Tuesday, February 5, 2013

ኢትዮጵያዊ ውስጥ እውነት ማለት ወረት ማለት ነው እንዴ?


ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም "መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ" የሚል መጽሐፍ ጽፈዋል። በገጽ194 ላይ ደግሞ ስለ "ኢትዮጵያዊ እውነት" እንዲህ ይላሉ፦
"ዞሮ ዞሮ ኅብረተሰቡን ያጫጨው የኢትዮ ሕዝብ ሰላምን አግኝቶ ለኑሮው እንዳያስብ፣ ኑሮውን እንዳያጣጥም፣ ሠርቶ ኑሮውን እንዳያዳብር፣ ሀብት አካብቶ ከችጋር እንዳይላቀቅ አስሮ የያዘው የአስተዳደር ማነቆ ነው። ይህ የአስተዳደር ማነቆ ከፈጠራቸው ክፍ ክፉ ጠንቆች አንዱ የሕግ እና የሥነ ሥርዓት አለመኖር ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ጉልበት ሥልጣን ነው። ጉልበት መብት ነው፤ ጉልበት ሕግ ነው፤ ጉልበት ሥነ ሥርዐት ነው። የገዢዎች መብት ያልተወሰነ ነው። የገዢዎችም ግዴታ ያልተወሰነ ነው።

ኅብረተሰቡን ያጫጨው ከአስተዳደር ጋራ የተያያዘ ሌላም ምክንያት አለ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰው የሚከበረው እና የሚከብረው በምን በምን ነው? አንዱ በመወለድ ነው፤ አንዱ ጮሌነት እና ለበላይ ጎንበስ ቀና ማለት ነው። ሁለቱ ደግሞ የዮፍታሄ ንጉሴ ግጥም እንደሚለው "ጋብቻ እና የሥርቆሽ በር" ናቸው። ሌላ የምንጨምረው ነገር ቢኖር ጀግንነት እና ሽፍታነት ናቸው። እንዲያው በአጋጣሚ እና ልዩ በኾነ ኹኔታ ካልኾነ በቀር በኢትዮጵያ ውስጥ እውቀትም ኾነ የምርት ሥራ የሚያስከብር እና የሚያከብር ኾኖ አያውቅም። እውቀት እና የምርት ሥራ ዋጋ በማያገኙበት ኅብረተሰብ ድህነት እና ኋላ ቀርነት ባሕርይ ይኾናሉ።
ከዚህ ሁሉ የተነሳ ኢትዮጵያ የእውነት አገር ኾና አታውቅም። ለእውነት ዋጋ ለመስጠት በቅድሚያ የእውቀትን ጥቅም መረዳት እና መቀበል ያሻል። ኢትዮጵያ የሃይማኖት አገር ስለኾነች እውነት የሚባለው ሁሉ የሚፈልቀው ከእምነት ነው። ከእምነት የሚፈልቅ እውነት አያከራክርም። ማለት ለክርክር ክፍት አይደለም። ኢትዮጵያዊ እውነት ሌላ ምንጭም አለው። ይኸውም ሥልጣን ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያዊ እውነት ከሥልጣን እና ከእምነት እየመነጨ በትዕዛዝ እና በግዴታ ወደታች የሚተላለፍ ነው። እንዲህ በመኾኑም አገዛዝ በተለወጠ ቁጥር ኢትዮጵያዊ እውነትም ይለወጣል። በመሥሪያ ቤት ደረጃም ብንመለከተው ባለሥልጣን በተለወጠ ቁጥር እውነት ተብሎ የነበረው ይለወጣል። ሲረገም የነበረው ይመረቃል፤ ሲመረቅ የነበረው ይረገማል፤ ባጭሩ ኢትዮጵያዊ እውነት ማለት ወረት ማለት ነው፤ ይህንን ሐቅ መቀበል ካልቻልን ተስፋ የለንም።" ታዲያ ከዚህ ወዲያ ክሽፈት ከየት ይመጣል?

               ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
                             ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment