Monday, February 25, 2013

በወጣቱ ትውልድ ላይ ኢንቨስት ይደረግ!


በወጣቱ ትውልድ ላይ የተለያዩ ወቀሳዎች ሲሰነዘሩ ይሰማል፡፡ ‹‹የጫትና የሺሻ ትውልድ ሆነ፤ ስደት ይወዳል፤ በአቋራጭ ሀብታም መሆን ይፈልጋል፤ ሥራ አይወድም፤ ሞራልና ሥነ ምግባር የለውም፤ ስለታሪክ ደንታ የለውም፤ ኢትዮጵያዊነት አይሰማውም…›› ወዘተ፣ ወዘተ የሚል፡፡እንደዚህ ዓይነቱ አመለካከት ከመነሻውም ስህተት ነው፡፡ መድረሻውም አያምርም፡፡ ከወዲሁ ሊታረምና ሊስተካከል ይገባል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ጠንካራ ሠራተኛ፣ አገር ወዳድ፣ በሥነ ምግባር የተሞላ፣ የበለፀገና ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ ግን በወጣቱ ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል፡፡ወጣቱን ጠንካራና ስኬታማ ትውልድ ለማድረግ ‹‹ወላጆች ይምከሩ›› ወይም ‹‹መንግሥት ይርዳው›› ተብሎ የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና መንግሥት በጋራ የሚሸከሙትና የሚወጡት ኃላፊነት ነው፡፡
ወጣቶች ከሕፃንነት ጀምሮ ትምህርት እንዲወዱ፣ ስፖርትና ሥነ ጥበብ እንዲያፈቅሩ፣ አገር ወዳድ እንዲሆኑ፣ ወዘተ የሚያደርግ ኢንቨስትመንት አለ? ወይስ የለም? የቤተ መጻሕፍትና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን የማግኘት ዕድልና አጋጣሚ እየተነፈጉ የሚያድጉ ሆነዋል፡፡ እያደጉና እየጎረመሱ ሲመጡም እንዳይበላሹና የመጥፎ ልማድ ምርኮኛ እንዳይሆኑ የሚረዳ፣ የሚያግዝ፣ የሚመክር፣ የሚያስተምርና የሚከታተል አካል ከመንግሥት በኩልም እየታጣ ነው፡፡
ስለሆነም የወጣቱ ትውልድ ዕጣ ፈንታ በመርህ ደረጃ እንዲህ ተደርጎ እንዲህ ይሆናል የሚባል ሳይሆን ገጠመኝ ሆኗል፡፡ በርካታ ወጣቶች ጥረው ግረው ራሳቸውን ሲያሻሽሉ ይታያሉ፡፡ ራሳቸውን ችለው ቤተሰቦቻቸውን ሲረዱ ይስተዋላሉ፡፡ ወንዶችም ሴቶችም፡፡ ነገር ግን የዚያኑ ያህል ደግሞ ወደ አልባሌ ተግባር ሲሰማሩና ለአደጋና ለውድቅት ሲዳረጉ ይታያሉ፡፡ ገጠመኝ እንጂ አስተማማኝ ሒደት የለም፡፡ አነስተኛና ጥቃቅን ሥራዎችን መንግሥት እየፈጠረ ለወጣቱ አመቺ ሁኔታ ለማስገኘት ቢጥርም፣ አሁን ካለው የወጣቶች ቁጥር አንፃር ሲታይ ጅምር እንጂ አስመኪ አይደለም፡፡
ስለዚህ?
ስለዚህ በመርህና በአቅጣጫ ተይዞ ወጣቱ አገሪቷን በመረከብ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያሸጋግር የሚያስችል አቅምና ዕውቀት ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ስለሆነም በወጣቱ ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል፡፡
ኢንቨስትመንት ሲባል ገንዘብ ወይም በጀት ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ምክር፣ ትኩረት፣ የትምህርት ማዕከላት፣ የአቅም ግንባታ ተቋማት፣ የክትትልና የውይይት መድረኮች፣ የማበረታቻና የሽልማት መርሐ ግብሮች፣ የብድርና የድጋፍ አሰጣጥ ማዕቀፎች ሁሉ በወጣቱ ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ናቸው፡፡
ወላጆች፣ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና መንግሥት ወጣቱን ትውልድ ከመውቀሳቸው በፊት እኔ ለወጣቱ ትውልድ ምን አደረግኩለት ብለው ሊጠይቁ ይገባል፡፡ ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው፣ ሥራ እንዲወዱ፣ አገራቸውን እንዲወዱና የድርሻቸውን እንዲወጡ እንዴት እንርዳቸው ብለው ሊጠይቁ ይገባል፡፡
በዕድሜ የገፉ በወጣቱ ትውልድ ይተኩ የሚል የመተካካት መርህ የግድ ነው፡፡  የፖለቲካ ድርጅቶችስ ወጣቱ ትውልድ መሪ እንዲሆን አስፈላጊውን ኢንቨስትመንት እያደረጉ ነው? ወይስ ወጣቱ ትውልድ የአመራር ብቃት የሚያገኝበት ሁኔታ ከታች ሳይፈጠር ከ60 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው ከ40 በታች ዕድሜ ባለው ይተካል የሚል አኀዛዊ ዕቅድ ነው ያላቸው?
ወጣት ሴቶች ዓረብ አገር እየሄዱ ተዋረዱ፣ ተንገላቱ፣ ተደበደቡ፣ ሞቱ፣ ወዘተ እያልን ማዘን ብቻ ነው የምናውቀው? ወይስ እነዚህ በስደት ሄደው አደጋ የሚደርስባቸው ወጣቶች አገራቸው ውስጥ ራሳቸውን ችለው፣ ኮርተውና ደፍረው የሚኖሩበት አቅም እየፈጠርንላቸው ነው?
የወጣቱ ትውልድ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው ነው፡፡ ወላጅና ቤተሰብም ልዩ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ መንግሥትም ልዩ ኃላፊነት አለበት፡፡ ብልጭ ድርግም የሚሉ የሚያበረታቱ ነገሮች ቢኖሩም፣ እርር ድብን የሚያደርጉ አሳዛኝና አስለቃሽ ፈተናዎችንም እያስተዋልን ነን፡፡
ወጣቱ ትውልድ ስለጦርና ጋሻ፣ ስለክላሽና ታንክ እያወራ የሚያድግና የሚኖር መሆን የለበትም፡፡ ስለዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ ስለግብርናና ኢንዱስትሪ፣ ስለስፖርትና ሥነ ጥበብ፣ ስለባቡርና አየር ትራንስፖርት፣ ወዘተ እያሰበ ማደግና መራመድ አለበት፡፡ ወጣቱ ትውልድ እንዳለፈው ዘመን ጠላት ሲመጣ አሳፍሮና መክቶ ስለመመለስ ብቻ የሚያስብና አገሩን ለነፃነቷ ቀናዒ ናት እያስባለ ስሙ የሚነሳ ብቻ ሳይሆን በኤክስፖርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢነርጂ፣ በትራንስፖርት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ ወዘተ ግንባር ቀደምና ተወዳዳሪ ናት እያስባለ አገሩን የሚያሳውቅና የሚያኮራ መሆን አለበት፡፡ የአገርን ደኅንነትና ሉዓላዊነት መጠበቅና ማስከበር እንዳለ ሆኖ፡፡
የሰው ኃይል ራሱን የቻለ ሀብት ነው፡፡ ሀብት የሚሆነው ኢንቨስት ሲደረግበት ነው፡፡ የሰው ኃይል በተለይም የወጣቱ ኃይል ቀጣይነቱ የተረጋገጠ በመሆኑ አስተማማኝ ኢንቨስትመንት ይሆናል፡፡
የወጣት ማኅበራት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የሙያ ማኅበራት፣ የሥነ ጥበብ ማዕከላት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት፣ ወዘተ ለወጣቱ ልዩ ትኩረት ያደርጉ ኢንቨስትመንት ያካሂዱ እንላለን፡፡
የተከበረች፣ የኮራች፣ የበለፀገችና ከድህነት የተላቀቀች ኢትዮጵያ በቀጣይነት ልትኖር የምትችለው የአገርን ኃላፊነት የሚሸከም ወጣት ትውልድ ሲኖር ነው፡፡
ኃላፊነትን የሚሸከም ወጣት ትውልድ የሚኖረውም ቀዳሚዎቹ አባቶችና እናቶች ለአገራቸው የሠሩትን ተረድቶና በታሪክ ላይ ታሪክ ጨምሮ ለመንቀሳቀስ አቅም ያለው ሲሆን ነው፡፡
ኢትዮጵያችን ቀጣዩን ጉዞዋም በወጣቱ ትውልድ ትከሻ ላይ አኑራለች፡፡ ወጣቱ ትውልድ ኃላፊነቱን ሊወጣና የበለጠ ታሪክ ሊሠራ ይችላል፡፡ ይገባልም፡፡
ይህን እውን ለማድረግ ግን በወጣቱ ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት መፍሰስ አለበት!
                              ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
                                     ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment