Sunday, February 3, 2013

መቆሚያ የሌለው የግብፅ ምስቅልቅል

የግብፅ ህዝብ አምጦ የወለደው የተሂሪር አደባባይ ህዝባዊ አብዮት ውሉ የለየለት አይመስልም። በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች አብዮቱ ጨንግፏል ሲሉ ቀላል የማይባሉት ደግሞ አብዮቱ በሙርሲና በዙሪያቸው ባሉ አክራሪ የእስልምና አማኞች ተነጥቋል ብለው ያምናሉ።
ግብፃውያን ዓመታት በላይ የተጫነባቸውን የሙባረክን አገዛዝ ከጣሉ በኋላ እፎይታን አላገኙም። በህዝቡ ምርጫ አብዛኛውን የፓርላማ መቀመጫ የያዘው የእስልምና ወንድማማቾች ፓርቲ ግብፅን ወደ አክራሪ የእስልምና አገዛዝ ይመልሳታል የሚል ስጋት በመኖሩ በፕሬዝዳንት ሙርሲ ላይ እምነት የሌላቸው በርካታ ግብፃውያን ተቃውሞ ሲያሰሙ ቆይተዋል።
በወናነት በሙርሲ መንግስት ላይ ተቃውሞ የሚያነሱ አክራሪ ያልሆኑ የእስልምና እምነት ተከታይ ግብፃውያንና የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አማኝ ግብፃውያን ናቸው። ይሁንእንጂ ሙርሲ የእሳቸውን ስልጣን ከፍርድ ቤቶችና ከህግ በላይ የሚያጎነፅፈውን ፣ ለሴቶች እምብዛም የእኩልነት መብት የማያሰጠውንና በአመዛኙ ወደሸሪያ ህግ የሚያዘነብለው ሕገ-መንግስት ላይ ህዝበ ውሳኔ አሰጥተው ውሳኔው ላይ የተሳተፉ ጥቂት ግብፃውያን ህገ-መንግስቱን መደገፋቸው አይዘነጋም።
ይሁንና የሙርሲ ተቃዋሚዎች ከመጀመሪያው ህዝበ -ውሳኔውን ከመቃወማቸውም ባለፈ በህዝብ ውሳኔውም ላይ ወጥተው ድምፅ የሰቱ ጥቂት ግብፃውያን ናቸው በሚል በድጋሚ የህዝቡ ውሳኔውን ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
ሀገሪቱ የሙባረክ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ በአክራሪና ለዘብተኛ እንዲሁም ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አማኞች የመክፈል አዝማሚያ አሳይታለች። በስልጣን ላይ ያለው የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ሀገሪቱ በእስልምና አስተምሮሆቶች መመራት አለባት ወደሚል አቋም ያዘነበለ በመሆኑ በእስራኤል፣ በአሜሪካና በአውሮፓ ህብረት በጥርጣሬ አይን እንዲታይ አድርጎታል። ምዕራባውያን የግብፅ የታሂሪሪ አደባባይ አብዮት በእነ- ኢራንና በሌሎች አክራሪ የእስልምና መንግስታት እንዳይጠለፉም ስጋት አላቸው።


የሙርሲ መንግስት በበኩሉ አብዮቱ ከመቀልበስ የምጠብቀው እኔ ነኝ፣ በህዝቡ የተመረጥኩትም እኔ ነኝ በማለት የሚነሳበትን ተቃውሞ እየመከተ ይገኛል። በዚህ አይነት የፖለቲካ ፍጥጫ ውስጥ ያላቸው ግብፅ ከሰሞኑ ደግሞ የታሂሪር አደባባይ የህዝባዊ ተቃውሞን ሁለተኛ ዓመት በመዘከር በወጡ ሰልፈኞች መላ ካይሮና ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች በተቃውሞ ሲናጡ ከርመዋል። አርብ ዕለት በተቀሰቀሰው የታሂሪር አደባባይ ላይ ሁከት ከዘጠኝ ያላነሱ ሰልፈኞች ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል።
በማግስቱ ቅዳሜ የሆነው ግን መላውን ዓለም ያስደነገጠ አጋጣሚ ነበር። በተቃውሞ ናዳ እየተርበደበደ ያለው የሞርሲ መንግስት ባለፈው ዓመት የሀገሪቱ ሁለት ታላላቅ የእግር ኳስ ክለቦች እየተጫወቱ እያለ በስታዲየም ውስጥ ግርግርና ሁከት በማስነሳት ለ74 ሰዎች ህይወት ማለፍ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን 21 ሰዎች በሞት እንዲቀጡ መወሰኑን ተከትሎ ፖርት በተባለችው ከተማ በተነሳ ሁከት ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል።
እንደ ዓለም አቀፍ የመገናኛ አውታሮች ዘገባ ሰዎቹ የተገደሉት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን ፍርደኞች ከታሰሩበት እስር ቤት ለማስለቀቅ አምባጓሮ በመፈጠሩ ነው። በከተማዋ የተሰማራው የፖሊስ ኃይል በወቅቱ የተነሳውን ህዝባዊ ማዕበል መቋቋም ባለመቻሉ የሀገሪቱ የጦር ይል ከተማዋን እንዲያረጋጋ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።
የፍርድ ውሳኔው በተሰጠባት የፖርት ከተማ የሚኖሩ የፍርደኞቹ ቤተሰቦችና አጋሮቻቸው የሞት ፍርዱን ከመቃወም አልፈው ታሳሪዎቹን ለማስለቀቅ ጥረት ሲያደርጉ በነበረበት በተመሳሳይ በካይሮ የሞት ፍርዱን በመደገፍ የድጋፍ ሰልፈኞች ትዕይንት ህዝብ አድርገዋል።
በታሳሪዎቹ ላይ የተሰጠው የሞት ፍርድን ተከትሎ የተፈጠረው ቀውስ ሳያንስ በሀገሪቱ ስዊዝ እና አልማስሪያ ከተሞች ፕሬዝዳንት ሙርሲን በመቃወምና የሙባረክ አገዛዝ የወደቀበትን ሁለተኛ ዓመት ለመዘከር ሲባል የተጠራው ሰልፍ ወደ ሁከት በመቀየሩ የሰው ህይወት ጠፍቷል።
በከተሞቹ በሁከቱ የተገደሉ ሰዎችን ለመቅበር የወጡ ሰልፈኞች በድጋሚ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል። የፖርት ከተማን ጨምሮ በተቀሩት ሁለት ከተሞች ያለው ሁከት አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ የ30 ቀናት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያወጁት ፕሬዝዳንት ሙርሲ ሲሆኑ የግብፅን ህዝብ የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለባቸው አዋጁን ማውጣታቸውን ነው የገለፁት።
ፕሬዝዳንት ሙርሲ እየተቀሰቀሰባቸው ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማርገብ ለተቀዋሚዎች የእንወያይ መልክት አስተላልፈዋል። ተቃዋሚዎቻቸው ግን ከውይይቱ በፊት አሳማኝ ባልሆነ የህዝበ-ውሳኔ የፀደቀው ህገ-መንግስት ካልተሻሻለ በውይይቱ መሳተፍ እንደማይፈልጉ እየገለፁ ነው።
የግብፅ ህዝብ የሙባረክን አገዛዝ ከጣለ በኋላ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እየተጎዳ ነው ፣ሥራ አጥነትና የሸቀጦች ዋጋ ንረት ነዋሪውን እያስመረረ ነው። ሰሞኑን በተከታታይ ቀናት በተቀሰቀሰው ሁከት የሀገሪቱ ፓውንድ ከዶላር ጋር ያለው የምንዛሪ መጠን ቀንሷል፣ የሀገሪቱ ፓውንድ ከአብዮቱ በኋላ በ12.5 በመቶ መቀነሱ ሮይተርስ ዘግቧል።
የግብፅ ኢኮኖሚ በሀገሪቱ ባለው የኢኮኖሚ አለመረጋጋትና የመንገድ ላይ ነውጥ እየተሽመደመደ ነው። ለጋሾችና በነዳጅ ዘይት ምርት የበለፀጉ አገራት ድጋፍ ቢደረግለትም የግብፅ ኢኮኖሚ የማገገም አዝማሚያ እያሳየ እንዳልሆነ ነው የተዘገበው። የዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ለግብፅ ለማበደር የፈቀደውን የ4.8 ቢሊዮን ዶላር አለመልቀቁ ደግሞ በሙርሲ መንግስት ላይ ተጨማሪ የራስ ምታት ሆኗል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ክምችት ከቀን ወደቀን እያሽቆለቆለ መምጣት ሌላው ከፍተኛ ስጋት እየፈጠረ ነው። የሮይተርስ መረጃዎች እንደሚመለክቱት በአሁኑ ወቅት የግብፅ የውጪ ምንዛሪ መጠን 15 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም የሀገሪቱን የገቢ እቃ ለመግዛት ለሶስት ወራት ብቻ የሚበቃ እንደሆነም ተገልጿል።
                                                                         ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment