Thursday, February 28, 2013

የፕሬሱስ ጉዳይ አያሳስበንም እንዴ?‹‹የት ይደርሳል ያሉት ጥጃ ልኳንዳ ተገኘ››



አስፈላጊ ሆና ስላገኘዋት እንዲ አድርጌ አቅርቤዋለው በአገራችን በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ እንዴት ነው ነገሩ? የሚያሰኝ  ዕድገት ማይታይባቸው ብዙ ዘርፎች አሉ፡፡በተፃራሪው ደግሞ ፈጣን ዕድገትና መሻሻል ሲጠበቅ ሒደቱና ውጤቱ ግን ‹‹የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ልኳንዳ ተገኘ›› የሚለው የአበው ተረት የሚተረትባቸው ዘርፎችም አሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ሕንፃዎችና ሰፋፊ መንገዶች ተገንብተዋል፤ አሁንም እየተገነቡ ናቸው፡፡ የከተማ ቀላል የባቡር መስመር እየተዘረጋ ነው፡፡ በርካታ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ የንግድ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የሕክምና ተቋማት፣ ወዘተ በብዛት ተገንብተዋል፡፡ ይህን ስናይ ይበል እንላለን፡፡ ከተማችን ከጥቂት ቀደምት የአፍሪካ ከተሞች አንዷ ሆና ስናያትም እንኮራለን፡፡ እውነትም የአፍሪካ መዲና እንላለንም፡፡ በሀቅ! ከልብ፡፡ዲሞክራሲን መጎልመስን አትወክልም! እንደውም ብሶበታል! እውነቴን ነው ምነው ፈራቹ መስክሩ እንጂ?
ግን በተፃራሪው በእጅጉ የሚያሳዝን ሁኔታም እየታዘብን ነው፡፡ ዕድገታቸው ተሽመድምዶና ራሳቸው ተዳክመው ሌላውን የሚያዳክሙና የሚያሽመደምዱ ተቋማትና ዘርፎችም አሉ፡፡ የሚደርስላቸው ያጡ፡፡ የመፍትሔ ያለህ የሚሉ፡፡ 
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከተቋቋመ ዘጠና ዓመታት ያህል ሆኖታል፡፡ ሲቋቋምም የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ነበር፡፡ ከእሱ በኋላም የት ይደርሳሉ የተባሉ በርካታ የማተሚያ ቤት ጥጃዎች ተወልደዋል፡፡ ከአገራችን አጠቃላይ ዕድገት ጋር ሲነፃፀርና በአፍሪካ ካሉት የሕትመት ዕድገቶች ጋር ሲወዳደር ግን ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በአሁኑ ጊዜ ‹‹የት ይደርሳል ያሉት ጥጃ ልኳንዳ ተገኘ›› የሚባልለት ሆኗል፡፡ 
በአሁኑ ጊዜ ይህ ማተሚያ ድርጅት የመንግሥት የሕትመት ጥያቄን መመለስ አልቻለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ ማተሚያ ድርጅት የግሉን ፕሬስ የሕትመት ጥያቄ መመለስ አልቻለም፡፡ የመንግሥት ፕሬስ እንደ ግል ፕሬሱ የሚያሽመደምድ የማተሚያ ቫይረስ ባያጠቃውም አልፎ አልፎ የሚያስነጥስ በሽታ እያጠቃው ነው፡፡ በማተሚያ ቤት የአቅም ችግር፡፡ 
