Monday, February 4, 2013

ፍትሕ ያስተፌሥሕ ልበ - ሰብ ( ፍትህና መልካም አስተዳደር )


መልካም አስተዳደር ያስተፌሥሕ ልበ - ሰብ፡፡ ፍትሕ ያስተፌሥሕ ልበ - ሰብ፡፡ ፍትሕ ያስተፌሥሕ አዕምሮ - ሰብ፡፡
ፍትሕ ያስተፌሥሕ አንጀተ - ሰብ፡፡ ፍትሕ ያስተፌሥሕ ሕይወተ - ሰብ፡፡ ፍትሕ ያስተፌሥሕ ኅብረተ - ሰብ፡፡ ፍትሕ ያስተፌሥሕ ሕዝብ፡፡
ፍትሕና መልካም አስተዳደር ለኅብረተሰቡም ሆነ ለግለሰብ የሚፈጥረው ደስታና እርካታ ከተራ የመልበስ፣ የመጉረስ፣ የመጎንጨት ደስታና እርካታ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ ሰው በሰው ልጅነቱ፣ ሰው በዜግነቱ እንዲኮራ የሚያደርግና ይበልጥ አገሩንና ወገኑን እንዲያገለግል የሚያስችለው እርካታ ነው፡፡ ጊዜያዊ እርካታ ሳይሆን ዘላቂ፡፡
በዚህም ምክንያት ነው ደግመን ደጋግመን ልዩ ትኩረት ለመልካም አስተዳደርና ለፍትሕ ይሰጥ የምንለው፡፡ ደግመን ደጋግመን ፍትሕንና መልካም አስተዳደርን እውን የሚያደርጉ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ተግባር ላይ ይዋሉ የምንለው፡፡ ለዚህም ነው ደግመን ደጋግመን የሕዝብን መልካም አስተዳደርና ፍትሕ የሚረግጡ፣ የሚሸጡ፣ የሚለውጡ ተጠያቂ ይሁኑ፣ ለፍርድ ይቅረቡ የምንለው፡፡
የውኃ ጥም የሚረካው ውኃ ፍሪጅ ውስጥ ስለተቀመጠ አይደለም፡፡ ሱቅ ውስጥም ስለተደረደረ አይደለም፡፡ ምንጮች ውኃ ስላላቸው አይደለም፡፡ የውኃ ማስታወቂያዎች ስለተሰሙ፣ ስለተነበቡና ስለታዩ አይደለም፡፡ በተጨባጭ የተጠማው ሰው ማግኘትና መጠጣት ሲችል ነው፡፡ 

ፍትሕና መልካም አስተዳደርም እንደዚሁ፡፡ ግለሰብም ሆነ ሕዝብ ፍትሕና መልካም አስተዳደር አለ ብሎ ሊተማመን፣ ሊኮራና፣ ሊረካ የሚችለው በሕገ መንግሥታችን ወይም በሌሎች አዋጆቻችን አንቀጾች ውስጥ ስለሰፈሩ አይደለም፡፡ በአንቀጽ የሰፈሩትን በተጨባጭ ሊነካቸው፣ ሊጠቀምባቸውና በዕለታዊ ሕይወቱ ሊያገኛቸው ሲችል ብቻ ነው፡፡
ስለሆነም ለተበደለና ፍትሕ ላጣ ዜጋ፣ መልካም አስተዳደር አጥቶ ለሚንገላታ ዜጋ ፍትሕና መልካም አስተዳደር እንዲኖር በአንቀጽ ተደንግጓል እያልን ብናወራ ዋጋ አይኖረውም፡፡ በተግባር ሕዝቡ ሊያገኘው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ‹‹ላም አለኝ በሰማይ ወተትዋንም አላይ›› ይሆናል፡፡
ሕዝብም እንደ ሕዝብ፣ ግለሰብም እንደ ዜጋ መንግሥት ካለ፣ ሕግ ካለ ማንም ንብረቴን አይቀማኝም፣ ማንም መብቴን አይነፍገኝም፣ ማንም አያጠቃኝም፣ አይገድለኝም፣ አይመታኝም፣ አያሳድደኝም ብሎ መተማመን አለበት፡፡
እንደዚህ ዓይነት የመብት ጥበቃ፣ ፍትሕና መልካም አስተዳደር የሚያገኝ ሕዝብና ዜጋ አገር በጠላት ሲወረር ይከላከላል፡፡ ከመንግሥት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ጠላቱን ይመክታል፡፡ አገሩን ከድህነት ለማላቀቅ ይረባረባል፡፡ ወገን ሁሉ ሕግን እንዲያከብርና ግዴታውን እንዲፈጽም ያደርጋል፡፡ በአገሩ እንደሚኮራ ሁሉ አገሩንም ያኮራል፡፡ በአገሩና በሥርዓቱ ስለሚኮራ አገሬንና ሥርዓቴን አትንኩ የሚል ሕዝብ ይሆናል፡፡ ጠንካራ ዜጋ ይሆናል፡፡ አልሚ ዜጋ ይሆናል፡፡ ፍትሐዊ ዜጋ ይሆናል፡፡
ፍትሕ ያስተፌሥሕ ልበ - ሰብ ስንል መንግሥት የሕዝብን መብት ሲጠብቅ ብቻ አይደለም፡፡ ሕዝብም ዜጋም ግዴታውን ሲወጣ ጭምር ነው፡፡ መልካም አስተዳደርና ፍትሕ ሊኖር የሚችለው መንግሥት በሚሠራው ነገር ብቻ አይደለም፡፡ ዜጋውና ሕዝብ በሚሠራው ሥራም ጭምር ነው፡፡ ፍትሕ ይኑር፣ መልካም አስተዳደር ይኑር ስንል ዜጎችም ግዴታቸውን ይወጡ ማለታችን ነው፡፡ የሚጠበቅባቸው ግብር ይክፈሉ፣ ማክበር ያለባቸውን ሕግ ያክብሩ፣ አያጭበርብሩ፣ አያወናብዱ፣ ለግል ጥቅም ብለው የሌላውን ዜጋ ጥቅምና መብት አይንኩ፣ አያስነኩ ማለታችንም ነው፡፡ ስለሆነም መልካም አስተዳደርንና ፍትሕን የማስፈን ጉዳይ የመንግሥትም፣ የሕዝብም፣ በግልም የዜጎች ግዴታና ኃላፊነት ይሆናል፡፡ ነውም፡፡

መልካም አስተዳደርንና ፍትሕን የሚያረጋግጡ አንቀጾች አሉን፡፡ የሕገ መንግሥትንም የአዋጆችንም፣ ስለፍትሕና መልካም አስተዳደር የሚነገሩ መግለጫዎችንም በየጊዜው እንሰማለን፡፡ ድክመቱ እዚህ ላይ አይደለም፡፡ ድክመቱ ተግባር ላይ ነው፡፡ አፈጻጸም ላይ ነው፡፡ ቁርጠኝነት ላይ ነው፡፡ መስዋዕትነት የመክፈል ዝግጁነት ላይ ነው፡፡

ከአንጀት የሚያለቅስ ጠፋና እንባ አልፈስ አለ እንጂ ካንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም፡፡ ስለዚህ ንግግራችን፣ ቃላችን፣ ዕቅዳችን ስለተግባርና ተግባራዊነት ይሁን፡፡
በተግባር መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ  ሕዝብም ቆርጠዋል? መልካም አስተዳደርን የሚጥስና የሚያደናቅፍ የመንግሥት አካልም ሆነ ባለሥልጣን፣ ዜጋም ሆነ ግለሰብ፣ በማስረጃ ሲታይና ሲረጋገጥ ዕርምጃ ለመውሰድ ሕግ ፊት ለማቅረብ ተግባራዊ ዝግጁነት አለን? ባለሥልጣንም ሆነ ባለ ሀብት፣ ታዋቂም ይሁን ተራ ዜጋ፣ ከፈለገው ብሔር ብሔረሰብ ይምጣ፣ የፈለገውን ሃይማኖት የሚከተል ይሁን፣ የጾታና የዕድሜ ልዩነት ሳይኖር ተቃዋሚም ይሁን ደጋፊ ሁሉም ሕግ ፊት፣ ፍትሕ ፊት፣ መልካም አስተዳደር ፊት እኩል መሆኑን አምነን በተግባር ለማዋል ቆርጠን ለመተግበር ዝግጁ ነን?
ለዚህ ሁሉ መልስ ‹‹አዎን!›› ሲሆን ነው መልካም አስተዳደርና ፍትሕ ሊረጋገጥ የሚችለው፡፡ ያኔ ሲረጋገጥም ነው ፍትሕ ያስተፌሥሕ ልበ - ሰብ የምንለው፡፡

ፍትሕንና መልካም አስተዳደርን የሚረግጡ ይጠየቁ፣ በሕግ ይቀጡ ሲባል ከልብና በእውነት የሕዝብና የአገር አገልጋይ ሆነው ፍትሕንና መልካም አስተዳደርን እውን የሚያደርጉ ዜጎች ደግሞ ይከበሩ፣ ይታወቁ፣ ይሸለሙ፡፡ የሚያጠፋውን መውቀስ ብቻ ሳይሆን ሀቀኛውን ማወደስና ማክበርም ይልመድብን፡፡ 

በአጠቃላይ ሲታይ ፍትሕና መልካም አስተዳደር በመጓደሉ የሕዝብም የዜጋም ልብ እየቆሰለ ነው፡፡ ተስፋው እየጨለመ ነው፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለሁምን እያሰኘ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለእኔ ምኔ ናት እያስባለ ነው፡
በተግባር በአስቸኳይ እንለውጠው፡፡ ጠንካራ፣ ፈጣን፣ ቆራጥ  የሕዝብ የጋራ ዕርምጃ ይኑር፡፡ መልካም አስተዳደር እውን ይሁን፡፡ ሕዝብ በአገሩ ይኩራ፤ በኢትዮጵያዊነቱ ይመካ፡፡ በአገሩ ኮርቶ አገሩን ያክብር፡፡
ፍትሕ ይንገሥ፡፡ አገርና ሕዝብ እንዲታደስ ፍትሕ ያስተፌሥሕ ግለ - ሰብ፣ ፍትሕ ያስተፌሥሕ አዕምሮ - ሰብ፣ ፍትሕ ያስተፌሥሕ እንዳታ - ሰብ፣ ፍትሕ ያስተፌሥሕ ሕይወተ - ሰብ፣ ፍትሕ ያስተፌሥሕ ሕዝብ፡፡
                                       ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
                                      ከሰብኣዊ              

No comments:

Post a Comment