርጌ ላስነብባችሁ! ) ደራሲ - ስለትምህርት ልትነግርኝ ትፈቅዳለህ? አንባቢው -- እንዴታ! አብዛኞቻችሁ የትምህርትን ትርጉም፣ ዓላማና ጥቅም በትክክል አልተረዳችሁትም፡፡ የትምህርት አሰጣጥ ሂደትንማ ባናነሳው ይሻላል፡፡ ---- አብዛኛው የሰው ዘር የትምህርት ትርጉምና ዓላማ እንዲሁም ጥቅም ዕውቀት ማስተላለፍ ነው ብሎ ደምድሟል፡፡ አንድን ሰው ማስተማር ማለት - የአንድን ቤተሰብ፣ ጐሳ፣ ህብረተሰብ፣ አገር፣ ዓለም የተከማቸ ዕውቀት መስጠት ሆኗል! ሆኖም ትምህርት ከዕውቀት ጋር እምብዛም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ደራሲ -ትምህርት ከዕውቀት ጋር ካልተገናኘ ከምን ጋር ነው የሚገናኘው ታዲያ? አንባቢው- ከጥበብ፣ ከብልሃት ደራሲ-ልዩነታቸው ምንድነው? አንባቢው- ጥበብ ወደ ኑሮ የተቀየረ እለት በእለት የተቀየረ ዕውቀት ነው፡፡ -- ለልጆቻችሁ ዕውቀት ስትሰጧቸው ምን ማሰብ እንዳለባቸው እየነገራችኋቸው ነው፡፡ ማወቅ ያለባቸውን ነው የምትነግሯቸው፤ እውነትን ነው እንዲረዱ የምትፈልጉት፡፡ ጥበብ ስትሰጧቸው ግን ማወቅ ያለባቸውን ወይም እውነቱን አይደለም የምትነግሯቸው፡፡ ይልቁንም የራሳቸውን እውነት እንዴት እንደሚያገኙ ታስተምሯቸዋላችሁ፡፡ ደራሲ -ግን እኮ ያለ ዕውቀት ጥበብ ሊኖር አይችልም፡፡ አንባቢው - እስማማለሁ፡፡
ለዚህ እኮ ነው ጥበብ ሰጥታችሁ ዕውቀትን መዘንጋት የለባችሁም ያልኩት፡፡ የተወሰነ መጠን ዕውቀት ከአንደኛው ትውልድ ወደ ቀጣዩ መተላለፍ አለበት፡፡ በተቻለ መጠን ግን ትንሽ ቢሆን ይመረጣል፡፡ የቀረውን ህፃኑ ፈልጐ ያግኘው፡፡ ዕውቀት ይረሳል፤ ጥበብ ግን ፈፅሞ የሚረሳ አይደለም፡፡ ደራሲ - ስለዚህ ት/ቤቶቻችን ትንሽ ትንሽ ማስተማር ነው ያለባቸው ማለት ነው? አንባቢ - ት/ቤቶቻችሁ አትኩሮታቸውን መለወጥ አለባቸው፡፡ አሁን በእጅጉ ያተኮሩት ዕውቀት ላይ ነው፡፡ ለጥበብ ትንሽ የተቆጠበች ትኩረት በመስጠት፡፡ በትንታኔያዊ አስተሳሰብ፣ በችግር መፍታትና በሎጂክ ዙርያ የሚሰጡ ትምህርቶች ለብዙ ወላጆች አስፈሪ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ትምህርቶች ከካሪኩለሙ እንዲወጡ ይሻሉ፡፡ እንዲህ የሚያደርጉት የራሳቸውን የአኗኗር ዘይቤ ጠብቀው ለማቆየት ነው፡፡ እንዴት ቢሉ … የራሳቸውን ሳይንሳዊ የአስተሳሰብ ስልት እንዲያዳብሩ የተፈቀደላቸው ህፃናት የወላጆቻቸውን ሥነ ምግባርና አጠቃላይ የኑሮ ዘይቤ መከተል አይፈልጉም፡፡ የአኗኗር ዘይቤያችሁን ጠብቃችሁ ለማቆየት ስትሉ የትምህርት ስርዓታችሁ የህፃናትን ችሎታ ሳይሆን ትውስታቸውን ብቻ እንዲያዳብር አድርጋችሁ ነው የቀረፃችሁት፡፡ እንግዲህ የቀረውን መፅሃፉን ፈልጋችሁ አንብቡት፡፡ እኔ ግን አንድ ነገር በጣም ተመኘሁ--- እንደዚህ አሜሪካዊ ደራሲ ከአንባቢው ጋር የወያየት እድል ባገኝ አልኩ ለራሴ፡፡ ስለአገሬ ፖለቲከኞች ብዙ ብዙ የምጠይቀው ነገር ስላለኝ እኮ ነው፡፡ የዘመናት የፖለቲካ እንቆቅልሻችን እንዴት እንደሚፈታ ብልሃቱን ይሰጠኝ ዘንድም መወትወቴ አይቀርም ነበር፡፡ የእኛ የፖለቲካ ችግር ሰው ሰራሽ ቢሆንም መፍትሄው በሰው አቅምና ችሎታ የማይገኝ መሆኑን አይተነዋላ!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
ከዘካሪያስ አሳዬ
No comments:
Post a Comment