Tuesday, February 26, 2013

የሚያዝያው ምርጫ ነጠላ አልበም - Quick Fix!



የመብራት ኀይል “ትራንስፎርመር” ተቃጠለ (ትራንስፎርሜሽኑስ?)
ቴሌኮም “ሲምካርድ ከእኔ፤ ኔትዎርክ ከእናንተ” ቢለን ይሻላል
ምርጫ ቦርድ “ምርጫው እንጂ ምህዳሩ አያገባኝም” ብሏል
ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ የሞባይሌ ቴክስት ሜሴጅ (SMS) ድምፅ ነው፡፡ በጣም ተናደድኩኝ፡፡ ሰዓቱ እኮ ገና አንድ ሰዓት አልሆነም፡፡ ቀን ቀን በኔትዎርክ መጨናነቅ ከአገልግሎት ክልል ውጭ የሚሆነው ሞባይሌ በዚህ ሌሊት እንዴት ይረብሸኛል? ይሄኔ እኮ የራሱ የቴሌኮም ማስታወቂያ ይሆናል… ብዬ አሰብኩ፡፡ “የ100 ብር ካርድ ስትሞሉ 15 ደቂቃ ነፃ የአየር ሰዓት ታገኛላችሁ” የሚለው አይነት ማለቴ ነው (ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ!) ሌላ ሌላው ማትጊያ ቀርቶብን ኔትዎርክ ብናገኝ እኮ ይበቃን ነበር፡፡ አሊያም ደግሞ ሃቁን በይፋ ቢነግረን ቁርጣችንን እናውቀዋለን፡፡ “አያችሁ ከዛሬ ጀምሮ የኔትዎርክ ጉዳይ አይመለከተኝም፤ ሲም ካርድ ከእኔ፤ ኔትዎርክ ከናንተ” ቢለን እኮ አርፈን እንቀመጣለን፡፡ ወይም ኔትዎርክ ከቻይና እናፈላልጋለን ፡፡

ባለፈው ሳምንት በኢቴቪ በቀረበ የፓናል ውይይት ላይ የመብራት ሃይል ኮርፖሬሽንና የቴሌኮም ተወካዮች ከነዋሪዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና ቅሬታዎች አጥጋቢ መልስ አጥተው ሲጨናነቁ አይቼ አፈርኩም አዘንኩም፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ ምን አሉ መሰላችሁ? “ለምን አልቻልንም ፤ ከአቅማችን በላይ ነው ብላችሁ እውነቱን አትነግሩንም? ስንት ዘመን ነው ይሄንን እየሰራን ነው… ያንን እያደረግን ነው የምትሉት!” ሲሉ አፋጠጧቸው፡፡ በነገራችሁ ላይ እቺ አባባል ለእነ ቴሌኮም ብቻ ሳይሆን ለእነኢህአዴግም ትሰራለች፡፡ አዎ አንዳንዴ እኮ ማመን አለባቸው (ስንት ዘመን በሽወዳ!) እናላችሁ --- እነ ኢህአዴግና ሌሎችም ሲያቅታቸው “አልቻልንም! ከአቅማችን በላይ ነው” ቢሉን ትልቅ ውለታ ነው (የሚችል እንፈልጋለና!) 
ኢህአዴግ ለምሳሌ “አልቻልኩም! ከአቅሜ በላይ ነው!” ማለት እየፈራ (እያፈረ ይሆን እንዴ!) ስንቱን ነገር ሞከረብን (ላብራቶሪ እኮ አይደለንም!) አሁን በቅርቡ እንኳን BPR ዒላማውን አልመታም ተብሎ የዜጐች ቻርተር የሚባል ነገር ተጀምሮ ነበር (እሱን ያስተዋወቁን ከፍተኛ ባለሥልጣን ግን የት ገቡ?) ከዚያስ? የእሱን ውጤት ሳናውቅ “ካይዘን” የሚባል የጣልያን መኪና ስም የመሰለ ነገር መምጣቱን ሰማን፡፡ ካይዘንን ጠግበን ሳንጨርስ ሰሞኑን ደግሞ “Quick fix” (ለብለብ ብየዋለሁ) የሚባል ነገር መጥቶብናል (መቼም መጥቶልናል አይባል!) ይሄ እንኳን ራሱ ስሙም ዕድሜው አጭር እንደሆነ ይጠቁማል - “Quick fix” ይላላ! ችግሮችን ለጊዜው በጥድፍያ የሚፈታ እንጂ ዘላቂ አይደለም፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ምን ይሉታል መሰላችሁ? “የምርጫ ጊዜ መፍትሔ” ለዚህ እኮ ነው የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (እንደመብራት ሃይል ያሉት ማለቴ ነው) ሰሞኑን ይሄን ቃል ደጋግመው ሲጠሩት የምንሰማው፡፡

የኢህአዴግ ቱባ ቱባ አመራሮችማ ከ“Quick fix” ጋር ፍቅር የያዛቸው ነው የሚመስሉት፡፡ (ማን ይሆን የዚህ ነጠላ አልበም ደራሲና አቀንቃኝ) እኔ በበኩሌ ግን ተመችቶኛል፡፡ (ስሙን ማለቴ ነው!) ለዚህ እኮ ነው “የሚያዝያው ምርጫ ነጠላአልበም”ያልኩት፡፡ 
ብዙ ሳመነታ ቆይቼ በማለዳ የተላከልኝን ቴክስት ልመለከት ሞባይሌን ከኮሜዲኖው ላይ አነሳሁት፡፡ የሻማ እንጥብጣቢ ተለጥፎበታል፡፡ ለካስ ትላንትናና ከትላንት ወዲያ የኛ ሰፈር “ከመብራት አገልግሎት ውጭ” ነበር፡፡ ይታያችሁ --- ሁለት ቀን ሙሉ ኤሌክትሪክ የለም፡፡ በእርግጥ መብራት ሃይሎች በኢቴቪ ከቀረበው የፓናል ውይይት በኋላ ተነስቶ የማያውቅ ስልካቸውን ማንሳት እንደጀመሩ አከራዬ እንደትልቅ ድል አብስረውኛል፡፡ ስልክ ማንሳት ማለት ግን መብራት ይመጣል ማለት አይደለም፡፡
የመብራቱ ነገር በአዲሱ ፈጣን የችግር አፈታት ዘዴም “Quick fix” ሊፈታ እንዳልቻለ ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ሰምቻለሁ፡፡ የመብራት ሃይል ችግር ምንድነው ብዬ ሳጠያይቅ ምን ተባለ መሰላችሁ? የትራንስፎርመር መቃጠል! እኔን ያሳሰበኝ ግን ይሄ አይደለም፡፡ የትራንስፎርመር መቃጠል “ትራንስፎርሜሽኑ” ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ነው ስጋት የሆነብኝ፡፡ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ከተቃጠለ እኮ ለየልን ማለት ነው፡፡ ሻማ በማብራት አናልፈውማ (ሻማውስ ሲገኝ አይደል!) እኔ የምለው ---- መብራት ሃይል ምን እያሰበ ይሆን? ለነገሩ የእውነት ዕቅዱን ቢጠየቅ ምን እንደሚል ታውቃላችሁ? “በአጭር ጊዜ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ለጐረቤት አገራት ለመሸጥ አስበናል” (የእኛን አጥፍቶ የጐረቤት ሊያበራ!)
ብዙም ሳልጓጓ በሞባይሌ የተላከልኝን ቴክስት ሜሴጅ ማንበብ ጀመርኩ፡፡
አንድ ወዳጄ ነው የላከልኝ፡፡እንዲህ  ይላል - 
ቴሌ            ኔትዎርክ                የለም!
ኤልፓ           መብራት               የለም!      
ውሃናፍሳሽ       ውሃ                   የለም!
ፓርላማ
      ተቃዋሚ    የለም!               የለም!                                      

  ባንክ                   ዶላር                       የለም!                                         
ኢትዮጵያ -ኑሮ የለም! በጠዋት ጨለምተኛ መልዕክት አነበብኩ - ያውም በባዶ ሆዴ! እኔ ደግሞ ከቴክስቱ መጨረሻ እንዲህ የሚል የግል እሮሮ ጨመርኩበት -
እኔ ቤት - እንቅልፍ የለም!
ምነው ቢሉኝ የመፃፍና መናገር መብት የለማ!
አይገርምም--- ወዲያው ደግሞ በሬ ተንኳኳ - ቴክስቱን የላከልኝ ወዳጄ ነው የመጣው፡፡ እንቅልፍ የማጣው በቴሌ በሚላከው ቴክስት ሜሴጅ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ የኑሮና የገቢ አለመመጣጠኑም ራሱ እንቅልፍ ይነሳል፡፡ ይታያችሁ----እኔ ደሞዝ የተጨመረልኝ የዛሬ ሦስት ዓመት ነው፡፡ የኑሮ ግሽበቱ ግን በሦስት እጥፍ ጨምሯል፡፡ ሌላው ቀርቶ አከራዬ ራሳቸው መስከረም ከጠባ ሶስቴ የቤት ኪራይ ጨምረውብኛል፡፡ ታዲያ እንዴት እንቅልፍ ይውሰደኝ ? በዚያ ላይ አንዳንድ የአገር ጉዳዮች አሉ- ከዚህ እኩል እንቅልፍ የሚነሱ፡፡ ሁሌም ወዳጄ ሲመጣ ቤቴ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢሮ ትመስላለች (የሃብታሞቹ ሳይሆን የምስኪኖቹ! ) በቃ ወሬያችን ሁሉ ፖለቲካ ይሆናል፡፡ በእርግጥ አንዳንዱ ደረቅ ሃቅ ነው (እንደዋጋ ግሽበቱ!) አንዳንዱ መሬት ያረገጠ ፍርሃትና ስጋት (ነፋስ አመጣሽ እንደሚሉት!) ጥቂቱ ደግሞ ምኞት ነው (ተስፋ ያላጀበው!) የሚበዛው ግን ሃሜት! (እውነትና ውሸት የተደባለቁበት!) 
ወዳጄ---- ከኢህአዴግ ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚገናኙ ጉዳዮችን ያነሳል ይጥላል፣ ይረግማል ይነቅፋል፡፡ ዛሬ የጨዋታ ማሟሻው ያደረገው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፣ ሲያወራ ቢውል የማይሰለቸውን ባለ ሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ እድገት ሲሆን እስኪበቃው ድረስ ቦጫጨቀው (እድገቱ ወደ አንድ ዲጂት መውረዱን አልሰማም ልበል?) ከዚያ በኋላ የሚያዝያው ምርጫ ተነሳ - ኢህአዴግ በሚሊዮኖች የሚሰሉ እጩዎች ያቀረበበትን ምርጫ ማለቴ ነው! (አንድ ከተማ ህዝብ ሙሉ እጩ!) የሚገርመው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ገዢው ፓርቲ እንዲህ በእጩዎች ሲትረፈረፍ፣ ተቃዋሚው ኢዴፓ ግን አንድ ሃባ እጩ ብቻ ነው ያቀረበው (ለመድሃኒት ነው እንዴ?) ለነገሩ ኢዴፓ እጩ አጥቶ እኮ አይደለም - ኢህአዴግን ሊያሳጣው ፈልጎ ነው፡፡ በቂርቆስ ክ/ከተማ (ወይዘሮ አዜብ የሚወዳደሩበት አካባቢ ማለት ነው!) የኢዴፓ ብቸኛው እጩ ከአንድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ “አንድ እጩ ብቻ በማቅረብ ለኢህአዴግ ብጫ ካርድ አሳይተነዋል” ሲሉ ተናግረዋል (ኢህአዴግ በብጫ ካርድ ሊደነግጥ?) 
ኢህአዴግን ወቅሶ የማይጠግበው ወዳጄ (አሁንማ ሆቢው ሆኗል!) ሃሜቱን ቀጥሏል። በመራጮች ምዝገባ ወቅት በገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ተፈፀመ ያለውን “ትልቅ ሴራ” ተረከልኝ፡፡ ፍቅረኛው ባትደውል ኖሮ ዛሬ ሲጨቀጭቀኝ ሊውል ነበር፡፡ አንድዬ ግን ቀናነቴን አይቶ ከጭቅጭቅ አወጣኝ፡፡ እሱ ሲሄድልኝ ተመልሼ ተኛሁ - የቴሌኮም ቴክስት ሜሴጅ እስኪቀሰቅሰኝ!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
ከሰብኣዊ አምደኛ

No comments:

Post a Comment