Monday, February 11, 2013

አንድ ለአምስት የልማት ወይስ የመንግስት የፖለቲካ ሠራዊት?

              
አንድ ለአምስት እንደ ኪራይ ሰብሳቢነት 
ኢሕአዴግ በፓርቲም ሆነ በመንግሥት ደረጃ በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ብዙ ብሏል፡፡  አንዳንድ ሰዎች በትክክል ምን ማለት እንደሆነ በውል አይገነዘቡትም፡፡ በቴሌቪዥን ወይም ደግሞ በሬዲዮ በሚተላለፉ የመንግሥት ዘገባዎች ይህ ጽንሰ ሐሳብ ሳይጠቅስ አይቀርም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋትና የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ፣ ወዘተ በልማታዊ አስተሳብ መቀየር እንዳለባቸው በስፋት ይነገራል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ሥልጣንን ተገን አድርጎ የተለያዩ ሰዎችን ያልተገባ ጥቅም የሚያገኙበት አካሄድ ከሆነ ከሙስና የሚለይበት መስመር አይታይም፡፡ ያም ሆነ ይህ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ  መመረቂያ ጽሑፋቸው የተከራከሩበት ልማታዊ መንግሥት ስለመፍጠር ነበር፡፡
በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ እንዲነግሥ የተፈለገው የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ራሱ ግን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ የመንግሥት እንቅስቃሴዎች ይስተዋሉበታል ብለው የሚሞግቱ አሉ፡፡ በዚህ አስተሳሰብ የሚሰባሰቡ አባላት፣ ባለሀብቶች፣ ሙዚቀኞች፣ ጋዜጠኞች፣ መምህራንና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በብዙዎች የኢሕአዴግ አጀንዳ አራማጆች ሆነው ይታያሉ፡፡ በዚህም መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትን ከኅብረተሰቡ ውስጥ በማጥፋት ስም እየዘረጋው ያለው አስተሳሰብ ራሱ የመንግሥት ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› እየፈጠረ እንደሆነ የሚያምኑ ይበዛሉ፡፡ የመንግሥትን ሀብት ለጥቅም በማቅረብ አባላትንና ደጋፊዎችን እያፈራ መሆኑን በመጠቆም፡፡ 

ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲጠፋና ልማታዊ አስተሳሰብ እንዲያነግሥ በስፋት እየተሠራ ያለው በአንድ ለአምስት አደረጃጀት መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ በገጠርም በከተማም በተለያዩ ዘርፎች እየተደራጁ ያሉት የልማት ቡድኖች ‹‹ልማታዊ ሠራዊት›› ለመፍጠር መሆኑ ከባለሥልጣናት አንደበት መገንዘብ ይቻላል፡፡ አወቃቀሩም ከጦር ኃይል አደረጃጀት የተወሰደ ሲሆን፣ የሚፈለገውን ልማት ለማሳካት አንድ ዓይነት የጠራ አመለካከትን መፍጠርን ያለመ ነው፡፡ አጀንዳውም እሱ ነው፡፡ ፅንሰ ሐሳቡ በሌላ አገር ይሠራበት አይሠራበት ግን ማረጋገጫ አልተገኘም፡፡ 

ጥያቄው መንግሥት የልማት ጠንቅ አድርጎ የሚመለከተውን የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ለመተካት እየፈጠረው ያለው ይኼው አደረጃጀት፣ እውነት የልማት አስተሳሰብ ነው ወይስ ሥልጣን ላይ ያለው አካል የፖለቲካ አጀንዳውን በኅብረተሰቡ ለማስረፅ እየተጠቀመበት ነው የሚል ነው፡፡ 

በቅርቡ ቀጣዩ የአካባቢና የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ሜዳውን ለማስተካከል በአንዳንድ አገራዊ ጉዳዮች እንነጋገር በሚል 18 ጥያቄዎች ለምርጫ ቦርድ ያቀረቡ 33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱና ዋነኛ ጥያቄያቸው ይኼው አደረጃጀት ነው፡፡ የፒቲሽኑ ፈራሚ ፓርቲዎች ጊዜያዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስራት ጣሴ፣ አንድ ለአምስት በሚባለው አደረጃጀት መላውን ሕዝብ አንድ ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት እንዲኖረው እየተሞከረ ያለው አካሄድ ነው ብለዋል ፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች መካከል መድረክና መኢአድ ምርጫ 2002 እንዲደገም ለፍርድ ቤት ባቀረቡት ክስ ያቀረቡዋቸው ማስረጃዎች መራጮች በዚሁ በአንድ ለአምስት ተደራጅተው መምረጣቸውን የሚያሳይ ነበር፡፡ 

ይኼው ተቀባይነት ያላገኘው ቅሬታ ግን በአንዳንድ ጋዜጦች በወቅቱ የተዘገበ ሲሆን፣ ገለልተኝነታቸውን ሁሌም አወዛጋቢ የሆነው ፍርድ ቤትና ምርጫ ቦርድ ቅሬታዎቹን ሳይቀበሉ ቀርተዋል፡፡ አሁንም ምርጫ ከመድረሱ በፊት ለመነጋገር ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ የሆነባቸው እነዚህ ተቃዋሚዎች ይኼው ‹‹የልማታዊ ሠራዊት›› ግንባታ ለፖለቲካ መጠቀሚያ እየዋለ መሆኑን ማስረጃ አለን በማለት እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

ጊዜያዊ ኮሚቴው ካቀረበው አንድ ማስረጃ ‹‹በደቡብ ክልል አርቤጎና ወረዳ የምርጫ ሥራ ለማሳካት የወጣ አጭር ማስፈጸሚያ ቼክ ሊስት›› በሚል በአርቤጎና ወረዳ የደኢሕዴን ///ቤት የተዘጋጀና ሾልኮ የወጣ የተባለ ሰነድ እንደሚያመለክተው፣ የሕዋስ ዕቅድ አደረጃጀትን አስመልክቶ፣ ‹‹አንድ አባል 4-5 ደጋፊዎቹን በማስተካከል መልኩ እንዲዘጋጅ ማድረግ›› ይልና፣ ‹‹ለልማት የፈጠርነውን የልማት ሠራዊት ወደ ምርጫ ተግባር በማዟዟር ምርጫውን በድል የምንወጣበት አግባብ መፍጠር›› ማስፈለጉን ይገልጻል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በመምህራንና ለመራጭነት በደረሱ ልጆች፣ በልማት ሠራተኛና በጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በመታገዝ በእነርሱ አማካይነት የቤት ለቤት ሥራ መሥራት ማስፈለጉንም ኮሚቴው አገኘሁት ያለው ሰነዱ ያስረዳል፡፡ በኮሚቴው ገለጻ መሠረት ይህ አደረጃጀቱ እንዴት ለምርጫ ጥቅም እንደሚውል የሚያሳይ ነው፡፡

የጊዜያዊ ኮሚቴው አባል ያልሆነው ኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ እንደሚሉት፣ መንግሥት ለልማት ሥራ ምንም ዓይነት አደረጃጀት መጠቀሙ አይጠላም፡፡ ‹‹ችግሩ መደበላለቁ ነው›› በማለት በመንግሥትና በፓርቲ መካከል ምንም ልዩነት በሌለበት አገር ገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ ሥራዎቹን በሙሉ እያከናወነ ያለው በመንግሥት ሀብትና በመንግሥት መዋቅር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ይኼንን አንድ አምስት የሚል አደረጃጀት ኢሕአዴግ የራሱን ፖለቲካ ለማራመድ እየተጠቀመበት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሥራ አጥነት ትልቅ ችግር በሆነበትና ትልቁ ቀጣሪ መንግሥት በሆነበት አገር፣ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች በዚሁ ዓይነት መንገድ እንዲደራጁ ማስገደድ ቀጥተኛ ይልሆነ የነፃነት ገፈፋ ነው ይሉታል ይኸ ነው፡፡ ‹‹መከላከያው፣ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤቱና ምርጫ ቦርዱ ገለልተኛ ባልሆነበት አገር ደግሞ ችግሩ የጎላ ይሆናል፤›› ፡፡ 

የተቃዋሚዎች ደጋፊ ወይም አባላት በሆኑት ይቅርና ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ የማይፈልጉ ዜጎች በግዴታ አማራጭ ሐሳብ ሳይቀርብላቸው አንድ አመለካከት እንዲጫናቸው እየተደረገ ነው ፡፡ ኢሕአዴግ ከእንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ እንዲታቀብ በማሳሰብ፣ አንድ ቀን ያልተፈለገ ተቃውሞና አመፅ ሊያስከትል እንደሚችል ማወቅ ያስፈልጋል ፡፡ ይህንን ሥጋ  ሥራው በሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ማኅበራት ሊሠራ ይችላል ፡፡ 

አንድ ለአምስት ያሸልማል
በተቃዋሚዎችና በገዥው ፓርቲ መካከል የተለያየ ትርጓሜ እየተሰጠው ያለው ይኼው አደረጃጀት በድብቅ የሚሠራ አይደለም፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ልማታዊ ሠራዊት ተፈጻሚ የሚሆንበት ማንዋል ተዘጋጅቶ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ በገጠር አካባቢ የተለያዩ የመስኖና የጤና ኤክስቴንሽን ሥራዎችን ለማስፈጸም እየዋለ ሲሆን፣ በአብዛኛው ግን ለፖለቲካ አጀንዳ መዋሉ ይነገራል፡፡ አቶ ሬድዋን ሁሴን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ አደረጃጀትና ተሳትፎ የአማካሪ ሚኒስትር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት የሚፈልገውን ለውጥ ለማምጣት የተመቸውን አደረጃጀት መጠቀም ይችላል፡፡ መብቱም ነው፡፡ ኢሕአዴግ የተደራጀ ሕዝብ ጉልበት አለው ብለው ያምናል፡፡ ‹‹ገጠር ውስጥ ብዙ ለውጥ መጥቷል፡፡ አሁንም ከተማ ውስጥ እንገባለን፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት አደረጃጀት ለምርጫ ትጠቀማላችሁ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ በአጋጣሚ ሆኖ ሥልጣን ላይ ያለ አካል የመንግሥት አደረጃጀትና ሀብት መጠቀሙ አዲስ ነገር አይደለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

በሰኔ 2004 .. በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ የተዘጋጀው ‹‹በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ የሠራዊት ግንባታ›› በሚል የተዘጋጀው ማንዋል፣ በየደረጃው የልማት ሠራዊት ለመገንባት የሚያስፈልግ አካሄድ የሚጠቁም ሲሆን፣ ዓላማውም የኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብ ለማጥፋት ነው ይላል፡፡ በአብዛኛው በማንዋሉ የቀረበው ጽሑፍ ይዘት ምንም ክፋት የሌለው ይመስላል፡፡ ነገር ግን በአጀንዳው ‹‹መካከለኛ ባለሀብቶች በስፋት የሚፈጠሩባቸው አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት በመሆናቸው፣ በልማታዊ አስተሳሰብ የተቃኙ ተቋማትን ከወዲሁ መገንባት በቀጣይ ልማታዊ ባለሀብቶች መበራከት ብሎም ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው፤›› ነው ይላል፡፡ የዛሬ 20 እና 30 ዓመት ጭምር ‹‹ልማታዊ›› አስተሳሰብ ያላቸውና የኢሕአዴግ ደጋፊ አካላትን ከወዲሁ ለማፍራት ያተኮረ ይመስላል፡፡ በዚሁ አደረጃጀት የታቀፉ ሠራተኞች 70 እስከ 80 በመቶ ጊዜያቸውን ለዚሁ ሥራ እንዲያውሉ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ልማታዊ አስተሳሰብ ለማስረፅ በሚል የተሰጠው ጊዜ ይህንን አስተሳሰብ ከኢሕአዴግ የፖለቲካ አጀንዳ ጋር እየተጣመረ በመሆኑ ጥያቄውን የበለጠ አሳሳቢ እንደሚያደርገው ተቃዋሚዎች ይከራከራሉ፡፡ 


የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር በቅርቡ 22 ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ባካሄደው የሪፎርም ግምገማ የመልካም አስተዳደር ለውጥ አለመምጣቱን ገልጿል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ሙክታር ከድር ከባለድርሻ አካላት ጋር በተወያዩበት ወቅት፣ ለውጥ ላለመምጣቱ በምክንያትነት ያስቀመጡት የአንድ ለአምስት አደረጃጀት አለመሳካትን ነው፡፡ አደረጃጀቱ ሦስቱ ክንፎች የያዘ ሲሆን የኢሕአዴግ ክንፍ፣ የመንግሥትና የኅብረተሰብ ክንፍ በሚል የተቀመጠ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል፡፡  

            ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!

                           ከሰብኣዊ
 

 

No comments:

Post a Comment