ስለ አንድ ድርጅት አንስተን እየተነጋገርን ያለነው ልዩ ዓላማ ኖሮን አይደለም፡፡ ማተሚያ ቤት ከፕሬስ ነፃነት መብት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ነው፡፡ በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 29 የፕሬስ ነፃነትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሙሉ በሙሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሮ ሰፍሯል፡፡  በእኛ ሕገ መንግሥትም የሰፈረው ቃል በቃል ዓለም አቀፍ ሕግ ነው፡፡
ግን! ነገር ግን! ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ሥራ ላይ ለማዋል ብዙ እንቅፋቶች ቢያጋጥሙትም አንዱ እንቅፋት የማተሚያ ቤት ችግር ሆኗል፡፡ አንዴ ወረቀት የለም፣ ቀለም የለም፣ ማሽን ተሰብሯል፣ ኤልሲ መክፈት አልተቻለም የሚል የእንቢታ መልስ ለጋዜጦችና ለመጽሔቶች ይሰጣል፡፡ የአናትምም መልስ፡፡ ሌላ ጊዜ ወረቀትና ቀለም ስለሌለ ገጽ ቀንሱ ይባላል፡፡ ባልታሰበ ጊዜ ደግሞ ‹‹ከለር›› አናትምም ይባላል፡፡ ከዚህም አልፎ ጋዜጦች በወቅቱ የመውጣት ችግር እያጋጠማቸው ነው፡፡ በድንገትና በማይገባ ምክንያት ደግሞ በየጊዜው ዋጋ ተጨምሯል የሚል መርዶ ለግሉ ፕሬስ ይደርሳል፡፡ ማተሚያ ቤቶች ‹‹ደንበኞቻችን ንጉሦቻችን ናቸው›› በሚሉበት ዘመን ብርሃንና ሰላም ‹‹ለደንበኞቻችን ንጉሣቸው ነኝ›› ባይ ሆኗል፡፡ በሽብርተኝነት አይወቀስም እንጂ ‹‹በአሰቃቂነት›› ይወቀሳል፡፡ 
ብርሃንና ሰላም አድጎ እጅግ የተሻለ የተሻለ አቅም አግኝቶ ብዙ ነገር ይሠራል ተብሎ ሲጠበቅ አቅም የለኝም፣ ማሽን ተሰብሮ የሚጠግልኝ አጥቻለሁ፣ ዘመናዊው ማሽን ስለተበላሸብኝ በድሮው ነው የምሠራው ሲል ሲደመጥና የግሉ ፕሬስ ችግር ላይ ሲወድቅ ሲታይ፣ ‹‹የት ይደርሳል ያሉት ጥጃ ሉኳንዳ ተገኘ›› የሚያስብል ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ 
ገጽ መጨመር፣ በቀለም ማሳመር፣ በወቅቱ ማውጣትና ማሰራጨት፣ ተቀባይነት ባለው ተመጣጣኝ ዋጋ ማሳተም የግሉን ፕሬሶች እየተፈታተነ ነው፡፡ ዕድገታቸው እየተደናቀፈ ነው፡፡ የት ይደርሳል ያሉት የሕትመት ጥጃም ሉኳንዳ እየተገኘ ነው፡፡ የት ይደርሳል ያሉት ፕሬስም ሉኳንዳ እየተገኘ ነው፡፡ 
በእንደዚህ ከቀጠለ የአቶ እከሌ ጋዜጣ ወይም እከሌ የተባለ መጽሔት ሉካንዳ ተገኘ ተብሎ የሚታለፍ ሳይሆን ትርጉሙ ከዚያ በላይ የላቀና የከበደ ይሆናል፡፡ 
‹‹
የት ይደርሳል ያሉት የፕሬስ ነፃነት ሉካንዳ ተገኘ›› የሚለውም ይከሰታል፡፡ 
በዚህም አያበቃም፡፡ የፕሬስ ነፃነት የዴሞክራሲ የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት መዳከም ካለና የት ይደርሳል ያሉት የፕሬስ ነፃነት ጥጃ ሉኳንዳ ከተገኘ ‹‹የት ይደርሳል ያሉት የዴሞክራሲ ጥጃ ሉኳንዳ ተገኘ›› የሚለውን ያስከትላል፡፡
መንግሥት ለዚህ ችግር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል፡፡ መንግሥት ‹‹በርካታ ማተሚያ ቤቶች ስላሉ መርጠው ሊያሳትሙ ይችላሉ›› የሚል አመለካከቱን ያቁም፡፡ ፕሬስን ማስተናገድ የሚችሉ ማተሚያ ቤቶች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ እጅግ ውድ ናቸው፡፡ እነሱም በፍርኃት ያልሆነ መመዘኛና ጥያቄ እያቀረቡ አናትምም የሚሉበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው፡፡ ስለሆነም የግሉ ፕሬስ የሚገኘው አንዱ አልተመቸኝም ሲል ወደ ሌላ ለመሄድ እየተቸገረ ያለበት ሁኔታ ላይ ነው፡፡ ‹‹የማኩረፍ መብት›› በራሱ በእጅጉ እየጠበበ ነው፡፡
ጋዜጦችና መጽሔቶች የራሳቸውን ማተሚያ ቤት ለምን አያቋቁምም የሚለው ጥያቄም ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህ ግን የተወሳሰበ ነው፡፡ ‹‹ሪፖርተር›› ጋዜጣን የሚያትመው ‹‹ሚዲያ ኤንድ ኮሚኒኬሽንስ ሴንተር›› የማተሚያ ቤት ሕንፃ ገንብቶ፣ የማተሚያ ማሽን አገር ውስጥ አስገብቶና ገጣጥሞ ሥራ ሊጀምር ሲል ባልታወቀ ምክንያት እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ሦስተኛ ዓመቱንም ይዟል፡፡ 
ይህ ችግር በመኖሩ የግል ፕሬሶች የራሳቸውን ማተሚያ ቤት ለማቋቋም ይሸማቀቃሉ ማለት አይደለም፡፡ አሁንም በጋራ በአክሲዮን ተደራጅተው እየሞከሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን መንግሥት ይህን ችግር እያየ ዝም ማለት የለበትም፡፡ ችግር የለም አማራጭ አለ የሚል ፌዝም ይቁም፡፡
በታዳጊ አገሮች በተለይ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካና በእስያ መንግሥታት የግል ፕሬስ እንዳይዳከም የጋዜጣና የመጽሔት ግብርና ቀረጥ እየቀነሱ፣ በኢኮኖሚ ችግር ሳቢያ ለሚከሰት ጉዳት መደጎሚያ እያዘጋጁና እያበረታቱ ናቸው፡፡ የሴኔጋል መንግሥት ራሱ በቀረጥ ቅናሽና የድጎማ በጀት በመመደብ እያበረታታ ነው፡፡ 
በእኛ አገር መንግሥት ይደጉመን ባንልም ድጋፍ ግን ያስፈልጋል፡፡ ችግሩን የመረዳት ድጋፍ፡፡ ማተሚያ ቤቶችን የማጠናከር ድጋፍ፡፡ አላስፈላጊ ጫናዎችን የማስወገድ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ ከፖለቲካ አንፃር በማየት ብቻ ሳይሆን በቢዝነስ አንፃርም እነ ብርሃንና ሰላም ቢያድጉ ትልቅ ገቢ ያስገኛሉ፤ መንግሥትም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ህንድ፣ ዱባይና ኬንያ እየታተሙ አገር ውስጥ በሚገቡ መጽሔቶች ምክንያት ማፈር ይገባል፡፡ ማተሚያ ቤቶች ለሌላ መትረፍ ሲገባቸው ለአገራቸው ብቁ መሆን አልቻሉም፡፡
ነገሩ ‹‹የት ይደርሳል ያሉት ጥጃ ሉኳንዳ ተገኘ›› ሆኗል፡፡ የት ይደርሳል የተባለ የፕሬስ ነፃነት ሉኳንዳ ተገኘ እንዳይሆን፡፡ የት ይደርሳል የተባለ ዴሞክራሲ ሉኳንዳ ተገኝቷል አረለ ፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment