Tuesday, February 19, 2013

በእምነት ጉዳይ ጣልቃ መግባት አረ እስከመቼ?


የስድስተኛው ፓትርያርክ የአስመራጭ ኮሚቴ የካቲት ሃያ የምርጫ ውጤቱ ይፋ ያደርጋል:: ይህ ምርጫ በመንግስት ጣልቃ ገብነትና ተጽኖ እየተከናወነ መሆኑ ግልጽ እየሆነ ነው:: ቤተ ክርስቲያን ድሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ ሰባዊ መብት ተጣሰ የማለት ሃላፊነት ሲኖርባት ለአገር አይደለም በራሷ ላይ የሚፈጸመውን መቃወም ያቃታት የወላድ መካን ሆናለች::ይህ በዘመናችን አሳዛኝ/አሳፋሪ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ሆኗል::በበኩሌ ይህን ምርጫ አልቀበለውም በምርጫው ውጤት ይፋ የሚደረጉትን ፓትሪያርክ አባትነት አልቀበለውም::

አብዛኛው ክርስቲያን እምነቱን አፍቃሪና አክባሪ ነው። መምህራኑን ይሰማል፣ ቃላቸውንም ይፈጽማል። ነገር ግን ከሚሰጡት ትምህርቶች አብዛኛዎቹ ሆን ተብሎም ይሁን በሌላ ምክንያት ሕዝቡን የሚያደነዝዙ፣ የጥንት ኦርቶዶክስ አባቶቹ እንዳደረጉት ለአገሩ፣ ለእምነቱና ለቤተሰቡ ከመሞት ይልቅ በቅኝ ግዛት እንደተያዙት ሌሎች አፍሪካውያን መጽሐፍ ቅዱሱን ገልጦ ሰማይ ሰማይ ብቻ የሚያይ ደካማ አድርገውታል። አባቶቹ አድዋ ላይ ታቦቱን ይዘው እንዳልውጡ፣ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሰዉንም ምድሪቱንም ለፋሺስቶች እንዳይገዙ ገዝተው እንዳልተሰዉ፣ ብዙዎቹ አበው ለአገራቸውና ለእምነታቸው ደማቸውን እንዳላፈሰሱ አይነገረውም። ስለዚህም በስመ ኦርቶዶክስ የሚመራው ክርስትና ከጥንቱአትንኩኝ ባይኦርቶዶክስ ጋር ምንም ግንኙነት ያለው አይደለም።
የተሳሳተ ትርጉም እየተሰጣቸው ሕዝቡ እንዲደነዝዝባቸው ከሚያደርጉት ትምህርቶች መካከልሁሉንም ለእግዚአብሔር እንስጠው፣እግዚአብሔር ያውቃል፣ እኛ የእርሱን ጊዜ እንጠብቅየምትል የራስን ኃላፊነት ሳይወጡ በስንፍና የመቀመጥ አደንዛዥ ትምህርት አንዷ ናት። እግዚአብሔርማ ሁሉን ያውቃል። ምን ጥርጥር አለው። ነገር ግን አዋቂነቱ በዓለም ላይ የሚፈጸመውን ግፍና መከራ ሁሉ እንዲከወን እንደፈቀደ መቁጠር ኑፋቄ ነው።
በዓለም ላይ በየሰከንዱ ብዙ ወንጀሎች ይፈጸማሉ። ሁሉ ወንጀልና ሰቆቃ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውን? በርግጠኝነት አይደለም!!! እግዚአብሔር ያውቀዋል ግን? እንዴታ!! እግዚአብሔር የማያውቀው ምን ነገር አለ? የሰው ልጅ ግን በነጻ ፈቃዱ የሚፈጽመው ወንጀል ነው። ለዚህ ጥፋቱ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ሲቆም ቅጣቱን ያገኝበታል።
ከዚሁ አያይዘን ስንመለከተው በቤተ ክርስቲያናችን እና በአገራችን ላይ የሚፈጸመውን ግፍ እግዚአብሔር ያውቀዋል። ታዲያ ለምን ዝም አለ ለሚል ግብዝ መልሱ ሰዎች በነጻ ፈቃዳቸው ተጠቅመው ያደረጉት ነገር ነው የሚል ነው። ክፉዎቹ በክፋታቸው ተገፋፍተው ይህንን ሲያደርጉ እኛስ በመልካምነታችን ተጠቅመን የአቅማችንን ለማድረግ ያልቻልነው ለምንድር ነው?
ከመጽሐፍ አንድ ምሳሌ እናንሣ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልአዛርን ከሞት ሊያሥነሣው በሄደ ጊዜ የተፈጸመውን ማወቃችን ከላይ ለመግለጽ የፈለግነውን ሐሳብ ግልጽ ያደርገዋል። ታሪኩ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 11 ላይ ይገኛል። አልአዛር ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ። ከተቀበረ ከአራት ቀን በኋላ ጌታ ወደዚያ ሥፍራ ሄደ። ከዚያም ከመቃብሩ ላይ ድንጋዩን አንሱ ብሎ ቤተሰቦቹን አዘዘ። ከዚያም አልአዛርን ከመቃብር አልጋ ከሞት ሸለብታ ቀስቅሶ ሕያው አደረገው። ከሞት ማሥነሣቱ ካልቀረ ድንጋዩን እንዲያነሱ ለምን አዘዛቸው? ለምን ሁሉንም ነገር ራሱ አልፈጸመውም? በዚህ የአልአዛር ድኅነት ውስጥ የሰው ድርሻ በቤተሰቦቹ ተሰርቷል፣ የእግዚአብሔር ድርሻ ደግሞ በራሱ በባለቤቱ ተሠርቷል። የሰው ድርሻ መቃብሩን መክፈት፣ የእግዚአብ ድርሻ ሙቱን ሕያው ማድረግ ነው። በዘመናችን ግን እያልን ያለነውሁሉንም ነገር አንተ ሥራው!!!” ነው።
መቃብሩን አንተው ቆፍር፣ ሙቱንም አንተው አስነሳው፤ እኛ ዝም ብለን እንመለከትሃለን።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment