ትግሉ የሥልጣን ብቻ ሳይሆን የርዕዮተ ዓለምም ነው!
ካርል ማርክስ “የዓለም ሰራተኞች ተባበሩ፤ ከሰንሰለቱ በስተቀር የሚቀርባችሁ ነገር የለም ብሎ ነበር”፤ እኔም እላለሁ፤ የኢትዮጵያ ተቀዋሚዎች ሁሉ ተባበሩ፣ ከእስራት ሰልሰለቱ በስተቀር የሚቀርባችሁ
ምንም ነገር የለም (All
Ethiopian Oppositions, Unite! You have nothing to lose but your chains) እዚህ ላይ ማርክስን መጥቀሴ ማርክስሲት ሆኜ አይደለም፤ አባባሉ እውነትነት ያለው ሆኖ ስለአገኘሁት
እንጂ! ለነገሩ ማርክስን በደንብ ሳያውቁ ማርክሲስትም ፀረ ማርክስሲትም መሆን አይቻልም።
ከቅርብ ጊዜ 28ቱ የተቃውሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲሰፋ፣ ምርጫው ፍትሃዊና ገለልተኛ
እንዲሆኑ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች በአግባቡ ሳይመለሱ ወደ ምርጫው እንደማይገቡ በሙሉ ድምፅ ወስኗል። ይህ ትብብር ቀጣይነት የሚኖረው
ከሆነ በእውነቱ በጣም ታሪካዊ ሊባል የሚችል ነው። የዛሬው ፅሁፌ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሆኖ በቀጣይ ቢደረጉ መልካም ነው ብዬ
በማስባቸው ነገሮች ላይ የራሴን ሀሳብ ለመሰንዘር ነው።
ሃያ ስምንት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች “ምንም ውጤት በሌለው ምርጫ አንሳተፍም፣ የአገር ሀብትም በማባከኑ ወንጀል ላይ ተሳታፊ አንሆንም” ብለው ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው በራሱ ትልቅ ነገር ነው። በእኔ እይታ ከዚህ ረብ የለሽ
የምርጫ ሂደት ራስን ማግለል ከሰላማዊ አመፅ -አልቦ ትግል አመራጮች አንዱ መንገድ
ነው -ከአንባገነን መንግስት ጋር አለመተባበር! ይህ
በራሱ ግን በቀጣይ እርምጃዎች እስካልተደገፈ ድረስ ውጤቱ “ምንም” ሊሆን ይችላል። ማርክስ “የፕሮግራም
ጋጋታ ብቻውን ለውጥ አያመጣም”
ብሏል። ይህ ሀቅ አሁንም ይሰራል። ወደ ውጤት የማይቀየር ዘጠና ዓይነት
ፕሮግራም መኖር ምንም አይፈይድም። ትግሉ ለማካሄድ መሰረታዊ በሆኑ ተጨባጭ አጀንዳዎች ላይ ብቻ ተመርኩዞ፣ ባለው ላይ እየተደመረ
የሚሄድ የተመረጠ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መኖር አለበት። ወደ ምርጫ መግባት አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ተመራጭ የትግል ስልት አይደለም።
ከዚህ አንፃር አሁን ወደ ምርጫ አለመግባቱ ቀዳሚው ተመራጭ ስልት ሆኖ ተገኝቷል ማለት ነው። ከዚህ በኋላስ ምን እናድርግ የሚል
ጥያቄ መምጣቱ የሚጠበቅ ነው። በተስፋ መቁረጥ ስሜት፣ አንገት ደፍቶ መቀመጥ “ፖለቲካዊ
ለውጥ ለማምጣት ተሰልፈናል”
ከሚሉ ሰዎች የሚጠበቅ ነገር አይደለም። በዚህ ጊዜ ትክክለኛው አማራጭ
የሚሆነው ሰላማዊ፣ አመፅ -አልቦ ትግል ለማካሄድ መነሳት ነው።
ይህ ሰላማዊ፣ አመፅ-አልቦ ትግል ጄን ሻርፕ “ከአምባገነንነት
ወደ ዴሞክራሲ”
በሚለው መፅሐፉ ላይ እንዳስቀመጠው 198 ደረጃዎች አሉት። አሁን በምርጫው ላለመሳተፍ ስንወስን፣ አንዱን ብቻ ነው በተወሰነ መልኩ
የተጠቀምነው። ገና 197
ደረጃዎች ይቀራሉ ማለት ነው። እንግዲህ ተግቶ ደረጃ በደረጃ አንድ
በአንድ መተግበር ያስፈልጋል።
ይህ ትግል ጥብቅ ዲሲፒሊን የሚጠይቅ፣ ነገሮች ባልታሰበ
ሁኔታ ወደ አመፅና ብጥብጥ እንዳያመሩ ጥንቃቄ ማድረግ ግድ የሚል፣ ሐላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች ብቻ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ነው።
እንደ ማህተመ ጋንዲ ያለ የሞራል ልዕልና ያለው መሪ፣ እንደ ህንዶች ያለ ስርዓት ያለውና በአንድ ላይ ያለልዩነት መሰለፍ የሚችል
ህዝብ መኖር የሚጠይቅ ነው። ስለዚህ ይህ እንዲሆን ከተፈለገ በመጀመሪያ እንደ ህዝብ ያሉብንን ልዩነቶች ለማጥበብና ለማመቻመች ጠንክሮ
መስራት ያስፈልጋል።
ቀጥሎ መስራት የሚኖርበት ስለሰለማዊ፣ አመፅ-አልቦ ትግል በስፋትና በጥልቀት ማስተማር፣ በተግበር ለዚህ መርህ መገዛት እንዲቻል ደረጃ
በደረጃ ማለማመድ ያስፈልጋል። በዚህ ዙሪያ ሞስሊም ወንድሞቻችን እስካሁን እያሳዩት ያለው ሰላማዊ ተቃውሞ የሚደነቅ ነው። አገር
በቀል የሰላማዊ ትግል ስልት በመሆኑ ለእኛ ጥሩ ትምህርትና ሞዴል ሊሆን የሚችል ነው። ይህ በራሱ የሚያሳየው ነገር አለ። ህዝባችን
በአግባቡ የሚመራውና አምኖ ሊከተለው የሚችል መሪ ድርጅት ካገኘ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ አያዳግተውም።
እዚህ ላይ መሰመር ያለበት አንድ ዋና ነጥብ ግን አለ።
የዚህ ዓይነቱ የፖለቲካ ትግል እርስ በእርስ ለስድብና ለዱላ የሚገባበዙ የፖለቲካ መሪዎች የሚመሩት ሊሆን አይችልም። በትምህርት
ብዛት ወይም በፖለቲካው ብዙ ዘመን በማስቆጠርም አይደለም። “እንትና ወደ
ፓርላማ የገባው ኢህአዴግ ስለደገፈው ነው፤ እንትና ደግሞ የኢህአዴግ ተለጣፊና ተቀላቢ ነው” እያሉ በማውራትና በማስወራትም የሚሳካ አይደለም። በተጨባጭ አጀንዳዎችና የፖለቲካ እስትራቴጂዎች
ላይ የተመስርተ፤ ሊታይ የሚችል ተጨባጭ እንቅስቃሴ ማድረግ ግድ የሚል ነው። ትርጉም የሌለው ስብሰባ በየጊዜው በማካሄድም አይደለም።
ስብሰባ በራሱ ቁም ነገር አስገሽቶ አያውቅም። ፖለቲካዊ ትግል ማካሄድ ማለት በየጊዜው ስብሰባ ማካሄድ ማለት አይደለምና ነው።
እንግዲህ ከዚህ በኋላ የፖለቲካ አመራሮቹ፣ ፖለቲካውን
በተገቢው ሁኔታ ለመምራት ወገባቸውን ጠበቅ፣ ምራቃቸውን ዋጥ አድርገው መነሳት ይኖርባቸዋል። ሕገ መንግስቱን ለማስከበር በሚደረገው
ትግል ሐላፊነት ወስደው ለመምራት፣ መታሰርም ካለ ለመታሰር ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል። “እኔ ሜዳ ሜዳውን ነው መታገል የምፈልገው እንጂ መታሰር እፈራለሁ” የሚል የፖለቲካ መሪ ካለ አቋሙን መመርመር፣ ካልሆነም ራሱን ከአሁኑ ከፖለቲካው ማግለል
አለበት። ከዚህ በኋላ በፖለቲካው የሚኖሩና
ለፖለቲካው
የሚኖሩ ሰዎች መንገዳቸው አንድ ላይ መሆን የለበትም። ሕገ መንግስቱን የሚጥስ መንግስት ባለበት አገር ሕገ መንግስቱን ለማስከበር
መነሳት በራሱ ወንጀል ሆኖ እስር ቤት ሊያስወርድ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።
ራሰቸውን ከምርጫ ያገለሉ ፓርቲዎች ቀጣይ እርምጃ መሆን
ያለበት ህዝቡን ሰብስቦ ማነጋገር ነው። መሰብሲቢያ ቦታ እንኳ ባያገኙ ሜዳ ላይም ቢሆን መጥራት ይኖርባቸዋል። በምርጫው ላይ ለመሳተፍ
“የምርጫውን ሜዳ ይስተካከል፣ ምርጫ ቦርድም ገለልተኛ ይሁን” ብለን የጠየቅነው ጥያቄ የኢህአዴግ መንግስትና ምርጫ ቦርድ የዝሆን ጆሮ ሰጥቶውታል። ስለዚህ
ይህ ነገር እስኪፈፀም ድረስ ህዝቡ ሰላማዊ ትግል እንዲያካሄድ መጥራትና መምራት ያስፈልጋል። ፓርቲዎቹ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን
ይዘው ሰልፍ መውጣት፣ አመራሮቹም መንገድ ላይ ተኝቶ ማደርና መቀመጥ መጀመር ይኖርባቸዋል። ሕዝቡ የፓርቲዎቹን ቁርጠኝነት ሲገነዘብ
በልቡ ሙሉነት ለመደገፍ ይነሳል፤ መብቱን ለማስከበርም በፅናት መቆም ይጀምራል።
የፓርቲዎቹ አመራሮች እንዲህ በሚያደርጉበት ጊዜ ሊታሰሩ
ስለሚችሉ ሌላ ተጠባበቂ አመራር ማዘጋጀት፣ እንደገና ያ አመራር ሲታሰር ደግሞ እንደዚሁ ሌላ እየተተካ ጥያቄው እስኪመለስ ድረስ
ትግሉን መቀጠል ያስፈልጋል። አንድ እውነት አለ። ሁላችንንም ለመታሰርና ለመሞት እስከተዘጋጀን ድረስ፣ ኢህአዴግ ሁሉንም ማሰር፣
ሁሉንም መግደል ፈፅሞ አይችልም። እነ አንዷለም እና እነ በቀለ ገርባ ታሰሩት ሌሎቻችን ዝም በማለታችን ነው። ይህ ስርዓት የመለወጡ
ቁርጠኝነት በሁላችን ዘንድ እስከሌለ ድረስ በተወሰኑ ሰዎች ትግል ብቻ ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።
ኢህአዴግ ሁኔታዎች አስገድደውት ካልሆነ በስተቀር በእኩልነት
ሜዳ፣ በገለልተኛ ዳኛ ስር ሆኖ በምርጫ አይወዳደርም። በማያጠራጥር ሁኔታ ቢሸነፍም ስልጣኑን በሰላም አያስረክብም። ስለዚህ እነዚህ
ቅድመ ሁኔታዎች ማለትም እኩል የመወዳደሪያ ሜዳና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ በትክክል እስኪኖር ድረስ በምርጫ የመሳተፉ ጉዳይ መታሰብ
የለበትም። በዚህ ጉዳይ ላይ ፓርቲዎቹ ቁርጠኛ አቋም ከያዙ ገዥው ፓርቲ በምርጫ ቦርድ በእኩል “በምርጫ ስላልተሳተፋችሁ” ብሎ የፓርቲዎቹ
ህጋዊ ሰርተፊኬት ወደ መቀማቱ እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህ ጊዜም ቢሆን ትግሉ ወደ ህዝባዊ ንቅናቄ እንዲሸጋገር ተግቶ
መስራት እንጂ መደናገጥ አያስፈልግም። የግብፁ ወንድማማቾች ፓርቲ ሕጋዊ እውቅናው በሙባረክ መንግስት በእኩል ቢያጣም እውነተኛ ህልውናውን
ግን አላጣም ነበር። ሌላው ቀርቶ አባላቱ በግል እየተወዳደሩ የፓርላማውን አስራ አምስት በመቶ መቀመጫ እስከመያዝ የደረሱበት ጊዜ
ሁሉ ነበር። ከዚህ የምንረዳው አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሴርተፊኬቱ ሲቀማ የሚጠፋ ከሆነ ሲጀመር የፖለቲካ ፓርቲ አልነበረም ማለት ነው።
የአንድን ፖለቲካ ፓርቲ ህልውና በጠንካራ ህዝባዊ መሰረት ላይ እንጂ በሰርቴፍኬት ላይ መቆም የለበትም። ስለዚህ ህልውናውን አላግባብ
በሚያጣበት ወቅትም ቢሆን ትግሉ ባለው ህዝባዊ መሰረት መቀጠል የሚችል፣ ከሰርተፊኬት በላይ የሆነ አቅም ያለው ኃይል መሆን መቻል
ይኖርበታል። አንድ ፖለቲካዊ ፓርቲ ፅኑ ህዝባዊ መሰረት፣ ጠንከራ አደረጃጀትና አመራር ከሌለው፣ በስለላ፣ በጦር፣ በኢኮኖሚና በመዋቅር
በደንብ የተደራጀን መንግስት ማሸነፍና ስርዓት መለወጥ አይችልም።
ከሁሉም በላይ በእኛ አገር ያለው ተጨማጭ ፖለቲካዊ
ሁኔታ በደንብ ማጤን ያስፈልጋል። የአገራቸን ችግር የስልጣን ጥያቄ ብቻ አይደለም። ትግሉ የርዕዮተ ዓለም ትግል መሆኑንም መረዳት
ያስፈልጋል። ሁለት አብረው ሊሄዱና ሊታረቁ የማይችሉ የአብዮታዊ ዴሞክራሲና የሌበራል ዴሞክራሲ ትግል ነው እየተካሄደ ያለው። ኢህአዴግ
መሰረቱ ማርክስሲት ድርጅት ስለሆነ ይህን ቅራኔ በሚገባ ይረዳዋል። ስለዚህ ዋናው ነጥብ ኢህአዴግ በትክክል በሁሉም ነገር እስካልተሸነፈ
ድረስ በምርጫ ስለተሸነፈ ብቻ ስልጣኑን ያስረክባል ማለት እንዳልሆነ በደንብ መታወቅ አለበት። ኢህአዴግ ሁልጊዜ በምርጫ የሚወዳደረው
እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ሆኖ ነው። እንደሚሸነፍ ቢያውቅ፣ ማወቅ ብቻ አይደለም ቢጠረጥር ወደ ምርጫ ውድድር አይገባም።
ስለዚህ ከገዥው ፓርቲ ጋር በምርጫ ለመወዳደር የሚቻለው
በመጀመሪያ ነፃና በገለልተኛ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ ሲፈጠር ብቻ ነው። ኢህአዴግ ይህን አምኖ እሰኪቀበል
ድረስ ግን ሰላማዊ ትግሉን ብቻ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። ኢህአዴግን ወደዚህ ደረጃ ሳያመጡ ከእርሱ ጋር በምርጫ መወዳደር
እርሱን ከማጀብ፣ የእርሱን ድል ከማድመቅ ውጪ ትርጉም አይኖረውም። በዚህ በማጀቡ ሂደት ከአሁን በፊት እንደታየው የተወሰኑ ተመራጮች
ወደ ፓርላማ ማስገባት ይቻል ይሆናል። የስርዓት ለውጥ ግን በዚህ መንገድ አይመጣም፤ እስካሁን የተጓዝንበት ልምድ የሚያሳየውም ይህ
ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
ወጣት ደራሲ አስራት አብርሃም የፖለቲካ ተንታኝና የመድረክ
አባል የሆነው የዓረና ትግራይ የተቃዊሚ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነው።
(ከአስራት አብርሃም)
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
ከሰብኣዊ
እውነት ነው የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ሁሉ ተባበሩ፣በጣም ነው አባባሉን የውደድኩት እውነት ነው ተቃዋሚዎች አሁን ነው ጊዜው ነፃ የምንውጣበት ዋናው ዓላማውን ጠንቅቀን በማውቅ ነፃዋን ኢትዮጵያ ነው የምንናፍቀው ውገን ጊዜው አሁን ነው ወገን ሁሉም የአቅሙን ለኢትዮጵያ ይሰንዝር እላለሁ።
ReplyDeleteአምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ፣ ይጠብቃት